ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 20 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 29, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 20

 

ጥቅምት ሃያ በዚህች ቀን ክቡርና ገናና የሆነ #የአባ_ዮሐንስ_ሐፂር እና የስሙ ትርጓሜ ጠባቂና አዳኝ የሆነ #የታላቁ_ነቢይ_ኤልሳዕ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው።


ጥቅምት ሃያ በዚህች ቀን ክቡርና ገናና የሆነ አባ ዮሐንስ ሐፂር አረፈ። የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ ከላይኛው ግብጽ ናቸው እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው ግን ከእርሱ በቀር ልጅ የላቸውም የዚህ ዓለምም ብልጽግና ቢሆን የላቸውም ነገር ግን በበጎ ሥራ ባለጸጎች ናቸው ይህንንም ቅዱስ እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት ።
የዚህም ቅዱስ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነው የእግዚአብሔር ቸርነት አነሣሥታው የመላእክት የሆነ አስኬማን ይለብስ ዘንድ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ ይኸውም የምንኵስና ልብስ ነው።
ከዚያም በደረሰ ጊዜ አባ ባይሞይ የሚባለውን አንዱን አረጋዊ አባት ተገናኘው ዮሐንስም ሰገደለትና ወደ እርስ እንዲቀበለው ለመነው ሽማግሌውም አባት ልጄ ሆይ ያንተ በዚህ መኖር ልክ አይደለም በዚች ገዳም የሚኖሩ በእጆቻቸው ይሠራሉ በቀንና በሌሊት ይጾማሉ ይጸልያሉ በሚተኙም ጊዜ ያለ ምንጣፍ በምድር ላይ ይተኛሉ አንተ ወጣት ጎልማሳ ስለሆንክ ይህን ሁሉ ችግር አትችልም። ነገር ግን ወደ ዓለም ተመልሰህ እንደ ሰው ሁሉ በጎ አኗኗርን ትኖር ዘንድ ይሻልሃል የዚች ገዳም ኑሮ ጭንቅ ነውና አለው።
አባ ዮሐንስም እንዲህ አለው እኔ በጥላህ ሥር ልኖር መጥቼአለሁና ስለ እግዚአብሔር ብለህ ተቀበለኝ እንጂ አትመልሰኝ ይህም አባ ባይሞይ እግዚአብሔርን ሳይጠይቅ ምንም ሥራ አይሠራምና በዚያን ጊዜ ሥራውን ይገልጥለት ዘንድ ስለ ዮሐንስ ሐፂር እግዚአብሔርን ለመነው የእግዚአብሔርም መልአክ ተገልጦለት እርሱ የተመረጠ መሳሪያ ይሆናልና ተቀበለው ብሎሃል አለው።
ከዚህም በኋላ ዮሐንስ ሐፂርን ወስዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገባው የምንኵስና ልብሶችንም አምጥቶ በላያቸው ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ጸለየ ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾ በመስቀል ምልክት በልብሶቹ ላይ አማተበ ሽማግሌውም እነዚያን ልብሶች ለአባ ዮሐንስ አለበሰው ።
ከዚያቺም ቀን ጀምሮ አባ ዮሐንስ ተጋድሎንና አገልግሎትን ጀመረ አባ ባይሞይም ሊፈትነው ወደደ በአንዲትም ቀን ደብድቦ ከአንተ ጋር መኖር አልሻም ብሎ ከበዓቱ አስወጥቶ አባረረው የከበረ አባ ዮሐንስም ከሜዳ መካከል በውጭ ቆመ በየቀኑም በጥዋት እየወጣ ከእዚህ ላይህ አልሻም እያለ ይመታዋል እርሱ ግን አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ ብሎ ከእግሩ በታች ይሰግዳል ።
በሰባተኛዪቱም ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊሔድ ሽማግሌው አባ ባይሞይ ወጣ አባ ዮሐንስንም ሰባት መላእክት ከበው አክሊላትን ሲያቀዳጁት አያቸው ከዚያንም ጊዜ ወዲህ መፈተኑን ተወው ወደ መኖሪያውም አስገባው።
ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን አባ ባይሞይ የደረቀ ዕንጨት አግኝቶ ወስዶ ለአባ ዮሐንስ ሰጠውና ይህን ዕንጨት ትከለው እስከሚበቅልና እስከሚአፈራ ድረስ ውኃን አጠጣው አለው ። አባ ዮሐንስም ለአባቱ ታዛዥ በመሆን ተቀብሎ ወስዶ ተከለው በየቀኑም ሁለት ሁለት ጊዜ ያጠጣዋል ውኃውም ዐሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል የራቀ ነው።
ከሦስት ዓመትም በኋላ ያ ዕንጨት አቈጥቊጦ በቀለ ታላቅም ዛፍ ሁኖ አብቦ ጣፋጭ ፍሬን አፈራ። አባ ባይሞይም ከፍሬው ለቅዱሳን አረጋውያን ወሰደላቸውና የታዛዡንና የትሑቱን ፍሬ እነሆ ብሉ አላቸው እነርሱም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው አደነቁ ለመምህሮቻቸው ለሚታዘዙ እንዲህ ያለ ጸጋ የሚሰጥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
አባ ባይሞይም ዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል በጽኑዕ ደዌ ውስጥ ተይዞ ኖረ አባ ዮሐንስም ያገለግለው ነበር አባ ዮሐንስን እንደፈተነው የተመረጠ መሥዋዕትን ይሆን ዘንድ በዚህ ደዌ እንዲፈተን እግዚአብሔር ፈቅዷልና።
በሚሞትበትም ጊዜ አባ ባይሞይ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትን ሰበሰባቸውና አባ ዮሐንስንም እጁን ይዞ እርሱ ሰው ያይደለ መልአክ ነውና ተቀብላችሁ ጠብቁት ብሎ ሰጣቸው ። እርሱንም ደግሞ እንዲህ አለው ከእረፍቴ በኋላ ያን ዕንጨት ወደ ተከልክበት ቦታ በዚያ ኑር እግዚአብሔር ላንተ ያዘጋጀልህ ነውና ብዙዎችም በአንተ እጅ ይድናሉ መታሰቢያህም በዚያ ጸንቶ ይኖራል ዜናህም በዓለም ሁሉ ይወጣል ይህንንም ተናግሮ አረፈ አክብረውም ቀበሩት።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባ ዮሐንስ አረጋዊ አባቱ አባ ባይሞይ እንደነገረው ወደዚያ ቦታ ሒዶ ኖረ ዜናውም በዓለም ሁሉ እጅግ እስከ ተሰማ ድረስ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ።
በራሱ ቤተ ክርስቲያንም አበ ምኔት ሁኖ ተሾመ በሹመቱም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ እጆቹን በራሱ ላይ ሲጭን አክዮስ አክዮስ አክዮስ የሚል ቃል ከሰማይ ተሰማ ይህም ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል ማለት ነው ። የቊርባን ቅዳሴን በሚቀድስ ጊዜ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል የማይገባቸውን ይለያቸዋል ዛሬስ ሒዳችሁ ንስሓ ግቡ ከዚያም በኋላ ተመልሳችሁ ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ ይላቸዋል።
ይህን አባ ዮሐንስንም ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ የቅዱሳን የሠለስቱ ደቂቅን ሥጋቸውን እንዲአመጣለት ወደ ባቢሎን ልኮታል ይህም በግንቦት ወር በዐሥረኛው ቀን ተጽፎአል ። በአንዲትም ዕለት አንድ መነኰስ ሊጎበኘው ወደ በዓቱ ቢመጣ አባ ዮሐንስን ተኝቶ አገኘው የእግዚአብሔርም መላእክት በላዩ ይጋፉ ክንፎቻቸውንም ያርገበግቡ ነበር አንዱም ሌላውን ተወኝ ክንፌን በላዩ ላኑር ይለዋል ይህንንም አይቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው ።
ከዚህም በኋላ የመነኩሳቱን መንደር ሊበረብሩ የበርበር አረማውያን ወደ አስቄጥስ ገዳም በመጡ ጊዜ አባ ዮሐንስም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ወደ ቁልዝም ሔደ በዚያም በአባ እንጦንስ ገዳም በጎኑ በአለ ቦታ ተቀመጠ እስከ ሚያርፍባትም ቀን ድረስ የሚያገለግለው አንድ የታመነ ሰውን እግዚአብሔር አመጣለት ።
ከዚህም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው በወደደ ጊዜ እግዚአብሔር ቅዱሳን ጻድቃኖቹን አባ እንጦንስን፣ አባ መቃርስን፣ አባ ጳኵሚስን ከእርሳቸውም ጋር መንፈሳዊ አባቱ አባ ባይሞይን ያረጋጉትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም መለየቱን ይነግሩት ዘንድ ወደርሱ ላካቸው ። እነርሱም እንዲህ ብለው አረጋጉት ደስ ይበልህ እግዚአብሔር የማያልቅ ተድላ ደስታን አዘጋጅቶልሃልና ክብር ይግባውና ጌታችንም እንዳዘዘ በእሑድ ቀን ሁለተኛ ወዳንተ መጥተን ወደ ዘላለም ሕይወት እንወስድኻለን ባርከውትም ከእርሱ ዘንድ ተመለሱ ።
በዐርብ ቀንም አገልጋዩን ወደ አንድ ቦታ ላከው ከዚህም በኋላ ጥቂት ታመመ በእሑድም ቀን ሌሊት ዶሮ ሲጮህ እሊያ ቅዱሳን ከሁሉም ቅዱሳን ማኅበር ጋር መጡ የመላእክትም ሠራዊት ሁሉ ወደርሱ መጡ በአያቸውም ጊዜ ደስ ብሎት በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ መላእክትም እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ነፍሱን አሳረጓት በዚያንም ጊዜ ረድኡ መጣ ነፍሱንም ከበው እያመሰገኑ ሲያሳርጓት የጻድቃንና የመላእክትን ማኅበር አይቶ እያደነቀ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ ። ከመላእክትም አንዱ ወደርሱ መጥቶ የቅዱሳንን ስማቸውን በመጥራት በጣቱ እያመለከተ ይህ አባ ዕገሌ ነው ብሎ አስረዳው ረድኡም መልአኩን እንዲህ ብሎ ጠየቀው ይህ በፊታቸው ያለ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚበራ ማን ነው መልአኩም የመነኰሳቱ ሁሉ አባት አባ እንጦንስ ነው ብሎ መለሰለት።
ወደ በዓቱም ያ ረድእ በገባ ጊዜ በምድር ላይ ሰግዶ እንዳረፈ አባ ዮሐንስን አገኘውና ታላቅ ልቅሶን በላዩ አለቀሰ ከዚያም በኋላ ወደ መነኰሳቱ መንደር ፈጥኖ በመሔድ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐፂር እንደ አረፈ ነገራቸው ። እነዚያም መነኰሳት አክብረው ገንዘው ሥጋውን ተሸክመው ወስደው በቦታቸው አኖሩት።
የደረቀ ዕንጨት ተክሎ በአበቀለበት ላይ በሠራት የራሱ በሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ልጆቹ ከዚህ አፍልሰው ወስደው እስከ አኖሩት ድረስ በዚያ ኖረ።

ዳግመኛም በዚህች ቀን የስሙ ትርጓሜ ጠባቂና አዳኝ የሆነ የታላቅ ነቢይ የኤልሳዕ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
እርሱም አሜሁላ ከሚባል አገር ከይሳኮር ነገድ ነው ብዙ ትንቢትን ተናግሮአል ብዙ ተአምራትንም አድርጓል። የኢያሪኮም ሰዎች ኤልሳዕን ጌታችን እንደምታያት የዚች አገር ኑሮዋ ያማረ የተወደደ ነው የአገሩ ውኃ ግን ክፉ ነው ሴቶች ሲጠጡት ይመክናሉ አሉት ኤልሳዕም ጨው ጨምራችሁ አዲስ ሸክላ አምጡልኝ አላቸው እነርሱም አመጡለት ።
ኤልሳዕም ወደ ውኃው ምንጭ ሒዶ ያንን ጨው በውስጡ ጨመረውና እግዚአብሔር እንዲህ አለ እርሱን ከመጠጣት የተነሣ የሚሞት እንዳይኖር የሚመክንም እንዳይኖር ይህን ውኃ ለውጥኩት አለ አላቸው ።
ከዚያችም ቀን በኋላ ኤልሳዕ እንደተናገረ እስከ አሁን ድረስ ያ ውኃ ተለወጠ። የዚህ የነቢይ ኤልሳዕ ተአምራቱ ብዙ ነው የሶርያውን ሰው ንዕማንን ከለምጹ ያነጻው እርሱ ነው ሁለት ሙታንን አንዱን በሕይወት ሳለ ሌላውንም ከሞተ በኋላ አስነሥቷል። የትንቢቱንም ወራት ፈጽሞ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages