በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያን እየታየ ያለው ሥርዓተ አልበኝነት እየጎላ ቢመጣም ተው የሚል ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቶቿም ሆነ ከሲኖዶስ፤ ከማህበረ ቅዱሳን ሆነ ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች አንዳቸውም እየተቃወሙ አይደለም። ከ20 ዓመት በፊት የነበረው የእነ በጋሻው የተሐድሶ እንቅስቃሴ እንዴት እንደነበር ሁላችንም የምናስታውሰው ጉዳይ ነው። የነበጋሻው የተሐድሶ ቡድን በቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል።
የእነ በጋሻውንና ግብራበሮቹን የምንፍቅና ማንነታቸውን የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት፤ ማህበረ ቅዱሳን፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ሌሎች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማህበራት በአንድነት በመስራታቸው የእነ በጋሻውን አመጣጥ ለህዝበ ክርስቲያኑ ከፍተኛ ግንዛቤ መስጠቱ ይታወቃል። ቢሆንም በብዙ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንቶቿ ከፍተኛ ጥረት ጠቅልሎ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር።
ይህ የተሐድሶ ቡድን ከቤተ ክርስቲያን ከወጣ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሰላም አግኝታ ነበር። የእነ በጋሻውንና ቡድኑን የተሐድሶ ዝማሪያቸውንና ስብከታቸውን የሚያዳምጥ እንኳ አልነበረም፤ በአውደ ምሕረቱም አይቀርብም ነበር። ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ በሙሉ ስለ ተሐድሶ በቂ ግንዛቤ አግኝቶ ነበር። ነገር ግን የኢሃዴግን መውደቅ ተከትሎ ዶክተር አቢይ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ በዚህ 7 ዓመት ውስጥ አሜሪካ ያሉት ተሐድሶ መናፍቃን (ከሊቀ ጳጳሳትነት ደረጃ የደረሱ መናፍቃንም ጭምር) በእርቅ ሰበብ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ፤ ተሐድሶዎች ተደራጅተው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመግባት እንደዚህ ዓይነት ሥራዓት አልበኝነት (ክራርን ገልብጦ የመምታትና የዳንስ እንቅስቃሴ በማድረግ፤ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ላይ ስህተት ትምህርት በቤተ ክርስቲያኒቱ አውደ ምሕረት ላይ ማስተማር፤ተከልክለው የነበሩ የተሐድሶ ዝማሬዎች ከእንደገና ወደ አውደ ምሕረቱ ማምጣት፤ በቅዱሳን ላይ ማላገጥ፤ በሶሻል ሚዲያ ስለ ቅዱሳንና እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የማታስተምረውን ታስተምራለች ብለው ራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን እንደወከለቻቸው አድርገው ስህተት ትምህርት ማስተማር) እንዲሁም የተሐድሶ ዝማሬ ተመልሶ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገባ በርትተው እየሰሩ ይገኛሉ። ነገር ግን በብዙ ድካም የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንቶቿ ስለ ተሐድሶ የሰጡት ግንዛቤ ጥሩ ቢሆንም አሁን ግን እየታየ ያለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ከባድ ነው።

No comments:
Post a Comment