የብሕትውና(የምንኩስና) ኑሮ - ክፍል 2 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, September 17, 2022

የብሕትውና(የምንኩስና) ኑሮ - ክፍል 2

 

2. የሥርዓተ ምንኩስና ታሪክ

 2.1   - አባ ጳውሊ  እና  አባ እንጦንስ
    2.1.1-  አባ ጳውሊ
Ss+Anthony+&+Paul
አባ ጳውሊ  እና  አባ እንጦንስ
በተባሕትዎ መኖር ከጥንት ዘመን የመጣ ይሁን እንጂ የብሕትውናን ኑሮ ሥርዓት በወጣለት መልኩ የጀመረው አባ ጳውሊ የተባለው ግብፃዊ አባት ነው፡፡ በንጉሥ ዳክዮስ ዘመነ መንግሥት በክርስቲያኖች ላይ በተነሣው ስደት ምክንያት አባ ጳውሊና ቆይቶም ደግሞ ሌሎች የአካባቢው ክርስቲያኖች በግብፅ በረሃዎች ውስጥ በምናኔ ይኖሩ ነበር፡፡
ይህንን አባ ጳውሊ የጀመረውን ሥርዓት አጠናክሮ ለማስፋፋት ያበቃው ደግሞ አባታችን አባ እንጦንስ ነው (251-356 ዓ.ም.)፡፡

  2.1.2- አባ እንጦንስ
አባ እንጦንስ ግብፅ ውስጥ ቆማ በተባለች መንደር ከሀብታም ቤተሰቦች በ251 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወዳጆቹ ገና የ2ዐ ዓመት ወጣት እያለ ስላረፉ በማቴ.19÷21 ላይ ያለውን ትምህርት መሠረት አድርጐ የወረሰውን ሀብት በሙሉ በመሸጥ ለድኾች አከፋፈለና ወደ ግብፅ በረሃ በመውረድ ለ85 ዓመት በተጋድሎ ኖሯል፡፡

የአባ እንጦንስ ዓላማ ከሰው ርቆ በብሕትውና በበረሃ ለመኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ተአምራቱን የሰማው ሕዝብ ከግብፅ ብቻ ሳይሆን ከመካከለኛው ምሥራቅና ከአውሮፖ ምድር ሳይቀር ወደ በአቱ ይጐርፍ ጀመር፡፡ በኋላም በሕይወቱ የተማረኩ ባሕታውያን በዙሪያው ባሉ ዋሻዎች መኖር ጀመሩ፡፡
የአባ እንጦንስን የሕይወት ታሪክ የጻፈለት አባታችን አትናቴዎስ ሲሆን አትናቴዎስም ሥርዓተ ምንኩስናን የተቀበለው ከዚሁ አባት ነው፡፡ ታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም ዝናውን በመስማቱ «በጸሎትህ አስበኝ» በማለት ደብዳቤ ጽፎለት እንደነበር ታሪኩ ይናገራል፡፡
አባ እንጦንስ ለ85 ዓመታት በብሕትውና ሲኖር ከበኣቱ የወጣው ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ የመጀመሪያው በንጉሥ መክስምያኖስ ትእዛዝ ስደትና መከራ የደረሰባቸውን ክርስቲያኖችን ለማፅናናት በመላዋ ግብፅ በ311 ዓ.ም. ያደረገው ጉዞ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አርዮሳውያን በቅዱስ አትናቴዎስ ላይ በተነሡበት ጊዜ ለመንፈስ አባቱ ለሐዋርያዋው አትናቴዎስና ለንጽሕት ተዋሕዶ እምነቱ ያለውን ቆራጥነት በመግለጥ ሕዝቡን ለማጽናት በ338 ዓ.ም ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ የተጓዘው ሐዋርያዊ ጉዞ ነው፡፡
የባሕታውያኑ በአባ እንጦንስ ዙሪያ መሰባሰብ ለማኅበር ጸሎት፣ ከዘራፊዎች ለመጠበቅና የደከሙ አበውን ለመርዳት አስችሏቸዋል፡፡ በዚህም የመጀመሪያው የገዳማውያን የማኅበር ኑሮ ተጀመረ፡፡
አባ እንጦንስ የመነኮሳቱ ልብስ ነጭ ፈረጅያና ቆብ፣ መታጠቂያቸውም ከቆዳ የተሠራና ሠቅ እንዲሆን ወስኖ ነበር፡፡
መነኮሳቱ ሳምንቱን በየበኣታቸው ሲጾሙና ሲጸልዩ ሰንብተው እስከ እሑድ ምሽት ድረስ ደግሞ በአባ እንጦንስ ዋሻ ዙሪያ ተሰባስበው ሲጸልዩና ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጽሙ ይውሉ ነበር፡፡ አባ እንጦንስ በዚህ ሁኔታ ሥርዓተ ምንኩስናን አስፋፍቶ በተወለደ በ105 ዓመቱ ዐርፎአል፡፡አባ ጳውሊ የጀመረውን ሥርዓተ ምንኩስና አጠናክሮ ያስፋፋው አባ እንጦንስ ነው፡፡
2.2 አባ ጳኩሚስ
በሥርዓተ ምንኵስና ታሪክ ሌላውን ታላቅ ሥፍራ የያዘው ደግሞ የአባ እንጦንስ ደቀ መዝሙር የነበረው አባ ጳኩሚስ ነው (23-346 ዓ.ም.)፡፡ አባ ጳኩሚስ ግብፅ ውስጥ ኤስና በምትባል መንደር ከአረማውያን ቤተሰቦች በ29ዐ ዓ.ም. ተወለደ፡፡ በቆስጠንጢኖስ ዘመነ መንግሥት ለውትድርናም ተመልምሎ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ በውትድርናው ዘመን የክርስቲያኖችን ቆራጥነት፣ደግነትና ርኀራኄ በማየቱ ልቡ ስለተነካ ግዳጁን ፈጽሞ ሲመለስ በ313 ዓ.ም. የክርስትናን እምነት ጠንቅቆ በመማር አምኖ ተጠመቀ፡፡
gedam
የአባ ጳኩሚስ ልቡና የቅዱስ እንጦንስ ደቀ መዝሙር በነበረው በአባ ጴላጦንስ ኑሮ ስለተማረከ ወደ በረሃ ወርዶ የብሕትውናን ኑሮና ሥርዓት ሲማር ከቆየ በኋላ በ32ዐዓ.ም. በዓባይ ወንዝ አጠገብ ታቤኒስ ከተባለው ቦታ የራሱን ገዳም መሠረተ፡፡ በዙሪያው ለተሰበሰቡት መነኰሳትም የአንድነት ኑሮ ሕግ አወጣላቸው፡፡ በአባ እንጦንስ ለተጀመረው የማኅበረ መነኰሳት ኑሮ የተጠናከረ ሥርዓት አውጥቶ የበለጠ ከማስፋፋቱም በተጨማሪ ዘጠኝ የወንድና ሁለት የሴቶች ገዳማት መሥርቷል፡፡
አባ ጳኩሚስ ያወጣው የመነኰሳት የአኗኗር ሕግ ዋናው ቅጂ ሲጠፋ ወደ ላቲን የተተረጐመው ግን እስከዛሬ ድረስ ይገኛል፡፡ ከሕግጋቱ መካከል፡-
Ø  መነኮሳት ጠዋትና ማታ በማኀበር እንዲጸልዩ፣
Ø  በኀብረት በአንድነት እንዲሠሩ፣
Ø ቅዱሳት መጻሕፍትን አዘውትረው እንዲመለከቱ፣
Ø  የቁም ጽሕፈት እንዲማሩ፣
Ø  ገቢና ወጪአቸው አንድ ላይ እንዲሆን፣
Ø  በአንድነት እንዲመገቡ፣
Ø  አንድ ዓይነት ልብስ እንዲኖራቸው፣
Ø  ንጽሕ ጠብቀው እንዲኖሩ፣
Ø  ደግነት፣ ፍቅርና ታዛዥነት እንዲኖራቸው፣የሚሉት ይገኙበታል፡፡
አንድ ሰው ወደ ገዳማቱ ሲመጣ የሦስት ዓመት አመክሮ ይሰጠውና ጠባዩና ፍላጐቱ ይገመገማል፡፡ ከዚያ በኋላም ብርታቱና ጽናቱ ታይቶ ወደ ማኅበረ መነኰሳቱ ይቀላቀላል፡፡ አባ ጳኩሚስ በዚሁ ዓይነት መንገድ ሥርዓት ሠርቶ ሕግ አጽንቶ ገዳማትን ካስፋፋ በኋላ በተወለደ በ56 ዓመቱ በ346 ዓ.ም. ዐረፈ፡፡

3. ሥርዓተ ምንኵስናን በሌላው ዓለም ያስፋፉ አበው

3.1 አትናቴዎስ ሐዋርያዊው (295-373 .ም.)

athanasius_0
አትናቴዎስ ሐዋርያዊው
ቅዱስ አትናቴዎስ ከታላቁ ርዕሰ ገዳማውያን ከአባ እንጦንስ ዘንድ ሥርዓተ ምንኵስናን ተምሮ ፈጽሟል፡፡ የአባ እንጦንስን የሕይወት ታሪክ (ገድል) የጻፈውም እርሱ ነው፡፡ አርዮሳውያን በቅዱስ አትናቴዎስ ላይ በግፍ በተነሡበት ጊዜ ወደ ሮም በመሰደድ ከ339-346 ዓ.ም. ተቀምጧል፡፡ የሮም ክርስቲያኖች አትናቴዎስና ተከታዮቹ የለበሱትን የመነኰሳት ልብስና ቆብ ተመልክተው ተገረሙ፡፡ እርሱም በቆየባቸው ሰባት ዓመታት ከአባ እንጦንስ የተማረውን የመነኰሳት ሕግና አኗኗር አስተምሯቸዋል፡፡ በሮማ ምድርም ሥርዓተ ምንኩስናን ለማስፋፋት የመጀመሪያው አባት አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ነው፡፡
                         
3.2 ቅዱስ ባስልዮስ ታላቁ (330-379 ም)
basil_icon


ባስልዮስ በግብፅ ገዳማት በብሕትውና ከቆየ በኋላ ከ36ዐ ዓ.ም. ጀምሮ በታናሽ እስያ (ዛሬ ቱርክ በሚባለው አካባቢ) የምነናን ኑሮ በመመሥረት ዛሬ የግሪክ፣ ሩሲያ፣ ወዘተ. አብያተ ክርስቲያናት የሚገለገሉበትን የመነኰሳት ሕግ ያወጣው እርሱ ነው፡፡

ቅዱስ ባስልዮስ ታላቁ



3.3 ዮሐንስ ካስያን (360-435 ዓ.ም.)
ግብፅ ውስጥ በቴብያድና ጥቂት ዓመታት በብሕትውና ከቆየ በኋላ ወደ ፈረንሳይ በመመለስ በ415 ዓ.ም. በፈረንሳይ ማርሴይ አጠገብ ሁለት ገዳማትን መሠረተ፡፡ በግብፅ ያጠናውን ሥርዓተ መነኰሳት መሠረት አድርጐ ሁለት መጻሕፍትንም አዘጋጅቷል፡፡
እንግዲህ በዚህ ሁኔታ በአባ ጳውሊ የተጀመረው የምንኵስና ሕይወት በመላው ዓለም ሊስፋፋና ወደሀገራችንም ለመድረስ በቅቷል፡፡ የመጀመሪያውን የሴቶች ገዳም የመሠረተችው ደግሞ የአባ ጳኩሚስ እኀት ማርያም ነች፡፡

ምንኵስና በኢትዮጵያ

ይቀጥላል - ይቆየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዋቢ
1.    ትንሣኤ ቁ.99/1978
2.    ገድለ አባ ሊባኖስ
3.    ገድለ አባ ዮሐንስ
4.    ዜና መንዝ
5.    የአንኰበር መሳፍንት የታሪክ መጽሐፍ
6.    ትንሣኤ ቁ.11/79
7.    ትንሣኤ ቁ.22/80
8.    Conti Rossini, steria PL.XLIV
9.    ሉሌ መላኩ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አ.አ 1986
10. አባ ጎርጎርዮስ፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ
11. አባ ጎርጎርዮስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪ
ሐመር መጽሔት

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages