ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 26 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, October 5, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም 26

 መስከረም_26

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ስድስት በዚች ቀን #መጥምቁ_ዮሐንስ የተጸነሰበት፣ የዮስጦስ ልጅ #ቅዱስ_አቦሊ የስጋው ፍልሰት የሆነበት ቀን ነው።




መስከረም ሃያ ስድስት በዚች ቀን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ገብርኤልን ወደ በራክዩ ልጅ ዘካርያስ ልኮት መጥምቁ ዮሐንስ ከእርሱ ስለ መወለዱ አበሠረው።
ስሙ የተመሰገነ እግዚአብሔር ልጅን ይሰጠው ዘንድ አስቀድሞ ሁል ጊዜ በመጸለይ ወደ እግዚአብሔር ይማልድ ነበር። ልጅ ያልወለደውን እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ምድርን ምሉዋት ያለውን በረከት ያጣ ነው በማለት እስራኤል ይገዳደሩት ነበርና።
ልመናውንም ሰማ በቤተ መቅደስም ቁሞ ዕጣንን ሲያሳርግ መልአኩን ላከለት በከበረ ወንጌልም እንደተባለ መንገዱን ይጠርግ ዘንድ በንጉሥ ክርስቶስ ፊት እንደሚሔድ የተነገረለት ታላቅ ነቢይ ዮሐንስ ከእርሱ መወለዱን አበሠረው።
ዘካርያስም የሰውነቱን መድከም የመውለጃውም ዘመን እንዳለፈና ፈጽሞ እንዳረጅ የሚስቱም እንዲሁ ዘመኗ እንዳለፈና ፈጽማ እንዳረጀች መካንም እንደሆነች ያውቃልና ስለዚህ ይህ ነገር እንዴት ይሆንልኛል እኔ ያረጀሁ ሽማግሌ ነኝ ሚስቴም እንዲሁ ዘመኗ አልፎ መካን ሁናለች ብሎ የእግዚአብሔርን መልአክ ተከራከረው።
መልአኩም እኔ ይህን ልነግርህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወዳንተ ተልኬ ነበር ልትጠራጠር ባልተገባህም ነበር አሁንም ይህ በጊዜው እስቲፈጸም ዲዳ ሁነህ መናገር ይሳንሃል ብሎ ገሠጸው። ዘካርያስም የወልደ እግዚአብሔርን መንገድ የሚጠርግ ዮሐንስ እስከሚወለድበት ጊዜ ድረስ ዲዳ ሆነ።
በሚገረዝበትም ቀን የሕፃኑን አባት ዘካርያስን የሕፃኑን ስም ምን ብለው እንደሚሰይሙት ጠየቁት እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ በዚያም ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው። ስለ ልጁ ዮሐንስም እርሱ የልዑል ነቢይ እንዲባል መንገዱንም ይጠርግ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንደሚሔድ ትንቢት ተናገረ።

በዚችም ቀን የዮስጦስ ልጅ ቅዱስ አቦሊ የስጋው ፍልሰት ሆነ። ይህም ቅዱስ አቦሊ ከመንግሥት ልጆች ውስጥ ነበር ዐላውያንን ወግቶ በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስን ክብር ይግባውና ክርስቶስን ክዶ አገኘው።
ያም አቦሊና አባቱ ዮስጦስ ሌሎችም የመንግሥት ልጆች ሁሉ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን ሊያጠፉትና መንግሥትን ከእርሱ ሊወስዱ ችሎታ ሲኖራቸው የማታልፍ ሰማያዊት መንግሥትን አሰቡ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ አቦሊ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አብዝቶ አባበለው። እንዲሁም አባቱ ዮስጦስንና የከበረች እናቱ ታውክልያን አባበላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም ልባቸው በመድኅን ክርስቶስ ፍቅር ተነድፏልና።
ንጉሡም እነርሱን በዚያ ማሠቃየትን ፈራ ስለዚህም ከመልእክት ደብዳቤ ጋር ወደግብጽ ስሙ ኄርሜኔዎስ ወደሚባል የእስክንድርያ ገዥ ላካቸው በመልእክቱም እንዲህ አለው ዮስጦስና ሚስቱ ታውክልያ ልጃቸው አቦሊም ወደአንተ በሚደርሱ ጊዜ አባብላቸው አለዚያም እየአንዳንዳቸውን ለያያቸው።
በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮስጦስና ለሚስቱ ታውክልያ ለልጃቸው አቦሊም ተገልጦላቸው አጽናናቸው ከእነርሱም የሚሆነውን ነገራቸው የጸና ቃል ኪዳንም ሰጣቸው።
ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስም በደረሱ ጊዜ ስለእነርሱ እጅግ አደነቀ እነርሱ መንግሥታቸውን ትተዋልና ክፋ ነገርንም ሊናገራቸው አልደፈረም ከምክራቸው ይመለሱ ዘንድ በለሰለሰ ቃል ሸነገላቸው እንጂ ነገር ግን አልሰሙትም።
ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለእየብቻቸው ለያያቸው ቅዱስ ዮስጦስን ወደ እንዴናው ከተማ ሚስቱን ታውክሊያን ፃ ወደ ሚባል አገር ልጃቸው አቦሊንም ብስጣ ወደ ሚባል አገር ሰደዳቸው ለእያንዳንዳቸውም የሚአገለግላቸው አንዳንድ አገልጋይ ሰጣቸው።
ቅዱስ አቦሊም ወደ ሀገር ብስጣ በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመኰንኑ ፉት ታመነ። መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን በእሳት ቃጠሎና በመንኰራኵር አሰቃየው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ለአንበሶች ጣለው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስም ከሥቃዩ ሁሉ አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አነሣው።
ብዙዎች ሰዎችም ስቃዩንና ዳግመኛ መዳኑን በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አምነው ሰማዕታት ሆኑ።
መኰንኑ ግን እጅግ ተቆጥቶ የቅዱስ አቦሊን ቆዳውን እንዲገፍፉትና ጨውና መጻጻን በማቅ አምጥጠው ቍስሉን እንዲያሹ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት።
ከዚህም በኋላ ቆዳውን አሸክመው በከተማ ውስጥ ሁሉ አዞሩት ወደ ጌታችንም እንዲህ ብሎ ጸለየ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጣ ሁለመናውንም ዳስሶ አዳነው።
መኰንኑም በእርሱ ላይ የሚያደርገውን እስኪያስብ ከእሥር ቤት እንዲጨምሩት አዘዘ። ቅዱስ አቦሊም ቁሞ ጸለየ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ተገለጠለትና የመረጥኩህ አቦሊ ሰላም ለአንተ ይሁን እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ አለው ጌታችንንም በአየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው ክብር ይግባውና ለጌታችንም ሰገደለት።
ስሙ አብስኪሮን የሚባል አንድ ባለ ጸጋ ነበር የቤቱንም ግድግዳ አፍርሰው አዲስ ይሠሩለት ዘንድ ሠራተኞችን አመጣ ሥራቸውንም እስኪጨርሱ ከዚያ ይቆሙ ዘንድ ሁለቱን ልጆቹን አዘዛቸው።
ከግርግዳውም ላይ በወጡ ጊዜ ግርግዳው ተደርምሶ ዐሥራ ስድስት ሰዎችና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ። ባለጸጋውም የሆነውን በአየ ጊዜ ልብሱን ቀደደ ጩኾም አለቀሰ ወደ ቅዱስ አቦሊም ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደለት እንዲህም አለው ራራልኝ ሁለቱ ልጆቼ ሙተዋልና ከእነርሱም ጋራ ዐሥራ ስድስት ሰዎች ሞቱ። ከሞትም ብታሥነሣቸው እኔ በአምላክህ አምናለሁ።
ያን ጊዜም ቅዱስ አቦሊ ተነሣ እንዲህ ብሎ ጸለየ ስለ ቅዱስ ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ የመረጥከኝ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በእኒህ በሞቱ ሰዎች ላይ ኃይልህን ግለጥ። እኒህ ሰዎች ሁሉ እንዲአምኑ ያለ አንተም ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ከሞት አንሣቸው። ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
ከዚህም በኋላ የተገፈፈ ቆዳውን ወስዶ በሞቱት ሰዎች ላይም ዘረጋውና በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሞት ተነሡ አለ። ወዲያውም ሁሉም ድነው ተነሡ በዚያ ያሉ ሕዝብም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ የክርስቲያን አምላክ የቅዱስ አቦሊም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነው እኛም እናምንበታለን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና እያሉ ጮኹ።
ባለ ጸጋው አብስኪሮንም መጥቶ ለቅዱስ አቦሊ እንዲህ እያለ ሰገደ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ዛሬ አወቅሁ እኔም አምንበታለሁ። ከቤተሰቦቹም ሁሉ ጋር አመኑ መኰንኑም አፈረ።
ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ አቦሊ ተገለጠለት እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው። በመከራ ውስጥ ያለ ሰው በስምህ ርዳታ ቢለምን እኔ እሰማዋለሁ ልመናውን ፍላጎቱንም እፈጽምለታለሁ። በስምህ ቤተ ክርስቲያን ለሠራም እኔ በሰማያት ብርሃናዊ ማደሪያ ቤት እሠራለታለሁ የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን ወይም የሚሰማውን እኔ በኪሩቤል ክንፎች ላይ ስሙን እጽፉለሁ በአብርሃም በይስሐቅና በያዕቆብ እቅፍም አሳርፈዋለሁ ተድላ ደስታ ካለባት ከገነት ፍሬዎችም እመግበዋለሁ።
ብዙ ኃጢአትን ሠርቶ የበደለውንም በስምህ ወደኔ እየለመነ ንስሐ ቢገባ በደሉን ሁሉ ይቅር እለዋለሁ። ከጻድቃንም ጋርም እቈጥረዋለሁ ሰላሜም ካንተ ጋራ ይሁን ይህንንም ብሎ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።
መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ የከበረች ራሱን ቆረጡት የሕይወት አክሊልንም ተቀበለ።
በዚህችም ቀን ሥጋውም ከምስር ከተማ ውጭ ሕንቅ በሚባል ገዳም የፈለሰበት ቀን ነውደ እስከዛሬም ድረስ የከበረ ሥጋው በዚሁ ገዳም ይገኛል።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages