የነገረ መለኮት ሊቅ፣ በዕውቀቱ እጅግ የመጠቀ በቅድስናውም "ምድራዊያን መላእክት" ከተባሉት ፍጹማን ውስጥ አንዱ የሆነው ቅዱስ ባስልዮስ የሰይጣንን የጽሕፈት ደብዳቤ በጸሎቱ በመደምሰስ ድንቅ ተአምር ያደረገበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፡- አንድ ጎልማሳ አገልጋይ የጌታውን ልጅ ስለወደዳት እርሷን ለማግኘት ሲል ወደ አንድ ሥራይኛ ዘንድ ሄደ፡፡ ሥራየኛውም ከአጋንንት ጋር ኅብረት ነበረውና ወጣቱን "እምነትህን ክደህ እኔ የማዝህን ብቻ ከፈጸምክ የጌታህን ልጅ በእጅህ አስገባልሃለሁ" አለው፡፡ ወጣቱም "ያልከኝን እፈጽማለሁ" ብሎ ከጠንቋዩ ጋር ተስማማ፡፡ ከዚህም በኃላ ሥራይኛው የክህደት ደብዳቤ ጽፎ ለወጣቱ ሰጠውና ወደ አረሚ መቃብር ሄዶ በመንፈቀ ሌሊት ደብዳቤዋን ይዞ በመቃሩ እንዲቆም አዘዘው፡፡ ወጣቱም እንደታዘዘው ባደረገ ጊዜ ከሰይጣናት አንዱ መጥቶ ወደ አለቃቸው አደረሰውና ያችንም የክህደት ደብዳቤም ከእጁ ወሰዳት፡፡ ሰይጣንም ‹‹የፈለከውን አደርግልሃለሁ ነገር ግን ምላክህን ክርስቶስን ትክደዋለህ ፈቃድህን ከፈጸምኩልህ በኋላም ወደ እርሱ አትምለስም›› ሲለው ወጣቱም በልጅቷ ፍቅር አብዶ ነበርና ‹‹አዎን ጌታዬ ያዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ›› አለው፡፡ ሰይጣኑም ‹‹ይህን ልታደርግ በእጅህ ጻፍልኝ›› አለውና አጻፈው፡፡
ከዚህም በኋላ ሰይጣን በጌታው ሴት ልጅ ልብ ውስጥ አደረና ያንን ወጣት እጅግ ወደደችው፡፡ የፍትወት እሳትንም በልቧ ላይ ስላነደደባት መታገስ አልቻለችምና ወደ አባቷ ቀርባ ልጁን አጋባኝ አለችው፡፡ የልጁም ፍቅር በየዕለቱ ይጨምርባት ነበርና ራሷን እንዳታጠፋ ቤተሰቦቿ አጋቧት፡፡ ከእርሱ ጋር መኖር ከጀመረች በኋላ ሲያማትብ እንኳን አይታው አታውቅም ነበርና ስትመረምረው ክርስቲያን አለመሆኑንና ያደረገውንም ሁሉ ነገራት፡፡ ይህንንም ስትሰማ እጅግ ደንግጣ ወደ አገሯ ሊቀ ጳጳስ ወደ ባስልዮስ ዘንድ ሄዳ ከእግሩ ሥር በመውደቅ የደረሰባትን በመንገር ከሰይጣን እጅ እንዲያድናት ለመነችው፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም በሏ የሆነውን የአባቷን ባርያ አስመጣውና በንስሓ ተመልሶ ክርስቲያን መሆን እንደሚፈልግ ጠየቀው፡፡ ወጣቱም ፈቃደኝነቱን ሲገልጥለት በአንድ ቦታ ውስጥ አስገብቶ ዘጋበትና ከላይ በመስቀል ምልክት አተመበት፡፡ እንዲጸልይም አዘዘው፡፡
ቅዱስ ባስልዮስም ስለ ወጣቱ ብዙ ጸለየ፡፡ ከሦስት ቀንም በኋላ ጎበኘውና በ፫ቱ ቀን የደሰበትን ጠየቀው፡፡ ወጣቱም በላዩ በመጮህ ሰይጣናት ሲያስፈራሩት ያንንም ደብዳቤ ሲያሳዩትና በእርሱ ላይ ሲቆጡ በመከራ ውስጥ እንደኖረ ነገረው፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ‹‹ከሰይጣናቱ ቁጣ የተነሣ አትፍራ አይዞህ እግዚአብሔር ይረዳናል›› ብሎ ጥቂት ከመገበው በኋላ መልሶ ዘጋበትና ሄዶ ይጸልይለት ጀመር፡፡ ዳግመኛም ከ፫ ቀን በኋላ መጥቶ ጠየቀው፡፡ ወጣቱም ‹‹የአጋንንቱን ጩኸታቸውን እሰማዋለሁ ነገር ግን አላያቸውም›› አለው፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ አሁንም ጥቂት ከመገበው በኋላ መልሶ ዘጋበትና እስከ ፵ ቀን ድረስ እንዲሁ አደረገ፡፡ ከ40 ቀንም በኋላ መልሶ ሲጠይቀው ወጣቱ ‹‹ቅዱስ አባቴ ሆይ ስለ እኔ ሰይጣንን ስትጣላውና ድል አድርገህ ጥለህ ስትረግጠው በዛሬዋ ሌሊት አየሁ›› አለው፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ይህን ሲሰማ እጅግ ደስ አለው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችንም ጠርቶ እግዚኦታ አደረሱና ከእግዚኦታው በኋላ ያ ወጣት ጽፎ ለሰይጣን የሰጠው የክህደት ደብዳቤ ከሰይጣን እጅ ተወስዶ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ወደቀ፡፡ ሁሉም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ ይኸውም የተደረገው መስከረም ፲፫ ቀን ነው፣ ዜና ሕይወቱን በዕረፍቱ ዕለት ጥር ፮ ስንክሳር ላይ ተዘግቧል፡፡
አቡነ ባስልዮስ ዘቂሳርያ
መስከረም ፲፫ በዚች ዕለት አባ ባስልዮስ ቅዳሴ ባስሊዮስን በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ጽፏል።
ቅዱስ ባስልዮስ አባቱ ኤስድሮስ ሲሆን እርሱም የከበረ ቄስ ነው፡፡ ባስልዮስ፣ ጎርጎርዮስ፣ ጴጥሮስ፣ ኬርዮን፣ መክርዮን የተባሉ አምስት ልጆችን የወለደ ሲሆን ሁሉም ከፍጹምነት የደረሱ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ይህም ባስልዮስ መንፈስ ቅዱስ ሞልቶበት የታወቀች ቅዳሴውን ደረሰ፡፡ እግዚአብሔርም በእጆቹ ብዙ አስደናቂ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ሊሠርቁ የመጡትን ሌቦች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ በጸሎቱ በሩን ዘግቶባቸዋል፡፡ በኋላም ምእመናን ሲመጡ በሩን ከፍቶላቸዋል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ መሆኑን ነው፡፡ የታላቁ አባት የቅዱስ ኤፍሬምም መምህሩ ነው፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ያደረጋቸው ተአምራት ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡
ወንድሙ የስብስጥያ ኤጲስቆጶስ ከሚስቱ ጋር በድንግልና ሲኖር ሕዝቡ ግን ያሙት ነበርና ቅዱስ ባስልዮስ መላእክት ሲጠብቋቸው እንደተመለከተ ለሕዝቡ ገልጦላቸው ሕዝቡ ከሐሜት ርቀው ንስሓ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ በተመለከተ ጊዜ ‹‹ይህ የቂሳርያው የባስልዮስ ነው›› የሚል ቃልን ሰምቷል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም ወደ ቂሳርያ ሄዶ ከቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ዲቁናና ቅስና ተቀብሏል፡፡ ቅዱስ ባልዩስም በቅዱስ ኤፍሬም በላዩ ጸልዮለት የማያውቀውን አዲስ የዮናኒን ቋንቋን እንዲናገር አድርጎታል፡፡
ቅዱስ ባስልዮስ ሰው ሁሉ የሚያምንበትና በአቆጣጠሩም የሚታወቀውን ጠንቋይም በተአምሩ አሳምኖታል፡፡ ይኸውም ቅዱስ ባስልዮስ በታመመ ጊዜ የሚሞትበትን ጊዜ ዐውቆ ይህን ጠንቋይ ጠርቶ ‹‹ንገረኝ እስቲ መቼ እሞታለሁ?›› አለው፡፡ ጠንቋዩም ‹‹ማታ ነፍስህ ከሥጋህ ትለያለች›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹እስከ ጠዋት ካልሞትኩ ክርስቲያን ትሆናለህ?›› በማለት ቃል አስገባው፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም ወደ ጌታችን በመጸለይ በዕድሜው ላይ ሦስት ቀናት አስጨመረ፡፡ ያም ጠንቋይ ሥራው ከንቱ እንደሆነ ታወቀበትና እርሱም አምኖ ከነቤተሰቦቹ ተጠምቆ ክርስቲያን ሆነ፡፡
ሌላው ተአምር ለቅዱስ ባስልዮስ እመቤታችን ስለ ሥዕሏ የነገረችው ነው፡፡ ይህም ቅዱስ ባስልዮስ የእመቤታችንን ቤተ ክርስቲያን ከሠራ በኋላ በውስጧ የሚያኖረውን የእመቤታችንን ሥዕል ሊያሠራ መሳያ ሠሌዳ ፈለገ፡፡ ሰዎችም በአንድ ባለጸጋ ቤት ጥሩ ሠሌዳ እንዳለ ነገሩትና ሄዶ ባለጸጋውን ሠሌዳውን እንዲሰጠው ለመነው፡፡ ባለጸጋውም የልጆቼ ነው አልሰጥም አለው፡፡ በትዕቢትም ሆኖ በታነጸቸው ቤተ ክርስቲያን ላይ የስድብን ነገር ተናገረ፡፡ ወዲያውም ወድቆ ክፉ አሟሟት ሞተና ልጆቹ ፈርተው ሠሌዳውን አምጥተው ለባስልዮስ ሰጡት፡፡ እርሱም ያንን ሠሌዳ የእመቤታችንን ሥዕል አሳምሮ ይስልበት ዘንድ ለሰዓሊ ወስዶ ሰጠው፡፡ በዚህም ጊዜ እመቤታችን በራእይ ለቅዱስ ባስልዮስ ተገለጠችለትና ከአመፀኛ ሰው የተገኘ ነውና በዚያ ሰው ሠሌዳ ሥዕሏን እንዳያስል ከለከለችው፡፡ ሥዕሏ የተሳለበትን ሠሌዳም የት እንደሚገኝ ነገረችውና ሄዶ በታላቅ ክብር አምጥቶ በቤተ ክርስቲያኑ አስቀመጠው፡፡ ከሥዕሉም ሥር ድውያንን ሁሉ የሚፈውስ የዘይት ቅባት መፍሰስ ጀመረ፡፡ በዚህም ብዙዎች ድንቅ የሆነ ፈውስን አገኙ፡፡ ይህም የተፈጸመው ሰኔ 21 ቀን ነው፡፡
አንዲት ሴት ኃጢአቷን ሁሉ በዝርዝር ጽፋ በክርስታስ አሽጋ እንዲጸልይላት ቅዱስ ባስልዮስን ለመነችው፡፡ እርሱም ከአንዲት ኃጢአቷ በቀር ሁሉንም በጸሎቱ ደመሰሰላት፡፡ ስለ አንዲቱም ኃጢአቷ ወደ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲትሄድ አዘዛት፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም ‹‹ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሳይሞት ፈጥነሽ ተመለሽ የካህናት ሁሉ አለቃ ስለሆነ የቀረች ኃጢአትሽን የሚደመስስልሽ እርሱ ነው›› ብሎ መለሳት፡፡ በተመለሰችም ጊዜ ቅዱስ ባስልዮስ ዐርፎ ሊቀብሩት ሲወስዱት አገኘችው፡፡ እርሷም መሪር ልቅሶን ካለቀሰች በኋላ በእምነት ሆና ያንን ክርስታስ ከአስክሬኑ ላይ ጣለችው፡፡ ስለ እምነቷም ጽናት ያች የቀረች በደሏ ተደመሰሰችላት፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደርሷል፡፡ ዕረፍቱም ጥር 6 ነው፡፡ ወንድሙ ጎርጎርዮስም ጥር 15 ቀን ከቅዳሴ በኋላ ከማረፉ በፊት ወደ ወንድሙ ዘንድ ሄዶ አግኝቶታል፡፡ ሥጋውንም በክብር በሣጥን አድርጎ ቀብሮታል፡፡ ከዚህም በላይ ቅዱስ ባስልዮስ ያደረገው ተአምር ከላይ እንዳየነው የሰይጣንን የጽሕፈት ደብዳቤ በጸሎቱ የደመሰሰ መሆኑ ነው፡፡ ይኸውም የተደረገው በዛሬዋ ዕለት መስከረም ፲፫ ዕለት ነው፡፡ የቅዱስ ባስልዮስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ አሜን።
ምንጭ፣ ስንክሳር ዘወርኅ መስከረም፣
No comments:
Post a Comment