ፍትሐት ማለት ከዚህ ዓለም በሞት ለሚለዩ ሰዎች በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ከሠሩትና ከፈጸሙት በደል እንዲነጹ ከማእሠረ ኃጢአት እንዲፈቱ ወደ እግዚአብሔር የሚቀብ ጸሎት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለሙታን ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ ታዝዛለች፡፡ ጸሎተ ፍትሐት ለበደሉት ሥርየት ኃጢአትን፣ ይቅርታን ዕረፍተ ነፍስን ያሰጣል፡፡ ለደጋጎች ደግሞ ክብርን፣ ተድላን፣ ዕረፍትን ያስገኛል፡፡
ሙታንና ሕያዋን የሚገናኙት በጸሎት አማካኝነት ነው፡፡ ሕያዋን ለሙታን ይጸልያሉ፤ ሙታንም ለሕያዋን ይለምናሉ፡፡ /ሄኖ. 12፤34/ ሕያዋን ለሙታን የሚጸልዩት ጸሎትና የሚያቀርቡት መሥዋዕት በግልጽ እንደሚታይ ሁሉ ሙታንም በአጸደ ነፍስ ሆነው በዚህ ዓለም ለሚቆዩ ወገኖቻቸው ሕይወትና ድኅነትን፣ ስርየተ ኃጢአትንና ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን፣ ጽንዓ ሃይማኖትን እንዲሰጣቸው፣ በንስሐ ሳይመለሱ፣ ከብልየተ ኃጢአት ሳይታደሱ እንዳይሞቱ ፈጣሪያቸውን ይለምናሉ፡፡ ይህም ሥርዓት እስከ ዕለተ ምጽአት ሲፈጸም የሚኖር ነው፡፡ ለሙታን ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ፣ መሥዋዕት እንዲቀርብላቸው በቤተ ክርስቲያንና በመካነ መቃብራቸው እንዲጸለይላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት በቀኖና ሐዋርያት አዝዘዋል፡፡ በክርስቶስ አምነው ስለሞቱ ወንድሞቻችሁ ክርስቲያኖችና ሰማዕታት በቤተ ክርስቲያን ያለሐኬት ተሰብሰቡ፡፡ በቤተ ክርስቲያን መሥዋዕት ሠውላቸው፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወደ መቃብር ስትወስዱአቸውም መዝሙረ ዳዊት ድገሙላቸው፡፡ ዲድስቅልያ አንቀጽ 33 ገጽ 481 ነቢዩ ዳዊትም የጻድቅ ሞቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ነው፡፡ ነፍሴ ሆይ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሽ፣ እግዚአብሔር ረድቶሻልና፣ ነፍሴን ከሞት አድኖአታልና፡፡ በማለት ሙታን በጸሎት፣ በምስጋና፣ በመሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር እንዲሸኙ በመዝሙሩ ተናግሯል፡፡ /መዝ. 115፤114-7/ የቤተ ክርስቲያን የሕግና የሥርዓት መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥትም በፍትሕ መንፈሳዊ በዲድስቅልያ የተጠቀሰውን ያጸናል፡፡ /አንቀጽ 22/ ስለ ሙታን የሚጸለየው መጽሐፈ ግንዘትም ካህናት ለሞቱ ሰዎች ሊጸልዩላቸው፣ በመሥዋዕትና በቁርባን ሊያስቧቸው ይገባል ይላል፡፡ ካህናት ጸሎተ ፍትሐት በሚያደርጉላቸው መሥዋዕት እና ቁርባን ስለ እነርሱ በሚያቀርቡላቸው ጊዜ መላእክት ነፍሳቸውን ለመቀበል ይወርዳሉ፡፡ ኃጢአተኞች ከሆኑ ስለ ሥርየተ ኃጢአት ይለምኑላቸዋል፤ ይማልዱላቸዋል፡፡ ንጹሐንም ከሆኑ ደስ ይላቸዋል፡፡ ሰውን ለወደደው ለእግዚአብሔር በሰማያት ክብር ምስጋና ይገባል፣ በምድርም ሰላም፡፡ እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ ይህም የመላእክት ምስጋናና ደስታ ስለ ሰው ልጅ ድኅነት ነው ተብሎ ተጽፎአል፡፡ የደጋግ ሰዎችን ነፍሳት ቅዱሳን መላእክት እንደሚቀበሏቸው በቅዱስ ወንጌል ተጽፎአል፡፡ አልዓዛርም ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም ዕቅፍ ወሰዱት፡፡ /ሉቃ. 16፤22/ ጸሎተ ፍትሐት የዘሐን ጊዜ ጸሎት ነው፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በእናንተ ባለው መሠረት ከመንጋው መካከል በሞተ ሥጋ የተለዩትን ምእመናን በጸሎትና በዝማሬ እንሸኛቸዋለን፡፡ /ያዕ. 5፤13/ ጸሎተ ፍትሐት የሚደረገው ለከሀድያንና ለመናፍቃን ሳይሆን ለሃይማኖት ሰዎች ነው፡፡ ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፣ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል፡፡ ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፡፡ ስለዚህ እንዲጠይቅ አልልም፡፡ ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፡፡ ሞትም የማይገባው ኃጢአት አለ፡፡ /ዮሐ. 5፤16/ ለምሳሌ በተለያየ መንገድ ራሱን ለገደለ ሰው ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ምክንያቱም ቤተ መቅደስ ሰውነቱን በገዛ እጁ አፍርሷልና፡፡ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖራችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ፡፡ ይላልና፡፡ /1ቆሮ. 3፤16/ እንዲሁም ለመናፍቃን፣ ለአረማውያንም ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ምክንያቱም ብርሃን ከጨለማ ጋር አንድነት የለውምና፡፡ /2ቆሮ. 6፤14/ ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጅ የማትጸልይበት ጊዜ የለም፡፡ ሰውን ያህል ክቡር ፍጥረት ከመጸነሱ በፊት የተባረከ ጽንስ እንዲሆን እንደ ኤርምያስ በማኅፀን ቀድሰው /ኤር. 1፤5/ እንደ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ በማኅፀን መንፈስ ቅዱስን የተመላ አድርገው እያለች ትጸልያለች፡፡ በወሊድ ጊዜም ችግር እንደያጋጥመው ትጸልያለች፣ በጥምቀትም የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን ትጸልያለች፣ ታጠምቃለች፡፡ በትምህርት እየተንከባከበች ጸጋ እግዚአብሔርን እየመገበች ታሳድጋለች፡፡ እርሷ የጸጋው ግምጃ ቤት ናትና፡፡ በኃጢአት ሲወድቅም ኃጢአቱ እንዲሠረይለት ንስሐ ግባ ትለዋች፡፡ እንዲሠረይለትም ትጸልያለች፡፡ በሞቱም ጊዜ እግዚአብሔር ኃጢአቱን እንዳይዝበት በደሉን እንዳይቆጥርበት ትጸልይለታለች፡፡ እንዲህ እያደረገች የእናትነት ድርሻዋን ትወጣለች፡፡ አንድ ሰው ሲሞት ዘመድ አዝማድ በዕንባ ይሸኘዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ዕንባዋ ጸሎት ነውና በጸሎቷ የዚያን ሰው ነፍስ ለታመነ ፈጣሪ አደራ ትሰጣለች፣ ነፍሳቸውን ተቀበል ብላ ትጸልያለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐትን የምታደርገው ይሆናል ይደረጋል ብላ በፍጹም እምነት ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን እስከ መጨረሻ ተስፋ አይቆርጥምና፡፡ ወኵሎ ዘሰአልክሙ በጸሎት እንዘትትአመኑ ትነሥኡ፡፡ በሃይማኖት ጸንታችሁ የለመናችሁትን ሁሉ ታገኛላችሁ፡፡ /ማቴ.21፤22/ ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የጸለያችሁትን ሁሉ እንዳገኛችሁ እመኑ ይሁንላችሁማል፡፡ /ማር.11፤24/ ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል፤ የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና የሚፈልገውም ያገኛል፡፡ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል፡፡ /ማቴ. 7፤7/ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ፡፡ /ዮሐ. 14፤13/ ይላልና፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስም በመልእክቱ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታወቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ፡፡ በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፡፡ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል፡፡ የምንለምነውንም እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደተቀበልን እናውቃለን፡፡ /ዮሐ. 5፤3/ ብሏል፡፡ እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቷ ሙሴን ከመቃብር አስነሥቶ ፊቱን ያሳየ አምላክ /ማቴ 17፤3/ ለእነዚህም ሳይንቃቸው የምሕረት ፊቱን ያሳያቸዋል የሚል ነው፡፡ መሐሪ ይቅር ባይ ለሆነው አምላክ የሚሳነው ነገር የለምና፡፡ /ዘፍ. 18፤13፣ ሉቃ. 1፤37/ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚህ እንዲጠይቅ አልልም፤ እንዳለ ቤተ ክርስቲያንም የምትከተለው ይህንኑ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቷቸው ከኃጢአት መመለስ ከበደል መራቅ፣ ንስሐ መግባት፣ ሥጋወደሙን መቀበል ሲችሉ በሕይወታቸውና በእግዚአብሔር ቸርነት እየቀለዱ መላ ዘመናቸውን የሚያሳልፉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህም በራሳቸው ላይ የፈረዱ ናቸው፡፡ ደግሞም ስሞት በጸሎተ ፍትሐት ኃጢአቴ ይሰረይልኛል ኃጢአትንም አልተውም ማለት በእግዚአብሔር መሐሪነት መቀለድና እርሱንም መድፈር ስለሆነ ይህም ሞት ከሚገባው ኃጢአት የሚቆጠር ነው፡፡ እንግዲህ ለበጎ የተሠራልንን ጸሎተ ፍትሐት ክብር የምናገኝበት ያደርግልን ዘንድ የእግዚአበሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡ ምንጭ፡-ሃይማኖት የለየንን መቃብር አንድ አያደርገንም፤ ገጽ 20
|
No comments:
Post a Comment