፵፩ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከሰኞ ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻ ፲ወ ፭ ዓ.ም ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ መካሔድ ይጀምራል።
***********************************
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለ፵፩ኛ ጊዜ ከሰኞ ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ከአገር ውስጥስና ከውጪ አህጉረ ስብከት ተወክለው የሚሳተፉ ጉባኤተኞች በተገኙበት ይካሔዳል።
ጉባኤውን በርዕሰ መንበርነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ሲሆኑ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጉባኤው መሪ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በዚሁ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የ፳፻ ፲ወ፬ ዓ.ም የጠቅላይ ቤተክህነትን የሥራ አፈጻጸም ሪፓርትን ለጉባኤው በንባብ ያሰማሉ።
በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዮወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይካሔዳል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ የሁሉም አህጉረ ስብከት የ፳፻ ፲ወ፬ ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ሪፓርትም በየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች በኩል በንባብ ይቀርባል። የዘንድሮ ፵፩ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ደረጃ በጉባኤው በሚጸድቁ የመወያያ ርዕሶች ላይ ውይይት ያደርጋል። በውይይቱ የተነሱ መሰረታዊ ሐሳቦችን በማካተተም የሚዘጋጀው የጉባኤው የአቋም መግለጫ ከጸደቀ በኋላ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሲጸድቅም በ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም በጀት ዓመት ሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል።
የ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች እንደ አመጣጣቸው ቅደም ተከተል መሰረት የመግቢያ ባጅና የጽሕፈት መሳሪያዎችን መረከብ የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል።ጉባኤው ሰኞ ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም በይፋ ይጀመራል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
ጥቅምት ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ ፭ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
No comments:
Post a Comment