ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 1 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Tuesday, October 11, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 1

 

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት አንድ በዚህችም ቀን #ቅድስት_አንስጣስያ በሰማዕትነት አረፈች፤ ዳግመኛም የማርታና የአልዓዛር እህት #የቅድስት_ማርያም_እንተ_ዕፍረት የእረፍቷ መታሰቢያ ነው።


በዚህችም ቀን በጥቅምት አንድ ቅድስት አንስጣስያ በሰማዕትነት አረፈች። ይችም ቅድስት መስተጋድልት ከሮሜ አገር ናት ወላጆቿም ክርስቲያኖች ናቸው ጠቃሚ የሆነ ትምህርትን በማስተማር ክብር ባለው በመልካም ሥርዓት አሳደጓት።
በአደገችም ጊዜ ወላጆቿ ሊያጋቧት ፈለጉ እርሷ ግን ይህን ሥራ አልፈለገችም የምንኲስናን ልብስ መልበስ ፈለገች እንጂ፤ ከታናሽነቷም መንፈሳዊ ገድልን መረጠች።
ስለዚህም በሥውር ሒዳ በሮሜ ካሉ ገዳማት ወደ አንዱ ገዳም ገባች ታናሽ ስትሆንም የምንኲስና ልብስን በመልበስ በጾም በጸሎት በረኃብ በጽምዕ በመጠመድ የዚህን ዓለም ሐሳብ ሁሉ ከልቡናዋ ቆርጣ በመተው በመጋደል ሥጋዋን አደከመች።
በቀኑ ርዝመትም ሁሉ የምትጾም ሆነች በየሁለት ቀኖችም ታከፍላለች በጌታችን ጾም ግን ያለ ሰንበታት ቀን የምትመገበው የለም። በሰንበታትም የምትመገበው ከቀትር ጸሎት በኋላ ነው። በነዚያም በምንኲስናዋ ወራት በእሳት ያበሰሉትን ወጥ አልቀመሰችም።
በገዳሟ አቅራቢያም ሌላ የደናግል ገደም አለ የዚያ ደብር በዓልም በደረሰ ጊዜ እመ ምኔቷ በዓሉን ለማክበር ይቺን ቅድስት አንስጣስያን ከእኅቶቿ ደናግል ጋር አስክትላት በአንድነት ተጓዙ። ሲጓዙም የንጉሥ ዳኬዎስን ወታደሮች አየቻቸው። ከእርሳቸውም ጋር የታሠሩ ክርስቲያኖች አሉ ወታደሮቹም አሥረው በቁጣ ይጎትቷቸው ነበር። ልቧም በሃይማኖቷ ፍቅር ነደደና ያን ጊዜ እንዲህ ብላ ዘለፈቻቸው የእውነት ፈጣሪን የካዳችሁ ልባችሁ የደነዘዘ እግዚአብሔር በመልኩና በአምሳሉ በፈጠራቸውና ስለእነርሱም ነፍሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠላቸው ላይ ለምን እንዲህ ትሠራላችሁ።
ይህንንም በአለቻቸው ጊዜ ወታደሮች ተቆጡ ይዘውም ወደ መኰንኑ አቀረቧት እርሱም እንዲህ ብሎ ጠየቃት በእውነት አንቺ የተሰቀለውን የምታመልኪው ክርስቲያን ነሽን? እርሷም ስለእኛ የተሰቀለውን ክብር ይግባውና እርሱን አመልከዋለሁ ብላ መለሰችለት።
በዚያን ጊዜም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያት በሥጋዋም እሳትን ጨመረ ከዚህም በኋላ ዘቅዝቆ ሰቀላት ከበታቿም አጤሱባት ከሃይማኖቷም ባልተናወጸች ጊዜ ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። በዚህ በታላቅ ሥቃይም ውስጥ ሳለች ራሷን በሰይፍ ቆረጧት። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች።


ዳግመኛም በዚህች ዕለት የማርታና የአልዓዛር እህት ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት የእረፍቷ መታሰቢያ ነው።
በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ 'እንተ ዕፍረት' (ባለ ሽቱ) ተብለው የሚጠሩ 2 እናቶች ነበሩ:: ሁለቱም ስማቸው ማርያም ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን 'ማርያም ኃጥዕት (ከኃጢአት የተመለሰች) ሁለተኛዋን ደግሞ 'ማርያም እኅተ አልዓዛር በቢታንያ የነበረችው ብለው አበው ይጠሯቸዋል።
በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐ. 12:1 ላይ ያለችው የአልዓዛር እህት (ድንግሊቱ) ናት። ዛሬም የምናስባት ይህቺውን እናታችን ነው።
ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተመርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት። ወላጆች ባልነበረበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል።
በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው። አልዓዛርን ከ72ቱ አርድእት: ማርያምና ማርታን ደግሞ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል። ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር።
ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ። በ4ኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት ሰግዳ "እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እኁየ" "አንተ በዚህ በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር" ብላ አለቀሰች። (ዮሐ.11)
ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ። ወዲያውም በስልጣነ ቃሉ አዞ አልዓዛርን አስነሳው። ከፋሲካ (ጌታ ከመሰቀሉ 6 ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር አገቡ። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው። (ዮሐ.12፥1)
በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ ቅድስት ማርያም ከጌታ ሥር ተንበርክካ ናርዶስ የሚሉትን የ300 ዲናር ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች። መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ" እንዲል የሚመስጥ ሽታ ቤቱን ሞላው።
በወቅቱ ይሁዳ ቢቃወምም ጌታ ምላሹን ሰጥቶታል። ቅድስት ማርያምንም "ማርያምሰ ኃርየት መክፈልተ ሠናየ ዘኢየኃይድዋ" ብሎ አመስግኗታል። ያስመሰገናት ቁጭ ብላ በተመስጦ መማሯ ብቻ እንዳልሆነ አባ ሕርያቆስ መስከሯል።
ሲመክረንም "አርምሞንና ትዕግስትን እንደ ማርያም ገንዘብ እናድርግ" ብሎናል። (ቅዳሴ ማርያም) ቅድስት ማርያም በጌታችን ክርስቶስ በኅማሙ ጊዜ ሲቀብሩት ነበረች። ትንሳኤውንም ዐይታለች።
ከጌታ እርገት በኋላም መንፈስ ቅዱስን ተከትላ ለወንጌል አገልግሎት ተግታለች። ቅድስት እናታችን ማርያም እንተ ዕፍረት ዛሬ እንዳረፈች እናዘክራለን።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages