ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 27 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, November 5, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት 27

 

ጥቅምት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
2.ቅዱስ መቃርስ ብጹዓዊ
3.አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ
4.አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ  

ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
3.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
4.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
5.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ሰባት በዚህች ዕለት የአምላካችን_የመድኃኔዓለም የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፣ የጻድቁ_አባ_መብዓ_ጽዮን የቃልኪዳን ቀን፣ የማህሌተ ጽጌ ደራሲው አባ_ጽጌ_ድንግል_ዘወለቃ የእረፍታቸው መታሰቢያ ነው፣ ቅዱስ አባት የሀገረ ቃው ኤጲስቆጶስ_አባ_መቃርስ አረፈ።



መድኃኔዓለም (በዓለ ስቅለት)
ጥቅምት ሃያ ሰባት በዚህች ዕለት የአምላካችን የመድኃኔዓለም የስቅለቱ መታሰቢያ ነው።
መድኃኒታችን ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና በቸርነቱ ስለኹላችን ድኅነት ሲል ራሱን ወድዶ ፈቅዶ ለሞት አሳልፎ በመስጠት ፍጹም ፍቅሩን አሳይቶናል። በቅዱስ ወንጌልም እርሱም መድኃኒታችን " ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም" ብሎ ነግሮናል። እውነት ነው፣ ራስን ነፍስን ስለጠላት ነፍስ አሳልፎ ከመስጠት በላይ ምን ድንቅ ነገርና ምን ድንቅ ፍቅር አለ?
ቸሩ አምላካችንን የአስቆሮቱ ይሁዳ ሊያስይዘው የሊቃነ ካህናቱን አገልጋዮች እየመራ አመጣቸው። እነርሱንም ማንን ትፈልጋላችሁ ሲላቸው የናዝሬቱ ኢየሱስን አሉት፣ እኔ ነኝ ቢላቸው የቸሩን አምላክ ድምጽ ሰምቶ አይደለም መቆም በሕይወት መጽናት የሚቻለው የለምና ወደ ኋላቸው ተስፈንጥረው ወደቁ። ደጋግሞም እንዲህ ኾነ። በኋላ ግን እኔ ነኝ ብሎ በፈቃዱ ይሁዳ ስሞ አሳልፎ ሰጣቸው።
ከያዙት በኋላ እያዳፉና እየጎተቱ በሰንሰለት አስረው ወደ ቀያፋና ሐና ግቢ ወሰዱት፣ እስከ ሦስት ሰዓትም አላሳረፉትም ሲያሰቃዩት አድረዋል፣ በራሱም ላይ ሰባ ሦስት ስቊረት ያለው ወደ ሦስት መቶ እሾኾችን የያዘ የእሾህ አክሊል ጎንጉነው ቢያደርጉበት የራስ ቅሉን ቀዶ ገብቶ እስከ ልቡ ዘልቋል። እንደምን ጭንቅ ነው? እንዲህም አድርገው ደግሞ እያፌዙ ርኲስ ምራቃቸውን ይተፉበትና በዘንግም ደጋግመው ይመቱት ነበር። እየተፈራረቁ ያለ ምንም ርኅራኄ ቸሩን አምላክ ሥጋው እየተቆረጠ እስኪወድቅ ድረስ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጽኑዕ ግርፋትን ገርፈውታል። የገረፉበትም ጅራፍ በላዩ ላይ ሥጋን እየጎመደ የሚጥል፣ ሕመሙ አንጀት ሰርሥሮ የሚገባ በስለት የተያያዘበት ነበር።
በኋላም አላሳረፉትም እንዲህ አድርገውትም በሊቶስጥራ አደባባይ ያንን ዕርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት። እርሱ ግን ይህን ኹሉ ግፍ ሲያደርሱበት አንድም አልተናገረም ነበር። በቀራንዮም በአምስት ጽኑዕ ቅንዋት (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ) ቸንክረው ዕርቃኑን ሰቀሉት።
በዚህች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተሰበረ መጽናናትንም አልፈለገች ነበር፤ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ እናቱንም እናት ትሆነው ዘንድ በእግረ መስቀሉ አደራን ተቀበለ። ቅዱሳት አንስት በፍጹም ሀዘንና በዋይታ ዋሉ። በስልጣኑም ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ። ሰባት ድንቅ የኾኑ ተአምራትንም አድርጎ አምላክ መኾኑን ገለጠ። ይህም ጽኑዕ የኾነ ለሰማይ ለምድር የከበደ ነገር ሲከሰት ፀሐይ አምላኬን ዕርቃኑ እንዴት አያለሁ ብላ ጨለመች። ጨረቃ ደም ኾነች፣ ከዋክብቱም ረገፉ፣ ንዑዳን ክቡራን ንጹሐን መላእክትም ትዕግስቱን እያደነቁ በጽኑዕ ሐዘንና መደነቅ ከቅዱስ ዕፀ መስቀሉ ፊት እንደሻሽ ተነጠፉ።
አስራ አንድ ሰዓት በሆነም ጊዜ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር ቅድስት ሥጋውን ከመስቀሉ አውርደው በክብር ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት። በሦስተኛውም ቀን እንደተናገረ ተነሳ።
በዛሬዋ ቀን ቤተ ክርስቲያን የመድኃኔለምን የስቅለት በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው መጋቢት 27 ቀን ነው፤ ይህ በዓል ግን በዐቢይ ጾም ስለሚውል በዐቢይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለና በዓል ማክበር ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን እንድናከብረው ቤተ ክርስቲያን ስርዓት ሰርታልናለች፡፡

አባ መብዓ ጽዮን በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ልጅ በማጣታቸው በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ከሚለምኑ ባልና ሚስት ተወለዱ። የንቡረ እድ ሳሙኤል ረባን የሆነው መብዓ ጽዮን አባቱ እስከ ዳዊት ያለውን ትምህርት አስተማረውና ዲቁናን ተቀበለ። ልጁ የትምህርት ዝንባሌ እንዳለው አባቱ ተረድቶ ቤተ ማርያም ከሚባለው ደብር ወስዶ ተክለ አማኅጸኖ ከሚባል የቅኔ መምህር ዘንድ አስገባው። በዚያም ቅኔና እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን እውቀቶችን ገበየ። ከዚህም በተጨማሪ ሥዕል መሳልና ጽሕፈት መጻፍ ተማረ።
መብዓ ጽዮን የልጅነቱን ዘመን ሲፈጽም ‹‹ለነፍሳቸው ድኅነት ዋጋ ያገኙ ቅዱሳን ብዙ ናቸው።በመጾም ያገኙ አሉ፤ በትምህርት ያገኙ አሉ፤ በድካም ያገኙ አሉ፤ በጸሎት በትጋት ያገኙ አሉ፤ እኔ ግን የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን የሞቱን መታሰቢያ ማድረግ ይገባኛል። በዚህም ፊቱን አያለሁ፤ እርሱ ጌታ ለደቀመዛሙርቱ "የትንሣኤዬን መታሰቢያ ብታደርጉ የሞቴን መታሰቢያ አድርጉ ብሏልና" በማለት ፍላጎቱ በምንኩስና በመኖር ፈጣሪን ማገልገል መሆኑን ለወላጆቹ ገለጸላቸው።
አባትና እናቱም "ፈጣሪህን ለማገልገል ኅሊናህ ከአሰበ እሺ፤ በጀ ደስተኛ ነን" ብለው ፈቀዱለት። ከዚያም መብዓ ጽዮን ዳሞት አባ ገብረክርስቶስ ወደሚባል መነኩሴ በመሄድ መነኮሰ። አባ መብዓ ጽዮን አባ ገብረክርስቶስ ጋር በመቀመጥ ሥርዓተ ምንኩስናን ካጠኑ በኋላ ከአባ ገብርኤል ዘንድ ሄደው የቅስናን ማእረግ ተቀበሉ። ከዚያም በኋላ በአበው ሕግ በምንኩስና ተወስነው፤ በበአታቸው ሆነው ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የዕለተ ዓርቡን መከራህን አሳየኝ፤ ስለራሴ ፈጽሞ አለቅስ ዘንድ›› ብለው በጸልዩ ጊዜ ‹‹መከራ መስቀሉን ለማየት ትፈቅዳለህን?›› ብሎ ጠየቃቸው። ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮንም ‹‹አዎ አይ ዘንድ እወዳለሁ›› ሲሉ ለጌታቸው መለሱለት። ያን ጊዜም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕፀ መስቀል ተተከለ። በመስቀሉ ላይም እጆቹና እግሮቹ ተቸንክረውና ተዘርግተው ታዩ ፤በራሱ ላይም የእሾህ አክሊል ደፍቶ ነበር።
እንዲህ ሆኖ በሮም አደባባይ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንደታየው ጌታችን ለአባ መብዓ ጽዮንም ታያቸው። ከዚህም በኋላ አባ መብዓ ጽዮን የጌታችን የመድኃኔዓለምን ሕማሙን፣ መከራውን፣ ግርፋቱን፣ እስራቱን በጠቅላላ ፲፫ቱን ሕማማተ መስቀል በማሰብ ጀርባቸውን በአለንጋ ይገርፉ ፤ራሳቸውንም በዘንግ ይመቱ ነበር። የጌታን መከራ መስቀል እያሰቡ ዐይኖቻቸው አስከሚጠፉ ድረስ ያለቅሱ ነበር ። ጌታችን ግንደ መስቀሉን (የመስቀሉን ግንድ) አንደተሸከመ በማሰብ ትልቅ ድንግያ ተሸክመው ይሰግዱ ነበር። መራራ ሐሞት መጠጣቱን በማሰብ ዓርብ ዓርብ ኮሶ ይጠጡ ነበር። የጌታ ደቀመዝሙር ዮሐንስ ወንጌላዊ ጌታ በተሰቀለ ጊዜ አብሮ ስለነበርና ዐይን በዐይን ስለተመለከተ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መስቀል እያሰበ ፸ ዘመን ፊቱን በሐዘን ቋጥሮ እንደኖረ ሁሉ ጻድቁ አባ መብዓ ጽዮንም እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ የጌታችንን መከራ መስቀል እያሰቡ ከዓለም ተድላና ደስታ ተለይተው በትምህርት ፣ በትሩፋት ፣ በገድል ጸንተው ኖረዋል። ጻድቁ መብዓ ጽዮን በሕይወተ ሥጋ ዘመናቸው የላመ የጣመ እንዳልተመገቡ፤በፈረስ በበቅሎ እንዳልሄዱ፤አልጋ ላይ እንዳልተኙ፤ገድላቸው ያስረዳል። የክርስትናን ትምህርት ለጋፋት ሰዎች እንዲስፋፋ ያደረጉት አባ መብዓ ጽዮን የጌታን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ዘወትር ስለሚያነቡ ዐይኖቻችው ጠፍተው ነበር። ነገር ግን እመ ብዙኃን የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ወደኚህ ጻድቅ አባት በአት የብርሃን ጽዋ ይዛ መጥታ ዐይኖቻቸውን ቀብታ አድናቸዋለች። ከዚህ የተነሳ በትረ ማርያም እየተባሉ ይጠሩ አንደነበር ገድላቸው ያስረዳል።
የጻድቁ መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ጥቅምት ፳፯ ቀን ከመድኃኔዓለም የስቅለት በዓል ጋር ይከበራል። ጥቅምት ፳፯ ቀን ለወዳጆቹ እውነተኛውን ዋጋ የሚከፍል መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለጻድቁ አባ መብዓ ጽዮን ብዙ ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው።
የአቡነ መብዓ ጽዮን ረድኤታቸው፣ በረከታቸውና አማላጅነታቸው አይለየን፤አሜን!!!

በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ሊቅ ሲኾን፤ አባ ጽጌ ድንግል (ጽጌ ብርሃን) ሀገሩ ይፋት ሃይማኖቱ ኦሪት ነበረ፡፡ በንጉሥ ሰሎሞን ፈቃድና በካህኑ አዛርያስ መሪነት የብሉያት መጻሕፍትን ከዕብራይስጥ ወደ ግእዝ ተርጕመው ሊያስተምሩ፣ ታቦተ ጽዮንን ከኢየሩሳሌም ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡትና የብሉያት መጻሕፍት ሊቃውንት ከነበሩት ከ318 ሌዋውያን (ከቤተ እስራኤላውያን) ነገድ ነው፡፡ የተወለደውም በሰሜን ሸዋ በይፋት አውራጃ ውስጥ ሲሆን፤ መጀመርያ ኢእማኒ (ያላመነና ያልተጠመቀ) ነበር።
ከዕለታት አንድ ቀን ይህ ሰው፤ በወጣትነት ዕድሜው አውሬ ለማድን ወደ ጫካ ሄደ፣ ጫካዋም በዚያው በይፋት አውራጃ የምትገኝና ልዩ ስሟ ደንስ (ገዳመ ደንስ) ትባላለች፣ በጫካዋ ውስጥም ፊቷ በጽጌረዳ አበባ የተከበበና ያጌጠ፣ እጅግም ደስ የምታሰኝ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል አይቶ በሥዕሏ ውበት እየተደነቀ ሥዕሏን ሲመለከት እንደ እርሱ ያልተጠመቀ ጓደኛው መጥቶ፣ "ምን እየፈለግህ ነው? የክርስቲኖችን ሥዕል ነውን?" ብሎ ለድንግል ማርያም ምስጋና ይግባትና በያዘው በትር ሥዕሏን ሲመታት ወዲያው ተቀሥፎ ሞተ። ከዚህ በኋላ ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ ያጌጡ የመሰለ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በነጭ ወፍ ተመስሎ ወደ እርሱ መጥቶ አንድ ቀይ መነኩሴ እሰኪመጣ ድረስ፣ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ በሰው አነጋገር ነግሮት ተሠወረ።
የአቡነ ዜና ማርቆስ የገድል መጽሐፍ፣ እንደሚናገረው ካህን ከነበረው ከአባቱ ከዘርዐ ዮሐንስ አና ከእናቱ ማርያም ዘመዳ በ1262 ዓ.ም. ኅዳር 24 ቀን በሰሜን ሸዋ ግዛት በሚገኘውና ልዩ ስሙ እቲሳ ቅዱስ ሚካኤል በሚባለው አጥቢያ የተወለደው አቡነ ዜና ማርቆስ ደብረ ብስራት ከሚባለው ገዳሙ ወደ ይፋት መጥቶ ከነብዩ ኢሳይያስ ትንቢት ከምዕ. 11፥1 ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ እያለ በግእዝ ቋንቋ ሲያነብ አባ ጽጌ ድንግል በሰማ ጊዜ አባቶቼ አይሁድ የነቢያትን ትንቢት ንባቡን አስተምረውኛል አውቀዋለሁ፤ ትርጕሙን ግን አላውቀውምና ተርጕምልኝ አለው፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስም ሲተረጕምለት እንዲህ አለ፤ ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ፣ የሚለው ንባብ ከእሴይ ነገድ የሕይወት በትር የኾነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትወለዳለች ማለት ነው፡፡ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ የሚለው ንባብ ደግሞ፤ እመቤታችን ተወልዳ፣ ከእርሷም ጌታ በድንግልና ይወለዳል፣ ከጌታም ክብር ይገኛል ማለት ነው፣ ይህም ጌታ ተወልዶ ትንቢቱ በእውነት ተፈጽሟል ብሎ ተረጐመለት፡፡ ኢሳ 7፥14፣ ማቴ18፥24፡፡
ይህ ሰውም (አባ ጽጌ ድንግልም) በዚህ ትርጕም ደስ ተሰኝቶ አባት ሆይ የኢሳይያስን ትንቢት በመልካም ሁኔታ ተረጐምከው፣ መልካም ነገርንም ተናገርክ አለውና፣ ሥዕሏ ወዳለችበት ቦታ ወስዶ ታሪኩ ከላይ እንደተገለጸው፣ በጫካ ውስጥ ያያትን ሥዕል ጓደኛው በያዘው ብትር ሲመታት ወዲያውኑ እንደተቀሠፈና ክንፎቹ በጽጌረዳ አበባ ያጌጡ፣ "አንድ ነጭ ወፍ /ቅዱስ ሩፋኤል/" ወደ እርሱ መጥቶ ቀይ መነኵሴ እስኪመጣ ድረስ ይህችን ሥዕል ጠብቃት ብሎ በሰው አነጋገር ያነጋገረውን ሁሉ ነገረው፣ አቡነ ዜና ማርቆስም ከሥዕሏ የተደረገውን ተአምር ሰምቶ፣ እጅግ ደስ አለውና በል መጀመሪያ እመቤታችን በድንግልና በወለደችው በፈጣሪ ልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን ይህችን ሥዕል ያስገኘ፣ ሰማይና ምድርን፣ በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ የፈጠረ፣ እርሱ እንደኾነ እውቅ አለውና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቆ ጽጌ ብርሃን ብሎ ሰየመው፡፡
ከዚህ በኋላ ሥዕሏን በገዳመ ደንስ ደብረ ብሥራት ወደሚባለው ገዳም ወስዶ በዘመነ ጽጌ ጥቅምት አንድ ቀን በክብር አስቀመጣት የምትከብርትንም ቀን ጥቅምት 3 እና ሰኔ 8 ቀን አደረገ፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስም ጽጌ ብርሃንን ለመዓርገ ምንኵስና አበቃው፤ የአባ ጽጌ ብርሃንም ጽጌ ድንግል የሚል ቅጽል ስም አለው፣ በማኅሌት አገልግሎት ጊዜም ታላቁ ጻድቅ አቡነ ዜና ማርቆስ ቤተ ክርስቲያኒቱንና ሥዕሏን እየዞረ ሲያጥን፣ እመቤታችን የካህናቱን አገልግሎት እንደምትባርክ፣ ካህናቱ በግልጽ ይረዱ ነበር፣ አባ ጽጌ ብርሃንም ከመጠመቁ በፊት በአባቶቹ በአይሁድ ሥርዓት እያለ የብሉያት መጻሕፍትን የተማረ ነበር፣ የሐዲሳት መጻሕፍት ትርጓሜን ግን ከአቡነ ዜና ማርቆስ ተማረ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ላሉ አሕዛብ ሁሉ የድኅነት ምክንያት ትሆኑ ዘንድ ብርሃናቸው፣ መምህራቸው አደረግኋችሁ ብሉ ጌታ ነቢዩ ኢሳይያስንና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን እንደመረጣቸው፣ ኢሳ 49፥6.፣ የሐ.ሥራ13፥47 ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ዜና ማርቆስ ስብከተ ወንጌልን እንደ ዕለት ጉርስና እንደ ዓመት ልብስ አድርጎ፣ መላ ኢትዮጵያን ዞሮ፣ አስተምሮና ባርኮ የዕድሜ ባለጸጋም ሆኖ በተወለደ በ140 ዓመት በ1402 ዓ.ም ታኅሣሥ 3 ቀን ፣ ዐርብ ጠዋት ዐረፈ፡፡
አባ ጽጌ ብርሃንም በወሎ ክፍለ ሀገር በወራይሉ አውራጃ፣ ልዩ ስሙ ደብረ ሐንታ ለሚባለው ገዳም የሕግ መምህር ሆኖ ከተሸመውና ከጓደኛው ከአባ ገብረ ማርያም ጋር እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ በመሆን፣ እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግነውን ማኅሌተ ጽጌ የተባለውን ድርሰት፣ በአባቷ በዳዊት መዝሙር መጠን 150 አድርጎ ደረሰ፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኝ ኹሉ በማኅሌተ ጽጌ እመቤታችንን በአበባ፥ ጌታችን በፍሬ፤ ወይም እመቤታችንን በፍሬ፥ ጌታችን በአበባ እየተመሰሉ የሚመሰገኑበት ምስጋና ነው። ሰቈቃወ ድንግል ማለት እመቤታችን ከልጇ ከመድኀኔዓለም፣ ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በስደቷ ወቅት ያየችውን መከራ፥ ልቅሶ ዋይታ የሚዘከርበት የማኅሌተ ጽጌ አርኬ ነው፡፡
(የሰቈቃወ ድንግልን ደራሲ በተመለከተ አባ ጽጌ ድንግል ደረሱት የሚሉ አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አባ ገብረ ኢየሱስ ዘገዳመ መጕና /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/ ወይም /አባ አርኬላዎስ/ ነው የደረሱት የሚሉም አሉ፡፡)
ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ የማያደርግ የሕግ ፍጻሜ ነውና፤ ሮሜ 13፥10-11፣ አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያምም የዘመነ ጽጌ የማኅሌት አገልግሎትን ሳይለያዩ በሰላምና በፍቅር (በአንድነት) አገልግለዋል፣ ማለትም አንድ ዓመት አባ ገብረ ማርያም የክረምት መውጫና የዘመነ ጽጌ ዋዜማ በሆነው መስከረም 25፣ ቀን ከደብረ ሐንታ መጥቶ ገዳመ ጽጌ (ደብረ ብሥራት) ገብቶ ከመስከረም 26 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ያለውን የዘመነ ጽጌ የ40 ቀን አገልግሎትን ከአባ ጽጌ ብርሃን ጋር ፈጽሞ ኅዳር 8 ቀን ወደ ደብረ ሐንታ ይመለሳል፤ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አባ ጽጌ ብርሃን ከገዳመ ጽጌ (ከደብረ ብሥራት) ወደ ደብረ ሐንታ ሄዶ እንደዚሁ እንደ አባ ገብረ ማርያም 40ውን ቀን አገልግሎ ይመለሳል፣ እኒህ ሁለቱ ቅዱሳን ሊቃውንትም ታሪኩ ከላይ እንደተገለጸው እንዲህ እያደረጉ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ በፍቅርና በትሕትና ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን ቅዱስ አባት የሀገረ ቃው ኤጲስቆጶስ አባ መቃርስ አረፈ።
ለዚህም ቅዱስ የዝንጉዎችን ምክር ተከትሎ ያልሔደ፣ በኃጢአተኞችም ጎዳና ያልተጓዘ፣ በዘባቾችም መቀመጫ ያልተቀመጠ፣ የእግዚአብሔርን ሕግ መጠበቅ ፈቃዱ የሆነ እንጂ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያነብ የሚያስተምር ብፁዕ ነው የሚለው የነቢይ ዳዊት ቃል ተፈጽሞለታል።
ይህ አባ መቃርስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጠበቅ በመክሊት ነግዶ ዕጥፍ አድርጎ አትርፎአልና እግዚአብሔርም በእጆቹ ያደረጋቸውን ታላላቆች ድንቆች ተአምራት ስንቱን እንናገራለን። ስለርሱም እንዲህ ተባለ እርሱ በሀገረ ቃው ተሾሞ በወንበር ተቀምጦ ሕዝብን በሚያስተምራቸው ጊዜ ዘወትር ያለቅሳል ። ከደቀ መዛሙርቱም አንዱ እጅግ የሚወደው አማለውና አባቴ ሆይ ሁል ጊዜ ለምን ታለቅሳለህ ንገረኝ አለው እርሱም ስለ መሐላው ፈርቶ ዘይት በብርሌ ውስጥ እንደሚታይ የወገኖቼን ኃጢአታቸውን የከፋች ሥራቸውንም በማይና በምመለከት ጊዜ አለቅሳለሁ ብሎ መለሰለት።
ሁለተኛ ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠዊያው ላይ ተቀምጦ የየአንዳንዱን የሰውን ሥራ መላእክት ሲያቀርቡለት አየው በዚያንም ጊዜ እንዲህ የሚል ቃል ሰማ ኤጲስቆጶስ ሆይ ለምን ቸለል ትላለህ ሕዝቡን አትገሥጻቸውምን አታስተምራቸውምን እርሱም አቤቱ እነርሱ ትምርቴን አይቀበሉም ብሎ መለሰ። ሁለተኛም እንዲህ አለው ለኤጲስቆጶስ ሕዝቡን ማስተማር ይገባዋል ትምርቱን ካልተቀበሉ ግን ደማቸው በራሳቸው ይሆናል።
ከዚህም በኋላ መናፍቁ ንጉሥ መርቅያኖስ ወደ ሰበሰበው ጉባኤ ከሊቀ ጳጳሳቱ ዲዮስቆሮስ ጋር ይሔድ ዘንድ ጠሩት የተሰበሰቡትም አንዱን ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ የሚሉ ናቸው በደረሰም ጊዜ ስለ ልብሱ አዳፋነት ወደ ንጉሥ አዳራሽ መግባትን ከለከሉት አባ ዲዮስቆሮስም ከእርሱ ጋር እንዲአስገቡት ጳጳስ መሆኑን ነገራቸው።
በገቡም ጊዜ አንዱን ክርስቶስን ሁለት ባሕርይ አድርገው ትስብእቱን ከመለኮቱ እንደለዩት እምነታቸውን ሰሙ ስለዚህም ንጉሡንና ጉባኤውን አወገዙአቸው እሊህ አባቶቻችን አባ ዲዮስቆሮስና አባ መቃርስ ስለ ቀናች ሃይማኖታቸው ነፍሳቸውን ለሞት አሳልፎ ለመስጠት ቆርጠዋልና ንጉሡም ወደ ደሴተ ጋግራ አጋዛቸው።
ከዚያም ከምእመን ነጋዴ ጋር ወደ እስክንድርያ አባ ዲዮስቆሮስን ሰደደው እርሱ ለአባ መቃርስ ትንቢት ተናግሮለት ነበርና እንዲህ ብሎ አንተ ግን በእስክንድርያ አገር የሰማዕትነት አክሊል ትቀበል ዘንድ አለህ።
አባ መቃርስም ወደ እስክንድርያ ሲደርስ በዚያን ጊዜ የመናፍቁ የንጉሥ መርቅያን በውስጡ የከፋች ሃይማኖቱ የተጻፈበት የመልእክት ደብዳቤ ደረሰ መልእክተኛውንም እንዲህ ብሎ አዞታል በእኛ ሃይማኖት አምኖ በዚህ መዝገብ ውስጥ መጀመሪያ የጻፈ በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ይሁን የሚል ነው አብሮታራ የሚባል አንድ ሰው ተቀዳድሞ በውስጡ ሊጽፍ ያንን መጽሐፍ ተቀበለ ቅዱስ አባ መቃርስም እንዲህ አለው ከእስክንድርያ አገር በሔደ ጊዜ ከእኔ በኋላ አንተ በቤተ ክርስቲያን የሠለጠንክ ትሆናለህ ብሎ የነገረህን የአባ ዲዮስቆሮስን ቃሉን አስብ ያን ጊዜ አብሮታራ ያንን ቃል አስታውሶ በዚያ በረከሰ መጽሐፍ ላይ ሳይጽፍ ቀረ።
የንጉሡም መልክተኛ አባ መቃርስ በንጉሥ ሃይማኖት እንደማያምን በአወቀ ጊዜ ተቆጥቶ ከኵላሊቱ ላይ ረገጠው ያን ጊዜም ሙቶ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ ሥጋውንም ምእመናን ወስደው ከነቢይ ኤልሳዕና ከመጥምቁ ዮሐንስ ሥጋ ጋር በአንድነት አኖሩት ወደ ወደደው ክርስቶስም የመንግሥት ዘውድን ተቀዳጅቶ ሔደ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages