መጻሕፍተ መነኮሳት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, September 17, 2022

መጻሕፍተ መነኮሳት

522314_2648171782349_1797345574_1639582_513908509_n

መጻሕፍተ መነኮሳት፤የመነኮሳት ሥራቸውን፤ ፆራቸውን፤ ታሪካቸውን፤ ጸጋቸውንና ክብራቸውን የሚናገር መጽሐፍ ነው።  መጻሕፍተ መነኮሳት ተብለው የሚጠሩት ሦስቱ መጽሐፍት
1ኛ) ማር ይስሐቅ
2ኛ) ፊልክስዮስ
3ኛ) አረጋዊ መንፈሳዊ ናቸው
1)     ማር ይስሐቅ
ማር ይስሐቅ የቅዱስ ኤፍሬም (ውዳሴ ማርያምን የደረሰው) ደቀ መዝሙር በመሆን ብሉይና ሐዲስ እንዲሁም ሥር ዓተ ቤተ ክርስቲያን ተምሮአል።  ከዚህ በኋላ ከአባማ እብሉይ ገዳም ገብቶ 25 ዓመት ረዳር አቅ።  አባ እብሎይ ሲያርፍ አናምርት አክይስት፤ አቃርብት፤ ካሉበት ነቅአ ማይ ልምላሜ ዕፅ ከሌለበት በረሃ ሄዶ ተባሕትዎ ያዘ።  በብሕትውና እያለ እግዚአብሔር የገለጸለትን ከሦስቱ መጽሐፍተ መነኮሳት አንዱ የሆነውንና “ማር ይስሐቅ” ተብሎ የተጠራውን መጽሐፍ ጻፈ።
መጽሐፈ ማር ይስሐቅ የመነኮሳትን ጾር፤ ትሩፋት ለመስራት የሚያስፈልጉ ነገሮችንና መንፈሳዊ ጥበብን፤ ሰይጣን ትሩፋት የሚሰሩ መነኮሳትን እንዴት እንደሚተናኮላቸውና ለ እነርሱም እንዴት መዘጋጀትና መጠንቀቅ እንዳለባቸው በአጠቃላይ ፈጣሪያቸውን ለማገልገል የገቡትን ቃል ኪዳን እንዴት አድርገው መጠበቅ እንዳለባቸው የሚገልጽ በድንቅ መንፈሳዊ  የተዋበ መጽሐፍ ነው።  በውስጡም ልዩ ልዩ ንዑስ ክፍሎችን የያዘ ነው። ለምሳሌም ስለ ትጋሃ ሌሊ፤ት ስለ ጾም፤ ስለ ተጋድሎ፤ ስለ ጸዋትወ መከራ፤ ስለ ጸሎት፤ ስለ ትሕትና፤ ስለ አጽንዖ በዓት፤ ስለ ትዕግስት እና ስለ ሌሎችም ብዙ ነገሮች የሚገልጽ፤ ራሳቸውን ብዙ መንፈሳዊ ሥራ ለማሰራት ለሚፈልጉ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠ መካሪ መጽሐፍ ነው።
2)     ፊልክስዮስ
ፊልክስዮስ፤ ከሦስቱ መጽሐፍተ መነኮሳት አንዱ ሲሆን የሚገልጸውም ስለ ገዳማውያን ታሪክ እና ተጋድሎ ነው።  ፊልክስዮስ በዜና አበው ከተጻፈው እና በቃል ሲነገር ከመጣው የአበው ብሂል ያልተተረጎመውን እየተረጎመ ያልተመሰለውን እየመሰለ ጽፏል።  አኃው ከቃለ አበው የሚለያይና የሚቃረን የሚመስላቸውን እየጠየቁት፤ እንዲሁም እርሱ መተርጎምና መታረቅ ያለበትን ከብሉይና ከሐዲስ እየጠቀሰ አስማምቶ ተርጉሟል። ሲተረጉምም በመጀመሪያው ከብሉይ እና ከሐዲስ ማስረጃ እያወጣ ካስረዳ በኋላ ከዚያ ደግሞ ከቃለ አበው እየጠቀሰ ነው።
3)    አረጋዊ መንፈሳዊ
አረጋዊ መንፈሳዊ ዮሐንስ ከሚባል የአንድ ገዳም አበምኔት ከነበረ ወንድሙ ጋር ይኖር ነበር። አረጋዊ በገዳሙ ሲኖር በትሕትና ነበር።  ጽሕፈት ያውቃልና ጻፍ ሲሉት እኔስ ብርዑን ቀረጬ፤ ቀለሙን በጥብጬ፤ ብራናውን ዳምጬ አቀርባለሁ እናንተ ጻፉ ይላል።  ንባብ ያውቃልና አንብብ ሲሉ እኔስ አትሮንስ አቀርባለሁ፤ መጽሐፍ አወጣለሁ፤ መብራት አበራለሁ፤ ፤ እናንተ አንብቡ ይላል። ቅዳሴ ያውቃልና ቀድስ ሲሉት እኔስ ጥላ እሰፍራለሁ፤ ቃጭል እመታለሁ፤ ማይን ቀድቼ መሥዋዕቱን ሠርቼ አቀርባለሁ፤ እናንተ ቀድሱ ይላል።
ከዕለታት አንድ ቀን፤ ቀዳሽ ታጥቶ ቀድስ ብለውት ሊቀድስ ገባ።  ጽዋትውን ጨርሶ ከፍሬ ቅዳሴው ሲደርስ መስ ዋ ዕቱን እንደ ደብረሲና  በአምሳለ እሳት፤ እንደ ደብረታቦር፤ በአምሳለ ብርሃን፤ በአምሳለ በግዕ፤ በአምሳለ ሕጻን ተለውጦ አየው። ከዚህ በኋላ በራዕዩ ተመልሶ ቅዳሴውን ቀድሶ ወጥቶ ከሰው ሳልለይ እንዲህ ያለ ምስጢር የተገለጸልኝ ከሰው ብለይማ እንደምን ያለ ምስጢር በተገለጸልኝ ኖሯል? ብሎ ከገዳሙ ወጥቶ አክይስት፤ አናምርት ካሉበት፤ ነቅዐ ማይ ልምላሜ ዕጽ ከሌለበት ዘር ተክል ከማይገኝበት ከጽኑ በረሃ ሄዶ ተቀመጠ።
ዮሐንስም ወንድሙ ጠፍቶት እያዘነ ሲኖር በኋላ ያለበትን ቦታ በማወቁ ወደ ገዳሙ እንዲመጣ ላከበት።  አረጋዊ ግን ተባህትዎውን ትቶ ለመምጣት ፈቃደኛ ስላልሆነ ዮሐንስም የማትመጣ ከሆን ባይሆን ከዚያው ባለህበት ሲደክምህ የምታርፍበት ጎጆ ላሰራልብ ቢለው “ ም ዕራፈ ኩሉ ጌታ ለ እኔ ማደሪያ አነሰኝን? እሱ ይበቃኛልና ይህንንስ አልፈልግም” አለው።  እንኩያስ ብቻህን ስትሆን የሚያነጋግርህ አንድ ሰው ልላክልህ ቢለው “ ለኑዛዜየሰ የአክሉኒ ዕፀወ ዝንቱ ደብር - ለመነጋገርስ የዚህ የበረሃው ዕፅዋት ይበቁኛል” አለው።  ወንድሙ ዮሐንስም ይህም ቢቀር ስትታመም የሚያስታምምህ ስትሞት የሚያሟሙትህ ሰው ልላክልህ ቢለው “ ወዝንቱ ው እቱ ተምኔትየ ከመ እኩን ግዱፈ በገጽየ - የሚያስታምመኝ፤ ብሞትም የሚያሟሙተኝ አጥቼ ባፌ በግንባሬ ተደፍቼ ጉንዳን ፈልቶብኝ፤ ጭጫን ወርሶኝ እንድገኝ ነውና ፈቃዱ ለዚህም አታስብ” አለው።  ያንም ያንም ቢለው የማይቀበለው ሆነ።
ከዚህ በኋላ ሁሉም በያሉበት ሆነው ሲላላኩ ኖረዋል።  ዮሐንስ ያየውን ራዕይና የሚጠይቀውን ጥያቄ ይልክለታል።  ይልቁንም ራዕይን አትመነው፤ እውነትም አለ፤ ሐሰትም አለ እያለ ይጽፍለታል።  ሲጽፍለትም “መል እክት ዘተፈነወ እምሐራውያ ገዳም /ከምድረ በዳ አውሬ የተላከ መልእክት እያለ ነበር። ዮሐንስ ግን ለውጦ “አኮ መፍትው ይበዎ ሐራዉአ ገዳም አላ አረጋዊ መንፈሳዊ ውእቱ - አረጋዊ መንፈሳዊ እንጂ የምድረ በዳ አውሬ ሊሉህ አይገባም” ብሎታል።  ስለዚህ የመጽሐፉም ስም “አረጋዊ መንፈሳዊ” ተብሏል።  ዮሐንስም አረጋዊ የላከለትን ተመልክቶ ሲያበቃ እየሰበሰበ ያስቀምጠዋል።  ኋላም መልእክታቱን ሁሉ ከአንድ ላይ ሰብስቦ ሠላሳ አምስት ድርሳን አርባ ስድስት መልእክት አድርጎታል።

አረጋዊ መንፈሳዊ በአጠቃላይ የሚናገረው ቅዱሳን ከዚህ ዓለም ተለይተው ትሩፋት ሰርተውና መከራ ተቀብለው የሚያገኙት ጸጋና የሚቀምሱትን ጣዕመ መንፈስ ቅዱስ ነው።  አረጋዊ መንፈሳዊ በቤተ መንግስት ያደገ ሰውን ይመስላል።  በቤተ መንግስት ያደገ ሰው የተመከረውን ምክርና የሰማውን ምሥጢር ሰምቶ ይወጣና ለሚመስሉት፤ ለወዳጆቹና ለባልንጀሮቹ ያጫውታል።  አረጋዊ መንፈሳዊም እርሱ ከብቃት ደረጃ ደርሶ ያየውንና የሰማውን ረቂቅ ምሥጢር በዚህ ዓለም ላሉት ለደጋጎቹ ያስረዳልና።  በመጠኑም ቢሆን የጸጋ እግዚአብሔርን ሁኔታ ላላወቀና ጣዕመ መንፈስ ቅዱስን ላልቀመሰ ሰው አረጋዊ መንፈሳዊን ለመረዳት ያስቸግራል።

 

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages