ስንክሳር_ዘወርኅ_ኅዳር 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, November 16, 2022

ስንክሳር_ዘወርኅ_ኅዳር 6

 ኅዳር 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም (ሚጠታ ለማርያም)
2.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
3.ቅድስት ሰሎሜ ቡርክት
4.ቅዱስ ዮሳ (ወልደ ዮሴፍ)
5.ቅዱስ ቴዎፍሎስ ሊቅ
6.አባ ጽጌ ድንግል ዘወለቃ
7.አባ ፊልክስ ዘሮሜ
ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ኅዳር ስድስት ቀን ክብርት እመቤታችን_ከተወደደ_ልጇ ጋር ደብረ ቁስቋም ገብተው ካገኛቸው ድካም ያረፉበት፣ የአረጋዊ ቅዱስ_ዮሴፍ#የቅድስት_ሰሎሜየአባ_ጽጌ_ድንግል መታሰቢያቸው ነው፤ የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ_ፊልክስ እረፍቱ ነው።


ኅዳር ስድስት በዚህች ዕለት ክብርት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ከስደት በሚመለሱበት ጊዜ ደብረ ቁስቋም ገብተው ካገኛቸው ድካም ዐረፉ፡፡
አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ከስደት በተመለሰች ጊዜ እንዲህ ሆነ፡- የብርሃን እናቱ ክብርት እመቤታችን ልጇን ይዛ ከእነ ዮሴፍ ጋር ወደ ምድረ ግብፅ ስትሰደድ ግብፅ ደርሰው በዚያ ቢቀመጡም ነገርን ግብፅ አልተመቸቻውም፡፡ ሕዝቡም በሰላም አልተቀበላቸውም፡፡ እንዲያውም በምድረ ግብፅ ብዙ ተሠቃይተዋል፡፡ ከግብፅም ተነሥተው ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ግን ኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በሰላምና በፍቅር ተቀበላቸው፡፡ ከመንገዱና ከርሃብ ጥሙ ጽናት የተነሣ እጅግ ደክማለችና የኢትዮጵያ ሰዎች እመቤታችንን አይተው እጅግ አዘኑላት፡፡ ‹‹ይህችስ የነገሥታት ዘር ትመሥላለች ነገር ግን አንዳች ችግር አጋጥሟት ተሰዳ ወደ ሀገራችን መጥታለች..›› ብለው እንክብካቤን አደረጉላት፡፡ እግራቸውን አጥበው በክብር ማረፊያዎች ላይ አሳረፏቸው፡፡ መልካም መስተንግዶም አደረጉላቸው፡፡ እመቤታችንም ከድካሟ ካረፈች በኋላ ሀገሪቱን በእጅጉ ወደደቻትና የተወደደ ልጇን ‹‹ይህን ሀገርና ሕዝቧን በመላ ወድጃቸዋልሁና በዚህ እስከ መጨረሻው እንኑር›› አለችው፡፡ ጌታችንም ክብርት እናቱን ‹‹ይህች ቅድስት ሀገር ናት፣ በኋለኛው ዘመን የቅዱሳን መነኮሳት ቦታ ትሆናለች፡፡ በውስጧም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እመሰገንባታለሁ፤ የአንቺም ስም ሳይጠራ አይውልባትም›› አላት፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን ደመና ጠቅሶ በእርሷ ላይ ተቀመጡ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤልም መጣና እየመራቸው መላ ኢትዮጵያን ጎበኟት፡፡ እመቤታችንም ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን ወዳቸዋለች ደስም ተሰኝታባቸዋለችና ጌታችን ለክብርት እናቱ ‹‹ይህችን ቅድስት ሀገር አሥራት አድርጌ ሰጠሁሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም እጅግ ተደስታ ‹‹ልጄ አምላኬ›› ብላ አመሰገነችው፡፡ ከዚህም በኋላ ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ እየተዘዋወሩ መላዋ ኢትዮጵያን በኪደተ እግራቸው ባረኳት፡፡ ጌታችንም ‹‹በዚህ ቦታ እንዲህ ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ይታነጻል፤ እከሌ የሚባል እንዲህ ዓይነት ቅዱስ ይነሣል…›› እያለ ብዙ ምሥጢራትን ለክብርት እናቱ ነገራት፡፡ ከዚህም በኋላ የስደቱ ዘመን ሲያልፍ ሄሮድስም በመጨረሻ ክፉ አሟሟትን ሲሞት መልአኩ ወደ ገሊላ አውራጃ እንዲመለሱ ነገራቸው፡፡ እመቤታችንም ‹‹ከዚህች ሀገርስ ባንሄድ እመርጣለሁ›› ስትለው የተወደደ ልጇ ግን ‹‹እናቴ ሆይ ጽድቅንና ፈቃድን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› ብሎ አጽናናትና ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡
ተመልሰውም ሊሄዱ ሲነሡ የኢትዮጵያ ሰዎች ልዩ ልዩ አምሐ እጅ መንሻ ሰጧቸው፡፡ ልዩ ልዩ ልብሶች፣ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ፣ ሽቱ እና ሥንቀቸውን በግመሎች ላይ ጭነው እመቤታችንንና የተወደደ ልጇንም በበቅሎ ላይ አስቀምጠው በክብር ሸኟቸው፡፡ እመቤታችንም ልጇን ታቅፋ በበቅሎ ተቀምጣ በበረሃው በመጓዝ ወደ መጣችበት አገር ሄደች፡፡ ኢትዮጵያንም የሰጧትን ብዙ እጅ መንሻዎች በግመሎች ጭና ይዛ ወደ አገሯ በተመለሰች ጊዜ ከአንድ ባሕር ዳር ደረሰች፡፡ ከዚያም የጀልባውን ባለቤት ‹‹እግዚአብሔርን ስለመውደድ አሻግረኝ›› ብላ ለመነችው፡፡ ባለጀልባውም ‹‹እነሆ ዕቃ የተጫኑ አምስት ግመሎችና ከአንቺ ጋር ከዚህም ሕፃን ጭምር አምስት ሰዎች እመለከታለሁ፣ አንቺ የተቀመጥሽባት በቅሎም አለች፡፡ ጀልባዋም ታናሽ ናት፣ የመቀመጫ ክፍሏም በውስጧ የተሳፈሩት ሰዎችም ተጨናንቀው ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ እንዴት ላሻግርሽ እችላለሁ? ነገር ግን እመቤቴ ሆይ! ይቅርታ አድርጊልኝ ይህን በክፋት አላደረግሁትምና›› አላት፡፡
ክብርት እመቤታችንም የጀልባው ባለቤት ሊያሻግራት እንዳልቻለ በተረዳች ጊዜ ‹‹ልጄ ሆይ የእግዚአብሔር ልጅ እንደመሆንህ ይህን ትልቅ ወንዝ ለመሻገር የአምላክነትህን ሥራ ትሠራ ዘንድ እለምንሃለሁ›› ስትል ማለደችው፡፡ ያንጊዜም ጌታችን ክብርት እናቱን ‹‹የወለደሽኝ እናቴ ሆይ! አትዘኝ›› ብሎ አረጋጋት፡፡ ዳግመኛም ‹‹በእኔ ፈቃድ በአባቴ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ካንቺ ሰው ሆኛለሁና ሰው መሆኔንም ከአባቴ በቀር መስተፍሥሒ ከሚሆን ከመንፈስ ቅዱስም በቀር ያወቀ የለም፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ ለሁሉም እንደየሥራው እከፍለው ዘንድ እመጣለሁ፡፡ ያችንም ሰዓት የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ የአዳም ልጆችም ቢሆኑም ከእኔና ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስም በቀር የሚያውቃት የለም፡፡ ያንጊዜ ‹ዐመፅን የሚናገር አንደበት ሁሉ ይዘጋል› ብሎ አባትሽ ዳዊት እንደተናገረ እከራከራለሁ የሚል አንደበት እንደድዳ ምላሽ ያጣል›› አላት፡፡
ክብርት እመቤታችን ማርያምም ይህንን ሁሉ ምሥጢር የተወደደ ልጇ የነገራትን ታስተውለው በልቧም ትጠብቀው ነበር፡፡ ጌታችንም አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለክብርት እናቱ ይህንን ከነገራት በኋላ ቀኝ እጁን ዘርግቶ ከወንዙ ማዶ ጢር በሚባል ተራራ ያሉትን ድንጋዮች ጠቀሳቸው፡፡ ያንጊዜም እነዚህ ድንጋዮች እየተገለባበጡ መጥተው እንደ ጀልባ ሆነው በወራጁ ወንዝ ላይ ተንሳፈፉ፡፡ ከዚያም እመቤታችንን ከሕፃኑ ጋር ከነቤተሰቧና ከነጓዟ አሻገረሯት፡፡
እነዚህንም ድንጋዮች ያዩ ሰዎች ሁሉ እጅግ አድንቀው ‹‹ብቻውን ድንቅ ተአምራት ያደረገ፣ እስራኤልን የፈጠረ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን የጌትነቱም ስም የተመሰገነ ነው›› እያሉ አመሰገኑ፡፡ እነዚህም የተባረኩ ሰዎች ወንዙን ከተሻገሩ በኋላ በዚህች አገር ለስምንት ቀን ተቀመጡ፡፡ ከዚህም በኋላ አምላክን የወለደች በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች ክብርት እመቤታችን ስለደረገላት መልካም ሥራ ሁሉ እግዚአብሔርን ፈጽማ እያመሰገነች ወደ አባቷ ወደ ዳዊት አገር ተመለሰች፡፡
ዳግመኛም በኋለኛው ዘመን ጌታችን በዚህ በደብረ ቍስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቶቹን ሰበሰባቸውና ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ የቍርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወገኖቹ ሰጣቸው፡፡ ለዚህም ነገር የእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሳን አባቶቻችን ቄርሎስና ቴዎፍሎስ ምስክሮቹ ሆኑ፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአረጋዊ ቅዱስ ዮሴፍ እና የቅድስት ሰሎሜም መታሰቢያቸው ነው።
አረጋዊ_ቅዱስ_ዮሴፍ፦ መልካም ሽምግልና የነበረው የእመቤታችን ድንግል ማርያም እጮኛዋ ድካሟን ለመሳተፍ ክብር ይግባውና ለጌታችንም አሳዳጊው ለመሆን የተገባው መታሰቢያው ነው።
እርሱም እምቤታችንን በርሱ ዘንድ ካስጠበቋት ጀምሮ በሁሉ ነገር ያገለግላት ነበር። በመከራዋም ሁሉ አልተለያትም። በወለደችም ጊዜ በቤተ ልሔም ከርሷ ጋራ ነበረ። ወደ ግብጽም በተሰደደች ጊዜ ከእርሷ ጋራ ብዙ መከራ ደረሰበት። ከዚህም ዓለም የሚለይበት ጊዜው በደረሰ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን ተሰናበታቸው እጆቹንም ጠርቶዘርግቶ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። የዘላለምንም ሕይወት ወረሰ።
በአረፈበትም ጊዜ ጌታችን ወደርሱ መጥቶ እጆቹን በላዩ ጫነ ለሥጋውም መፍረስና መበስበስ እንዳያገኘው ኃይልን ሰጠው በአባቱ በያዕቆብም መቃበር አኖሩት።
ቅድስት_ሰሎሜ፦ አምላክን የወለደች የቅድስት ድንግል የእመቤታችን የአክስቷ ልጅ መታሰቢያዋ ነው። እርሷም የማጣት ልጅ የሌዊ ልጅ የሚልኪ ልጅ የካህን አሮን ልጅ ናት። ለማጣት ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱ ስም ማርያም ነው የሁለተኛዪቱ ስም ሶፍያ የሦስተኛዪቱም ሐና ነው ይቺም ማርያም ሰሎሜን ወለደቻት ሶፍያም ኤልሳቤጥን ወለደቻት ሐናም አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደቻት።
እመቤታችንም ድንግል ስትሆን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በወለደችው ጊዜ ይቺ ቅድስት ሰሎሜ የእመቤታችንን አወላለድ እንደ ሴቶች ሁሉ አወላለድ መስሏት ተጠራጠረች ከዚህም በኋላ የድንግል እመቤታችን ገላዋን ዳሠሠቻት ያን ጊዜ እጇ ተቃጠለ ሕፃኑን በዳሠሠችው ጊዜ ደግሞ ዳነች።
በዚህም በኅቱም ድንግልና አምላክን እንደወለደች አወቀች። ከተረገመ ኄሮድስ ፊት እመቤታችን በሸሸች ጊዜ ከዮሴፍ ጋራ በመሆን አብራ በመሰደድ የእመቤታችንን ድካሟን ተካፍላ አገለገለቻት ከስደት እስከ ተመለሱ ድረስ ሕፃኑን ታዝለዋለች የምታጥብበትም ጊዜ አለ።
መድኃኒታችን ሰው በሆነበት ወራት ሁሉ አልተለየችም በመከራውም ቀን ከእመቤታችን ጋራ ከከበሩ ሁሉ ሴቶች በትምህርቱ ወራት ከተከተሉት ጋራ እያለቀሰች ነበረች።
በተነሣባት ዕለት ወደ መቃብር ገሥግሣ ከሐዋርያት ቀድማ ያየች ናት። በኃምሳኛውም ቀን መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከባልንጆሮቿ የከበሩ ሴቶች ጋራ ሰማያዊ ሀብትን ተቀብላ በክብር ባለቤት መድኃኒታችን ስም ሰበከች ብዙዎችንም አሳመነች። ከአይሁድም ብዙ ስድብና ሽሙጥ አገኛት ከዚያም አረፈች።

ጻድቁ አቡነ ጽጌ ድንግል በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩ ሊቅና ገዳማዊ ናቸው። የዘር ሐረጋቸው ምንም ከቤተ እሥራኤል እንደሚመዘዝ ቢታወቅም ኢትዮዽያዊ ናቸው። አስቀድመው አይሁዳዊ በመሆናቸው ኢየሱስ ክርስቶስንና ድንግል እናቱን አያምኑም ነበር።
የተማሩትም ብሉይ ኪዳንን ብቻ ነበር። በጊዜውም "ክርስቶስ አልተወለደም ትክክለኛው እምነት ይሁዲ ነው" እያሉ ከክርስቲያኖች ጋር ይከራከሩ ነበሩ። አንድ ቀን ግን ከታላቁ ሊቅና ገዳማዊ አቡነ ዜና ማርቆስ ጋር ተገናኙ።
ጻድቁን ስላልቻሏቸው ተሸንፈው በክርስቶስ አመኑ። አቡነ ዜና ማርቆስም አስተምረው ክርስትና ሲያነሷቸው/ሲያጠምቁዋቸው 'ጽጌ ድንግል' አሏቸው። ሲመነኩሱም 'ጽጌ ብርሃን' ተብለዋል። ቀጥለውም በጾምና በጸሎት ሲጋደሉ እመቤታችንንም ሲለምኑ ምሥጢር ተገለጠላቸው።
የእመ ብርሃንን ስዕለ አድኅኖ በአበባ ተከባ: በብርሃንም ተውጣ ተመለከቱ። በዚህ ምክንያትም ዛሬ በጣፋጭነቱ የሚታወቀውን ማኅሌተ ጽጌን 150 ዓርኬ አድርግው ደረሱ። እስከ ዕለተ ዕረፍታቸውም እመቤታችንና ልጇን በገዳማቸው (ወለቃ አካባቢ የሚገኝ) ሲያመሰግኑ ኑረዋል። ጻድቁ ያረፉት ጥቅምት 27 ሲሆን ዛሬ የቃል ኪዳን በዓላቸው ነው።

ዳግመኛም በዚህች ቀን የሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ፊልክስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ክርስቲያኖች ናቸው የቤተክርስቲያንንም ትምህርት አስተማሩት የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት አንስጣስዮስም ዲቁና ሾመው ደግሞ የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ዮስጦስም ጠባዩን የጽድቁንና የትሩፋቱን ደግነት አይቶ ቅስና ሾመው።
ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮናስዮስ በአረፈ ጊዜ ይህን አባት ፊልክስን መረጡት በእግዚአብሔርም ፈቃድ በሮሜ ሀገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት የክርስቶስንም መንጋዎች በመልካም አጠባበቅ ጠበቀ።
ትሩስ ቄሣርም ከሞተ በኋላ ቴዎድሮስ ቄሣር ነገሠ ። እርሱም በምእመናን ላይ ታላቅ መከራ አምጥቶ ጭንቅ በሆኑ ሥቃዮች አሠቃያቸው። ብዙዎችም በእርሱ እጅ በሰማዕትነት ሞቱ። ይህም አባት ከዚህ ከሀዲ ታላቅ መከራና ኀዘን ደረሰበት። ስለርሱም ወደ እግዚአብሔር ማለደ ክብር ይግባውና ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ ይህንን ከሀዲ በሁለተኛ ዘመነ መንግሥቱ አጠፋው።
ከዚህም በኋላ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖችን አብዝቶ ማሠቃየትን ጀመረ ይህም አባት ፊልክስ የክርስቲያኖችን ሥቃይ እንዳያይ ክብር ይግባውና ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በዲዮቅልጥያኖስም በመጀመሪያው ዘመነ መንግሥቱ አረፈ።
ይህም አባት ብዙዎች ድርሳናትንና ተግሣጾችን ደርሶአል ከእርሳቸውም ስለ ውግዘትና ስለ ቀናች ሃይማኖት የተመላለሱበት አለ እሊህም ለክርስቲያን ወገን እጅግ የሚጠቅሙ በጎዎች ናቸው።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከስደቱ በረከትም ያድለን። በቅዱሳኑም ጸሎቱ ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages