ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ (መዝ 88፤3) - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, September 21, 2022

ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ (መዝ 88፤3)

 ኪዳነ ምሕረት – በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ – ማኅበረ ቅዱሳን

“ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ” 88፥3 በማለት በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት አድሮ ራሱ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አበው ነቢያት ጻድቃን ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ቃል ኪዳን እንደ ገባና እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እግዝአብሔር እንደሚጠራ እንደሚያከብር እንደሚቀድስ ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ ነግሮናል፡፡ /እንግዲህ እርሱ ራሱ ከጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎት የሚቃወማቸው ማን ነው? ብሏል፡፡ ሮሜ.8፥33 ቅዱስ ዳዊትም “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነውብሏል፡፡ መዝ.86፥3 ስለዚህ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የገባው ቃል ኪዳን ከቅዱሳን ቃል ኪዳን ሁሉ ልዩ ነው፡፡ ቃል ኪዳን መሐላ የሚለው መዝገበ ቃላዊ ፍች እንደሚከተለው ተገልጿል፡- ኪዳነ ምሕረት የካቲት 16 ቀን እመቤታችን ከልጇ የምሕረት ቃል ኪዳን /ውል / ስምምነት፣ የተቀበለችበት ዕለት የበዓል ስም ነው፡፡ ኪዳን ማለት ኪዳን፡- ውል፣ መሐላ፣ ቃል ኪዳን፣ የውል ቃል ማለት ነው፡፡ ተካየደ፡- ተዋዋለ፣ ቃል ኪዳን ተጋባ፣ ተማማለ ማለት ነው፡፡ ዘዳ.29፥1፣ ኤር.31፥31-33፣ መዝ.88፥3 በሌላ በኩል ኪዳን፡- የጸሎት ስም ነው፡፡ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ያስተማራቸው ጸሎት “ኪዳን” ይባላል፡፡ በየዓመቱ የካቲት 16 ቀን የምናከብረው በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎልጎታ በልጇ በመቃብር ላይ ሁና ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ “ኦ ወልድየ ወፍቁርየ እስእለከ በእንተ ዘተሰባእከ እምኔየ ወበማሕፀንየ ዘጸረተከ፤ ልጄ ወዳጃ ሆይ ከሥጋዩ ሥጋ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በቻለችህ ማኅፀኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” እያለች ስትጸልይ÷ ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ “ሰላም ለኪ ማርያም እምየ፤ እናቴ ማርያም ሰላም ላንቺ ይሁን እንዳደረግልሽ የምትለምኚኝ ምንድን ነው?” አላት፡፡ ኩሉ ዘጸውአ ስምዬ፤ በስሜ የተማጸነውን ወዘገብረ ተዝካርየ፤ መታሰቢያዬን ያደረገውን ስለስሜ ለችግረኛ የሚራራውን በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጸውን በስሜ ለቤተ ክርስቲያን ዕጣንና ዘይት መብአ የሰጠውን ከሃይማኖት ፍቅር ጽናት፣ ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ” አለችው፡፡ ጌታም “ይህን ሁሉ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው” ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላት ዐርጓል፡፡ ከዚህ የተነሣ ነው ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው “ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል÷ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት÷ አንተ መታሰቢያሽን ያደረገ÷ ስምሽንም የጠራ ÷የዘላለም ድኅነትን ይድናል ብለሃታልና፡፡” ያለው (ገጽ 242) በዚህ ዕለት የሚታሰብ በተአምረ ማርያም መጽሐፍ….. የተገለጸ ሁለት ተአምር አለ፡፡ ስምዖን የሚባል እንግዳ ተቀባይ ደግ ሰው ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያፍርምና ከዕለታት አንድ ቀን በእንግድነት እቤቱ ገብቶ “ልጅህን አርደህ ካላበላኸኝ÷ ሌላ ምግብ አልበላም” አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ስምዖን ወደ እርሱ የመጣውን “የእግዚአብሔር እንግዳ” ላለማሳዘን አወጣ አወረደ፤ በዚያውም ላይ “አብርሃም ልጁን ሰውቶ ነው፡ የእግዚአብሔር ሰው የተባለው፣” በማለት÷ ልጁን አርዶ ሰጠው፡፡ “በግድ ቅመስልኝ” አለው፡፡ ስምዖን አርዶ የቀቀለውን የልጁን ሥጋ በቀምሰ ጊዜ ተዋሕዶት፤ ቤተሰቦቹን ጎረቤቶቹን መንገደኛውን ሁሉ ይበላ ጀመር፡፡ በዚህም 78 ሰው በልቶ አንድ በቁስል የተመታ ሰው ሊበላው ሲል፡- “በሥላሴ ስም፣ በቅዱስ ሚካኤል ስም፣ በቅዱስ ገብርኤል ስም ውኃ አጠጣኝ” ብሎ ለመነው፤ ዝም አለው፡፡ በመጨረሻም “በድንግል ማርያም ስም” አለው፡፡የእመቤታችንን ስም በሰማ ጊዜ በላኤሰብእ ወደ ልቡናው ተመልሶ “እስኪ ድገመው” አለው፤ “ስለ ድንግል ማርያም ውኃ አጠጣኝ” ብሎ ለመነው፡፡ ያን ጊዜ “ይህችስ እንደምታስምር በልጅነቴ ሰምቻለሁ” ብሎ ጥቂት ውኃ ሰጠው፣ ጉሮሮ እንኳን ሳይርስለት ጨረስህብኝ ብሎ ነጥቆት ሄደ፡፡ “ገበሬው በላኤ ሰብ የምትባል አንተነህ?” አለው፡፡ ያን ጊዜ “ለካስ ሰው ሁሉ አውቆብኛል” ብሎ ዋሻ ገብቶ በመጸጸት በዚያው ሞተ፡፡ ነፍሱን መላእክተ ጽልመት መጥተው ሲወስዷት እመቤታችን “መሐር ሊተ ዛተ ነፍሰ ኦ ወልድየ ዘይትሔሰው ቃልከ፤ ልጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ ቃልህ ይትበላልን” አለችው፡፡ “ሰባ ስምንት ነፍስ ያጠፋ÷ ፈጣሪውን የካደ ይማራልን?” አላት፤ እመቤታችንም “በስሜ የተጠማውን ውኃ አጥጥቶ የለምን?” ብላ አስምራዋለች፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ብርሃን መጥተው ወደ ገነት አስገብተዋታል፡፡ ከክርስቲያን ወገን የሆነ ሀብት አግኝቶ ያጣ አንድ ሰው ነበር፡፡ “ከብሬ በኖርሁበት ሀገር÷ተዋርጄ አልኖርም” ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ሲሄድ፣ ሰይጣን ያዘነ መስሎ÷ ደንጊያውን፡- በምትሐት ወርቅ አስመስሎ÷ “አብን ወልድን መንፈስ ቅዱስን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታትን፣ መላእክትን ካድልኝና ይህን እሰጥሃለሁ” አለው፡፡ ካደለትና ተቀብሎ ዞር ሲል፤ “ምእመናን የሚመኩባት ድንግል ማርያም `የአምላክ እናት አይደለችም` ብለህ ካድልኝ” አለው፡፡ “እሷንስ አልክድም” አለው፡፡ በደንጊያ ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ መላእክተ ጽልመት ነፍሱን እጅ አደረጉ፤ መላእክተ ብርሃንም አብረው ቀረቡ እመቤታችንም ቀርባ፤ “ልጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ” አለችው፡፡ “ከልብኑ ይታመሐር እምየ፤ እናቴ ውሻ ይማራልን” አላት፡፡ “ስምሽን የጠራውን መታሰቢያሽን ያደረገውን እምርልሻለሁ ያልኸው ቃል ይታበላልን” አለችው “ምሬልሻለሁ” አላት፡፡ እግዚአብሔር ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ ባለው መሠረት ከቅዱሳን ጋር ያደረጋቸው ቃል ኪዳኖች ብዙዎች ናቸው (መዝ.88፥3)፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የእመቤታችን ኪዳን/አማላጅነት/ ነው፡፡ አማላጅነትዋ እንደሚታወቀው ማማለድ ማለት ስለሌላው መጸለይ፣ መለመን፣ የደረሰውን ችግር እንዲወገድ ማስደረግ፣ ማስማር ማለት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከእግዚአብሔር በታች ከቅዱሳን ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት የማማለድ ሥልጣን “ሰአሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኚልን” እያሉ ለሚለምኑአት ሁሉ ከእግዚአብሔር እያማለደችና እየለመነች ምሕረትን እንደምታሰጥ ቀናውንና የተመሰገነውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሁሉ ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናትና አገልጋይ በመሆንዋ ከሁሉም ቅዱሳን በበለጠ ለእግዚአብሔር ቅርብ ናትና፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም ሆነ በሰው ዘንድ ባለሟልነት ወይም ቅርብ መሆን ጉዳይን ያስፈጽማል፡፡ ለምሳሌ መልአኩ ቅዱስ ገብርአል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ባለሟል በመሆኑ የድኅነትን ምሥጢር አብሣሪ ሆኗል፡፡ ሉቃ.1፥19፣ 1፥26 አስቴር የንጉሡ አርጤክስስ ሚስት በመሆኗ በወገኖቿ አይሁድ የታወጀውን የሞት አዋጅ አስለውጣለች፡፡ መጽሐፈ አስቴር.3፥10 ነቢዩ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟል በመሆኑ ለእስራኤላውያን ምሕረት አሰጠ፡፡ ዘጸ.32፥14 “ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን እኔን ከጻፈከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለው እግዚአብሔርም ራራላቸው፡፡” የቅድስት ድንግል ማርያምም አማላጅነት እንደ ፀሐይ የበራ ሐቅ ነው፡፡ ይህንን እውነት ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር “ወታስተሠርዪ ኀጢአተ ሕዝብኪ ተበውሀ ለኪ እም አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወከመ ትኩኒ ተንከተመ ለውሉደ ሰብእ ለሕይወት ዘለዓለም” ማለት “ለሕዝብሽ ለወገኖችሽ የኃጢአት ይቅርታን ታሰጪ ዘንድ ዘለዓለማዊ ሕይወትንም ለሚወርሱ ሁሉ መሸጋገሪያ ድልድይ ትሆኚ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ÷ከአንድ አምላክ ሥልጣን አግኝተሻል በማለት አመስግኗታል፡፡” /አንቀጸ ብርሃን ተመልከት/ በአባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌው “ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም አሰጠመ ኩሎ፤የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ፤መርገም /ኀጢአት/ ባጠፋን ነበር” ብሏል፡፡ በሥርዓተ ቅደሴአችንም ድኅነትን የምንለምንሽ ክብርን የተመላሽ ቅድስት ሆይ ደስ ይበልሽ ሁል ጊዜ ድንግል የምትሆኚ አምላክን የወለድነሽ የክርስቶስ እናት ሆይ ኀጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ወዳጅሽ ወደ ላይ ጸሎታችንን አሰርጊ፣ በእውነት የጽድቅ ብርሃን የሚሆን አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን ንጽሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፣ ንጽሕት ድንግል ሆይ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግ ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ጌታችን ለምኚልን፡፡ በእውነት ለሰው ወገን አማላጅ የምትሆኝ አምላክን የወለድሽ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ የኀጢአታችንን ሥርየት ይሰጠን በልጅሽ በክርስቶስ ፊት ለምኝልን፣ በእውነት ንግሥት የምትሆኝ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ የባሕርያችን መመኪያ ሆይ ደስ ይበልሽ አምላካችን አማኑኤልን የወለድሽልን ሆይ ደስ ይበልሽ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እውነተኛ አስታራቂ ሆነሽ ታስቢን ዘንድ እንለምንሻለን፡፡ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግልን ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ” በማለት እንማጸናታለን፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ ማዓትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ ለጻድቃን ያይደለ ለኀጥአን አሳስቢ ለንጹሐን ያይደለ ለተዳደፉት አሶስቢ ብሏል፡፡ ቁ.165-171 የእመቤታችን ክብር ከቅዱሳን ክብር ሁሉ የተለየ ነው፤ ይህም እንደምን ነው ቢሉ ለአምላክ እናትነት የተመረጠች ልዩ እናት በመሆኗ ሉቃ.1፥26 አምላክ ከሥጋዬ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከእርሷ በመወለድ ከመለለዷ በፊት በወለደች ጊዜ ከወለደች በኋላ ምን ጊዜም ድንግል በመሆኗ ኢሳ.7፥14 በሁለቱም ወገን /በአሳብም በገቢርም/ ድንግል በክልኤ በመሆኗ አማላጅነቷ የወዳጅነት ሳይነሆን የእናትነት በመሆኑ ዮሐ.2፥5 ዓለም ይድን ዘንድ የድኅነት ምክንያት አድርጎ አምላክ የመረጣት ስለሆነ የእመቤታችን ክብር /ቃል ኪዳን/ ከቅዱሳን ክብር ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወዷታልና ይህች ለዘለዓለም ማረሪያዬ ናት መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ፡፡” በማለት ነግሮናል፡፡ እግዚአብሔር የመረጠውንና የከበረውን መቃወም እንደሣይቻ ሐዋርያውቅ ቅዱስ ጳውሎስም “እንግዲህ እርሱ ራሱ ከጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወመቸው ማን ነው” ብሏል፡፡ ስለዚህ ብዙ ከንቱ አሳቦችን ትተን እንደበላኤሰብ በቃል ኪዳኗ ተጠቅመን ንስሐ ገብተን ቅዲስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀበልን የስሙ ቀዳሽ የመንግሥቱ ወራሽ ለመሆን ያብቃን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ተራደኢነት አይለየን፡፡ ዋቢ መጻሕፍት ተአምረ ማርያም

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages