አትሮንስ ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም
ሰበር ዜና፦ ገበገባኒ (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓል አከባበር ሥርዓት እና ባህል ከነትርጓሜው) ክፍል አንድ
አዲስ መጽሐፍ በገበያ ላይ ዋለ
አዘጋጅ፤ መምህር ቀለመ ወርቅ ደምሌ (ጥር 2010 ዓ/ም)
አሳታሚ፡ መምህር ቀለመ ወርቅ ደምሌ
ዋጋ፤ 120 ብር
የገጽ ብዛት፤ 308
እሁድ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገበገባኒ የተሰኘውን መጽሐፍ ምርቃት እንዲታደሙ ጥሪ የተደረገላቸው በመንበረ መንግስት መድሃኔዓለም አዳራሽ መሰብሰብ የጀመሩት እንግዶች ማለትም ከተለያየ አብያተ ክርስቲያናት የመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፤ የጎንደር አብያተ ክርስቲያናት አለቆች፤ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናት እንደየ ማዕረጋቸው፤ የቤተክርስቲያን ምዕመናን እናቶች፤ አባቶች እና የቆሎ ተማሪዎች፤ ወጣቶች ከትንሽ እስከ ትልቅ ቦታ እስኪጠብ ድረስ ሞልቶ ነበር። ከአዳራሹ ውጭም በበሩና በመስኮቶቹ አካባቢ በታዳሚ ተጨናንቆ ውሏል።
የመጽሐፉ ምርቃት ፕሮግራም በጸሎት ከጀመረ በኋላ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ከተደረገ በኋላ የዕለቱ ፕሮግራም ተጀመረ። በዕለቱ የመጽሐፍ ምርቃት መርሐ ግብር የታደሙት አባቶችም መጽሐፉ ንባብ ብቻ ሳይሆን አንድምታ አዘል በመሆኑ አዘጋጁን አድንቆ ዝም ማለት ሳይሆን ብዙ ድካም የፈሰሰበት መሆኑን ገልጸው መጽሐፉን ገዝተን ብናነብ እና እውቀት ብንሸምትበት ለአዘጋጁም ታላቅ ደስታ ይሆናል እንዲሁም ሌሎች መጻሕፍትንም እንዲያዘጋጁ ያበረታታቸዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ስለ መጽሐፉ ትርጉም እና በውስጡ የያዛቸው መንፈሳዊ ቁም ነገሮች በሰፊው ዳሰሳ እናደርጋለን::
ስለ መጽሐፉ አስተያየት ከሰጡ መካከል
ዶ/ር ያረጋል አበጋዝ ስለዚህ መጽሐፍ ያላቸው አስተያየት
የድጓል የተክሌ (ቤተ ማርያም) አቋቋም እና የመጽሐፉ መምህር የሆኑት መምህር ቀለመ ወርቅ ደምሌ በዜማ እውቀት ከበለጸጉ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት አንዱ ሲሆኑ ክርስቲያናዊ የሆኑ በዓላት ያላቸውን ትርጉምና መንፈሳዊ ሀብት ከዚህም ጋር በይትበሃል በሥርዓተ አምልኮ መልክ የሚለለጸውንና በዕለት ተዕለት ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚኖረውን ሕያው የክርስትና ሕይወት የሚያብራራ መጽሐፍ ጽፈው ለአንባብያን ሲያቀርቡ ማየት ደስ የሚያሰኝ ተግባር ነው። ይህ ገበገባኒ በሚል ርዕስ ያዘጋጁት መጽሐፋቸውም ዋና ዋና የሆኑትን በዓላት ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘት እንዲሁም በዓላቱ ያላቸውን ይትበሃላዊ ገጽታ በመልካም ሁኔታ የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው። መምህር ቀለመ ወርቅ ደምሌ ለወእፊቱም በመሰል ጉዳዮችም ሆነ በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደዚሁ መጻጅፍትን በማዘጋጀት እንደሚያስነብቡን ተስፋ አደርጋለሁ ብሏል።
ይቆየን……..…
No comments:
Post a Comment