ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም 24 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, October 5, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም 24

 መስከረም_24

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ አራት #ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ ወደ ደብረ ሊባኖስ የገባችበት፣ ከላይኛው ግብጽ የሆነ ቅዱስ አባት #መነኰስ_ጎርጎርዮስ ያረፈበት እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ለአንዱ #ሐዋርያ_አድሊጦስ የምስክርነቱ መታሰቢያ ነው።

መስከረም ሃያ አራት ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ወደ ደብረ ሊባኖስ የገባችበት ነው። ቅድስት እናት ክርስቶስ ሠምራ ቅንነቷ፣ ደግነቷና ቅድስናዋ እጅግ የበዛ ነው። አንድ ቀን ግን ገና በትዳር ውስጥ እያለች ከአገልጋዮቿ አንዷን ትጠራትና ታዛታለች። ያቺ አገልጋይ ግን የታዘዘችውን ጀሮ ዳባ ልበስ ብላ ሳትታዘዛት ትቀራለች።
ደጋግማ ብትነግራትም ልትሰማት አልቻለችም። ያን ጊዜ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልትገስጻት ብላ ጠጠር ብትወረውርባት ያች አገልጋይ ወድቃ ሞተችባት። ቅድስቲቱ እጅግ ደንግጣ አለቀሰች። የምታደርገውንም አጣች።
ወዲያው ግን ፈጠን ብላ: ወገቧን ታጥቃ ትጸልይ ጀመረች። "ጌታየ ሆይ! ከሞት አስነሳልኝና ዓለምን ትቼ በቀሪ ዘመኔ አንተን አገልለግልሃለሁ" ብላ ፈጣሪን በብዙ እንባ ተማጸነችው:: ያን ጊዜም አገልጋዩዋ ከሞት ተነሳችላት።
ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ጊዜን አላጠፋችም። ልጆቿን በቤት ትታ ሃብትን ብረቷን ንቃ አንድ ልጇን አዝላ ቤቷን እንደ ተከፈተ ትታው ወደ ገዳም ወጣች። በዚህ ዕለትም (መስከረም 24 ቀን) ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገባች።

ዳግመኛም በዚህች ቀን ከላይኛው ግብጽ የሆነ ቅዱስ አባት መነኰስ ጎርጎርዮስ አረፈ ። የዚህም የቅዱስና የተመሰገነ ጎርጎርዮስ ወላጆቹ ደጎች ናቸው በዚህ ዓለም ገንዘብም እጅግ ባለጸጎች ነበሩ ይህን ልጃቸውን ጎርጎርዮስንም በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት ። መንፈሳዊ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ሁሉ ሥጋዊም የሆነ ጥበብንና ቋንቋን አስተማሩት ።
ከዚህም በኋላ የሀገራቸው ኤጲስቆጶስ ወደ ሆነ ወደ አባ ይስሐቅ ወሰዱት እርሱም እጁን በላዩ ጭኖ አናጒንስጢስነት ሾመው ።
ከዚህም በኋላ ወላጆቹ ሊአጋቡት አሰቡ እርሱ ግን ይህን ሥራ አልወደደም ሁለተኛም ወደ ጳጳስ ወስደውት ፍጹም ዲቁናን ተሾመ ወደ አባ ጳኲሚስም አዘውትሮ በመሔድ ከእርሱ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚማር ሆነ ከወላጆቹም ብዙ ገንዘብን ወስዶ ወደ አባ ጳኲሚስ አቅርቦ በገዳማቱ ለሚሠሩ ሕንፃዎች ሥራ ያደርግለት ዘንድ ብዙ ልመናን ለመነው እርሱም ተሳትፎ እንዲሆንለት ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ለመነኰሳት ቤት መሥሪያ አደረገለት ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዓለምን ትቶ ጥሪቱንና ገንዘቡን ሁሉ ንቆ በመተው ወደ ቅዱስ አባ ጳኲሚስም ሒዶ የምንኲስና ልብስን ለብሶ በጾም በጸሎት በመትጋት በመስገድ ከትሕትና፣ ከቅንነት፣ ከፍቅር ጋር ይጋደል ጀመረ አርአያነቱንና ምሳሌነቱን በአዩ ጊዜ ከእርሱ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ተምረው አመንዝራዎች የከፋ ሥራቸውን እስከ ተውና ንስሐም ገብተው ንጹሐንም እስከ ሆኑ ድረስ ተጋደሉ ። ከአባ ጳኲሚስም ዘንድ ዐሥራ ሦስት ዓመት ኖረ ።
አባ መቃርስም ወደ አባ ጳኲሚስ በመጣ ጊዜ ሰውነቱን በማድከም ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ ጥቂት ቀኖች ኖረ ከዚያም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሊመለስ ወደደ አባ ጳኲሚስም ከአባ መቃርስ ጋር እንዲሔድ አባ ጎርጎርዮስን አዘዘው እርሱም አብሮ ሔደ በእርሱም ዘንድ ብዙ ዘመናት ኖረ ።
ከዚህም በኋላ በዋሻ ብቻውን ይኖር ዘንድ እንዲአሰናብተው የከበረ አባ መቃርስን ለመነው እርሱም እንደ ወደድክ አድርግ አለው ። ያን ጊዜ ወደ ተራራ ሒዶ ታናሽ ዋሻ ቆርቁሮ በውስጧ ሰባት ዓመት ኖረ አባ መቃርስም በየዓመቱ ሁለት ጊዜ መጥቶ ይጎበኘዋል አንደኛ ለከበረ የልደት በዓል ሁለተኛ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተነሣባት በትንሣኤ በዓል ቀን ከርሱ ጋርም ሥጋውንና ደሙን ተቀብሎ ወደ ቦታው ይመለሳል ። አባ መቃርስም ስለ ሥራው ሁሉ ይጠይቀዋል እርሱም የሚያየውንና በእርሱ የሆነውን ሁሉ ይገልጽለታል አባ መቃርስም ሊሠራው የሚገባውን የምንኲስና ሥራን ይሠራ ዘንድ ያዘዋል ።
በተጋድሎም ውስጥ ሃያ ሁለት ዓመታት ሲፈጽሙለት ከዚህ የድካም ዓለም ያሳርፈው ዘንድ እግዚአብሔር ፈቅዶ መልአኩን ላከለት እርሱም ከሦስት ቀን በኋላ ከዚህ ከኀላፊው ዓለም ወጥተህ ወደ ዘላለም ሕይወት ትገባለህ አለው ።
አባ ጎርጎርዮስም በአስቄጥስ ገዳም ያሉ አረጋውያንን አስጠራቸውና ተሳለማቸው በጸሎታቸውም እንዲአስቡት ለመናቸው እነርሱም ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲአስባቸው ለመኑት ከሦስት ቀንም በኋላ አርፎ ወደ ዘላለም ሕይወት ገባ ።

ሐዋርያው_አድሊጦስ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)
በዚህችም ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ለአንዱ ሐዋርያ አድሊጦስ የምስክርነቱ መታሰቢያ ነው ። ይህም ሐዋርያ ትውልዱ ከአቴና አገር ከታላላቆቿና ከምሁራኖቿ ነው እርሱም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ አገለገለውም ።
አጽናኝ የሆነ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በሃምሳኛው ቀን ከተቀበለ በኋላ ወደ ብዙዎች አገሮች ሒዶ ሕይወት የሆነ ወንጌልን ሰበከ መግኒን ወደሚባልም አገር ደርሶ በውስጧ የከበረ ወንጌልን ሰበከ የብዙዎችንም ልቦና ብሩህ አድርጎላቸው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ። የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ሕይወት የሆኑ የወንጌልንም ትእዛዞች አስተምሮ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው ።
ከዚህም በኋላ ከእሳቸው ዘንድ ወጥቶ ወደ አቴና አገር ተመለሰ በውስጧም የከበረ ወንጌልን አስተማረ በዚያን ጊዜም በደንጊያ ወገሩት ጽኑዕ የሆነ ሥቃይንም አሠቃዩት ። ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ወረወሩትና በዚያ ተጋድሎውንና ምስክርነቱን ፈጽሞ የሕይወት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages