አባ ኖቭ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, April 15, 2020

አባ ኖቭ


ሐምሌ ፳፬ (24) አባ ኖብ (ኖቭ) ፃድቅ ዘግብጽ ንሂንሳ በሰማዕትነት አረፉ ☞ “የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ” ት/ዳን.፫፥፲፯¬-፲፰ (3፥17¬-18) ☞ ኖቭ ማለት ጽሩይ ወርቅ ማለት ነው። ሀገራቸው ደቡብ ግብጽ ንሂሳ ነው። በዘመነ ዲየዮቅልጥያኖስ ዓላውያን አብየያተ ክርስቲያናትን ሲያፈርሱ የምዕመናን ደማቸውን ሲያፈርሱ በመንፈሳዊ ቅናት ተነሳስተው ለመመስከር ወደ ገምኑዲ ሄዱ። የጣዖትን ከንቱነት የእግዚአብሔርን አምላክነት ሲመሰክሩ መስፍነ ብሔሩ ሉኪዮስ ፈጣሪህን ክደህ ለጣዖት ስገድ አላቸው። ፈጣሪዬን አልክድንም ለጣዖት አልሰግድም አሉ። በሰይፍ እቀጣሃለሁ አላቸው። ከዚህ ሁሉ አምላክ እንደሚያድን አምናለሁ። ያገኛቸው መርከብ ሲሳፈር ነበርና በመርከቡ ምሰሶ ቁልቁል አሰቅሎ ሥጋቸው እስኪተፈተፍ ድረስ አስገረፋቸው። ☞ ከዚህ በኋላ ብላቴኖቹ ምግቡን መጠጡን አቀረቡለት። እመገባለሁ ቢል ድንጋይ ሆኖበታል። ብላቴናዎቹም ዓይናቸው ታውሯል። እሳቸው ግን የታዘዘ መልአክ ፈውሶ ከስቅላት አውርዷቸዋል። ምድረ አትሪክ ሲደርሱ ወደ ጌታ ቢያመለክቱ ብላቴናዎቹ ዓይናቸው በርቶላቸዋል። በአምላካቸው አምነው አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተው በሰማዕትነት አርፈዋል። ☞ አባ ኖቭን ወይም ኖብን ግን ሥቃዩ ይጽናበት ብሎ በብረት አልጋ በብረት ችንካር ቸንክሮ እሳት አስነደደባቸው። መልአኩም መጥቶ ፈወሳቸው። የተቀበሉት መከራ ይህ ብቻ አይደለም። ዓይን ከማየት ጆሮ ከመስማት እንዳያቋርጥ እሳቸውም ስመ እግዚአብሔርን ጠርተው አምላክነቱን መስክረው ከመሰቃየት ያረፉበት ጊዜ አልነበረም። ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታ በቃል ኪዳነቸው የተማጸነውን ሁሉ እሳቸው ከገቡበት መካነ ዕረፍት እንዲያገባላቸው ተስፋቸውን ነግሮሯቸው አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተው በሰማዕትነት አርፈዋል። በሺህ የሚቆጠሩ አማንያንም አሠራቸውን ተከትለው አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተው በሰማዕትነት አርፈዋል። ☞ የነበሩበት በ፬ኛው (4ኛው) ም/ዓመት ድ/ል/ክ ሲሆን በሀገራችን በቡልጋ ውስጥ እቲሳ አከባቢ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት የትውልድ ገዳም ወደ ማዶ በስማቸው የታነጸ ቤተ ክርስቲያን በነብርና አንበሳ የሚጠበቅ አለ። ☞ የጻድቁ ሰማዕት አባ ኖቭ ጣዕመ ገድላቸው፣ መዓዛ ሕይወታቸው፣ ትሩፋታቸው አይለየን፤ የአቁራሪተ መዓት፣ መዝገበ ፀሎት፣ ሰዓሊተ ምህረት የድንግል ማርያም አማላጅነቷ ለዘወትር ከሁላችን ጋር ይሁን። የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔርም ፍጹም ምህረት ቸርነት ይብዛልን አሜን ይቆየን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages