ስለ መነኮሳት ፍትሐ ነገሥት ምን ይላል? - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, July 15, 2026

ስለ መነኮሳት ፍትሐ ነገሥት ምን ይላል?


 

ዓሣ ከባሕር በወጣ ጊዜ እንደሚሞት፣ መነኵሴም ከገዳሙ ከወጣ ይጠፋል" (መጽሐፈ መነኰሳት ፊልክስዩስ ተስእሎ 54)

ምእመናን ሁሉ፣ ቅዱስ ሲኖዶስም ከተማ ላይ የሚኖሩ መነኰሳት ወደገዳም እንዲመለሱ ማድረግ ይገባዋል። ከተማ ላይ የደብር አለቃ የሆኑ መነኰሳትንም ወደ ገዳም መመለስና ሕጋውያን ካህናትን (ሚስት ያገቡ ካህናትን) የየደብሩ አለቃ ማድረግ ተገቢ ነው።
ፍትሐ ነገሥት ምን ይላል?
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 10 ስለመነኰሳት ይናገራል። መነኵሴ ማለት ዘርኅቀ እምዓለም (ከዓለም የራቀ) ማለት ነው። አንድም እንደ ዜና አበው (መጽሐፈ ገነት) አገላለጽ መነኵሴ ማለት የሞተ ማለት ነው። መነኵሴ ለምን ይመነኵሳል የሚለውን ደግሞ መጽሐፈ መነኰሳት ሲያብራራ ከማየት፣ ከመስማት፣ ከመናገር ከሚመጡ በደሎች ለመራቅ እንደሆነ ይናገራል። ይህ ከሆነ መነኮሳት ስልክም መጠቀም የለባቸውም። ገዳም ገብተው ሥራቸው ላይና ጸሎታቸው ላይ ብቻ ነው ትኩረት ማድረግ ያለባቸው።
ስልክ ከያዙ ግን የሚሰማውንም እየሰሙ ነው፣ የሚታየውንም እያዩ ነው። እንዲህ ከሆነ ምኑን ከዓለም ተለዩአ። መነኵሴ ሹመትን የሚጠላ መሆን እንዳለበት ተገልጿል። ስለዚህ ጵጵስና ካልሾማችሁኝ ብሎ ድርቅ የሚል ሳይሆን ጵጵስና እንሹምህ ባሉት ግን እምቢ አልሾምም ብሎ ድርቅ የሚል መሆን አለበት።
አሁን ላይ ዘረኛ መነኰሳትን እያየን ነው። እነዚህ ሰዎች መጀመሪያውንም አልመነኰሱም። ምክንያቱም ስለሚኖሩባት ዓለም ያውም በጎጥ በሰፈር እያሰቡ ነውና። ዓለምን የናቀ ሰው እንዴት ስለሰፈር ያስባል!? መነኰሳት ከሰው ተለይተው፣ በገዳም ተከተው መኖር አለባቸው። ከሰው የሚለዩት ለምንድን ነው ከተባለ በመንግሥተ ሰማያት ከብረው ይኖሩ ዘንድ ነው። ከሰው የሚርቁት ሰውን ወደእግዚአብሔር ለማቅረብ ነው።
♥ፍትሐ ነገሥት ስለ መነኰሳት ምን ይላል♥
፨፨፨አንቀጽ 10 ስለ መነኮሳት፨፨፨
©መነኩሴ መኖር ያለበት በገዳም ነው።
©መነኮሳት ምድራውያን መላእክት ናቸው።
©ፈቃደ ሥጋን በመተው እግዚአብሔርን ብቻ የሚያገለግሉ ናቸው።
© መነኩሴ የማይነዋወጥ ጽኑ ሕሊና ሊኖረው ይገባል
© መንፈሰ ጋኔን ያደረበት ሰው አይመንኩስ
© መነኩሴ የሐዋርያትን ስራ ሊሰራ ይገባል።
© ከገዳሙ ፈቃድ ውጭ ማንም መነኮስ ከገዳሙ መውጣት አይችልም።
© መነኮሳት ለገዳሙ አስተዳዳሪ ይታዘዙ
© የመነኮሳት ልብሳቸውም ከደጓሳ ግምጃ የመናንያን ልብስ ይሁን።

ለገዳሙ አራሽ መነኮሳት በቀን ሁለት ጊዜ እንዲበሉ ይፈቀድላቸዋል። በ6 ሰዓት እና በ12 ሰዓት። ገበሬዎች ባይሆኑ ግን አንድ ጊዜ ይበቃቸዋል በ9 ሰዓት ወይም በ12 ሰዓት
አንድ ጊዜ ይብሉ። በአልጋ ሳይሆን በምድር ይተኙ። ሲተኙም ልብሳቸውን ከሰውነታቸው አያውልቁ። መነኮሳት ለየብቻቸው ይተኙ። የሞተ ሰው ከዘመዶቹ እንደሚለይ መነኩሴም ከዘመድ
ከወላጆቹ ፈጽሞ መለየት አለበት። ከሐዋርያት መካከል ይሁዳ እንደነበረ ሁሉ ከመነኮሳት መካከልም ምንኩስናን የማይወክል ስራ የሚሰሩ አንዳንድ መነኮሳት ቢኖሩ በተናጥል መናገር እንጂ
በጅምላ መነኮሳት እንዲህ ናቸው ማለት አይገባም።

ከመነኮሳት ጋር በማኅበር ሲኖር ቆይቶ መስፈርቱን አሟልቶ ብሕትውና የሚጀምር ሰው ባሕታዊ ይባላል። ባሕታዊ ማለት ብቸኛ ማለት ነው። የሚኖር ብቻውን በጫካ ከአራዊት ጋር
ስለሆነ ነው ይህ ስያሜ የተሰጠው። ፍጹምነትን የሚፈልግ ሰው ስለ እግዚአብሔር የመጣበትን መከራ ሁሉ ይቀበል።በጊዜው ሁሉ ለመሞት ዝግጁ ይሁን። መነኩሴ የምንኩስናውን ሕግ ንቆ
ከገዳሙ ቢወጣ በሕዝባውያን መዓርግ ይኑር።
ምንጭ፤ © በትረ ማርያም አበባው ካሣ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages