ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ክፍል ፫ (ከመምህር ዘለዓለም ገጽ የተወሰደ)
የመጀመሪያዋ የሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን አሠራርዋና ምሳሌዋ
ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ እንዲሁ የተሠራ ሳይሆን ከጉልላቱ እስከ መሠረቱ ድረስ በምስጢርና በምሳሌ የተከናወነ ነው የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የተሠራችው ፊልጵስዩስ በተባለች ቦታ በሦስት ደንጋዮች ብቻ ሲሆን የሠሯትም ከአናጕሥጢስነት እስከ ፓትርያርክነት ድረስ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ናቸው ሲሠሯትም ቁመቷን ፳፬ ስፋቷንና ወርዷን አሥራ ሁለት ክንድ አድርገው እንዲሠሩ ያዘዛቸው ራሱ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ነው እመቤታችን ባረገች በአራተኛው ዓመት በ53 ዓ.ም ሰኔ ሃያ ቀን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ተጀምሮ በዚያው ዕለት በአንድ ቀን ተፈጽሟል በሃያ አንደኛው ቀን እመቤታችን ጽላት (ታቦት) ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ ጌታ ዐቢይ ካህን ሁኖ ቀድሶ አቊርቧቸዋል “እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ” ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንዲህ አድርጋችሁ ሥሩ ብሏቸው የቤተ ክርስቲያንን አሠራር አሳይቷቸው ዐርጓል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሠራት የተጀመረም ከዚያ ወዲህ መሆኑን የቤተ ክርስቲያኗ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ሐዋርያት በደረሱበት ቦታ ያስተምሩ ያጠምቁ ሥጋውን ደሙን ያቀብሉ ነበር እንጅ ታቦት መንበር ንዋየ ቅድሳት አላስፈለጋቸውም ይህን ኃላፊነት ከቦታው ላይ ሹመዋቸው ለሚሄዱት ደቀ መዛሙርቶቻቸው ይተውት ነበር እንዲህ ማለት ግን ያላመነውን ለማሳመን ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከአንዱ ቦታ ወደሌላኛው ቦታ ስለሚፋጠኑ እንጅ ጽላት የማያስፈልግ ሁኖ አይደለም እንደዚያማ ቢሆን ሲኖዶስ በተባለው የሥርዓት መጽሐፋቸው ስለጽላት አቀራረጽ ስለቤተ ክርስቲያን ዐሠራር ሥርዓት ወስነው አያልፉም ነበር ጌታም የቤተ ክርስቲያንን አሠራር አሳይቶ እንዲህ ሥሩ ያላቸው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለአምልኮት መፈጸሚያ አስፈላጊ ስለሆነ ነው ፡፡
በሦስት ደንጋዮችም የተሠራችበት ምክንያት የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማር ለማስረዳት ነው ሦስቱ ደንጋዮች ከታች አቀማመጣቸው ሦስት ሁኖ ከላይ ጉልላቱ አንድ ነበር ደንጋዮቹ ከታች ሦስት መሆናቸው ሥላሴ በስም ፣ በግብር ፣ በአካል ሦስት መሆናቸውን ጉልላቱ አንድ መሆኑ በሥልጣን በፈቃድ በአገዛዝ በመለኮት ይህን በመሳሰለው አንድ መሆናቸውን ለማስረዳት በዚህ መስሎ ለማስተማር እንዲመች ነው ፡፡
ይህንም አባ ጽጌ ድንግል ማኅሌተ ጽጌ በተባለው ድርሰቱ እንዲህ ሲል ገልጾታል “በሠላስ አዕባን ገጸ ሥላሴሁ ለአምሮ ሐኒጸ ቤትኪ ድንግል ድኅረ ፈጸመ ሣርሮ አመ ወረደ ለበዓል ምስሌኪ በአማኅብሮ ” አንድነቱንና ሦስትነቱን ለማስረዳት በሦስት ደንጊያዎች በእምቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያኗን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ በሃያ አንደኛው ቀን በዓሉን ለማክበር መውረዱን እንዲህ ሲል ገልጾታል ፡፡
ዛሬም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ ሦስት ክፍል ሦስት በር አንድ ጉልላት ሊኖረው ይገባል የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የምንረዳበት የምንማርበት ነውና ፡፡
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን ሦስቱ በሮች ለሥላሴ ምሳሌ መሆናቸውን አባ ጊዮርጊስ “ለቤተ ክርስቲያን ሥላሴ አናቅጺሃ አንትሙ ሱራፌልኒ በቅዳሴሆሙ ያኤምሩ ግጻዌክሙ”ሥላሴ የቤተ ክርስቲያን በሮች እናንተ ናችሁ ማለት ሦስቱ በሮች የናንተን ሦስትነት ያስረዳሉ ሱራፌልም ሦስት ጊዜ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ማመስገናቸው ሦስትነታችሁን ለማስረዳት ነው ሲል ሦስቱ የቤተ ክርስቲያን በሮች የሥላሴን ሦስትነትእንደሚያስረዱ ገልጾታል ፡፡ የሕንፃው ቁመት በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይና በሃያ አራቱ ነቢያት ፣ ወርዱና ስፋቱ በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ቁጥር ልክ የተወሰነበትም ምስጢር እስከ ዕለተ ምጽአት ቤተ ክርስቲያን የምትተዳደርበትን ሥርዓት የሠሩ ነቢያት ሐዋርያት ስለሆኑ ቤተ ክርስቲያን ከነቢያትና ከሐዋርያት ከካህናተ ሰማይ ሥርዓት የወጣ ሥርዓት የላትም ሥርዓቷ ከነሱ የተገኘ ነው ለማለትና ነቢያት ሐዋርያት ካህናተ ሰማይ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምንጮች መሆናቸውን ለማስረዳት ነው ፡፡ በፍትሐ ነገሥትም የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምንጮች የነቢያት መጻሕፍት (ብሉይ ኪዳን)የሐዋርያት መጻሕፍት (ሐዲስ ኪዳን) የሠለስቱ ምዕትና የሌሎችም ሊቃውንት መጻሕፍት መሆናቸው ተገልጾአል ፡፡ በማኅሌቱና በሰዓታቱ በቅዳሴው በኩል ላለው ሥርዓትም ምንጮቻችን የጌታን ዙፋን የተሸከሙት ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ሱራፌል ናቸው ዛሬ ላይ ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ካህናትና ዲያቆናት የሰዓታቱን የማኅሌቱን የኪዳኑን ሥርዓት የወረሱት በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ስለሆነ ቅዱስ ያሬድም ይህን ሥርዓት ያመጣው ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ በመሆኑ የቁመቱ የወርዱ የስፋቱ መጠን በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ በሃያ አራቱ ነቢያት (በመጽሐፈ ነገሥትያሉ) በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ቁጥር ልክ የሆነበት ምሥጢር ይህ ነው ::
Post Top Ad
Thursday, June 3, 2021
Tags
# ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን
Share This
About አትሮንስ ሚዲያ
ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን
Labels:
ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Post Bottom Ad
Author Details
Templatesyard is a blogger resources site is a provider of high quality blogger template with premium looking layout and robust design. The main mission of templatesyard is to provide the best quality blogger templates which are professionally designed and perfectlly seo optimized to deliver best result for your blog.
No comments:
Post a Comment