ጾም
ስጋችንን ለነፍሳችን የምናስገዛበት ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት የጽድቅ መንገድ ለስጋ ጤንነትም ቢሆን አስፈላጊያችን
የሆነ አንዱና ዋነኛዉ የጽድቅ እቃ ጦራችን ነዉ፡፡ሆኖም የጾም ወቅት ሲመጣ አቀበት የሚወጡ ይመስል የሚፈሩትና
የሚያማርሩት ሳይሆን እንኳን መጣልን ተብሎ በጉጉት የሚናፈቅ መሆን አለበት፡፡ስለሆነም ማንኛዉም ሰዉ ጾሙን ሲጀምር የሚከተሉትን ጉዳዮች በደንብ ሊያጤናቸዉ ይገባል፡፡
† የጾም አላማዉን መገንዘብ፡- ክርስትና
በአላማ የሚጓዙት እንጂ በልማድ የሚኖሩት ኑሮ አይደለም፡፡ ዓላማን ሳይረዱ መንገድ መጀመር መዳረሻዉ ስለማይታወቅ
በጉዞው አቅጣጫን መሳት መዉደቅና መንገድ መቅረት ያስከትላል፡፡ በዓላማ መራመድ ያልቻለ ሰዉ መልህቅ እንደተሰበረበት
ጀልባ በፈተና ሲንገላታ ይታያል፡፡ ስለሆነም የጾማችንን ዓላማ በደንብ ጠንቅቀን ልንገነዘብ ይገባል እርሱም
ከእግዚአብሔር ጋር ተወዳጅቶ መንግስቱን መዉረስ ነዉ፡፡
† ጾምን የተቀደሰ ማድረግ ፡- ጾምን የተቀደሰ ማድረግ ማለት የጾምን ቀናት ለእግዚአብሔር መቀደስ መለየት ማለት ነው፡፡የጾም ዕለታት ለእግዚአብሔር ብቻ ይውላሉ እንጅ አለማዊ ስራዎች አይሰራባቸውም ፡፡ይህም በነብዩ ኢዩኤል (ጾምን ቀድሱ )ተብሎ የተነገረው ነው ፡፡በዚህ አዋጅ እጅም ፤እግርም ፤አይንም ፤ጀሮም ፤እንዲሁም መላ የሰውነት አካላችን ከበደል እና ከእርኩሰት አብዝተው መራቅ አለባቸው ይኸኔ ጾምን በትክክል ቀድሰናል ማለት ነው ፡፡
ስንት ዓይነት አጽዋማትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ደንግጋለች
እናት ቅድስት ቤተ ክርስትያን ሰባት የሚደርሱ አጽዋማትን በአዋጅ ደንግጋለች ከእነዚህም ውስጥ
v ጾመ ኢየሱስ፡-መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በመጣ ጊዜ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾመ፡፡ በዲያቢሎስም ተፈትኖ የጾምን ኃይል
አሳይቶበታል ፡፡ፈታኙም በስስት ቢመጣበት በትዕግስት በትዕቢት ቢመጣበት በትህትና ፡በፍቅረ ንዋይ ቢፈትነው
በጸሊአ ንዋይ ድል ነስቶታል ፡፡እኛም የፈጣሪያችን በረከት ያድርብን ዘንድ ለጾሙ ልዩ ቦታ ሰጥተን እንጾመዋለን፡፡
v ጾመ ድህነት፡-ከበዓለ 50 ውጭ በሳምንት ረቡዕ እና አርብ የሚጾመው ነው ፡፡ረቡዕ የአይሁድ ቤተ-መንግስትና ቤተ-ክህነት ክርስቶስን ይገድሉት ዘንድ
ምክራቸውን
ያጸኑበት ዕለት ሲሆን አርብ ደግሞ ለቤዛ ዓለም በስጋ የተገለጠው አምላክ የከበረ ስጋውን ቆርሶ ቅዱስ የሆነዉን
ደሙን አፈስሶ መላውን ዓለም ያዳነበት ዕለት በመሆኑ ዕለተ አርብን በጾም እናከበረዋለን፡፡
v ጾመ- ገሃድ ፡-በዓመት
አንድ ጊዜ በጥምቀት ዋዜማ የሚጾም ሲሆን ከስሙም ትርጓሜ ስንነሳ ገሀድ ያልነ እንደሆነ የተገለጠ፤የታየ
የሚለውን ትረጉም ይሰጠናል፡፡ይኸም በጥምቀቱ የአንድነቱን የሦስትነቱን ምስጢር በገለጠልን ዋዜማ የሚጾም ጾም በመሆኑ
ነው፡፡
v ጾመ- ሐዋርያት ፡-ክርስቶስ
ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰማያዊ ተልዕኮ ስለተሰጣቸው ከ50 ቀናት በኋላ በበዓለ
ጰራቅሊጦስ ማግስት መጾም ጀመሩ፡፡የአበው ቀደምትን አሰረ ፍኖትን የምትከተል ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ትንሳኤ በዋለ
በ50ኛው ቀን የጾሙን አዋጅ እንዲሁ ለልጆቿ አውጃለች፡፡
v ጾመ ነቢያት፡- ከልደት በዓል በፊት ባሉት 44ዕለታት የሚጾመው ነው፡፡ይኸም ጾም የነቢያት ትንቢት መፈጸሙን የ5500 የመከራ ዘመን ማብቃቱን እያሰብን የምንጾመው ጾም ነው ፡፡
v ጾመ ነነዌ፡-በየዓመቱ
ከጾመ ሁዳዴ 15 ቀን ቀድሞ ከሰኞ እስከ ረቡዕ የሚጾም ጾም ሲሆን፡፡ ጾሙም የነቢዩ ዮናስን ስብከት የሰሙ የነነዌ
ሕዝቦች ንስሃ ገብተው በእሳት ከመቀጣት የዳኑበት ነዉ፡፡ እኛም በሰውነታችን ክፋት ምክንያት አታጥፋን በማለት
ሦስቷን የነነዌ ጾም በጾምና በጸሎት ሆነን እናሳልፋለን፡፡
v ጾም ፍልሰታ፡-በየዓመቱ
ከነሐሴ አንድ ጀምሮ ለሁለት ሱባዔ የሚቆይ ጾም ነው፡፡ጾሙ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የእመቤታችን አስከሬን
እንዲሰጣቸውና በክብር እንዲቀብሩት እንዲሁም ትንሳኤዋን ለማየት የጾሙት ጾም ሲሆን እኛም የእመቤታችን በረከት
ይደርብን ስንል የኸንን ጾም በፍቅር እንጾመዋለን፡፡ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ በሚቀጥለው ጊዜ አብይ ጾምን በስፋት እናቀረባዋለን፡፡ እስከዚያው ይቆየን፡፡
‹‹ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወለዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር››
No comments:
Post a Comment