መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል አሳድገን
ጳጉሜ የሚለው ስያሜ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “ጭማሪ” ማለት ነው ፡፡ በግእዝ “ወሰከ – ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ተውሳክ (ተጨማሪ) ማለት ነው፡፡ ምዕራባዊያኑ ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ቀን አድርገዋታል፡፡ እኛ ግን የዓመት ተጨማሪ ወር አድርገናታል፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወርኃ ጳጕሜን የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ ይህም ጳጉሜ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት፣ ከክረምት ወቅት ወደ ጸደይ መሸጋገሪያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ፣ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ፣ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነትና ነው፡፡ ጳጉሜ የክረምቱ ማብቂያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም በመጨረሻው ዘመን መከራ የሚበዛበት የዚህ ዓለም ማብቂያ ናት፡፡ ወርኃ ጳጉሜ አዲሱን ዓመት ለመቀበል የዝግጅት ጊዜ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ጻድቃል አዲሲቷን ምድር (መንግስ ሰማያትን) ለመውረስ ተዘጋጅተው “ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግስት ውረሱ” የሚባሉባት ናት፡፡
በዚህም የተነሣ ብዙ ምእመናን በጾምና በጸሎት (በሱባዔ) ያሳልፏታል፡፡ በተለይም በቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ሰማያት የሚከፈቱበት (ርኅዎተ ሰማይ) መኾኑን በማመን ምእመናን የጸሎታቸውን ማረጊያ (ማሳረጊያ) መሆኑን በማመን ከምንጊዜውም በበለጠ በእምነት ይጸልያሉ፡፡ ርኅወተ ሰማይ የስሙ ትርጉም የሰማይ መከፈት እንደማለት ሲሆን በክርስቶስ ክርስቲያን የተባሉ ሁሉ ፀሎት፣ ልመናቸው ምልጃቸው የሚያርግበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት የምእመናንን ልመና መስዋእቱን የሚያሳርጉበት እና የአምላካችንን ምህረት ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት ዕለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ውኆች እንደሚባረኩ በሚረዳ ጽኑ እምነት ምዕመናን ወደ ወንዞች በመሔድና በሚዘንበው ዝናብ ይጠመቃሉ፡፡
በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው ጾመ ዮዲት ነው፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ (ዮዲ ፪፡-፪)፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ ፲፪ ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ ፲፪ ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋት በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡
ዮዲት ባለቤቷ ምናሴ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖር ነበር:: በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለጸላት (ዮዲ ፰፡፪)፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡ ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንንና ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡
በወርኀ ጳጉሜን ከሚታሰቡ እና ከሚከበሩ በዓላት መካከል በየዓመቱ ጳጕሜን ፫ ቀን የሚከበረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በታላቅነቱ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ “ሩፋኤል” የሚለው የስሙ ትርጓሜ “ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ” ማለት ነው፡፡ በሌላም መልኩ ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ሰሙ የዕብራይስጥ ሁለት ቃላት ጥምረት ውጤት ነው፡፡ “ሩፋ” ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት ማለት ሲሆን “ኤል” ሚለው በሌሎቹም መላእክት ስም ላይ የሚቀጠል ስመ አምላክ ነው:: ይህም “መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ….. ስሜ በእርሱ ስለሆነ አታስመርሩት” (ዘጸ.23÷20-22) እንዳለው ነው፡፡ ታዲያ “ሩፋኤል” የሚለው በጥምረት “ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ” የሚለውን ይተካል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ስሙም ከሚካኤልና ከገብርኤል ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ይቀመጣል፡፡ “ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡ ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን ይጠብቃቸዋል (ዳን.4÷13 ዘጸ. 23÷20 መዝ. 90÷11-13 ) ያማልዳል፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡ (ሉቃ. 13፡6-9፣ ዘካ.1÷12) ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያለ ማቋረጥ ፈጣሪያቸው ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርገው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን በሚከተሉት ሰባት አንኳር ነጥቦች ይገልጡታል፡፡
ፈዋሴ ዱያን፡ ሕሙማንን የሚፈውስ
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ እየተመላለሰ ሲያስተምር ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን ደግሞ በትምህርቱ ይፈውስ ነበር፡፡ ለምሳሌ ለሠላሳ ስምንት ዘመን በአልጋ ላይ የነበረውን መጻጉዕን ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሄድ በማለት ከደዌው ፈውሶታል (ዮሐ ፭፡í-፲)፡፡ ማዳን (መድኃኒትነት) ለእርሱ የባህሪው ነው፡፡ የማዳንን ጸጋ ለቅዱሳን ሰጥቷል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ድውያንን ሲፈውሱ የነበረው፡፡ ከቅዱሳን መላእክትም ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኃጢአት ቍስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የሚረዳ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ዅሉ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል (ሄኖክ ፲፥፲፫)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ኾነ ቍስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” እንዳለ ሄኖክ (ሄኖክ ፮፥፫)፡፡ ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው መልአክ ነው፡፡ ዛሬም ሁላችንን በአማላጅነቱ ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰናል፣ ይጠብቀናልም፡፡
ፈታሔ ማኅፀን፡ ማኅፀንን የሚፈታ
በብሉያና በአዲስ ኪዳን ብዙ እናቶች ከመካንነት የተነሳ ሀዘን ጸንቶባቸው ቢቆይም ምንም የማይሳነው አምላክ እጅግ ድንቅን ያደረጉ የተባረኩ ልጆችን ሰጥቷቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የይስሐቅ እናት ሣራ፣ የያዕቆብ እናት ርብቃ፣ የዮሴፍ እናት ራሄል፣ የሶምሶን እናት እንትኩን፣ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና፣ የመጥምቀ መለኮት የዮሐንስ እናት ኤልሳቤጥ፣ የድንግል ማርያም እናት ሐና ይገኙበታል፡፡ እግዚአብሔር የመካኒቱን ማኅፀን ፈትቶ የተባረከ ልጅን የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ይህንንም ጸጋ ለቅዱሳን መላእክት ሰጥቷል፡፡ ይህም ስልጣን ከተሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል አንዱ ነው፡፡
የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ ስለተሾመ ከጌታ አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ ሴቶች ሁሉ የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ይላሉ ማየጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ፡፡ የይስሐቅን እናት ሣራን፣ የሶምሶንን እናት (እንትኩይን) ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም ያበቃቸው ይኸው ፈታሔ ማኅጸን የልዑል እግዚአብሔር መልአክተኛ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ለነፍሰጡር ሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ (ኗ) በማኅፀን እያለ (ች) ተሥዕሎተ መልክዕ (በሥላሴ አርአያ መልኩ /ኳ/ መሳል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያቸውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀልላቸዋል፡፡ ሕጻናትን በእናታቸው ማኅፀን የሚጠብቃቸው እናቶችንም ከመፅነስ እስከ መውለድ የሚራዳቸው፣ የመካኖችንንም ማኅፀን የመፍታት ጸጋ የተሰጠው መልአክ ነው፡፡
ሰዳዴ አጋንንት፡ አጋንንትን የሚያሳድድ
ከጌታችን ሠላሳ ሦስት ታላላቅ ተአምራት ውስጥ አራቱ አጋንንትን ማስወጣት ነበሩ፡፡ ይህ ስልጣን ለቅዱሳን ሰዎችና መላእክት በጸጋ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም በተሰጠው ስልጣን አጋንንትን የሚያሳድድ መልአክ ነው፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በሣራ (ወለተ ራጉኤል) ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል (ጦቢት ፫፥፰-፲፯)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል “ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሄኖክ ፫፥፭-፯) ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው (ሄኖክ ፪፥፲፰)፡፡ ዛሬም ከእግዚአብሔር ተልኮ ለሰው ልጆች የተንኮልን፣ የጥላቻን፣ የመገዳደልን ሀሳብ እንዲያፈልቁ የሚያደርገውን የመልካም ነገር ጠላት የሆነውን ጠላታችንን አስጨንቆ የሚያባርር መልአክ ነው፡፡
አቃቤ ኆኅት፡ የምህረትን ደጅ የሚጠብቅ
ቅዱሳን መላእክት የሰውን ልጅን ጸሎት ከምድር ወደ ሰማይ የእግዚአብሔርን ምህረት ደግሞ ከሰማይ ወደ ምድር የሚያደርሱ መልእክተኛች ናቸው (ራዕ ፰፡፪)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም ስለራሱ ማንነት በሰጠው ምስክርነት “የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው” (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሩፋኤል መዝገበ ጸሎት እና አቃቤ ኆኅት ይባላል፡፡ ከዚህ ጋርም በቅዱስ ሩፋኤል ተራዳዒነት ከተደረጉ ተአምራት መካከል በእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት በታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ ያደረገው ተአምር አንደኛው ነው፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር እና በድርሳነ ሩፋኤል እንደ ተጻፈው በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀመናብርቱ ክብር በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ነበረች፡፡
ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ጠላት ዲያቢሎስ አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፋ አሣ አንበሪውን ቢያውከው ቤተክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጠች፤ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ዓሣ አንበሪው ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ምእመናኑም ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔር በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጾ “እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጥ ጸጥ ብለህ ቁም!” ባለው ጊዜ አንበሪው ጸጥ ብሎ ቆሟል፡፡ ምዕመናኑንም ከጥፋት ታድጓቸዋል፡፡
መራኄ ፍኖት፡ መንገድ መሪ
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡ የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡
“በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ (ዘጸ ፳፫፡፳)።” ተብሎ ለመላእክት ሰውን መንገድ የመምራትና የመጠበቅ ስልጣን እንደተሰጣቸው የጦቢትን ልጅ ጦቢያን ከነነዌ የሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደምትባለው ሀገር ሲሄድ አዛርያስ (ቅዱስ ሩፋኤል) በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል “መራኄ ፍኖት” (መንገድ መሪ) ይባላል፡፡ ጦቢያና አዛርያስ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው፤ ዓሣውን እንዳትለቀው አለው፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን አለው፡፡ ዛሬም በመንገዳችን እንዲመራን በጉዞአችንም ፈተና ሲገጥመን እንዲራዳን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን ሊልክልን አምላካችን የታመነ ነው፡፡
መልአከ ከብካብ: ጋብቻን የሚባርክ መልአክ
የራጉኤል ልጅ ሣራ ሰባት ሰዎች አግብተዋት ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ አድረዋል፡፡ ይህንንም ከነነዌ ወደ ራጌስ የመጣው የጦቢት ልጅ ጦቢያ ያውቅ ነበር፡፡ ለአዛርያስም “ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁ” አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን ያዘው ያልኩህ ለምን ይመስልሃል? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳየው ሚስቱ አድናን “ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል” አላት ከዚያም ጋር አያይዞ “ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?” አላቸው፡፡ እነሱም “ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን” አሉት፡፡ “ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት “እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ” አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል “የወንድሜ ልጅ ነህን?” ብሎ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡
እራትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገኝቶ በዶኪማስ ቤት የነበረውን ሠርግ ባርኮታል፡፡ የወይን ጠጅ ቢያልቅባቸውም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦ ቤቱን በበረከት ሞልቶታል (ዮሐ ፪፡í)፡፡ ቅዱሳንም ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ ጋብቻን በጸሎታቸው ይባርካሉ፡፡ በመሆኑም የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ “መልአከ ከብካብ” ይባላል፡፡ ዛሬም በምልጃው ላመኑት ጋብቻን ይባርካል፣ ትዳርንም ያጸናል፡፡
ከሳቴ እውራን፡ ዓይነ ስውራንን የሚያበራ
ራጉኤልና ሐና የሣራንና የጦቢያን የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን የአሥራ አራት ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡ የአሥራ አራት ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡ በምራቁ አፈር ለውሶ በደረቅ ግንባር ላይ ዓይንን የሚሠራው እግዚአብሔር (ዮሐ ፰) በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል አማካኝነት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን በራለት፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ዛሬም በምልጃው ለሚያምኑት ሥጋዊ ዓይንና መንፈሳዊ ዓይንን (ዓይነ ልቡናን) የሚያበራ መልአክ ነው፡፡
ማጠቃለያ
በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት ወርኃ ጳጉሜ የዕለተ ምጽአት መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ በወርኃ ጳጉሜ የአሮጌውን ዘመን የኃጢአት ቆሻሻ በንስሃ አጥበን ከዕለተ ምጽዓት በኋላ ለምትገለጠው የእግዚአብሔር መንግስት ምሳሌ ለሆነ አዲስ የምህረት ዓመት እንዘጋጅባታለን፡፡ የታደሉትም በፈቃድ ጾምና በሱባኤ እንደሚያሳልፏት ይታወቃል፡፡ በወርኃ ጳጉሜ በገናንነት የሚከበረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል በዓል የአሮጌው ዘመን በዓላት መዝጊያ ለአዲሱ ዘመን ርዕሰ አውደ ዓመት ለቅዱስ ዮሐንስ በዓልም መሸጋገሪያ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የሊቀ መልአኩን የቅዱስ ሩፋኤልን በዓል በማሰብ በወርኃ ጳጉሜ ውኆች እንደሚባረኩ በእምነት በመረዳት “ሩፋኤል አሳድገን (እርዳን፣ ጠብቀን)” እያልን በሃይማኖት እንጠራዋለን፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን በመጽሐፈ ጦቢት፣ በመጽሐፈ ሄኖክ፣ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በጻፈው አክሲማሮስ በተባለው መጽሐፍና በድርሳኑ ላይ እንደተገለጠው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጸጋ ድውያነ ሥጋንና ድውያነ ነፍስን የሚፈውስ፣ የሚካኒቱን ማኅፀን የሚያለመልም፣ ሕጻናትንም በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ የሚጠብቃቸው፣ የክፋት አባት የሆነውን ጠላት ሰይጣንን የሚያሳድድ፣ በመንገድ ያሉትን የሚመራ፣ ምህረትን ለሚሹ ፈጥኖ የሚደርስ፣ በጋብቻና በትዳር የሚፈተኑትን የሚረዳ መልአክ ነው፡፡ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ጸሎትና አማላጅነት ልጅ በማጣት ለተጨነቁ መልካም ፍሬን፣ ለተወለዱት በሃይማኖት ማደግን፣ ለታመሙት ፈውስን፣ ለባለትዳሮች እግዚአብሔር የሚደሰትበት ትዳርን እንዲሰጥልን የሰራዊት ጌታ የአምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን ሩፋኤል አሳድገን፡፡
No comments:
Post a Comment