ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም 25 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, October 5, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም 25

 መስከረም_25

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ አምስት በዚች ቀን የከበረች #ቅድስት_በርባራ መታሰቢያዋ ነው፣ #ታላቁ_ነቢይ_ዮናስ እረፍቱ ነው።

መስከረም ሃያ አምስት በዚች ቀን የከበረች ቅድስት በርባራ መታሰቢያዋ ነው። ይችም ቅድስት በርባራ በከሀዲው መክስምያኖስ ዘመነ መንግሥት በቤተ መንግሥት ውስጥ ታላቅ መስፍን ለሆነ ሰው ልጁ ናት ስሙም ዲዮስቆሮስ ነው እርሱም ለልጁ ለበርባራ ማንም እንዳያያት ታላቅ ጽኑ የሆነ ሕንፃ አሠራ ከዚህም ዳግመኛ መታጠቢያ የውሽባ ቤት በግንብ ሠራ የሚከፈቱ ሁለት መስኮቶችንም በውስጡ እንዲሠሩ አዘዘ። ቅድስት በርባራም ሁለቱን መስኮቶች በአየች ጊዜ ሦስተኛ መስኮትን እንዲሠሩ ሐናፂዎችን አዘዘቻቸው ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝ የሆነ የመስቀሉን ምልክት በውኃ መታጠቢያው ላይ አሠራች።
አባቷም ወደዚህ ሕንፃ በገባ ጊዜ ይህን ልጁ ያሠራችውን አይቶ አናፂዎችን ጠየቀ እነርሱም ይህን እንድንሠራ ልጅህ አዘዘችን አሉት እርሷንም ጠርቶ ለምን እንዲህ አደረግሽ አላት። እርሷም አባቴ ሆይ አስተውል ልዩ ሦስት በሆነ በሥላሴ ስም ሥራ ሁሉ ይፈጸማልና ስለዚህ ሦስተኛ መስኮት አሠራሁ ይህም መስቀል ዓለሙ ሁሉ በእርሱ በዳነበት በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አምሳል ነው አንተም አባቴ ሆይ ከስሕተትህ ተመልሰህ የፈጠረህን አምላክ አምልከው አለችው።
አባቷም ከእርሷ ይህን በሰማ ጊዜ ሰይፉን መዝዞ በኋላዋ ሮጠ እርሷም ሸሸች በፊቷም የነበረች ዐለት ተሠንጥቃ በውስጧ ገብታ ሠወረቻት። ከዚህም በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች እርሱም እንዲአሠቃያት ለሌላ መኰንን አሳልፎ ሰጣት እርሱም ታላቅ ሥቃይን አሠቃያት በዚያም ዮልያና የምትባል ሴት ነበረች ቅድስት በርባራንም አየቻትና የምታጽናናትና የምታረጋጋት ሆነች ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለቅድስት በርባራ ተገለጸላትና አረጋጋት።
ከዚህም በኋላ አባቷ በሰይፍ ራሷን እንዲቆርጡ የባልንጀራዋ የዮልያናንም ራስ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጧቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ። በዚያንም ጊዜ ከሰማይ እሳት ወርዶ አባቷንና ጓደኛው የሆነ መኰንን መርትያኖስን አቃጠላቸው ያም በውሽባ ቤት ውስጥ በመስቀል ምልክት ያሠራቸው መታጠቢያ ለታመመ ሁሉ ከእርሱ በታጠበ ጊዜ የሚያድን በውስጡ ታላቅ ፈውስ ያለበት ሆነ።
ከዚህም በኋላ የቅዱሳት ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወስደው ከከተማ ውጭ ባለች ቤተ ክርስቲያን ስሟ ገላልያ በሚባል ቦታ አኖሩአቸው ይህ ሥጋቸውም በቅዱሳን ሰማዕታት በአቡቂርና በዮሐንስ በምስር አገር ባለ ቤተ ክርስቲያናቸው እስከ ዛሬ አለ።

በዚህች ቀን ታላቁ ነቢይ ዮናስ አረፈ። ይህም እውነተኛ ነቢይ ዮናስ የሲዶና ክፍል በምትሆን ስራጵታ በምትባል አገር ለምትኖር መበለት ልጅዋ የሆነ ነቢይ ኤልያስም ከሙታን ለይቶ ያሥነሣው ኤልያስንም ያገለገለውና የትንቢት ጸጋ የተሰጠው ነው።
ከዚህም በኋላ ስሙ ከፍ ከፍ ያለና የተመሰገነ እግዚአብሔር ወደ ነነዌ አገር ሒደህ ሀገራቸሁ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ትጠፋለች ብለህ አስተምር ብሎ አዘዘው።
እግዚአብሔርም ይህን በአለው ጊዜ ዮናስ በልቡ እንዲህ ብሎ አሰበ እግዚአብሔር ሊአጠፋቸው ቢወድ ኖሮ ሒደህ አስተምር ብሎ ባላዘዘኝ ነበር እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ሲምራቸው እኔ በእነርሱ ዘንድ ሐሰተኛ ነቢይ እንዳልባል እፈራለሁ ከቶ ትምህርቴን አይቀበሉኝም ወይም ይገድሉኛል ወደዚያች አገርም ሒጄ እንዳላስተምር ከእግዚአብሔር ፊት ብኰበልልና ብታጣ ይሻለኛል።
ወንድሞች ሆይ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ፊት ለፍጡር ማምለጥ ይቻለዋልን። ይህስ ዮናስ የእስራኤልን ልጆች ከሚያስተምሩ ነቢያት ውስጥ ሲሆን ይህን አያውቅምን ነገር ግን አግዚአብሔር በረቀቀ ጥበቡ ይህን አደረገ እንጂ የዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አድሮ መውጣት መድኃኒታችን በመቃብር ሆድ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አድሮ ከዚህ በኋላ ከሙታን ተለይቶ ለመነሣቱ ምልክት ይሆን ዘንድ ነው።
ዮናስም ከዓሣ አንበሪ ሆድ ያለ ምንም ጥፋት እንደመጣ እንዲሁ መደኃኒታችን ያለመለወጥ ተነሥቷልና።
እንዲህም ሆነ ከእግዚአብሔር ፊት ዮናስ ሸሽቶ ወደ ተርሴስ አገር ሊሔድ ተነሣ ወደ ኢዮጴ አገርም ወርዶ ወደ ተርሴስ አገር የሚሔድ መርከብን አግኝቶ በገንዘቡ መርከቡን ተከራየ።
ከእግዚአብሔር ፊት ኰብልሏልና ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሔድ ዘንድ ወደ መርከቡ ወጣ እግዚአብሔርም ታላቁን ነፋስ ወደ ባሕር አመጣ የባሕሩም ማዕበል ከፍ ከፍ አለ መርከባቸውም ሊሰበር ቀረበ። ቀዛፊዎችም ፈርተው ወደ ጣዖቶቻቸው ጮኹ መርከባቸውም ይቀልላቸው ዘንድ ገንዘባቸውን፣ ዕቃቸውን አውጥተው ወደ ባሕር ጣሉ። ዮናስ ግን በዚያን ጊዜ ወደ ከርሠ ሐመሩ ወርዶ ተኝቶ ያንኰራፋ ነበር።
መርከቡንም የሚቀዝፍ ቀዛፊ ወደ ርሱ ወርዶ ምን ያስተኛሃል እንዳንሞት እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ተነሥተህ የፈጣሪህን ስም ጥራ አለው። ይህች መከራ ያገኘችን ስለማናችን ኃጢአት እንደ ሆነ እናውቅ ዘንድ እርስ በርሳቸው ኑ ዕጣ እንጣጣል ተባባሉ በተጣጣሉም ጊዜ ዕጣ በዮናስ ወጣበት። እነርሱም ይህች መከራ ያገኘችን በማናችን ኃጢአት እንደሆነ ንገረን አንተስ የምታመልከው ምንድንነው ከወዴትስ መጣህ አገርህስ የት ነው ወዴትስ ትሔዳለህ ወገንህስ ማንነው አሉት።
ዮናስም እኔስ የእግዚአብሔር ባርያው ዕብራዊ ነኝ ፈጣሪዬም ምድርንና ሰማይን ባሕሩንና የብሱን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው አላቸው። እነዚያም ሰዎች ታላቅ ፍርሀትን ፈርተው ምን አድርገሀል አሉት እሱ ነግሮአቸዋልና ከእግዚአብሔር ፊት ኰብልሎ እንደሔደ እነርሱም አወቁት።
ባሕሩ ይታወክ ነበርና ታላቅ ማዕበልም ተነሥቶ ነበርና ባሕሩ ይተወን ዘንድ እንግዲህ ምን እናድርግህ አሉት። ዮናስም አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ ባሕሩም ይተዋችኋል ይህ ታላቅ የማዕበል ሞገድ የመጣባችሁ በእኔ ምክንያት እንደ ሆነ አውቃለሁ አላችው።
ባሕሪቱ ትታወካለችና ማዕበሊቱም በእነሣቸው ትነሣለችና እነዚያ ሰዎች ወደ ምድር ሊመለሱ ወደዱ ነገር ግን ተሳናቸው። ሁሉም አንድ ሁነው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ አቤቱ ስለዚህ ሰው በእውነት ልታጠፋን አይገባህም አቤቱ እንደ ወደድክ አድርገሃልና የጻድቅ ሰው ደም አታድርግብን አሉ። ከዚህም በኋላ ዮናስን አንሥተው ወደ ባሕር ጣሉት ባሕርም ድርጎዋን ተቀብላ ጸጥ አለች። እነዚያም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈሩት ለእርሱም መሥዋዕትን ሠዉ ስእለትንም ተሳሉ።
እግዚአብሔርም ታላቅ ዓሣ አንባሪን ዮናስን ይውጠው ዘንድ አዘዘው ዮናስም በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ኖረ። ዮናስም በአንበሪ ሆድ ውስጥ ሳለ ጸሎትን ጸለየ ከዚህም በኋላ በነነዌ አገር በኩል ያ ዓሣ አንበሪ ዮናስን ወደ የብስ ምድር ተፋው።
የእግዚአብሔርም ቃሉ ዳግመኛ ወደ ዮናስ መጣ ቀድሞ አስተምር ብዬ እንደ ነገርኩህ ወደ ታላቂቱ የነነዌ አገር ተነሥተህ ሒደህ አስተምራቸው አለው።
ዮናስም እግዚአብሔር አስተምር ብሎ እንደ ነገረው ተነሥቶ ወደ ነነዌ ሔደ። ነነዌ ግን ለእግዚአብሔር ታላቅ አገር ናት በዙሪያዋ ያለ ቅጽርዋም ከበር እስከ በር ድረስ በእግር የሦስት ቀን ጐዳና ነው። ወደ ከተማም ሊገባ ደርሶ ያንድ ቀን መንገድ ሲቀረው ነነዌ እስከ ሦስት ቀን ትጠፋለች ብሎ አስተማረ።
የነነዌም ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል አመኑ ጾምን እንጹም ብለው አዋጅ ነገሩ የክት ልብሳቸውንም ትተው ማቅ ምንጣፍ ትልቁም ትንሹም ለበሱ። የነነዌ ንጉሥም ይህን ሰምቶ ከዙፋኑ ተነሣ ልብሰ መንግሥቱንም ትቶ ማቅ ለበሰ በአመድ በትቢያ ላይም ተቀመጠ።
ሰዎችም ቢሆኑ ከብቶችም ምንም ምን አይብሉ ትልልቆችም ትንንሾችም አይጠጡ እንስሶችም ወደ ሣር አይሠማሩ ውኃም አይጠጡ ብሎ አዋጅ ነገረ። እግዚአብሔርም ከክፉ ሥራቸው እንደ ተመለሱ አይቶ በእነርሱ ላይ ያደርገው ዘንድ ከተናገረው ክፉ ነገር ተመለሰ በእነርሱ ላይም ክፉ ጥፋትን አላደረገም።
ዮናስም ጽኑ ኀዘንን አዘነ ወደ ፈጣሪው እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ለመነ ጥንቱን በአገሬ ሳለሁ እንዲህ ብዬ የተናገርሁ አይደለሁምን አንተ ይቅር ባይ ርኅሩኅም ከመዓት የራቅህ ቸርነትህ የበዛ እውነተኛ የሆንክ ክፉ ነገርን ከማምጣት እንደምትመለስ አውቃለሁ ስለዚህ ከአንተ ኮብልዬ ወደ ተርሴስ ሔድሁ።
ነቢየ ሐሰት እየተባልኩ ከመኖር ሞት ይሻለኛልና አቤቱ አሁን ነፍሴን ከሥጋዬ ለያት አለ። እግዚአብሔርም ዮናስን በዚህ ነገር አንተ እጅግ ታዝናለህን አለው እርሱም አዎን አዝናለሁ አለ። ከዚህም በኋላ ዮናስ ከከተማ ወጥቶ ከከተማው ውጭ ተቀመጠ ጎጆም ለራሱ ሠራ በአገር ላይ የሚደረገውን ነገር እስኪያይ ድረስ ከጥላዋ ሥር ተቀመጠ።
ይበቅል ዘንድ በዮናስ ራስ ላይ ይሸፍነው ዘንድ እግዚአብሔር ቅልን አዘዘ ቅሉም በዚያን ጊዜ በቅሎ የዮናስን ራስ የፀሐይ ትኩሳት እንዳያሳምመው በዮናስ ራስ ላይ ሸፈነው ዮናስም በቅሊቱ መብቀል ታላቅ ደስታ አደረገ።
እግዚአብሔርም በማግሥቱ ትሉን ይምጣ ቅሉንም ይምታ ብሎ አዘዘ ቅሊቱንም ቆረጣት እርሷም ደረቀች እግዚአብሔርም ፀሐይ በወጣ ጊዜ የሚያቃጥል ሐሩር ያለበት ነፋስ ይምጣ ብሎ ዳግመኛ አዘዘ። ነፋሱም መጥቶ የዮናስን ራስ አሳመመው እርሱም አእምሮውን እስከማጣት ደርሶ በልቡናውም ተበሳጭቶ ከመኖር ሞት ይሻለኛል አለ።
እግዚአብሔርም ዮናስን በቅሊቱ መድረቅ እጅግ አዘንክን አለው እርሱም አዎን ልሙት እስከ ማለት ደርሼ አዘንኩ አለ። እግዚአብሔርም አንተስ በአንድ ሌሊት በቅላ በአንድ ሌሊት ለደረቀች ውኃ ላላጠጣሃት ላልደከምክባት ቅል ታዝናለህ። ቀኝና ግራቸውን ላልለዩ ከዐሥራ ሁለት እልፍ የሚበዙ ሰዎች እንዲሁም ብዙ እንስሶች ላሉባት ታላቅ አገር ለሆነች ነነዌ እኔ አላዝንላትምን ከበደሉ ተመልሶ ንስሐ ለሚገባ እኔ መሐሪና ይቅር ባይ ነኝና አለው።
ከዚህም በኋላ ዮናስ ተነሥቶ ወደ አገሩ ተመልሶ በሰላም አረፈ መላው ዕድሜውም መቶ ሰባ ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages