ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 5 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, November 16, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 5

ኅዳር 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ ቅዱስ ዮሐኒ (ዘትግራይ)
2.አባ አሞኒ ዘናሕሶ
3.ቅዱስ ለንጊኖስ ሰማዕት
4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት
5.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት
ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)
4.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር አምስት በዚህች ቀን የደብረ ዓሣው አባ_ዮሐኒ የተሰወሩበት፣ አባ_አሞኒ_ዘናሕሶ ያረፉበት፣ የቅዱስ_ለንጊኖስ ራሱ የታየችበት፣ የሐዋርያው ቅዱስ_ጢሞቴዎስ መታሰቢያ፣ የቅዱስ_ቴዎድሮስ ሰማዕት ሥጋው የፈለሰበት ዕለት ነው።


ኅዳር አምስት በዚህች ቀን የደብረ ዓሣው አባ ዮሐኒ የተሰወሩበት እና አባ አሞኒ ዘናሕሶ ያረፉበት ዕለት ነው።
አባ ዮሐኒ መጽሐፍ አባታቸውን ዘስዩመ ተንቤን እሁሁ ይላቸዋል፡፡ እናታቸው ደግሞ ዓመተ መንፈስ ቅዱስ የሚባሉ ደገኛ ምግብራቸው ያማሩ ሀገር ወዳድ ናቸው፡፡ አቡነ አሞኒ የካቲት 5 ቀን አክሱም ውስጥ ሲወለዱ ሰይጣናት የወላጆቻቸውን ቤት ከበው በማየታቸው እንደተወለዱ በእጃቸው ቢያመለክቱ በአንድ ጊዜ 60 ሰይጣናት ተሸንፈው እንደጢስ በነው ጠፍተዋል፡፡ አሞኒ ማለት አሸናፊ ማለት ነው፡፡አባ አሞኒ የራስ ፀጉራቸው ልብስ መጎናጸፊያ ሆኖላቸው የኖሩ ታላቅና ቀደምት አባት ናቸው፡፡ በደመና ተጭነው ደብረ ዘይት ድረስ በመሄድ ከአባ እብሎይ ጋር ተገናኝተው ብዙ ምሥጢርን አውርተዋል፡፡ አባ ዮሐኒን ያሳደጉት አስተምረው ያሳደጓቸው አባ አሞኒ ናቸው፡፡ የእናቱን ጡት ፈጽሞ ጠብቶ የማያውቀውን የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸውን አባ ዮሐኒን እሳቸው እያጫወቱት የታዘዘ አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው ቶራ (ሰሳ) እያጠባችው ነው ያደገው፡፡
መነሻ ታሪኩም እንዲህ ነው፡- የተንቤን አውራጃ ገዥ የነበረው ሰው በዘመኑ ዐፄ ካሌብ የነበሩበት ዘመን ነበርና አብሯቸው ወደ ምድረ ኖባ ሄደው ሰባት ዓመታትን የፈጀ የጦር ዘመቻ ክርስያኖችን በሚያሠቃዩ ነገሥታት ላይ አዳሄዱ፡፡ የተንቤኑ አውራጃ ገዥም ወደ ዘመቻው ከሄደ ቆይቶ ነበርና ታናሽ ወንድሙ የገዥውን ሚስት ‹‹ወንድሜ የቀረው ሞቶ ነው እንደ ኦሪቱ ሕግ እኔው ላግበሽና ልጆቹን ላሳድግ›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹ባሌ ቢሞት ይነገረኝ ነበረዘመቻ የሄደው ሁሉ አልተመሰም›› ብላ እምቢ ብትለው በግድ ተገናኛት፡፡ በዚህም ጊዜ አባ ዮሐኒ ተፀነሱ፡፡ በሚያዝያ 5 ቀንም ተወለዱ፡፡
ከዘጠኝ ወር በኋላ ባሏ ከዘመቻ መጣና ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ የአካባቢውም ሰው ወጥቶ በክብር ሲቀበለው ሚስቱ ግን ምጥ ተይዛ ታማ ስለነበር ወጥታ አልተቀበለችውም፡፡ ‹‹የት ሄደች? ምንስ ሆነች?›› ብሎ ሲጠይቅ ልጅ አይደብቅምና አንድ ሕፃን ‹‹አርግዛ ልትወልድ በምጥ ላይ ትገኛለች›› አለው፡፡ የአውራጃውም ገዥ ያለችበት ድረስ ሄዶ ቢያያት ያማረ ወንድ ልጅ ታቅፋ አገኛት፡፡ ከዚህም በኋላ ከቤቱ ምሰሶ ጋር ጥፍንግ አድርጎ አስሮ እየገረፋትና እያስጨነቃት ከማን እንዳረገዘች ጠየቃት፡፡ እርሷም የወንድሙን ምሥጢር ለመጠበቅና ወንድማማቾቹን ላለማጣላት ሥቃዩን ታግሳ ዝም አለች፡፡ በዚህ ቅጽበት የራማው ልዑል ቅዱስ ገብርኤል 40 ዓመት ሙሉ ዘግተው በበረሃ ለሚኖሩት ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸው እንደ አውሎ ነፋስ አምዘግዝጎ ወስዶ አውራጃ አገረ ገዥው ቤት አደረሳቸው፡፡
እንደደረሱ ዓመተ ማርያም በጽኑ ድብደባና ግርፋት እየተሠቃየች እያለ አባ አሞኒ የጸጉራቸውን አጽፍ ለብሰው ራቁታቸውን ደጇ ላይ ቆመው አየቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ለባሏ ‹‹ያውና ከዚህ መነኩሴ ነው የወለድኩት››፣ አለችው፡፡ የአውራጃ አገረ ገዥውም አባ አሞኒን ይዞ ጽኑውን ግርፋት በወታደሮቹ አስገረፋቸው፡፡ በመቀጠልም ገና የእናቱን ወተት እንኳን ያልቀመሰውን ጨቅላ ሕፃን አንሥቶ ‹‹እንካ ልጅህን ይዘህ ጥፋ ከዚህ›› ብሎ ሰጣቸው፡፡ አባ አሞኒም በዚህ ጊዜ ‹‹ዮ ሀበኒ ዮ ሀበኒ›› አሉ፡፡ በትግርኛ እሽ ስጠኝ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው ሕፃኑ በኋላ ላይ ‹‹አባ ዮሐኒ›› የተባሉት፡፡ አባ አሞኒም ሕፃኑን ተረክበው ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ ሥር ሄደው ልጁን ከወይራ ዛፍ ሥር አስተኝተው ‹‹አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ኃጢአቴን ተመራምረህ ይህንን ሕፃን የሰጠኸኝ አላጠባው ጡት የለኝ አላበላው እህል የለኝ›› ብለው የጨቅላው ሕፃን ነገር እጅግ ቢያስጨንቃቸው ምርር ብለው አለቀሱ፡፡ ጸሎታቸውንም እንደጨረሱ ተራራውን በመስቀል ምልክት ቢባርኩት በተራራው መሐል ላይ እንደመደብ ያለ አልጋ በተአምራት ተሠርቶ አገኙት፡፡ ሕፃኑንም ከዚያ አስተኝተው ድጋሚ ጸሎት ሲጀምሩ ቶራ (ሰሳ) መጥታ እግርና እግሯን አንፈራጣ ሕፃኑን አጠባችውና ሄደች፡፡
አባ አሞኒም በዚህ ደስ ተሰኝተው ሕፃኑን ‹‹የምግብህ ነገር ከተያዘ ግዴለም›› ብለው ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልዩ አድረው መለስ ቢሉ ዳግመኛም ሕፃኑን የታዘዘ ንስር አሞራ በክንፎቹ ጋርዶ አልብሶትና አቅፎት እንዳደረ ተመለከቱ፡፡ አባታችንም እጅግ ደስ ተኝተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ቀን ቀን ቶራዋ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራው አልብሶት እያደረ ሕፃኑ ሦስት ዓመት ሆነው፡፡ አባ አሞኒም ከሰባት ዓመቱ ጀምረው እስከ 12 ዓመቱ ድረስ ፊደል፣ ንባብ ከነትርጓሜው፣ ብሉይንና ሐዲስን፣ ምግባር ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተ ክርስያንን ሁሉ አስተማሩት፡፡
አባ አሞኒ ልጃቸው አድጎ 12 ዓመት ሲሆነው ከዚህም በኋላ ዲቁና ሊያሾሙትና አክሱም ጽዮን ወስደው ሊያስባርኩት ቤተ ካህናት ከተባለው ቦታ ይዘውት ሲሄዱ ልዩ ስሙ ሲሂታ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ ከወገባቸው በላይ እራቁታቸውን የሆኑ እንስራ የተሸከሙ ዓሥር ሴቶች አገኙ፡፡ አባ ዮሐኒም አባታቸውን ‹‹አባቴ እነዚህ ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ጽጉራቸው የረዘመ ምንድናቸው? እንደእኛ የሆኑ መስህታን የሚባሉት እነዚህ ናቸውን?›› አሏቸው፡፡ አባ አሞኒም ‹‹አይደሉም ልጄ ዝም ብለህ ሂድ›› አሏቸው፡፡ በኋላ ግን ትዝ ሲላቸው ‹‹በዱር እንስሳት ያሳደኩት ልጄ ወንድና ሴት ለይቶ ሲያውቅ በዚያው ሊሳሳት አይደልምን?›› ብለው በማሰብ ዲቁናና ክህነቱ ይቅርበት ብለው ተመልሰው ወደ በዓታቸው ይዘውት ገቡ፡፡
ከዚህም በኋላ አባ አበይዶ ወደ አባ አሞኒ መጣና እሳቸውን ከአባ ዮሐኒ ጋር እያገለገሏቸው ተቀመጡ፡፡ ዮሐኒ እየጻፈ አበይዶ የሚጻፍበትን ቆዳ እያዘጋጁ ሦስቱም በአንድነት በተጋድሎ መቀመጥ ጀመሩ፡፡
አባ ዮሐኒ 20 ዓመት አባ አሞኒ ደግሞ 40 በሆናቸው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸውና ‹‹አሞኒ ሆይ ከእንግዲህስ እግዚአብሔር ወደኔ ና ብሎሃል›› አላቸው፡፡ እሳቸውም ልጆቻቸውን አባ ዮሐኒንና አባ አበይዶን ጠርተው ‹‹በሉ እንግዲህ እኔ ወደ እግዚአብሔር መሄዴ ነውና ጸልዩልኝ›› አሏቸው፡፡ ከማረፋቸውም በፊት አባ ዮሐኒን ለብቻቸው ጠርተው ‹‹አንተ አባ ዮሐኒ ካሁን በፊት ሲሂታ ላይ ያየሃቸው ሴቶች ናቸው፣ አዳምንም ከገነት ያስወጡ ናቸው፡፡ ወደፊትም እንደ እነርሱ ያለ የደረሰብህ እንደሆነ ካለህበት ገደል ተወርውረህ ውደቅ በባሕር ውስጥ ጥለቅ›› ብለው ነግረዋቸው በዛሬዋ ዕለት ኅዳር 5 ቀን በሰላም ዐረፉና ወደ ጠራቸው እግዚአብሔር ሄዱ፡፡
አባ አሞኒ ካረፉ ከ12 ዓመት በኋላ የአባ ዮሐኒ ወላጅ እናታቸው የልጇን ነገር ስታጠና ኖራ ነበርና አሁን ባሏም ስለሞተ አባ አሞኒም ስላረፉ ልጇን ልታይ ከ32 ዓመት በኋላ መጣች፡፡ ቀሚስ ለብሳ ፀጉሯን ተሠርታ በሴትነቷ ልጇ ካለበት ቦታ በመሄድ ማነጋገር እንደማትችል ስላወቀች ፀጉሯን ተላጭታ የወንድ ልብስ ቁምጣ ለብሳ በሁለመናዋ ወንድ መስላ ወደ ደብረ ዓሣ ተራራ አመራች፡፡ እዚያም እንደደረሰች በቅዱሳን ሥርዓት መሥረት ሦስት ጊዜ ‹‹አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን፣ አውሎ ግሶን›› አለች፡፡ ሰይጣን ይህን ስም ሲሰማ 40 ክንድ ይርቃል፡፡ የደብረ ዳሞ መነኮሳት እንደ ሰላምታ መለዋወጫ ይጠቀሙበታል፡፡ አባ ዮሐኒም ይህን ድምጽ ከውጭ በሰሙ ጊዜ ‹‹አንተ ማነህ?›› አሉ፡፡ እርሷም ‹‹ዓመተ መንፈስ ቅዱስ ነኝ›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም አንድም ድምፁዋ ወትሮ ከሚያውቁት ድምፅ ስተለየባቸው ደግሞም ትዝ ሲላቸው እነዚያ እንስራ አዝለው ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ሆነው ውኃ ቀድተው ሲሄዱ በመነገድ ያዩአቸው ሴቶች ድምፅ ሆነባቸው፡፡ ደግሞም ‹‹ወልደ እከሌ፣ ክንፈ እከሌ›› ሲባል እንጂ ‹‹ዓመተ፣ ወለተ›› ሲባል ሰምተው አያውቁም ነበርና አባታቸው አባ አሞኒ የነገሯቸው ትዝ አላቸው፡፡ በዚያውም ቅጽበት የሚጽፉባትን ብዕር ጆሮአቸው ላይ እንደሰኩ 500 ሜትር ርዝመት ካለው ትልቅ ተራራ ላይ ራሳቸውን ቁልቁል ወረወሩ፡፡ ነገር ግን መሬት ሳይደርሱ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በአየር ላይ እንዳሉ ተቀበላቸው፡፡ ብዕራቸው ግን መሬት ላይ ወድቃ ሸምበቆ ሆነች፡፡ ወዲያውም አባ ዮሐኒ ክንፍ አውጥተው ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ጎን ለጎን ሆነው በዛሬው ዕለት ኅዳር 5 ቀን ወደ ብሔረ ሕያዋን ይዟቸው ገባ፡፡
ብሔረ ሕያዋን ያሉ እነ ሄኖክና ኤልያስም ‹‹ሰው ከሚሞትበት ሀገር ሞት ወደሌለበት አገር ማን አመጣው?›› አሉ፡፡ መልአኩም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ባዘዘኝ ጊዜ እኔ ገብርኤል ነኝ ያመጣሁት›› አላቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ ‹‹አንተ ሄኖክ ምንም ንጹሕ ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ሚስት አግብተህ ወልደሃል፣ እግዚአብሔርም እዚህ ያደረሰህ በንፅህናህ ነው፤ አንተም ኤልያስ ምንም ድንግል ብትሆን በሥርዓተ ሥጋ ተወልደህ በሥርዓተ ሥጋ አድገህ ከዚህ ደርሰሃል፤ ይህ አባ ዮሐኒ ግን ከተወለደ ጀምሮ የእናቱን ጡት አልቀመሰም፣ ቀን ቀን ሰሳ እያጠባችው ሌሊት ሌሊት ንስር አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው አድጓል እንጂ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድል ዘርዝሮ ከነገራቸው በኋላ ሊሞት ያለበትንም የአሟሟቱን ነገር ከነገራቸው በኋላ ‹‹ታዲያስ እንዲህ ያለውን አምጥቼ ከብሔር ሕያዋን ባስገባው ፍርዴ እውነት አይደለምን?›› አላቸው፡፡ ሄኖክና ኤልያስም ይህን ጊዜ ‹‹ይገባዋል›› ብለው አባ ዮሐኒን በምስጋና ተቀበሉት፡፡
ከዚህም በኋላ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ደብረ ዓሣ ተመልሶ መጥቶ ለአባ አበይዶ ተገለጠላቸውና አባ ዮሐኒን ብሔረ ሕያዋን እንዳስገባው ነገራቸው፡፡ በመጀመሪያ ሄኖክና ኤልያስ አላስገባ ብለው እንደነበርና በኋላም መልአኩ ራሱ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን ከነገራቸው በኋላ በምስጋና እንደተቀበሉት ለአባ አበይዶ ነገራቸው፡፡ ቀጥሎም መልአኩ የአባ ዮሐኒን ገድላቸውን እንዲጽፉትና እንዲያስተምሩበት ለአባ አበይዶ አዘዛቸውና ዐረገ፡፡ አባ አበይዶም አባ ዮሐኒ ከገደሉ ተወርውረው ሲወደቁ አንድ ደስ የሚል ወንድ ሲቀበለው አይተው ነበርና አሁን መልአኩ ሲነግራቸው እጅግ ደስ አላቸው፡፡ አባ አበይዶም በመልአኩ በታዘዙት መሠረት የአባ ዮሐኒን ገድል ጻፉት፡፡

በዚህች ቀን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ ጐኑን የወጋ የቅዱስ ለንጊኖስ ራሱ የታየችበት ነው። ይህም ቅዱስ በጌታችን ከአመነ በኋላ በቀጰዶቅያ አገር ወንጌልን የሚሰብክ ሆነ ከሀድያን አይሁድም በላዩ ተነሡበት በመኳንንት ዘንድ በሐሰት ወንጅለው በቀጰዶቅያ አገር ራሱን አስቆረጡት ራሱንም ብቻውን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱዋት። በኢየሩሳሌም የሚኖሩም አይሁድ በአዩዋት ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው ከዚህም በኋላ ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ በአንድ ኮረብታ ላይ ቀበሩዋት።
ከብዙ ቀኖችም በኋላ እንዲህ ሆነ በቅዱስ ለንጊኖስ ስብከት ያመነች አንዲት ሴት በቀጰዶቅያ አገር ነበረች ራሱን ከቆረጡበት ጊዜ ጀምራ በተቆረጠበት ቦታ በመቆም ስለርሱ ታለቅስ ነበር ክብር ይግባውና በእግዚአብሔርም ፈቃድ የዚያች ሴት ዐይኖቿ ታወሩ።
ከዚህም በኋላ ምናልባት ዐይኖቿ ቢገለጡላት በማሰብ ከከበሩ ቦታዎችና ክብር ይግባውና ከጌታችን መቃብር ለመባረክና ለመለመን ተነሥታ ልጅዋን ይዛ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች። ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሰች ጊዜ በዚያ ልጅዋ ሞተ ኀዘንም ተጨመረባት ወደ አገርዋም መርቶ የሚያደርሳት አጣች ስለዚህም የመረረ ልቅሶን አለቀሰች ከኀዘኗም ብዛት የተነሣ ተኛች።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ለንጊኖስን ከሞተው ልጅዋ ጋር በሕልሟ አየችው። ዕገሌ ከሚባልም ቦታ ሒደሽ ራሴን ከዚያ ውሰጂ አላት። ከእንቅልፍዋም በነቃች ጊዜ ስለዚያ ቦታ ጠየቀች ሰዎችም ወደርሱ አደረሱዋት። ያንንም ቦታ በቆፈረች ጊዜ መዓዛው እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ መዓዛ ወጣ። ራሱ ወደአለችበትም ስትደርስ ታላቅ ብርሃን ተገለጠላትና ዐይኖቿም በዚያን ጊዜ ተገለጡላት እግዚአብሔርንም አመሰገነችው።
ከዚህም በኋላ ከልጅዋ ሥጋ ጋር የቅዱስ ለንጊኖስን ራስ ወደ አገርዋ ወሰደቻት። በታላቅ ክብርም በአማረ ቦታ አኖረቻት።

በዚህች ዕለት አሕዛብን ለሚያስተምር ለከበረ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነ የከበረ ሰማዕት ሐዋርያው ጢሞቴዎስ መታሰቢያው ነው። የዚህም ቅዱስ ልደቱና እድገቱ ልስጥራን ከሚባል አገር ነው አባቱም ከዋክብትን የሚያመልክ ዮናናዊ ነው እናቱ ግን በኦሪት ሕግ ጥላ ሥር ያለች ናት።
የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም በልስጥራን ሀገር በሰበከ ጊዜ ይህ ጢሞቴዎስ ስብከቱንና ትምህርቱን ሰማ እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያደርጋቸውን ድንቆች ተአምራቶችን አይቶ እሊህም ተአምራቶች አስተዋዮችና ጥበበኞች የሚደነግጡባቸው ናቸው ስለዚህም ወደ ሐዋርያ ጳውሎስ ሒዶ በእርሱ ትምህርት በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ። በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቆ የሐዋርያ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ ሆ። ወደ ብዙ አገሮችም ተከትሎት በመሔድ ከእርሱ ጋር ደከመ ታላቅ መከራና ብዙ ኀዘንም ደርሶበታል ሐዋርያው ጳውሎስም በኤፌሶን ውስጥ በአንዲት አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾመው።
በዚያንም ጊዜ ወደርሷ ገብቶ ለሰዎቿ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ ብዙዎችንም ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው ከዚህም በኋላ በዙሪያዋ ወዳሉ ብዙዎች አገሮች በርቀትም ለሚገኙ አገሮችም የከበረ ወንጌልን ሰበከላቸው።
የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም ሁለት መጻሕፍቶችን ጽፎ ወደርሱ ልኳል እርሳቸውም ሕዝቡን የሚያስተምርባቸው ራሱም ከቢጽ ሐሳውያን የሚጠበቅባቸው ቅስና ወይም ዲቁና ሊሾም የሚገባውንና የማይገባውን የሚለይበት ክህነት በማይገባው እጁን እንዳይጭን የሚያስጠነቅቁ ናቸው ጢሞቴዎስን ደግሞ ለርሱ ተወዳጅ ልጁ አድርጎ ይጠራዋል መልእክቶቹንም በእርሱ እጅ ወደ አገሮች ልኳል።
በላያቸው የተሾመባቸውን የክርስቶስን መንጋዎች ፈጽሞ በጠበቀ ጊዜ በትምህርቶቹ በተግሣጾቹና በድርሰቶቹ ልቡናቸውን ብሩህ አደረገ አይሁድንና ዮናናውያንን ይገሥጻቸውና ይዘልፋቸው ነበር እነርሱም ቀንተውበት ሁሉም በጠላትነት ተነሡበት ተሰብስበውም ገደሉት ምእመናንም ሥጋውን አንሥተው ቀበሩት ጻድቅ ቈስጠንጢኖስም እስከ ነገሠ በዚያው ኖረ እርሱም ስለ ሥጋው አስቦ ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ በጥር ወር በሃያ ሰባት ቀን አፈለሰው በዚያችም ቀን በዓል አደረገለት።

ቅዱስ_ቴዎድሮስ (የሠራዊት አለቃ)
ዳግመኛም በዚህች ቀን ታላቅና ክቡር የሆነው የሠራዊት አለቃ የቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕትነት የሥጋው ፍልሰት ሆነ። የዚህ ቅዱስ አባት ስሙ ዮሐንስ ይባል ነበር። እርሱም ከላይኛው ግብጽ ሰጥብ ከምትባል መንደር ነበር። ወደ አንጾኪያ ከተማም ከሠራዊቱ ጋራ ወሰዱትና በዚያ ኖረ ከዚያች ከተማ መኳንንቶችም ያንዱን ልጅ አገባ እርሷም ጣዖትን ታመልክ ነበር። ባሏ ዮሐንስ የሚያመልከውን ግን አታውቅም ነበር።
ከዚህም በኋላ ይህን ቅዱስ ቴዎድሮስን በወለዱት ጊዜ እናቱ ወደ ጣዖቷ አቅርባ አምልኮትዋን ልታስተምረው ፈለገች አባቱ ግን አስተወው ስለዚህም ተቆጥታ ባሏ ዮሐንስን አባረረችው ሕፃኑ ቴዎድሮስም በእናቱ ዘንድ ቀረ።
አባቱ ዮሐንስም ልጁ ቴዎድሮስን ወደ እውነተኛ መንገድ ይመራው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይና ይማልድ ነበር። ሕፃኑ ቴዎድሮስም በአደገ ጊዜ ጥበብን ተማረ ጌታችንም ልቡን ብሩህ አደረገለት ስሙ አውላኪስ ወደሚባል ኤጲስቆጶስም ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። እናቱም ታላቅ ኅዘንን አዘነች።
ከዚህም በኋላ ስለ አባቱ በሕይወት እንዳለ ወይም እንደሌለ ጠየቀ ከአገልጋዮቹም አንዱ የአባቱን ሥራ በሥውር ነገረው። ቅዱስ ቴዎድሮስም ጐለመሰ እጅግም ብርቱ ሆነ ንጉሡም የሠራዊት አለቃ አድርጎ ሾመው።
የፋርስ ሰዎችንም ሊወጋቸው በወጣ ጊዜ ይህ ቅዱስ ቴዎድሮስ በረታ የፋርስ ንጉሥንም ልጅ ይዞ ማረከው ከእርሱም ጋር ምሥራቃዊው ቴዎድሮስ ነበር የፋርስንም ሠራዊት አሳደዱአቸው።
ከጥቂት ወራቶች በኋላም የፋርስና የበርበር ስዎች በሮማውያን ላይ ተነሡ። ብዙ ከተሞችንም አጠፉ ዲዮቅልጥያኖስም በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ ቴዎድሮስንም ጠርቶ ምን እናድርግ ሠራዊትህን ሁሉ የጦር መሣሪያህንም ሁሉ ይዘህ ወደ ሰልፍ ውጣ አለው።
ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ የጦር መሣሪያህን ወስደህ ለአሽከሮችህ ስጣቸው እኔ ክብር ይግባውና በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ርዳታ እተማመናለሁና የጦር መሣሪያ አልሻም እኔም ብቻዬን ወደ ጦርነቱ እሔዳለሁ ከወታደሮችም አንድ እንኳ ከእኔ ጋራ አልወስድም። በእጄ ውስጥ ያለ ይህ ጦር የተቀመጥኩበትም ፈረስ የበቃኛል ከእኔ ጋራ የሚወጣ ፈጣሪዬ እርሱ ይረዳኛልና። ንጉሡም እነሆ ጠላቶቻችን ወደእኛ ቀርበዋልና የወደድከውን አድርግ አለው።
በማግሥቱም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ሰልፍ ወጣ ንጉሡም የበርበርን ሰዎች ትወጋቸው ዘንድ ምን ኃይል አለህ እነርሱ ብዙ ወገኖች ናቸውና አለው። ቅዱሱም ለንጉሡ እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ ከሠራዊትህ ጋራ በዚህ ቁም እኔም ወደ እነርሱ ብቻዬን እሔዳለሁ በነርሱም ላይ ደሚደርሰውን ታያለህ። እኔ በእግዚአብሔር ኃይል እንደማጠፋቸው አውቃለሁና። ከእነርሱም አንዱ እንኳ ወደቤቱ አይመለስም። ንጉሡም አደነቀ ከእርሱ ጋር ያሉትም አደነቁ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደ ጦርነቱ ብቻውን ሔደ ንጉሡንም ከእርሱ ሩቅ በሆነ ቦታ ተወው። ወደ በርበር ሰዎችም ደርሶ ትዋጋላችሁን ወይስ በሰላም ወደ አገራችሁ ትመለሳላችሁ አላቸው። እነርሱም ከአንተ በቀር ለሰልፍ የመጣ አናይምና ከማን ጋር እንዋጋለን አሉት እርሱም ማንም ከእኔ ጋር እንዲመጣ አልሻም። እኔ ብቻዬን በፈጣሪዬ ኃይል አጠፋችኋለሁ አላቸው።
ምናልባት ውሻ ልታባርር መጥተህ ይሆናል ከፈቀድህ ግን ወደ አንተ ይመጣ ዘንድ ከእኛ ውስጥ አንዱን ምረጥና ሁለታችሁ ተጋጠሙ አሉት።
ያን ጊዜ ቅዱስ ቴዎድሮስ ከፈረሱ ላይ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ እንዲህ እያለ ጸለየ ጣዖታትን እስከ አጠፋቸውና የባቢሎንን ከተማ ዘንዶ እስክ ገደለው ድረስ ነቢዩ ዳንኤልን ያጸናኸው ጌታዬ አምላኬ ሆይ እንዲሁም ዛሬ ከአእኔ ጋራ ሁን በረድኤትህም አጽናኝ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ምስጋና ይገባሀል ለዘላለሙ አሜን።
ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ጦሩን አንሥቶ በላዩ በመስቀል ምልክት አማተበ በፈረሱ ላይም ተቀምጦ በበርበር ሰዎች ላይ እንዲህ እያለ ጮኸ እንዋጋ ዘንድ ወደኔ ኑ ክብር ይግባውና ለእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ባሪያው ነኝ እንዲህም እያለ በመካከላቸው ገብቶ የበርበርን ሰዎች አጠፋቸው ከእነርሱም ፈረሰኛንም ሆነ እግረኛን ምንም አላስቀረም የመኳንንቶቻቸውንም ቸብቸቦ ቆርጦ ወደ ንጉሡ አቀረበ። ንጉሡም ተቀበለው ሠራዊቱም ሁሉ ሰገዱለት። የአንጾኪያም ከተማ ሰዎች ሁሉም ወጥተው የበርበርን አገር ማረኩ።
አውኪስጦስ በሚባል አገርም ሰዎች የሚያመልኩት ታላቅ ዘንዶ ነበረ ይበላቸውም ዘንድ በየዕለቱ ሁለት ሁለት ሰዎችን ይሰጡት ነበር ሁለት ልጆችም ያሏት አንዲት ክርስቲያናዊት መበለት ነበረች ። እንዲበላቸውም ልጆችዋን ወሰደው ለዘንዶው አቀረቧቸው።
በዚያን ጊዜም ቅዱስ ቴዎድሮስ ወደዚያ አገር ደረሰ ያች መበለትም በፊቱ ቆመች ልጆቿን ወስደው እንዲበላቸው ለዘንዶው እንዳቀረቧቸው በእርሷ ላይ የሆነውን ሁሉ አልቅሳ ነገረችው።
ክርስቲያን እንደሆነችም ባወቀ ጊዜ በልቡ ይችን ሴት በድለዋታል እግዚአብሔርም ይበቀልላታል አለ። ወዲያውኑም ከፈረሱ ወረደና ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ጸለየ። ከዚህም በኋላ ወደ ዘንዶው ቀረበ የከተማው ሰዎችም ሁሉ ወደርሱ ይመለከቱ ነበር። በጦሩም ወግቶ ያንን ዘንዶ ገደለው። ርዝመቱም ሃያ አራት ክንድ ሆነ የመበለቷንም ልጆች አዳናቸው።
ከዚህም በኋላ አባቱን ይፈልገው ዘንድ ወደ ላይኛው ግብጽ ሔደ አባቱንም አገኘው አባቱም ልጁ እንደሆነ በምልክቶቹ አወቀው ቅዱሱም አባቱ እስከ አረፈ ድረስ በዚያ ኖረ።
ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ከተማ ተመለሰ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስንም ክብር ይግባውና ክርስቶስን እንደካደና ጣዖትን እንደአመለከ ክርስቲያኖችንም ሲአሠቃያቸው አገኘው።
ከዚህም አስቀድሞ የከተማው ሰዎች የሚያመልኩትን ዘንዶ እርሱ እንደ ገደለው የአውኪስጦስ አገር ሰዎች ወደ ንጉሥ ከሰውት ነበርና ስለዚህ ንጉሥ ልኮ አስቀረበው።
ቅዱስ ቴዎድሮስም ወደ ንጉሡ በቀረበ ጊዜ ንጉሡን እንዲህ ብሎ ዘለፈው አንተ የክፉ ሥራ ሁሉ መገኛ የሆንክ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የክብር ባለቤትን ትተህ የረከሱ ጣዖታትን ያመለክ የኃጢአት ልጅ ሆይ ወዮልህ እግዚአብሔርም ፈጥኖ መንግሥትህን ያጠፋታል።
በዚያን ጊዜም ንጉሡ ተቆጥቶ ከመሬት ላይ ጥለው ይገርፉት ዘንድ ወታደሮችን አዘዛቸው። ይህንንም አደረጉበት ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ። እጆቹንና እግሮቹንም ከግንድ ጋር ቸነከሩት።
በሥቃይም ውስጥ ሳለ ከእግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ ወረደ እንዲህም አለው ጽና እነሆ የገድልህ ፍጻሜ ቀርቦአል ሥጋህ በውስጡ በሚኖርበትም ቦታ ድንቆችና ተአምራቶች ይገለጣሉ እነሆ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠህ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ፣ ወይም በስምህ የተራበ ለሚያጠግብ፣ የተጠማውን ለሚያጠጣ፣ ወይም ለቤተክርስቲያንህ መባን መጻሕፍትንም ለሚሰጥ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስስለታለሁ። ገድልህንም የሚጽፈውን፣ ወይም የሚያነበውን፣ የሚሰማውን፣ ወይም የሚገዛውን እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ።
ከዚህም በኋላ ብዙዎች ከንጉሥ ሠራዊትና ከሕዝቡ ተሰብስበው በንጉሡ ላይ እንዲህ ብለው ጮኹበት አንተ ከሀዲ እግዚአብሔር ያጥፋህ ከጠላቶቻችን ያዳነንን ኃያልና ጽኑዕ የሆነውን የከበረ ቴዎድሮስን ታሠቃየዋለህና ይህንንም ብለው በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ያን ጊዜም ንጉሥ ተቆጥቶ ሁሉንም አስገደላቸው ሰማዕትም ሆኑ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ ንጉሡ አዘዘ የብረት ዐልጋም አምጥተው ቅዱሱን በላዩ አስተኙት ከበታቹም እሳትን አነደዱ ቅዱስ ቴዎድሮስም እንዲህ ብሎ ጸለየ አቤቱ ፈጣሪዬ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ምድጃ እንደ አዳንካቸው አድነኝ። ወዲያውኑም ያ እሳት ጠፋ እንደ ንጋት ጊዜ ቊርም ሆነ።
ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ክብር ይግባውና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የተሰጠህ ሆይ ጽና በርታ ያን ጊዜም ቅዱሱ ተነሥቶ በንጉሡ ፊት ቆመ እንዲህም አለው ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አድኖኛልና አንተ ከሀዲ እፈር አለው። የንጉሡም የጭፍራ አለቃ ይህን በአየ ጊዜ ክቡር ቴዎድሮስ ከሚያመልከው ክብር ይግባውና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብሎ ጮኸ ርሱንም ራሱን አስቆረጠውና በሰማዕትነት ሞተ።
ቅዱስ ቴዎድሮስንም ብዙ ከአሠቃየውና ማሠቃየቱ ከሰለቸው በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ ሥጋውንም እንዲአቃጥሉ አዘዘ። በጌታችንም ፈቃድ ከእናቱ ደጅ ወስደው እራሱን ቆረጡ ከእርሱም ደም፣ ወተትም ፈሰሰ ታላቅ እሳትም አንድደው ሥጋውን በውስጡ ጨመሩ እሳቱም ከቶ አልነካውም። እናቱም ለወታደሮች ብዙ ወርቅ ሰጥታ ሥጋውን ወሰደች በአማሩ ልብሶችም ገነዘችው እስከ መከራው ፍጻሜም በቤቷ ውስጥ አኖረችው።
በዚህችም ቀን የሠራዊት አለቃ ቴዎድሮስ ሥጋውን ከሀገረ ሰጥብ ወደ ሀገረ አስዩጥ ሥጋው አፍልሰውታል።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages