የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከልን አገልግሎት ለማጠናከርና
ለማስፋፋት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተከናወነ፤
የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማራጭ ድምፅ በመሆን በዲጂታል ሚዲያው ዘርፈ በርካታ አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኘው የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከልን አገልግሎት ለማጠናከር እና ለማስፋፋት በትላንትናው ዕለት ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ የሆነ ኦርቶዶክሳዊ የኪነጥበብ ምሽት ፣ የእራት ግብዣና እና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ተከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሚዲያው የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሄኖክን ጨምሮ በርካታ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፤የገዳማት እና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች ፤ መምህራነ ወንጌል እና ዘማርያን፤ ኦርቶዶክሳውያን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።
በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ብፁዕ አቡነ ሄኖክ "አምላካችን ስለ መንፈሳዊ አገልግሎታችን መተባበር እና መደጋገፍን መሠረት አድርገን በዚህ ሥፍራ እንድንገናኝ ስለረዳን ክብር ምስጋና ይግባው ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም ሚዲያው በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት የተወሰነ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚገኙ አህጉረ ስብከትንም ጭምር ተደራሽ በማድረግ ዘመኑ በፈቀደው ቴክኖሎጂ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል አማራጭ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ድምፅ በመሆን የቤተ ክርስቲያንን የወንጌል አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋት ዓላማ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ያነሱት ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የኦርቶዶክሳውያን ድጋፍና ትብብር ከታከለበትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከማኅበራዊ ሚዲያአማራጮች በተጨማሪ በሜን ስትሪም ሚዲያ መምጣትን ዓላማው እንዳደረገ ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያን በሚዲያው ዘርፍ አንድ እርምጃ እንድትራመድ ለማድረግ የሚዲያው የአስተዳደር ቦርድ ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ብሎም በየደረጃው የሚገኙ አካላት በጠንካራ አደረጃጀት ኃላፊነቶቻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቁመው ነገር ግን ሚዲያውን በበለጠ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ለማገልገል መስፋፋት እና መጠናከር የሚገባው መሆኑን አንስተው ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፤ ሲል ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል ዘግቧል።
Source: ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል
No comments:
Post a Comment