አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም 21 በዚህች ቀን #ብዙኃን_ማርያም (ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ከሩቅም ከቅርብም የተሰባበሰቡት ቀን፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት ነው) እንዲሁም #ቅዱስ_ቆጵርያኖስና #ድንግሊቱ_ዮስቴና በሰማዕትነት ያረፉበትም ቀን ነው።
በ፫፻፳፭ ዓ.ም አር*ዮስ የሚባል መና*ፍቅ የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም በሚል ክህ*ደት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል ኾነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አር*ዮስ ክህ*ደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ የአር*ዮስ ክህ*ደትም በሊቃውንቱ መካከል መለያየትን ፈጥሯል፡፡ ጊዜው ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ‹‹አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!›› የሚል ዐዋጅ የነገረበት ወቅት ነበርና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአር*ዮስ ክህ*ደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሔድ በየአገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡
በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ኒቅያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያትም ጳጳሱን ከማኅበረ ካህናቱ፤ ንጉሡን ከሠራዊቱ ጋር አጠቃላ ለመያዝ የምትችል ሰፊና ምቹ ቦታ ከመኾኗ ባሻገር ለኹሉም አማካይ ሥፍራ ስለ ነበረች ነው፡፡ በጉባኤው ከተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከልም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ፣ ለምጽ ያነጹ፣ አንካሳ ያረቱ፣ የዕውራንን ዓይን ያበሩ ድውያንን የፈወሱ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ተአምር ያደረጉ፤ እንደዚሁም ስለ ርትዕት ሃይማኖታቸው በመጋደል ዓይናቸው የፈረጠ፣ እጃቸው የተቈረጠ ይገኙበታል፡፡
ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን "ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ" ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ (2348) መካከል ፫፻፲፰ (318) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው "ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው" ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም "ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን" ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት ፫፻፲፰ቱ የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው /ዘፍ.፲፬፥፲፬/፡፡
፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮ*ስን አው*ግዘው በመለየት "ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን" የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎችን ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት "#ብዙኃን_ማርያም" እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡
በቤተ
ክርስቲያናችን ከሚዘከሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላት መካከል መስከረም ፳፩ ቀን የሚውለው
በዓል ‹‹ብዙኃን ማርያም›› በመባል ይታወቃል፡፡ በዓሉ በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ይከበራል፤ የመጀመሪያው ሊቃውንተ
ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ከሩቅም ከቅርብም የተሰባበሰቡት ቀን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጌታችን
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት መኾኑ ነው፡፡
ሁለቱንም ታሪኮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፤
በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤
ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው "የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በአገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል" አሏቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር "የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ" የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ "ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት" ብለው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡
ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡
መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ "አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ" የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደ ወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ "አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ" ይላቸው ነበር፤ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ም የጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡
ከዚህ በኋላ ንጉሡ ‹‹መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!›› ብለው ዐዋጅ ነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡
በዚችም ቀን ቅዱስ ቆጵርያኖስና ድንግሊቱ ዮስቴና በሰማዕትነት አረፉ። ይህም ቅዱስ ቆጵርያኖስ አስቀድሞ ከሀ*ዲና ሥራ*የኛ ነበር እርሱም ለሥራ*የኞች ሁሉ አለቃቸው ነው።
ቆጵርያኖስም ወደ አንጾኪያ ከተማ በደረሰ ጊዜ ወሬው ተሰማ በአንጾኪያም ከተማ ከሀገር ታላላቆች ተወላጅ የሆነ አንድ ጐልማሳ አለ እርሱም ላህይዋ የሚያምር አንዲቷን ድንግል ብላቴና ተመኛት ወደ ቤተ ክርስቲያን በምትሔድ ጊዜ እያያት በእርሷ ፍቅር ልቡ እንደ እሳት ተቃጠለ በምንም በምን ሊአገኛት አልተቻለውም ገንዘብ በመስጠትም ቢሆን ወይም በማስፈራራት ወይም በሥ*ራይ ሥራ አልሆነለትም።
የቆጵርያኖስም ወሬው በተሰማ ጊዜ እርሱ ከሥራ*የኞች ሁሉ እንደሚበልጥ ስለርሱ ተነግሮአልና ያም ድንግል ዮስቴናን የተመኛት ጐልማሳ ወደ ቆጵርያኖስ ሒዶ በልቡ ያለውን ጉዳዩን ድንግሊቱን ዮስቴናን እንደተመኛትና እርሷን ማግኘት እንደተሳነው ነገረው ቆጵርያኖስም እኔ የልብህን ፍላጎት እፈጽምልሃለሁ አትዘን አለው።
ከዚያም በኋላ ያን ጊዜ ዮስቴናን ወደርሱ ያመጧት ዘንድ በሥራ*ዩ የአጋንንትን ሠራዊት ወደርሷ ላከ እነዚያም አጋንንት ወደርሷ በቀረቡ ጊዜ እርሷን መውሰድ አልቻሉም ከጸሎቷ የተነሣ ይቃጠላሉና እንዲህም ብዙ ጊዜ ላካቸው ግን ወደርሱ ሊያመጧት አልቻሉም ቆጵርያኖስም ሁሉንም አጋንንት ጠርቶ ድንግል ዮስቴናን ካላመጣችሁልኝ እኔ ከእናንተ ተለይቼ ክርስቲያን እሆናለሁ አላቸው።
ከዚህም በኋላ የሰይጣናት አለቃ ሊሸነግለው አሰበ አንዱንም ሰይጣን ከሰይጣናት ውስጥ በዮስቴና አምሳል ተመስሎ ለቆጵርያኖስ እንዲታየው አደረገ። ሰይጣኑም አለቃው እንዳዘዘው እንዲህ አድርጎ ተዘጋጀ እነሆ አሁን የዮስቴናን መምጣት ለቆጵርያኖስ ነገረው እርሱም እውነት መስሎት እጅግ ደስ አለው ሊቀበላትም ተነሣ። በእርሷ አርአያ የተመሰለውንም ምትሐት በአየ ጊዜ የሴቶች እመቤት ዮስቴና መምጣትሽ መልካም ሆነ አለ ይህንንም ስሟን በጠራ ጊዜ ያ በእርሷ አምሳል የተመሰለ ሰይጣን እንደ ጢስ ሁኖ ተበተነ።
በዚያንም ጊዜ የሽንገላው ምክንያት ምትሐ*ቱም ከንቱ እንደሆነ ቆጵርያኖስ አወቀ አስተዋለም በልቡም እንዲህ አለ። ስሟን በጠሩበት ቦታ እንደ ጢስ የሚበተኑ ከሆነ በፊቷ ሊቆሙ ሊሸነገሏትስ እንዴት ይቻላቸዋል ይህንንም ብሎ ወዲያውኑ የጥን*ቆላ መጻሕፍቶቹን አቃጠለ።
ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠምቆ የምንኲስና ልብስን ለበሰ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ዲቁና ሾመው። ዳግመኛም ቅስና ሾመው በትሩፋት ሥራና በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ለሀገሩ ምዕራብ ለሆነች ቅርጣግና ለምትባል አገር ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ ተገባው ያን ጊዜም ቅድስት ዮስቴናን ወስዶ ለደናግል ገዳም እመ ምኔት አደረጋት።
በቅርጣግናም የቅዱሳን የአንድነት ስብሰባ በሆነ ጊዜ ከጉባኤው አባላት እርሱ አንዱ ነው።
ከብዙ ወራት በኋላም ከሀ*ዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ስለእነርሱ ሰማ ወደርሱም አስቀረባቸውና የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክደው ለጣዖቶቹ እንዲሰግዱ አዘዛቸው። ትእዛዙንም ባልሰሙ ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው ብዙ ሥቃይንም ከአሠቃያቸው በኋላ የቅዱስ ቆጵርያኖስንና የቅድስት ደንግል ዮስቴናን የሦስት ወንዶችንም ራሳቸውን አስቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment