መስከረም ፱ በዚች ዕለት ቅዱስ አባ ቢሶራ በሰማዕትነት አረፈ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 2, 2021

መስከረም ፱ በዚች ዕለት ቅዱስ አባ ቢሶራ በሰማዕትነት አረፈ

ስንክሳር ዘመስከረም ፱ ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል
___________________ መስከረም ፱ በዚህች ዕለት የመላእክት ሁሉ አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በሮም አገር ታላቅ ተአምር ያደረገባት ዕለት ናት፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በሮም አገር ያደረገው ታላቅ ተአምር፡- ይኸውም በሮም አገር ፍሩምያ በምትባል ከተማ የተደረገ ተአምር ነው፡፡ በዚህች ከተማ ውስጥ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ በዚህችም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገናናው መልአክ ብዙ አስደናቂ ተአምራትን ሲሠራ ኖረ፡፡ በዚህም ምክንያት ዮናናውያን ሰዎች ሰይጣናዊ ቅናት ቀንተው በአካባቢው የሚወርደውን የወንዝ ውሃ አቅጣጫውን መልሰው ቤተ ክርስቲያኗን የሚጠባቃትን መጋቢውንም ጭምር በውኃው ሊያሰጥሟት ተነሡ፡፡ በዚህም ጊዜ ቅዱስ ሚካኤል ለቤተ ክርስቲያኑ መጋቢ ለናርጢኖስ ተገለጠለትና ‹‹አይዞህ ጽና አትፍራ›› አለው፡፡ ይህንንም ብሎ በእጁ ላይ ባለው በትር ዓለቱን መታው፡፡ ዓለቱም ተሰንጥቆ እንደበር ሆነ፡፡ የዚያ ወንዝ ውኃም በውስጡ አልፎ ሄደ፡፡ ይህንንም ያዩ ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ ገናናውን መልአክ ቅዱስ ሚካኤልንም አከበሩት፡፡ ከዚያች ቀን እስከዛሬ የወንዙ ውሃ በዚያች በተሰነጠቀች ዓለት ውስጥ አልፎ ሲሄድ ያዩታል፣ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ግን ከቶ አይቀርብም፡፡ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ጥበቃ አይለየን፡፡ ቅዱስ አባ ቢሶራ _____________ መስከረም ፱ በዚች ዕለት ቅዱስ አባ ቢሶራ በሰማዕትነት አረፈ፡፡ ቅዱስ አባ ቢሶራ በግብጽ አገር መጺል የምትባል ከተማ ኤጲስ ቆጶስ ሲሆን ዲዮቅልጥያኖስ የክርስቲያኖችን ደም እንደ ውኃ ሲያፈስ አባ ቢሶራም በጌታችን ስም ሰማዕት ይሆን ዘንድ ወደደ፡፡ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ በሃይማኖት እንዲጸኑ ከመከራቸው በኋላ ወደ ከሃዲዎች ዘንድ ሄዶ የጌታችንን ክብር መስክሮ ለመሞት እንደወሰነ ነገራቸው፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ታላቁም ታናሹም እያለቀሱ ‹‹ከእኛ ተለይተህ ወደ ሞት አትሄድም፣ እኛንስ እንደሙት ልጆች ለምን ትተወናለህ?›› እያሉ ለመኑት፡፡ ነገር ግን አባ ቢሶራ ሰማዕትነት ዕጣ ክፍሉ መሆኑን ነግሯቸው በሃይማኖት እስከመጨረሻ እንዲጸኑ ከመከራቸው በኋላ ተሰናብቷቸው ወደ ሰማዕትነት ሄደ፡፡ ሕዝቡም መሪር ልቅሶን እያለቀሱ ሸኙት፡፡ ሌሎች ሦስት ኤጲስ ቆጶሳትም ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ ተከትለውት ሄዱ፡፡ቅዱስ አባ ቢሶራ እና ሦስት ኤጲስ ቆጶሳትም የክርስቲያኖችን ደም ያፈስ በነበረው መኮንን ፊቱ ቆመው የጌታችንን አምላክነት መሰከሩ፡፡ መኮንኑም ይዞ ጽኑ ሥቃይ አደረሰባቸው፡፡ ይልቁንም ኤጲስቆጶሳት መሆናቸውን ሲያውቅ ሥቃይን አበዛባቸው፡፡ ነገር ግን ጌታችን እያጸናቸው መከራውን በትዕግስት ተቀበሉ፡፡ በመጨረሻም በዚህች ዕለት ቅዱስ አባ ቢሶራና ሦስት ኤጲስ ቆጶሳት (ቢስኮስ፣ ፊናቢክስ እና ቴዎድሮስ) አንገታቸውን ተሰይፈው ሰማዕትነታቸውን በድል ፈጽመዋል፣ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን አሜን። #መስከረም ፱ በዚች ዕለት ከቅዱስ ፋሲለደስ ጋር ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ሰላሳ ሰባት (14737) አማኞች በሰማዕትነት አረፉ፡፡ በዚህች ዕለት ከቅዱስ ፋሲለደስ ጋር ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ሰላሳ ሰባት (14,737) አማኞች በሰማዕትነት አርፈዋል፡፡ ከሰማዕቱ የዕረፍት ዕለት ጋር መስከረም ዓሥራ አንድን ቀን ስንክሳር ይዘክራቸዋል፡፡ የሰማዕታቱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን ይማረን። #እንዲሁም መስከረም ፱ በዚች ዕለት ‹‹ተጋድሎውን በዛፍ ላይ ሆኖ የፈጸመ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ ንጉሥ ያሳይ ዕረፍቱ ነው›› በማለት ስንክሳሩ በስም የገለጸው ጻድቁ ንጉሥ ያሳይ አረፈ፡፡ ረድኤት በረከቱ በሁላችን ላይ ይደርብን። ምንጭ:- ስንክሳር ዘወርኅ መስከረም ፱/፲፩

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages