ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 4 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, November 16, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 4

 ኅዳር 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ቶማስ ዘደማስቆ
2.ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስ
3.ቅዱሳን አቢማኮስ ወአዛርያኖስ
4.አባ አበጊዶ ዘትግራይ
5.ታላቁ አባ ዘካርያስ
6.ጉባኤ ቅዱሳን ሰማዕታት
ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
በዚህችም ቀን የደማስቆው ቅዱስ_ቶማስ አረፈ፣ ቅዱስ_ያዕቆብና_ዮሐንስ በሰማዕትነት አረፉ፣ ቅዱሳን_አቢማኮስና_አዛርያኖስ በሰማዕትነት አረፉ፣ የአባ ዮሐኒ ደቀ መዝሙር የሆኑት አቡነ_አበይዶ ዕረፍታቸው ነው፡፡


ኅዳር አራት በዚህችም ቀን የደማስቆ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ ቶማስ በግብጽና በሶርያ እስላ*ሞች በነገሡ ጊዜ በሰማዕትነት አረፈ።
ቅዱስ ቶማስ በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ተወልዶ ያደገ ሶርያዊ ክርስቲያን ነው። ከልጅነቱ እንደሚገባ መጻሕፍትን ተምሮ ለዲቁና፣ ለቅስና፣ ከዚያም ለዽዽስና በቅቷል። በወቅቱ የሶርያ ዋና ከተማ በሆነችው ደማስቆ ላይ ተሹሞ ያገለግልም ነበር።
ታዲያ ዘመኑ በየቦታው ደም የሚፈስበት ነበርና የክርስቶስን መንጋ መጠበቁ ቀላልና የዋዛ ሥራ አልነበረም። በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ያፈሱ የነበሩት ደግሞ ተንባላት (የመሐ*መድ ተከታዮች) ናቸው። 7ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሲደርስም ተንባላት ግብጽንና ሶርያን በቁጥጥር ሥር በማድረጋቸው ክርስቲያኖች ተቸገሩ።
በወቅቱም ቅዱስ ቶማስ ሲያስተምር የሰማው አንድ መሐ*መዳዊ "እንከራከር" አለው። ቅዱሱም ሊቅ ነበርና ስለ መሐ*መድ ሐሰ**ተኛነት ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ካስረዳው በኋላ ንጹሕና ሰማያዊ ሕግ ቅዱስ ወንጌል እንጂ ቁር**ዓን እንዳልሆነ ነገረው።
በአደባባይ በመረታቱ ያፈረው መሐመ*ዳዊም በብሽቀት ሒዶ ለደማስቆው ገዢ ከሰሰው። ቅዱስ ቶማስም ተይዞ ቀረበ። "እንዴት እምነታችን እስል*ምናን ትሳደ**ባለህ?" ቢለው ቅዱሱ "እውነቱን ተናገርኩ እንጂ አልተሳደብኩም" ሲል መለሰለት።
መኮንኑም "እሺ! ክርስቶስ ማን ነው? ስለ ወንጌልና ቁርዓ**ንስ ምን ትላለህ?" ሲል የተሳለ ሰይፍ አውጥቶ ጠየቀው። የቀናችው እመነት ክርስትና ክብርነቷ በሰማይ ነውና መጨከንን ትጠይቃለች።
ቅዱስ ቶማስ ምንም ሳይፈራ "ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማይና የምድር ፈጣሪና አምላክ ነው።
ቅዱስ ወንጌል ሰማያዊና የሕይወት ሕግ ሲሆን ቁር**ዓን ደግሞ የመሐ**መድ የፈጠራ መጽሐፍ ነው።" ይህንን የሰማው መኮንን በቁጣ አንገቱን እንዲመቱት አዘዘ። ቅዱስ ቶማስም በዚህች ቀን ስለ ቀናች ሃይማኖቱ አንገቱን ሰጠ።

በዚህችም ቀን ያዕቆብና የሀገረ ፋርስ ኤጲስቆጶስ ዮሐንስ የሐርመዝ ልጅ በሆነ በፋርስ ንጉሥ በሳቦር እጅ በሰማዕትነት አረፉ።
አሁን ደግሞ ወደ 4ኛው መቶ ክ/ዘመን ተመልሰን ወደ ምድረ ፋርስ (ኢራን) ወርደን ቅዱሳንን እናዘክር። እነዚህ ቅዱሳንም በሃገረ ፋርስ (ኢራን) በመንግስተ ሳቦር ዘመን የነበሩ አበው ናቸው። ሳቦር ማለት ጸሐይንና እሳትን የሚያመልክና እጅግ ጨካኝ የነበረ ንጉሥ ነው።
ቅዱሳኑ ያዕቆብና ዮሐንስ የሐዋርያትን ስም ብቻ ሳይሆን ግብራቸውን ቅድስናቸውንም የያዙ ነበሩ። ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት ባይሆንም ፋርስ ግን በዚህ ዘመንም ለክርስቲያኖች የግፍ ከተማ ነበረች።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ ከቅዱስ መርምሕናም እስከ ቅዱስ ኮቶሎስ ሰማዕትነትን የተቀበሉት በዚህችው ሃገር ውስጥ ነው። ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስም ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በልኩ ተምረው መጻሕፍትንም ተረድተው ለክህነት ተመርጠዋል።
በኋላም ቤተ ክርስትያን "ይገባቹሃል" ስትል ዻዻሳት አድርጋ ሾመቻቸው:: እነርሱም አላሳፈሯትም። የክርስቶስን መንጋ እያስተማሩ እየናዘዙ ጠበቁላት። ንጉሡ ሳቦር ግን ሕዝቡን ለፀለሐይና ለእሳት ሊያሰግድ ላደረገው ጥረት እንቅፋት ሁነውበታልና ጠላቸው።
በወታደሮቹ አስይዞም በፍርድ አደባባይ አቆማቸው። ሕዝቡን በአዋጅ ጠርቶ። አስፈሪ እሳት አስነድዶ "ሕዝቡ ለፀሐይ እንዲሰግድ እዘዙ" ቢላቸው "እንቢ" አሉት።
ከነ ልብሳቸው አንስተው ወደ እሳቱ ወረወሯቸው። ቅዱሳኑም በመከራው (በነደደው እሳት) መካከል ሆነው ለሕዝቡ ተናገሩ።
"አምላክ አንድ እግዚአብሔር ነውና እንዲህ በሃይማኖታችሁ ጽኑ" አሏቸው። እሳቱም አቃጥሎ ገድሏቸው የክብርን አክሊል ተቀዳጁ።

በዚህች ቀን ከሮሜ አገር ቅዱሳን አቢማኮስና አዛርያኖስ በሰማዕትነት አረፉ።
አሁን ደግሞ ወደ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ወደ ዋናው ዘመነ ሰማዕታት እንመለስ። በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩ ቅዱሳን ሰማዕታት 2ቱ አቢማኮስና አዛርያኖስ ናቸው። አውሬዎቹ መክስምያኖስና ዲዮቅልጥያኖስ ዓለምን ለ2 ተካፍለው በክርስቲያኖች ላይ ግፍን ሲሰሩ 2ቱ ቅዱሳን በሮም ግዛት ሥር ይኖሩ ነበር።
በዘመኑ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ማነጸ መዘመር እምነትን መግለጥ ይቅርና ሲያማትቡ መታየት እንኩዋ ያስገድል ነበር። ነገሥታቱ የሾሟቸው ተከታዮቻቸው ክርስቲያኖችን ከዋሉበት አላሳድር ካደሩበትም አላውል አሉ።
ታላቅ ግፍ ሰቆቃና ጭንቅ በሆነበት በዚያ ወራት የሞተው ሙቶ እኩሉ ሲሰደድ አቢማኮስና አዛርያኖስ ግን በከተማ መሐል ተረጋግተው ክርስቶስን ያመልኩ ነበር። ይህም ተደርሶባቸው ተከሰሱና ተይዘው ቀረቡ።
መኮንኑ 2ቱን ክርስቲያን ወጣቶች ሲመለከታቸው ምንም የፍርሃት ምልክት አልተመለከተባቸውምና ተገረመ። "ማንን ታመልካላችሁ?" አላቸው። እነርሱም "የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን!" ሲሉ መለሱለት።
"ክርስቶስን ትክዳላችሁ ወይስ ትሞታላችሁ?" ቢላቸው "ሰነፍ!" ሲሉ በአደባባይ ገሰጹት። "የፈጠረ፣ ያከበረ፣ ሥጋውን ደሙን የሰጠ ጌታ እንዴት ይካዳል?!" ሲሉም እቅጩን ነገሩት። በድፍረታቸው የደነገጠው መኮንኑም በዚያች ሰዓት ሞትን አዘዘባቸው። በዚህች ቀንም አንገታቸውን ተሰይፈው ለክብረ ሰማዕት በቅተዋል።

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአባ ዮሐኒ ደቀ መዝሙር የሆኑት የኢትዮጵያዊው አቡነ አበይዶ ዕረፍታቸው ነው፡፡ የታላቁ አባት የአባ ዮሐኒ ደቀ መዝሙር ናቸው፡፡ አባ ዮሐኒ ዕረፍታቸው ኅዳር 5 ስለሆነና የአቡነ አበይዶም ታሪክ ከአባ ዮሐኒ ጋር የተገናኘ ስለሆነ በዚሁ ዕለት አንድ ላይ እናየዋለን፡፡ ኅዳር 4 ቀን ግን የአቡነ አበይዶ ዕረፍታቸው መሆኑን ብቻ ጠቅሰን እናልፋለን፡፡ ስንክሳሩም ስማቸውን ብቻ ጠቅሶት ያልፋል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages