ግማደ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ ማን አመጣው ? እንዴት ? - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

ግማደ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ ማን አመጣው ? እንዴት ?

" ግብፅን ለመውጋት ሀገራቸው ድረስ ምን አስኬደኝ? በጦርነትስ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ነፍስስ ምን አስጠፋኝ? ከሀገሬ ምድር መንጭቶ የእነርሱ እስትንፋስ የሆነውን የአባይን ወንዝ ለምን አልገድበውም "……… : በመካከለኛው ዘመን ታሪክ በ14ኛው ምዕተ ዓመት የኦቶማን ቱርኮች እስላማዊ እንቅስቃሴ መላው አለምን ወደ አንድ ሃይማኖት ለመውሰድ አስቦ በተነሳበት ሰዓት በተለያዩ ሀገራት ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ላይ ትንሽ የማይባሉ ችግሮች መፈጠር ጀምረው ነበር።የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ሕዝቦች መሀከልም በግብፅ ውስጥ የሚገኙ የእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተከታዮች አንደኞቹ ናቸው። በግብፅ ሀገሪቷን የሚያስተዳድሩት ከሊፋወች የእስልምናን ሃይማኖት የያሚራምዱበመሆናቸው በዛ የሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ የበዛ መከራን ያደርሱባቸው ነበር። ገዳማትና አድባራቶቻቸውን ያወድሙባቸዋል፣የሃይማኖት አባቶቻቸውን ያሰድዳሉ እነሱንም ይገሏቸው ነበር። ከመከራና ከእንግልት የተረፉት ደግሞ በዬ አቅራቢያቸው ወደሚገኙት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ክርስቲያን ነገሥታት ወደሚገዟቸው ምድሮች እየሄዱ እየደረሰባቸው ያለውን በመናገር እንዲታደጓቸው እርዳታን ይጠይቁ ነበር።ያኔ ደግሞ በሀገራችን ኢትዮጵያ ነገሠው የነበሩት ደጉ ንጉሥ አፄ ዳዊት ነበሩና መልእክቱ በደረሳቸው ጊዜ ልክ ቀደምቶቻቸው እነ አፄ ካሌብ እነ ቅዱስ ይምርኃነ ክርስቶስ እንዳደረጉት ክርስቲያኖችን ለመታደግ ተነሱ በጊዜው የሚያስፈልገውን የጦር ዝግጅትም አድርገው ወደ ግብፅ ዘመቱ መንገዳቸውም በሱዳን በረሀ በኩል ነበርና ጉዟቸውን አጋምሰው ካርቱም አካባቢ ሲደርሱ የአባይን ወንዝ ተመልክተው " ግብፅን ለመውጋት ሀገራቸው ድረስ ምን አስኬደኝ? በጦርነትስ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ነፍስ ምን አስጠፋኝ? ከሀገሬ ምድር መንጭቶ የእነርሱ እስትንፋስ የሆነውን የአባይን ወንዝ ለምን አልገድበውም "ብለው አሰቡና ሰራዊታቸውን እዛው አስፍረው አባይን ማስገደብ ጀመሩ የወንዙን ውሀም ተፈጥሯዊ ከሆነ መንገዱ አስቀይሰው ወደ በረሀው ያለ ጥቅም እንዲፈስ አደረጉትና ለግብፅ ሰወች ውሀውን የሚለቁት በክርስቲያኖች ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ ካቆሙ ብቻ እንደሆነ የሚገልፅ መልእክት ላኩባቸው። ይህን የተመለከቱት የግብፅ ከሊፋወች በሆነው ነገር እጅግ ተደናግጠው ንጉሡ አፄ ዳዊት ያሉትን እንደሚፈፅሙና እስካሁን ላደረጉትም ይቅርታ በመጠየቅ እጅ መንሻ የሚሆን 24ሺ ወቄት ወርቅ በማስያዝ የእስክንድርያ አባቶችን ንጉሡ ወዳሉበት ሽምግልና ላኩባቸው። አፄ ዳዊትም ሽማግሌወቹ ወደርሳቸው በደረሱ ጊዜ ነገራቸውን ሰምተው በመደሰት ያመጡትን እጅ መንሻ ለፈራረሱት የእስክንድርያ አብያተ ክርስቲያናት ማደሻ እንዲሆን መልሰው ሰጧቸው። ነገር ግን የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል በእጃቸው እንደሚገኝ ሰምተው ነበርና ቃል ኪዳናቸው በውል እንዲታሰር እንደመያዣ እርሱን እንዲሰጧቸው ጠየቁ።አፄ ዳዊት የጌታችን ግማደ መስቀል በግብፅ እንዳለ ያወቁትና ጥያቄውን ለማቅረብ ምክንያት የሆናቸው ሰራዊታቸውን ይዘው በሱዳን በረሀ በሚመጡበት ጊዜ የበርካታ ሰወችን የወዳደቁ አፅሞች አይተው ስለነበር የዛን ምክንያት ሲጠይቁ አንድ መነኩሴ ከመንገድ አግኝተው "ኢየሩሳሌም ሄደን ቅዱሳና መካናትን እንሳለማለን፣ በግብፅ ከሚገኘውም የጌታ ግምደ መስቀል በረከት እንቀበላለን ብለው ከሀገራቸው ወጥተው በከባዱ ጉዞ ተዳክመው በበረሀ ወደቀው የቀሩ የክርስቲያኖች በድን አንደሆነ "ነግረዋቸው ነበርና ነው። ይህ ነገር ንጉሡን በሰሙት ነገር እንዲያዝኑና በዘመቻቸው የግብፅ ክርስቲያኖችን ከመታደግ ሌላ ግማደ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ የማምጣት ፍላጎት እንዲያድርባቸው እንዳደረገ ታሪክ ይነግረናል።ጥያቄውንም ያቀረቡት ከዚህ በኋላ ነው። የእስክንድርያ አባቶች አፄ ዳዊት የጠየቁትን ነገር ሲሰሙ የጌታችን መስቀል ለእነርሱ ምን ማለት እንደሆነ ይረዳሉና ከፉኛ ተደናግጡ ተቆጡም ጭምር የግብፅ አስተዳዳሪ ከሊፋወች ግን መስቀልን እንደተራ እንጨት ቆጥረውና ውሀውን ለማስለቀቅ ቀላል ነገር እንደተጠየቁ አስበው ግምደ መስቀሉ እንዲሰጣቸው አዘዙ።በስተመጨረሻም የእስክንድርያ አባቶች በነገሩ መክረው እኛ ጋር ሆኖ አህዛቦች ከሚያጠፉት፤ በክርስቲያኖች ሀገር በክብር ቢቀመጥ ይሻላል ብለው ስላሰቡ ለመስጠት ፈቃደኞች ሆኑ። አባ ሚካኤል አባ ገብርኤል በሚባሉ ጳጳሳት አባቶችን አስይዘውም ከሌሎች ንዋየ ቅዱሳት ጋር ወደ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ላኩት በ1395 ዓ,ም በመስከረም ወር በ10 ኛው ቀንም ግማደ መስቀሉ በአፄ ዳዊት እጅ ገባ። ንጉሡም በሆነው ነገር እጅግ ተደስተው የአባይን ውሀ ለቀቁላቸውና በሆታና በእልልታ መስቀሉን ወደሀገራቸው ይዘው መመለስ ጀመሩ። ነገር ግን ንጉሡ በጉዞው መሀል "ስናር" በተባለችው የኢትዮጵያና የሱዳን አዋሳኝ ድንበር ላይ ሲደርሱ ከፈረሳቸው ላይ ወድቀው ሕይወታቸው በማለፉ የመስቀሉ ወደ መሀል ሀገር የመግባት ጉዞ ተስተጓጎለ።አፄ ዘርዐ ያዕቆብ እስከነገሡበት ጊዜ ድረስም ግማደ መስቀሉ በዛው ቦታ ላይ በግብፃውያኑ ጳጳሳት እጅ በአደራ ተቀመጠ። አፄ ዘርዐ ያዕቆብ የአፄ ዳዊት ስምንተኛ ወንድ ልጅ ናቸው።አባታቸው የጀመሯቸውንም ነገር በማስፈፀም ይታወቃሉ።የቅዱስ መስቀሉንም ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከእርሳቸው በፊት ነግሠው ከነበሩት ታላላቅ ወንድሞቻቸው በላይ ይናፍቁ ነበርና ልክ ሀገርን የማስተዳደሩ ኃላፊነት ሲሰጣቸው የእግዚአብሔርን መልካም ፈቃድ በመጠየቅ መስቀሉ ወዳለበት ቦታ ተጓዙ። በመንገዳቸውም አንብር መስቀልዬ በዲበ መስቀል (መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አስቀምጥ) የሚል ህልም ይታያቸው ነበር።በቦታው ሲደርሱም ግብፃውያኑ አባቶች ሁሉንም ንዋያትና ግማደ መስቀሉንን መስከረም 21·1443 ዓ,ም በፍፁም ታማኝነት ጠብቀው አስረከቧቸው። አፄ ዘርዐ ያዕቆብም በታላቅ ደስታና ምስጋና ቅዱሱን መስቀል ወደ ሀገራቸው ክልል ይዘው በመግባት ሕልማቸው የሚፈፀምበትን መስቀለኛ ተራራ እየተዘዋወሩ ይፈልጉ ጀመር። በዚህም ብዙ ቦታወችን አካለሉ እንደ መናገሻ እና እንጦጦ ተራራወች ላይም አስቀምጠውት ነበር ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ በዛ ቦታ ሳይሆን ሲቀር ምልክት እያሳየ ቦታውን እንዲቀይሩ ያደርጋቸው ነበር። እንዲህ እንዲህ እያሉ ታላላቅ ተራራወችን ሲመርጡ ቆይተው በስተመጨረሻ ወሎ ውስጥ አምባሰል አውራጃ በግሸን ደብረ ከርቤ መስቀለኛ ተራራ ላይ ሲደርሱ እግዚአብሔር አምላክ ለመስቀሉ የመረጠው ቦታ ያ መሆኑን አሳወቋቸው በዚያ እንዲያስቀምጡት አዘዘ። ንጉሡ አፄ ዘርዐ ያዕቆብም ወደ ተራራው አናት ወጥተው ሲያዩት ቦታውን ስለወደዱት በአንደኛው አቅጣጫ ላይ መስቀሉን ለማስቀመጫ የሚሆን ሰፊ ጉድጓድን አስቆፈሩ የጌታችንን የቀኝ እጅ ያረፈበትን ግማደ መስቀሉንና ሌሎች ቅዱሳን ንዋያትንም ከወርቅ፣ ከብር፣ከነሐስንና ከብረት በተሰራ ትልቅ የመስቀል ቅርፅ ባለው ሳጥን ውስጥ በመክተት በተቆፈረው ጉድጓድ መሀከል በብር ሰንሰለት ከአራቱም ማዕዘን ተወጥሮ እንዲቀመጥ አደረጉ በላዩም ላይ እንጨት አስረብርበው የእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያንን መቅደስ አነፁበትና እለት እለት እየታጠነ እየተወደስ እንዲኖር አደረጉት። እንግዲህ የጌታችን ግማደ መስቀል ወደ ሀገራችን የመምጣቱ ታሪክ ከብዙ በጥቂቱ ከላይ እንዳየነው ነው። መስቀልን የሚመለከቱ በዓላት በሀገራችን በስፋት የመከበራቸውም ነገር የመጣው ከዚህ ዘመን በኋላ ነው። አፄ ዘርዐ ያዕቆብ መስቀሉን በሚገባው ቦታ አስቀምጠው ካበቁ በኋላ፣ መስከረም ፲፯ ቀን ንግስት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን በማሰብ ሕዝበ ክርስቲያን ከዋዜማው ጀምሮ በአደባባይ ወጥቶ ደመራ በማብራት እንዲያከብር፣ መስከረም ፳፩ ቀን እርሳቸው መስቀሉን ከግብፃውያን የተቀበሉበትን ቀንና በግሸን ደብረከርቤ አምባ ላይ ያሰቀመጡበትን ቀን በማሰብ በቦታው ተግኝቶ እንዲያከብር ሥርዓት እንዲሠራ አዘዙ። ይሄው እኛንም እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ከዓመት ዓመት እነዚህ እለታት ከታላላቅ ሃይማኖታዊ ክንዋኔወች ጋር ለማክበር እንድንበቃ አደረጉን። ወዳጆቼ እንኳን ለዚህ ታላቅ የብርሃነ መስቀል በዓል አደረሳችሁ። አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ኃይል የሀገራችንን አንድነቷን ይጠብቅልን እስከዛሬ ድረስ ተጠብቆ የቆየውን ባህልና ሃይማኖታዊ ሥርዓታችንም ያፅናልን በዓሉንም የሰላም ያድርግልን ለዘላለሙ አሜን። . ምንጭ፣ መጽሐፈ ጤፉት ዘግሸን ደብረ ከርቤ

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages