EOTCTV ሐምሌ ፱/፳፻፲፰ ዓ/ም
"ቤተ ክርስቲያን በዲጂታል ዓለም፣ የተቀናጀ የሚዲያ አገልገሎት ለተቀደሰ ዓላማ" በሚል መሪ ሐሳብ የውይይትና የሥልጠና መርሐ ግብር ተካሄደ።
የሥልጠናና የውይይት መርሐ ግብር በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ መመሪያ ሰጪነትና በአስተዳዳር ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ሐምሌ 3/2018 ዓ/ም የተከናወነ ሲሆን በሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት፣ ሚዲያና የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍሎች አዘጋጅነት የ8ቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የሚዲያና ለህዝብ ግንኙነት ሐላፊዎች የሀገረ ስብከቱ የሚዲያ ዋና ክፍል፣ የህዝብ ግንኙነት ዋና ክፍልና የስብከተ ወንጌል ክፍል ሠራተኞች የተሳተፉበት ነው።
በመርሐ ግብሩ በባለሙያዎች የውይይት መነሻ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ቤተ ክርስቲያን ከዘመናዊ የመገናኛ ብዙኃን ቴክኖሎጂዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ መሥራት እንደሚገባት ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂን፣ ማኅበራዊ ሚዲያንና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ን (AI) ለወንጌል ሥርጭት፣ ለምእመናን ትምህርትና ለተቋማዊ የመረጃ አገልግሎት በአግባቡ መጠቀም የዘመኑ ግዴታ መሆኑን አስረድተዋል።
በሥልጠናው የሚዲያ ፋይናንስ፣ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የተቋማዊ ምላሽ ፍጥነት፣ የሐሰት መረጃዎችን መከላከል፣ የሚዲያ ፖሊሲና የቁጥጥር ሥርዓት እንዲሁም የዲጂታል ሚዲያ ተግዳሮቶችና ዕድሎች በስፋት ተዳሰዋል።
በማጠቃለያው መምህር ኃይሉ ቤተክርስቲያን የዘመኑን የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ በመጠቀም፣ የሠለጠኑ የሚዲያ ባለሙያዎችን በማፍራትና የተቀናጀ የሚዲያ አሠራርን በመዘርጋት ወንጌልን ለብዙኃን ይበልጥ ተደራሽ ማድረግና ሕያውን ተልእኮ ማስፈጸም እንደምትችል ገልጸዋል።
በ«ቤተ ክርስቲያንና ዲጂታል ሚዲያ» በሚል ርእስ የሁለተኛውን ሥልጠና የሰጡት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ባለሙያ ዲያቆን ሙሉዓለም ዐሥራት የቤተ ክርስቲያን ዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም በተማከለ አሠራር፣ በግልጽ ፖሊሲና በሙያዊ ሥነ ምግባር ሊመራ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም የሳይበር ጥቃት፣ የሐሰት መረጃ ስርጭትና የዲጂታል ሚዲያ ሱስ ተቋሙ የሚገጥሙት ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በቤተ ክርስቲያናትና ገዳማት ስም የተከፈቱ አንዳንድ የሚዲያ ዓይነቶች ግልጽ የባለቤትነትና የተጠያቂነት ሥርዓት ባለመኖራቸው የቁጥጥር ክፍተት መፈጠሩ ገልጸው፣ የተቀናጀ የመረጃ አስተዳደር፣ ግልጽ ፖሊሲና ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ችግሩን ለመቅረፍ ወሳኝ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ለዚህም በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መመሪያ ሰጪነትና ክትትል ሰነዶችን በዲጂታል እንዲቀመጡ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲጠናከር ያደረጉ መሆናቸውን አስታውሰው በቀጣይ ከቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን አጠቃቀም አኳያ መመሪያው እየተዘጋጁ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊ የሆኑት መጋቤ ሐዲስ ዘለዓለም ምሕረቴ እየተከናወነ ባለው ሥራ ላይ ወደፊት በክፍለ ከተሞች፣ በአድባራትና በገዳማት የሚገኙ የሚዲያ መዋቅሮችን በማስተሳሰር የተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ሥራ እንደሚጠናከር ገልፀዋል።
በተጨማሪም የአቅም ግንባታ ሥልጠናው በየክፍለ ከተማው በመውረድ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በማጠቃለያው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ፣ የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ወንጌልን ማዳረስና ሰውን ማዳን መሆኑን በማስታወስ፣ የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ይህንን ተልዕኮ ለማሳካት የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። አክለውም ሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎችና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በአንድነት፣ በፍቅር፣ በሙያዊ ብቃትና በኃላፊነት ስሜት በመሥራት የቤተ ክርስቲያኒቱን እውነተኛ መልእክት ለሕዝቡ በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ እንዲያደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ፣ ሊቀ ትጉኃን ደመላሽ ቶጋ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል ሐላፊ፣ ሀገረ ስብከቱ ስብከተ የሕብ ግብር ኙነት ዋና ክፍል ሐላፊ መጋቤ ሐዲስ ዘለዓለም ምሕረቴ ፣ መምህር ኃይሉ በላይ የሀገረ ስብከት ሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊ ፣ የክፍላተው ከተማው ቤተ ክህነት የህዝብ ግንኙነት ሐላፊዎች፣ የሦስቱ ዋና ክፍሎች ሠራተኞች ተግኝተዋል ።
ምንጭ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት/Addis Ababa Diocese Media Service








No comments:
Post a Comment