የጸሎት ጊዜያት - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, October 8, 2022

የጸሎት ጊዜያት

 

የጸሎት ጊዜያት

ምን ዓይነት ጸሎት በየትኛው ሰዓት ልጸልይ? ኢትዮጵያውያንና የያዕቆብ የመጨረሻ ልጅ የቢኒዖን (ብንያም)ነገድ 
 

የጸሎት ቦታ እንዴት ላዘጋጅ?

 

1. የጸሎት ጊዜያት

ልበ አምላክ ነቢየ ልዑል ቅዱስ ዳዊት”ስብዓ ለእለትየ እሴብሐከ በእንተ ኵነኔ ጽድቅከ ፣ስለ ጽድቅህ ፍርድ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለው”/መዝ 118-164/ብሎ እንደተናገረ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ሰባት ጊዜ በየእለቱ እንዲጸልይ ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች፡፡ሰባቱ የጸሎት ጊዜያትም የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

1.1 ጸሎተ ነግህ

ቅዱስ ዳዊት “አምላኬ አምላኬ በማለዳ ወደ አንተ እገሰግሳለሁ” መዝ 62÷11 እንዳለ ሌሊቱ አልፎ ቀኑ ሲተካ፣ከመኝታችን ስንነሳ ምንጸልየው የጸሎት ዓይነት ጸሎተ ነግህ ይባላል፡፡በዚህ ጊዜ የሚከተሉትን ምስጢራት እያሰብን መጸለይ ይገባናል፡፡
.ሌሊቱን አሳልፎ ቀኑን ስለተካልን እያመሰገንን ወጥተን እስክንገባ በሰላም ጠብቆ ውሎአችንን የተባረከ እንዲያደርግልን እንጸልያለን።

·የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረበትም ሰዓት በመሆኑ ያንን እያሰብን እንጸልያለን፡፡
·የሰውን ልጅ በመዓልትና በሌሊት የሚጠብቁ መላእክት ለተልዕኮ ሲፋጠኑ የሚገናኙበት ሰዓት ነው፡፡የሌሊቱ መልአክ ሲሄድ የቀኑ መልአክ ሲቀርብና ሲተካ የሚገናኙበት በመሆኑ በዚህም ሰዓት እንጸልያለን፡፡

.ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች በደል በጲላጦስ አደባባይ የቆመበት ሰዓት በመሆኑ እንጸልያለን።

 

1.2 ጸሎተ ሠለስት (3 ሰዓት)

ከነግህ በመቀጠል የምንጸልየው ጸሎት ጸሎተ ሠለስት (የሦስት ሰዓት) ጸሎት ይባላል፡፡ይህ የጸሎት ጊዜ
. ሔዋን የተፈጠረችበት
. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቅዱስ ገብርኤልን ብሥራት የሰማችበት
. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሲል በጲላጦስ አደባባይ የተገረፈበት
. ነቢዩ ዳንኤል ፊቱን ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ መልሶ የቤቱን መስኮት ከፍቶ የጸለየበት
. ለአባቶቻችን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት /በኢየሩሳሌም ጸንተው በመቆየታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይህንን ታላቅ ጸጋ የተቀበሉበት /ሰዓት ነው፡፡

 

1.3 ቀትር(6 ሰዓት)

በእለቱ እኩሌታ ላይ የምናገኘው ይህ ሰዓትም እንደዚሁ የጸሎት ጊዜ ነው፡፡ይህም ጊዜ
.ሰይጣን አዳምን ያሳተበት
.በዕፀ በለስ ምክንያት ለስሕተት የተዳረገውን አዳምን ለማዳን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ የዋለበት
.የቀን እኩሌታ በመሆኑ የፀሐይ ሙቀት የሚያይልበት የሰው ልጅ ለድካም የሚዳረግበት በዚህም ምክንያት አጋንንት የሚበረታቱበት ጊዜ ነው።
.ስለዚህ የአዳምን ስሕተት፣ የዳግማዊ አዳም የኢየሱስ ክርስቶስ መሰቀልና መሞት፣እያሰብን የቀን እኩሌታ በመሆኑ መዳከማችንን ተገን አድርጎ አጋንንት እንዳይሰለጥንብን እየለመንን እንጸልያለን፡፡

 

1.4 ተሰዓተ ሰዓት (9 ሰዓት)

ዘጠኝ ሰዓት ላይ አራተኛውን ጸሎት እናደርሳለን።በዚህ ጊዜ
.ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ነጻ ለማውጣት በፈቃዱ ቅዱስ ሥጋውን ከቅድስት ነፍሱ የለየበት ሰዓት ነው።
·ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን በጎም ሆነ ክፉ ተግባር ወደ ፈጣሪ የሚያሳርጉበት ነው
·ቆርኖሌዎስ የተባለ መቶ አለቃ በጸሎት ጸንቶ ደጅ ሲጠና ከሰነበተ በኋላ ከፈጣሪው ምላሽ ያገኘበት ሰዓት ነው (ሐዋ 10÷ 9)
በዚህ ጊዜ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ እና ሞት አያሰብን ቅዱሳት መላእክት ከፈጣሪያቸው እንዲያስታርቁን እየለመንን የቆርኖሌዎስ እድል እንዲገጥመን እየተማጸንን እንጸልያለን፡፡

 

1.5 ጸሎተ ሰርክ (11 ሰዓት)

አምስተኛው የጸሎት ጊዜ የሠርክ ጸሎት ነው፡፡ስለዚህ የጸሎት ሰዓት ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ይላል፡፡”ጸሎቴን እንደ ዕጣን በፊትህ ተቀበልልኝ እጅ መንሳቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን” (መዝ 140 ÷2)
·ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው ከለየ በኋላ ወደ መቃብር የወረደበት ሰዓት ነው፡፡ (ማቴ. 27÷ 57)

 

1.6 ጸሎተ ንዋም (የመኝታ ጊዜ ጸሎት)

ይህ ጊዜ ዕለቱን በሰላም አሳልፈን ለሌሊቱ ዕረፍት የምንዘጋጅበት ነው፡፡በሰላም ላዋለን ፈጣሪ በሰላም አሳድረን ብለን ራሳችንን በእምነት የምናስረክብበት ነው፡፡እኛ ተኝተን የሚሆነውን አናውቅም እርሱ ግን የማያንቀላፋ እረኛ ስለሆነ ይጠብቀናል።ስለዚህ ከመተኛታችን በፊት ሊሌሊቱን እንዲባርክልን እንጸልያለን።
በዚህ ጊዜ፡-
·ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ ዛሙርቱን በጌቴሴማኒ ጸሎት አስተምሯቸዋል፡፡
·ቀኑ አልፎ በሌሊቱ ይተካል
ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጸሎት ማስተማሩን እያሰብን እንጸልያለን፡፡ሰላም አሳድረንም ብለን ለፈጣሪ ራሳችንን በእምነት አደራ እናስረክባለን፡፡

 

1.7 መንፈቀ ሌሊት (እኩለ ሌሊት)

·እኩለ ሌሊትም እንደ ቀናቱ የጸሎት ሰዓታት የተለያዩ ትርጉሞች አሉት ።
ቅዱሰ ዳዊት ‘’መንፈቀ ሌሊት እትነሣእ ከመ እግነይ ለከ በእንተ ኵነኔ ጽድቅከ”“ስለ ጽድቅህ ፍርድ በእኩለ ሌሊት አመሰግነህ ዘንድ እነሳለሁ”/መዝ 118-62/በማለት ይህ ሰዓት ከእግዚአብሔር ጋራ የሚነጋገርበት እንደሆነ ገልጿል፡፡

· ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ዋሻ የተወለደበት ሰዓት ነው።

 
· ሞትን ድል አድርጎ በታላቅ ኃይልም የተነሳው በሌሊት ነው።

 
· ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ለፍርድ ሚመጣበትም ሰዓት ነው።

 
ከዚህ የተነሳ ለእኛ ሲል ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ መወለዱን በማሰብ ሞትን ድል እንደነሳልንም አስበን በማመስገን ዳግመኛ ለፍርድ ሲመጣ በቀኙ ከሚያቆማቸው ወገን እንዲያደርገን እየለመንን በዚህ ሰዓት እንጸልያለን፡፡

 

ሰባቱን የጸሎት ጊዜያት ጠብቀን መጸለይ ካልተቻለንስ?

በሰባቱ የጸሎ ሰዓታት የታቻለንን ያህል እንድንጸልይ ታዘናል፡፡እነዚህን የጸሎት ሰዓታት በገዳም ያሉ መነኮሳት በየበረሃው የሚዞሩ ባሕታውያን ይጠብቋቸዋል፡፡ይጸልዩባቸዋልም፡፡በከተማ በሥራ ምክንያት ሩጫ በዝቶበት በሁሉም ሰዓት መጸለይ የማይችል ክርስቲያን ግን ቢያንስ በማለዳ ከእንቅልፉ ሲነሳ እና ማታ ወደ መኝታው ሲያመራ መጸለይ ይገባዋል።ጠዋት እና ማታ በመጸለይ ከፈጣሪ ጋራ ያለው የአባትና ልጅ ግንኙነት እንዳይቋረጥ ማድረግ ይገባዋል፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages