ህያውን ከሙታን መካከል ለምን ትፈልጋላችሁ?
እንደተናገረ ተነስቷል
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላምና በፍቅር
አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
የዓለማት ሁሉ ፈጣሪ : የዘለዓለም አምላክ ወልድ
ዋሕድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ዕለት መግነዝፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በባሕርይ ኃይሉና ሥልጣኑ ተነስቷልና እንኳን ደስ አለን::
ከዚህ በኋላ ለ፶ ቀናት እንዲህ እያልን ሰላምታ እንለዋወጣለን:-
ክርስቶስ ተንስአ እሙታን፣
በዐቢይ ኃይል ወስልጣን፣
አሠሮ ለሰይጣን፣
አግዐዞ ለአዳም፣
ሰላም፣
እምይእዜሰ፣
ኮነ፣
ፍሥሐ ወሰላም!
በእርግጥም አምላካችን በሞቱ ሞትን ገድሎ በትንሣኤው ሕይወትን አድሎናልና ደስታ ይገባናል:: መድኃኔ ዓለም በኅቱም ድንግልና እንደ ተወለደ በኅቱም መቃብር ተነስቷል::
ለደቀ መዛሙርቱም "ሰላም ለእናንተ ይሁን" ሲል በዝግ ደጅ ገብቷል::
በዕለተ ትንሣኤው የመጀመሪያውን ደስታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተካፍላለች:: የእርሷን ያህል በሃዘን የተጐዳ የለምና:: ቀጥለው ቅዱሳት አንስት እነ ማርያም መግደላዊት
ትንሣኤውን አይተዋል:: ሰብከዋልም::
በዚች ቀን ማዘን አይገባም:: በትንሣኤው
የደነገጡና የታወኩ የአጋንንትና የአይሁድ ወገኖች ብቻ ናቸውና::አምላካችን ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በረከት አይለየን:: በዓሉንም የሰላም : የፍቅርና የበረከት ያድርግልን:: የጌታችን በጐ ምሕረቱ በሁላችን ትደርብን::
"ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም:: 'የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ
አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል: በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው' እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደተናገረ አስቡ::"
(ሉቃ. ፳፬፥፭-፰) "አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነስቷል:: ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኗልና:: ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና::"
(፩ቆሮ. ፲፭፥፳)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment