ቅድስት ቤተክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለውን አንድ ሳምንት ሰሙና ሕማማት (የሕማማት ሳምንት) በማለት ትዘክረዋለች፡፡ ሕማማት የሚለው ቃል ‹ሐመ፤ ታመመ› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን፤
2/ በሌላም በኩል ይህ ሳምንት ከአዳምእስከ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነበሩ ነፍሳት በሲኦል የቆዩበት የአምስት ሺ አምስ መቶ የመከራ፤ የፍዳና የኵነኔ ዘመን መታሰቢያ ስለሆነ የሕማማት ሳምንት የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡
3/ እንደዚሁም ይህ ሳምንት ‹ቅዱስ ሳምንት›ይባላል፡፡ ከሌሎቹ ሳምንታት ሁሉየተለየየከበረነውና፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሳምንት በእያንዳንዱ ዕለት ስለ ፍጹምፍቅርየተከፈለየመሥዋዕትነት ሥራ ስለተሠራበት፤ የሰው ልጆች ድኅነት ስለተፈጸመበት፤ መድኃኔዓለም ስለእኛ ቤዛ ሆኖ ለመስቀል ሞት ታዛዥ ሆኖ ነፍሱን ስለካሰልን ‹ቅዱስ ሳምንት› ተብሏል፡፡
4/ በተጨማሪም ‹የመጨረሻ ሳምንት› ተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በመዋዕለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነት፤ የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመሆኑ ነው፡፡
በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምዕመናን በነግህ፤ በሠለስት፤ በቀተር፤ በተሰዓትና በሰርክ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመጓዝ ስለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡
ሰሙነ ሕማማት ለምን ይታሰባል?
ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ዐቢያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፤ ስብሐተ ነግህ አይደርስም፤ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፤ ጸሎተ አስተሥርዮም አይደረግም፡፡ እንዲሁም ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሳዕና ይከናወናሉ፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ እንዲከበር ይተላለፋል፡፡ ይህ ብያኔ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ዐቢያተ ክርስቲያናት ዘንድ የጸና መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡
ሕማምና ሞት የማይገዛው ጌታችንኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሕማምና ሞትለራሱ በማድረግ በዚህ ሳምንትለእኛቤዛሆኗል፡፡‹ደዌያችንንተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ ከዐመጸኞችምጋር ተቆጠረ፡፡እርሱግን ግፍን አላደረገም ተንኮልም ከክፉ አልተገኘበትም፡፡› (ኢሳ.42 4-12) ተብሎ እንተጻፈ፡፡ ምእመናን ክርስቶስ የተቀበለውን የእኛን ሕማም መሆኑን በማዘክር በሰሙነ ሕማማት ከማንኛውም የሥጋ ሥራ መታቀብ በዋዛ ፈዛዛ ባለመነጋገር፤ በሐዘን ልናከብረው ይገባል፤ ብድራትን የማያስቀረው አምላክም መተላለፋችንና በደላችንን በመደምሰስ የመንግሥቱ ወራሽ ያደርገናልና፡፡
ሰሙና ሕማማት እስከ አራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከጾሙ ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር፡፡ በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም ሕማማቱም ትንሣኤውም ተያይዘው እንዲከበሩ ተደረገ፡፡ ምዕራባውያን ከአርባ ጾም ውስጥ የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙና ሕማማት ያደርጉታል፡፡ የምሥራቃውያን /ኦሪየንታል/ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ዐቢያተ ክርስቲያናት የሆን ግን አርባውን ጾም ጨርሰን ከኒቆዲሞስ በኋላ ያለውን ተከታዩን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት አድርገን እናከብራለን፡፡ በእነዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በየዕለቱ ያከናወናቸው የድኅነት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
እሑድ፡- ሆሳዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ‹ሆሺዕናህ› የሚል ሲሆን ትርጉሙም ‹እባክህ አሁን አድን› ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ ‹እባክህ አሁን አድን‹እባክህ አሁን አቅና፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው፡፡› (መዝ.117 25-26) የሆሣዕና በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ ተለይም አእሩግና ሕፃናት ‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሳዕና በአርያም› በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሣዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተመሰገነው ምሥጋና ነው፡፡
ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የሆነ ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ ላይ እንደተቀመጠ ሁሉ ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት ዛሬም ያድራል፤ የሕሊና ሰላምን ይሰጣል ስለዚህ ንስሐ ገብተን ጌታችንን ሆሳዕና በአርያም እያልን ልናመሰግነው ይገባል፡፡
ሰኞ፡አንጽሖተ ቤተመቅደስና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ ያድራል፡፡ በማግሥቱም ከቢታኒያ ሲመጡ ተራበ (ማር.11፤11-12) ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፤
በለስ የተባለች ቤተ-እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች ሃይማኖትና ምግባር ናት፤ ከእስራኤል ፍቅርን፤ ሃይማኖትን፤ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፤ እስራኤል (ሕዝበ እግዚአብሔር) መባልን እንጂ፤ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ በመርገሙ ምክንያት እርሱ ከለያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት፡፡
በለስ ኦሪት ናት፤ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና፤ ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፤ ደኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡
በለስ ኃጢአት ናት፤ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ደስ ያሰኛል፤ ኋላ ግን ያሳዝናል፤ ወደ እርሷም ሄዶ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፤ ኃጥእ ከመባል በቀር በአንደበቱ ሐሰት፤ በሰውነቱ ክፋት እንዳልተገኘበት ለማመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፤ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፤ ስትረገም ፈጥና መድረቋም፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ ካሣነት እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ቤተመቅደስ ሄደ፤ ቤተመቅደስ፣ቤተጸሎት፣ ቤተመሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፤ ይህም የሚያሳየው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡
በዚህ በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቤተ-ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፤ በሠለስተ፣ በሰድስቱ ሰዓት፤ በተሰዓቱ ሰዓትና በሠርክ መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፤ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ ምክንያቱም የደረሰብን መከራ ኀዘኑን እና 5ሺ ከ5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ይኖር እንደነበረ ለማዘከር ነው፡፡
ይቆየን
በስመዓብ በወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኦርቶዶክስ መንፈሳዊ የሬድዮ ፕሮግራም ቢከፈት ከቴሌቪዥን በበለጠ በሁሉም ህዝበ ክርስቲያን ተደራሽ ይሆናልና ለምን አልታሰበበትም ቢከፈት እጅግ ለክርስትናች መስፉፉት ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ
ReplyDelete