_____________________________________
መስከረም ፬ ቀን ጌታችን በስብከቱ ‹‹ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልሏቸው›› ብሎ ካቀፋቸውና ካስተማረባቸው ሕፃናት አንዱ የሆኑትና በግብፅ ፵ ዘመን ነግው ሳለ ንግሥናቸውን ትተው ወደ ኢትዮጵያ መተው አስራ ስድስት ፍልፍል ቤተ መቅደሶችን የሠሩት የድባው አቡነ ሙሴ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ዳግመኛም በዚህች ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ልደቱ ነው፡፡
በዚህች ዕለት ሙሴ በሞት ካረፈ በኋላ እስራኤላውያንን መርቶ ምድረ ርስት ያወረሳቸው፣ የዮርዳኖስን ባሕር ከፍሎ ያሻገራቸው፣ በገባኦን ምድር በኤሎን ቆላ ፀሐይን ያቆመው፣ የአሕዛብንም ነገሥታት ድል የመታ ታላቅ ነቢይ መስፍንና ካህን የሆነው የነዌ ልጅ ኢያሱ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን አሜን።
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ(ወልደ ዘብዲዎስ)
_________________________________
በዚህች ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ልደቱ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ለመስበክ ዕጣ የደረሰው እስያ ስለነበር ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ይኽችውም ኤፌሶን በጥንቱ በታናሽ እስያ በዛሬው የቱርክ ግዛት ውስጥ ከተማ ናት፡፡ ዛሬ ኢያዞሎክ ተብላ የጥንት ታሪኳ ጠፍቷል፡፡ አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሰብኮባታል፡፡ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጢሞቴዎስንም በከተማዋ ላይ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ እርሱም በግፍ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስን እየረዳው በከተማዋ ብዙ አገልግሏል፡፡ በኋላ ግን በግፍ ገድለውታል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን ለመሄድ በመርከብ ሲሳፈር መርከቡ በማዕበል ተሰበረ፡፡ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን መዕበሉ ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በመርከቡ ስባሪ ተንጠልጥሎ በባሕሩ ማዕበል መካከል 40 ቀንና 40 ሌሊት ከኖረ በኋላ ማዕበሉ ተፍቶ አብሮኮሮስ ካለበት ደሴት አደረሰውና ተያይዘው ኤፌሶን ከተማ ገቡ፡፡ የከተማይቱም ሰዎች እጅግ ክፉዎች ስለነበሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አልቻሉም ነበር፡፡ እነርሱም እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ስላወቀ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ዕጣው ሲደርሰው በሀዘን አልቅሶ ነበር፡፡ አሁንም ከተማው በገቡ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ምክንያት በመፍጠር ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤቷ እሳት አንዳጅ ሆኖ አብሮኮሮስም ዕቃ አጣቢ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ የቀጠረቻቸው ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ጀመር፡፡ ባሮቿ እንደሆኑ ተስማምተው ስለጻፉላት ትደበድባቸውም ነበር፡፡
እነርሱም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እየኖሩ እያለ በአንዲት ዕለት የአገረ ገዥው ልጅ ለመታጠብ ወደ ውሽባው ቤት ገባ፡፡ በውሽባ ቤቱም የሰይጣን ኃይል ስለነበረበት የመኰንኑን ልጅ አንቆ ገደለው፡፡ የአገሪቱም ሰዎች ሁሉ ለሞተው የመኰንን ልጅ ሊያለቅሱ ሲሰበሰቡ ቅዱስ ዮሐንስም አብሮ ቆሞ ሲመለከት ሮምና መጥታ ‹‹በጌታዬ ልጅ ሞት ልትደሰት መጣህን›› እያለች ረገመችው፡፡ እርሱም ‹‹አይዞሽ አትዘኚ›› አላትና
ወደ ሞተው ልጅ ቀርቦ በመስቀል ምልክት ካማተበበት በኋላ በፊቱ እፍ አለበት፡፡ የሞተውም ልጅ ድኖ ተነሣ፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች እጅግ ደነገጡ፡፡ ሮምናም ደንግጣ ‹‹እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን›› ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹በፍጹም እኔ አምላክ አይደለሁም፣ እኔ የእርሱ አገልጋዩና ሐዋርያው ነኝ እንጂ›› አላት፡፡ ሮምናም ስለበደለቻቸው በደል ሁሉ መሪር ዕንባን እያለቀሰች ይቅር እንዲሏት ለመነቻቸው፡፡ እነርሱም አረጋጉዋት፡፡ ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ በጌታችን አመኑ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ሌሎች ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ከጣዖት አገልጋዮች በቀር ሁሉንም አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ አገልጋዮችን ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ ወደ ሌሎች አቅራቢያ አገሮች ሄደ፡፡
በመጨረሻም በከሃዲውና በጨካኙ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ፡፡ በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋለ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት፡፡ በዚያም ሳለ ራእዩን ተመልክቶ ጻፈው፡፡ ድምጥያኖስም ከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱንና ቅዱስ ወንጌሉን ጽፏል፡፡ ጌታችንም አስቀድሞ ሞትን እንደማይቀምስ ለዮሐንስ ቃል ገብቶለት ነበርና (ዮሐ 21፡22) ጥር 4 ቀን እንደ ኤልያስና ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስታል፡፡
ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ…›› ብሎ የጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ ‹‹ምን ማድረግህ ነው›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው›› ሲለው ዮሐንስም መልሶ ‹‹ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹አዎን›› አለው፡፡ ዮሐንስም ‹‹በከንቱ ደከምክ›› አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ ‹‹አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ ‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..› ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንዴት ጨልፌ አልጨርሰው ብሎ የሥላሴን ርቀት ምጥቀት የባህርይ መለኮትን ረቂቅነት አስተምሮታል።
ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ "ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…" ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለአስራ ስድስት ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከጌታችን ጋር ይመሳል ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ዮሐንስም ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ "በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?" ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ "እንዴት አድርጌ ልሳልህ?" ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም "ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ" አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፦
በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር " ፍቁረ እግዚእ" ተባለ፣ የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል "ዮሐንስ ወልደ ዘብድዮስ" ተባለ፣ ለጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የጌታችንን አምላክነት በመግለጡ "ወልደ ነጎድጓድ" ተብሏል፡፡ ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ "ነባቤ መነኮት ወይም ታኦሎጎስ" ተብሏል። ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ "አቡቀለምሲስ" ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ ባለራእይ ማለት ነው፡፡ የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ 70 ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ "ቁጹረ ገጽ" ተብሏል።
የድባው አቡነ ሙሴ
_________________
የትውልድ አገራቸው እስራኤል ልዩ ቦታው ቃና ዘገሊላ ነው፡፡ ጽንሰታቸውን ቅዱስ ሩፋኤል መጋቢት 8 ቀን ሲያበስር ልደታቸውን ደግሞ ቅዱስ ገብርኤል ታኅሣሥ 8 ቀን የመወለዳቸውን ብሥራት ተናግሯል፡፡ ሲወለዱ ሚካኤል ወገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጠው ‹የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ›› ብለው ስም አወጡላቸው፡፡ በተወለዱም በ40ኛ ቀናቸው ከተጠመቁ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል አቅፎ ይዟቸው ጌታችን በቅዱሳን እጆቹ አቁርቧቸዋል፡፡ በእሳቸውም ምክንያት በዚያች ዕለት በቤተ ክርስቲያን የነበሩት ሰዎች ሁሉ ክቡራን በሆኑ በጌታችን እጆች ቆርበዋል፡፡
የአቡነ ሙሴ አባታቸው ዮስጦስ ለሐዋርያው ናትናኤል አጎቱ ነው፡፡ እናታቸው ጵርስቅላ ጌታችን በሠርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የለወጠለት የዶኪማስ ልጅ ናት፡፡ ጌታችን ወደ ዶኪማስ ቤት ሠርግ ተጠርቶ የሄደው ዶኪማስ ናትናኤልን ‹‹ሠርጌን እንዲባርክልኝ ጌታ ኢየሱስን ከእናቱ ጋር ጥራልኝ›› ብሎት ነው፡፡ ጌታችን በስብከቱ ‹‹ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልሏቸው›› ብሎ ብሎ ካቀፋቸውና ካስተማረባቸው ሕፃናት አንዱ ይኽ አቡነ ሙሴ ናቸው፡፡ ጻድቁ ዋሻዎችን እየፈለፈሉ የቅዱሳን ሐዋርያትን ዐፅም በክብር ያስቀምጡ ነበር፡፡ የተሠወሩ አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ ወንጌልን በማስተማር ብዙ መከራ የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ በግብፅ ‹‹ንጉሥ አንስጣስዮስ›› ተብለው 40 ዓመት በንግሥና እና በድንግልና ኖረዋል፡፡ ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ በመልአክም ምክር ዮናኒ የተባለውን ሌላ ሰው አንግሠው ወደ አስቄጥስ ገዳም ገብተው መነኮሱ፡፡ በገዳሙም በታላቅ ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሲያርፉ በቅዱስ አትናቴዎስ ተሹመው 2ኛው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው ‹‹አቡነ ሰላማ ካልዕ›› ተብለው ተሾመው ወደ አገራችን መጡ፡፡ ከመሾማቸው በፊት የእኛ አባቶቻችን አቡነ አትናቴዎስን ‹‹ጳጳስ ይላኩልን›› ብለው መልእክት ሲልኩባቸው አቡነ አትናቴዎስም ወደ አስቄጥስ ገዳም በመሄድ እግዚአብሔርን በጸሎት ቢጠይቁት የታዘዘ መልአክ መጥቶ ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሙሴን ላክላቸው›› አላቸው፡፡ መነኮሳቱም ሁሉ እንዲሁ አሉ፡፡ ከዚህም በኋላ ሲሾሙ ሚካኤልና ገብርኤል በወርቅ ወንበር ላይ አስቀምጠዋቸው ‹‹ይገባዋል ይገባዋል›› ብለው ቅብአ ክህነት ቀብተዋቸዋል (ጵጵስና ሾመዋቸዋል፡፡) አቡነ ሙሴም ከተሾሙ በኋላ 14000 መነኮሳትን አስከትለው ወደ ቅድስት አገራችን መጡ፡፡
አቡነ ሙሴ ንግሥናቸውን ትተው ወደ ኢትዮጵያ መተው 16 ፍልፍል ቤተመቅደሶችን የሠሩ ሲሆን 8ቱ የተሰወሩ ናቸው፡፡ በገዳማቸው በቅድስቱ ውስጥ ጥልቀቱ የማይታወቅ እጅግ ጥልቅ የሆነ ጉድጓድ አለ፡፡ በውስጡም ስውራኑ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበታል፡፡ ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተቀረጸውና ፍልፍል የሆነው የገዳማቸው የቤተልሔሙ ስፋት ሜትር ከሃያ ሲሆን ጣራው እንደ አቡነ አሮን ክፍት ሆኖ ሳለ ዝናብ ግን አይገባበትም፡፡ ዝናብ የማያስገባው የቀዳዳው ስፋት አንድ ሜትር በአንድ ሜትር ነው፡፡ ጻድቁ በሀገራችንም ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ብዙ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽና ወንጌልን በማስተማር ብዙ ደክመዋል፡፡ በተለይም በዋናነት የሚታወቁት በሰሜን ወሎ አውራጃ ወልድያ ወረዳ መቄት ልዩ ቦታው ገረገራ የሚገኘው ‹‹ሐዲስ አንባ ዋሻ መድኃኔዓለም›› እና መጀመሪያ እንደመጡ ያረፉባት ‹‹ድባ ማርያም›› ይጠቀሳሉ፡፡ ይህችውም ድባ ማርያም ገዳም ታላቁ አባት እስትንፋሰ ክርስቶስ የመነኮሱባት ናት፡፡ ጻድቁ አቡነ ሙሴ መስከረም 4 ቀን ጌታችን ቃልኪዳን ሲገባላቸው እነዚህን ሁለት ገዳማቸውን ‹‹እንደ ዘስቄጥስ ገዳም እንደ አቡነ እንጦንስ ማኅበር ይሁኑልህ›› ብሏቸዋል፡፡ በገዳማቸው ከሞኖሩት ቅዱሳን ውስጥ 400 ወንዶች መነኮሳትና 200 ሴቶች መነኮሳያት እንደተሰወሩ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡
ጻድቁ ሌላው ለየት የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ገና በእናቷ ማኅፀን ሳትፀነስ የቅድስት አርሴማን ጽላት ያሠሩላት መሆናቸው ነው፡፡ ቁመቱ 2 ሜትር ከ70 የሆነ ግሩም ቤተ መቅደስም ፈልፍለው አንጸውላታል፡፡ ጌታችንም የሰማዕቷን ጽናትና ረድኤት ከቦታው እንደማይለይባቸው ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ በቃል ኪዳናቸው የታመኑትን ልጆቻቸውን መተትና መርዝ አይጎዳቸውም፡፡ ይህም ጌታችን የሰጣቸው ልዩ ቃልኪዳናቸው ነው፡፡ ጻድቁ እንደ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ 12 ክንፍ የተሰጣቸው ታላቅ የምሕረት አባት ናቸው፡፡ የአቡነ ሙሴ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ አሜን።
Post Top Ad
Saturday, October 2, 2021
መስከረም ፬ ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ዘንስር (አቡቀለምሲስ)
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
Post Bottom Ad
Author Details
Templatesyard is a blogger resources site is a provider of high quality blogger template with premium looking layout and robust design. The main mission of templatesyard is to provide the best quality blogger templates which are professionally designed and perfectlly seo optimized to deliver best result for your blog.
qale hiwot yasemalin. berta beteley degmo TV bitijemir tiru neber. yih yene asteyayet new
ReplyDelete