የደብረ ወገግ አሰቦት ሥላሴ ገዳም መነኮሳት ጥሪ - EOTCMK TV የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, July 16, 2026

የደብረ ወገግ አሰቦት ሥላሴ ገዳም መነኮሳት ጥሪ - EOTCMK TV የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም

 





‘’አስከሬናቸው ሲገኝ የተወሰነ ሰውነታቸው በአውሬ ተበልቶ ነበር…ሌሊት ለጸሎት ቤተ ክርስቲያን ሲደወል ለመሄድ እየፈራን ነው። ምክንያቱም መቼ እንደሚያግቱንና እንደሚገሉን አናውቅም’’
የደብረ ወገግ አሰቦት ሥላሴ ገዳም መነኮሳት ጥሪ
ከ800 ዓመት በላይ የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው የደብረ ወገግ አሰቦት ሥላሴ ገዳም ውስጥ ስውራን አባቶች ፣ በበረሃ በኣት ዘግተው ለሀገርና ለዓለም የሚጸልዩ መነኮሳትና መነኮሳዪት ፣ ገዳማውያን ፣ የአብነት ትምህርት እንዳይነጥፍ ወንበር ዘርግተው ቀን ከሌት የሚያስተምሩ መምህራንና ደቀ መዛሙርት ፣ ለገዳሙ በስእለት የተሰጡ እንዲሁም ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ በርካታ ሕጻናት የሚያድጉበት ነው።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለገዳማት በሰጠችው ኃላፊነት መሠረት የገዳም ሥርዓት ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገር ብሎም በአበው መነኮሳት ጸሎት የሀገርና ወገን ሰላም እንዲጠበቅ የራሱን ጉልህ ሚና እየተወጣም ይገኛል።
ይሁን እንጂ ይህ አይነቱ መልካም ተግባር የማያስደስታቸው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ ታጣቂዎች ግን ዛሬም ድረስ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥቃቶች ሲፈጸሙበት ይታያል።
ለዚህ አንዱ ማሳያ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በገዳሙ ላይ ሲፈጸም የነበረው የእሳት ቃጠሎ ይገኝበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የገዳማውያኑ መግቢያና መውጫ ሰዓት እየተጠ መነኮሳትን ማገት እና መግደል ሲፈጸም ይታያል።
በያዝነው ዓመትም ጥቅምት 13 ቀን የገዳሙ መነኮሳት እንዲሁም በገዳሙ አቅራቢያ የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ታግተው ተወስደው ይህንን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ እነዚህ ሰዎች የት እንደደረሱ ማንም እንደማያቅ ለመረዳት ችለናል።
በዚህ ያላበቃው ጥቃት ዛሬም ድረስ ቀጥሎና በመሣሪያ ታጅቦ የደብረ ወገግ አሰቦት ሥላሴ ገዳምን ከተቀላቀሉ 7 ዓመት በዓት ከዘጉ ደግሞ ከ2 ዓመት በላይ የሆናቸውን አባ ወልደ ሚካኤል የተባሉ አንድ ባሕታዊ መነኩሴ በጥር መገባደጃው ላይ አምላካቸውን በጾምና በጸሎት በሚማጸኑበት በዚያው በአታቸው ውስጥ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን ከገዳሙ የወጡ መረጃዎች ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ደርሰውናል።
አስከሬናቸውም በሕክምና ተመርምሮ በጥይት መገደላቸው ተረጋገጠ በኋላ ሥርዐተ ቀብራቸው በገዳሙ ተፈጽሟል፡፡
አባ ወልደ ሚካኤል በተገደሉበት በአት ውስጥ አስክሬናቸው ሲገኝ የተወሰነ አካላቸው በአውሬ ተበልቶ ተመልክተናል የሚሉት የገዳሙ መነኮሳት በተፈጠረው ነገር በማዘን በአሁኑ ሰአት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነግረውናል።
በበርሃ ውስጥ የዱር አውሬን ተቋቁመው ፣ዳቤና እና ቆሎ እየተመገቡ በአት ዘግተው ከፈጣሪያቸው ጋር በጸሎትና በጾም የሚገናኙ መነኮሳትና መነኮሳይት በታላቁ ገዳም ውስጥ ይገኛሉ የሚሉት ገዳማውያኑ በሚፈጸሙት አሰቃቂ ጥቃቶች ምክንያት ነገ ባሕታውያኑ በሕይወት ስለመቆየታቸው ስጋት አለን ብለዋል።
‘’ሌሊት ለጸሎት ቤተ ክርስቲያን ሲደወል ለመሄድ እየፈራን ነው ምክንያቱም መቼ እንደሚያግቱንና እንደሚገሉን አናውቅም’’ ብለው የነገሩን የደብረ ወገግ አሰቦት ሥላሴ ገዳም መነኮሳት ሀገረ ስብከቱ ከመንግሥት የፀጥታ አካላት ጋር በመነጋገር ገዳሙ እንዲጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በገዳሙ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስቆም የምዕራብ ሔረርጌ ሀገረ ስብከት በዘህ ጉዳይ ምን እየሠራ ነው ስንል ለመጠየቅ ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና ጸሐፊ ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ በእጅ ስልካቸው ብንደውልም ሊያነሱልን አልቻሉም።
የደብረ ወገግ አሰቦት ሥላሴ ገዳም በ13ኛው መቶ ክፍለዘመን የተመሠረተ ሲሆን በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአህመድ ግራኝ እንደወደመ ፣ በ1928 ጣሊያን ፣ በ1969 ደግሞ የሶማሊያ ጦር ገዳሙን ለማጥፋት በአደረጉት ከፍተኛ ጥረት አደጋ ሲያንዣብብበት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ገዳሙ ከአዲስ አበባ ወደ ሐረር በሚወስደው መንገድ ላይ ሚኤሶ ወረዳ ሥር ያለ ሲሆን ከዋናው አስፓልት 17 ኪሎ ሜትሮች ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ይገኛል።
ምንጭ፤ EOTCMK TV የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages