ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 3 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, November 16, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 3

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ሦስት በዚህች ቀን አቡነ መድኃኒነ እግዚእ አረፉ።
ከደጋግ ክርስቲያኖች ከቀሲስ ሰንበት ተስፋነ እና ከኅሪተ ማርያም በ1180 ዓ.ም በሥዕለት የተወለዱት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅግ አስደናቂ ገድልና ትሩፋት ያላቸው ጻድቅ ቢሆኑም ብዙው ሕዝበ ክርስቲያን እንደሚገባቸው መጠን ያላወቃቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መዘንጋታቸው እጅግ ከሚያስቆጩን አባቶች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የደብረ በንኮሉ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፡፡ እስቲ ቀጥሎ ስማቸውን የጠቀስኳቸውን እነዚህን ቅዱሳን አባቶች ታሪካቸውንና የጽድቅ ሕይወታቸውን አስታውሱት፡- እነርሱም አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘቆየፃ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልታርዋ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤ እና አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቄ እነዚህን የመላእክትን ሕይወት በምድር የኖሩ ታላላቅ የሀገራችንን ቅዱሳን አስተምረውና አመንኩሰው ለጽድቅ ያበቋቸው አባት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፡፡
አቡነ መድኃኒነ እግዚእ እነዚህን ሰባቱን ቅዱሳን በአንድ ጊዜ ሲያመነኩሷቸው በዚያው ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን ደብረ በንኮልን በብርሃን አጥለቅልቆት ታይቷል፡፡ ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰምቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ላይ የመነኮሱት እነዚህ ሰባቱ ቅዱሳን ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ እነዚህም ሰባቱ ከዋክብት የጣናን ባሕር በእግራቸው ጠቅጥቀው ተሻግረው ብዙዎቹን ደሴቱ ላይ ያሉ አስደናቂ የጣና ገዳማትን የመሠረቱት ናቸው፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይን እንደጀልባ ተጠቅመው በእርሱ ላይ ሆነው ወደ ደሴት የገቡ አሉ፡፡ በእግራቸውም እየረገጡ ባሕሩን የተሻገሩ አሉ፡፡ በሌላም ቦታ በየብስ የተሰማሩትም ቢሆኑ መጻሕፍቶቻቸውን በአንበሳ ጭነው የተጓዙ አሉ፡፡ በደብረ ሊባኖሱ ሐዲስ ሐዋርያ የኢትዮጵያ ብርሃኗ በሆኑት በአቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ ከመነኮሱ በኋላ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም በተራቸው ያስተማሯቸውና ያመነኮሷቸው መነኮሳት ቁጥራቸው በውል አይታወቅም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ለአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ‹‹ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት ቅዱሳንን›› በመንፈስ ቅዱስ እንደሚወልዱ ትንቢት ተናግረውላቸው ነበር፡፡ የተንቤኑን አቡነ ዐቢየ እግዚእን፣ የዞዝ አምባውን አቡነ አብሳዲን ጨምሮ አባታችን መድኃኒነ እግዚእ ብርሃን ሆነው በጣም ብዙ ቅዱሳንን የለኮሱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን›› ይባላሉ፡፡
የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ልጆች ዛሬ ግሸን ላይ በክብር ተቀምጦ ሀገራችንን ከመዓት እየጠበቀ ያለውን የጌታችንን ቅዱስ መስቀል ያመጡትም እነርሱ ናቸው፡፡ ዐፄ ዳዊት በዘመናቸው ረኃብ ስለነተሳ የደብረ ቢዘኑን አቡነ ፊሊጶስን ከገዳማቸው አስጠርተው ‹‹ምን ባደርግ ይሻለኛል?›› ብለው አማከሯቸው፡፡ አቡነ ፊሊጶስም ‹‹የጌታችንን መስቀል ያስመጡ›› ብለው መከሯቸው፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም ከኢየሩሳሌም፣ ከቍስጥንጥንያና ከእስክንድርያ መንግሥታት ጋር ተጻጽፈው ዓሥሩን ታላላቅ ቅዱሳን መርጠው ይዘው ሄደው መስቀሉን መስከረም 10 ቀን አምጥተውታል፡፡ በጽድቅ ሥራቸውና ተአምራትን በማድረግ በወቅቱ ታዋቂ የነበሩትና ቅዱስ መስቀሉን ያመጡት ዐሥሩ ቅዱሳንም የደብረ ቢዘኑ አቡነ ፊሊጶስ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ ኂሩተ አምላክ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ እንድርያስ፣ አቡነ በትረ ማርያም፣ አቡነ ዮሐንስ፣ አቡነ ታዴዎስ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አቡነ ዘካርያስ፣ አቡነ ያሳይና አቡነ ቶማስ ናቸው፡፡
የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ተአምራታቸው እጅግ ብዙ ነው፡፡ አራዊት ሁሉ እንደሰው ያገለግሏቸው የነበር፡፡ ውኃ የሚያመላልስላቸውንና የሚያገለግላቸውን አህያ አንበሳ ቢበላባቸው በአህያው ምትክ አንበሳውን ድፍን 7 ዓመት ለገዳማቸው ውኃ አስቀድተውታል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ለአባታችን ውኃ የሚያመላልስላቸውና የሚያገለግላቸው አንድ አህያ ነበራቸው፡፡ ውኃው የሚገኘው እርሳቸው ካሉበት በጣም እርቆ በእግር የ3 ሰዓት መንገድ ከተሄደ በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን አህያቸው እንደ ሰው እየተላላካቸው ይቀዳላቸው ነበር፡፡ አንድ ግን ከመንገድ አንበሳ አግኝቶት ግማሽ አካሉን በልቶት ሄደ፡፡ አባታችንም የአህያቸውን ተረፈ በድን አግኝተው በማዘን ‹‹ውኃ የሚያመላልስልኝ ረዳቴ ይህ አህያ ብቻ ነበር፣ አሁንም አህያዬን የበላህ አውሬ እንድታነጋግረኝ እፈልጋለሁ›› ቢሉ በአንበሳ ተበልቶ የሞተው የአህያው ግማሽ አካል አፍ አውጥቶ አንድ አንበሳ እንደበላው ነገራቸው፡፡ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም በዚህ እጅግ ደስ ተሰኝተው ፈጣሪያቸውን ካመሰገኑ በኋላ አህያቸውን የበላውን አንበሳ ከጫካው ውስጥ ጮኸው ጠሩት፡፡ አንበሳውም ከሌሎቹ አንበሳ ተለይቶ ወደ እርሳቸው በመምጣት እግራቸው ሥር ወድቆ ሰገደ፡፡ አባታችንም ‹‹አህያዬን የበላኸው አንተ ነህን?›› ብለው ሲጠይቁት አንበሳውም በሰው አንደበት ‹‹አዎ እኔ ነኝ›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ፈጣሪያቸውን በድጋሚ ካመሰገኑ በኋላ አንበሳውን ‹‹በል ና ተከተለኝ በአህያዬ ምትክ ታገለግለኛለህ›› አሉት፡፡ አንበሳውም ተከትሏቸው ወደ በዓታቸው በመግባት ለ7 ዓመታት እንደ አህያቸው ውኃ እየቀዳ አገልግሏቸዋል፡፡ የአንበሳው ቆዳ ዛሬም በገዳማቸው ደብረ በንኮል በክብር ተቀምጠቷል፡፡
አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባንም አመንኩሰው መርቀው ሲሸኟቸው እንዲያገለግሏቸው አንበሶችን ከጫካ ጠርተው ያዘዙላቸው አባታቸው አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፡፡ የዋልድባው አቡነ ሳሙኤል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ከመነኮሱ በኋላ በደብረ በንኮል 12 ዓመት አባታችንን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ እሳት እስከማያቃጥላቸው ድረስ ከብቃት ደረጃ ላይ ሲደርሱ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ መርቀው በማሰናበት በዓት እንዲያጸኑ ሲያደርጓቸው አቡነ ሳሙኤል በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ጣና ደሴት ገብተው ሱባኤ ያዙ፡፡ በዚያም ሳሉ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ማረፋቸውን በመንፈስ ዐውቀው ሲያለቅሱ ጌታችን የአቡነ መድኃኒነ እግዚእን ነፍስ በእቅፉ አድርጎ ወደ ገነት ሲያሳርጋት አሳያቸው፡፡ ወዲያውም ጌታችን በብርሃን ሰረገላ አድርጎ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባን ደብረ በንኮል አድርሷቸዋል፡፡ በዚያም እስከ 40ኛው ቀን ከቆዩ በኋላ በዚሁ ዕለት ሲቀድሱ ክንድ ከስንዝር ከመሬት ከፍ ብለው ቅዱሳን ሐዋርያት እየተራዱዋቸው ከቀደሱ በኋላ ወደነበሩበት መልሷቸዋል፡፡ የጻዲቁ የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዕረፍታቸው ኅዳር 3 ቀን 1360 ዓ.ም ሲሆን ጠቅላላ ዕድሙያቸውም 180 ዓመት ነው፡፡
ዐፄ ፋሲል ጻድቁ የተከሏቸውን የጥድ ዛፎች በሙሉ ተቆርጠው የአክሱም ቤ/ክ እንዲሠራበት አዋጅ አወጁና መልእክተኞች መጥተው ዛፎቹን ሲቆርጡ መነኮሳቱ ግን ‹‹ጻድቁ አባታችን የተከሏቸው የጥድ ዛፎች መቆረጥ የለባቸውም›› ብለው ቢከራከሩም ሰሚ አላገኙም፡፡ መነኮሳቱም ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ጩኸታቸው ተሰምቶላቸው ወዲያው እየተቆረጡ ያሉት የጥድ ዛፎች በሙሉ በተአምራት ወደ ወይራ ዛፍነት ተለወጡ፡፡ የወይራ ዛፎቹም ለዐፀድ እንጂ ለሕንፃ የማይመቹ ጎባጣ ሆኑ፡፡ የዚህም ምልክቱ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ግንዱ ጥድ ዛፉ ግን ወይራ የሆነ ትልቅ ዛፍ ‹‹ወይራ ዘገብረ ተአምር›› በሚባል ቦታ አሁንም ድረስ ቆሞ ይታያል፡፡
ጻድቁ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ በ1312 ዓ.ም የመሠረቱት ገዳማቸው ደብረ በንኮል ከአክሱም በእግር ሦስት ሰዓት ያስኬዳል፡፡ ይኸውም በንግሥተ ሳባ ቤተ መንግሥት አድርጎ የቀዳማዊ ሚኒሊክን መቃነ መቃብር አልፎ በመሄድ ነው፡፡ ወይም በመኪና ለመጓዝ አክሱም ጉበዱራን አቋርጦ ውቅሮ ማራይ ከተማን አልፎ በስተ ሰሜን አቅጣጫ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በስተ ምዕራብ የአቡነ አላኒቆስ ዘማይበራዝዮን ገዳም፣ በስተ ምሥራቅ የአቡነ ሰላማን ገዳም እየተለመከቱ እንደተጓዙ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነውን ደብረ በንኮልን ያገኙታል፡፡ ኅዳር 20 ጻድቁ ስለሚነግሱ ገዳሙም ለአክሱም ቅርብ ስለሆነ ይህ ለአክሱም ጽዮን ተጓዦች ተጨማሪ ትልቅ በረከት ነው፡፡
ደብረ በንኮል ማለት ‹‹ሙራደ ቃል›› ማለት ነው፡፡ ትርጉሙም የምሥጢር መውረጃ ማለት ነው፡፡ በቦታው ላይ ሱባኤ ለያዘ ሰው እንደ ቅዱስ ያሬድና እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ምሥጢር እንደሚገለጥለት የሚጠቁም ነው፡፡ በ14ኛው መ/ክ/ዘ የነበሩት ደጋግ መነኮሳት ሕይወታቸውን በሙሉ በምንኩስና፣ በጸሎትና በታላቅ ተጋድሎ መኖር ሲፈልጉ ከደብረ ዳሞ፣ ከሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ከደብረ ሊባኖስና ከሌሎቹም የሀገራችን ክፍሎች እየተነሡ ወደ ደብረ በንኮል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ነበር የሚሄዱት፡፡
የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ቃልኪዳን፡- ጻድቁ ባርከው ያፈለቁት ጸበላቸው ላበደ ሰው መድኃኒት ነው፡፡ ከመቃብራቸው ላይ የሚነሣውን አፈር ጻድቁ ባርከው ባፈለቁት ጸበላቸው ታሽቶ በእጃቸው መስቀል ተባርኮና ታሽቶ የሚዘጋቸውን የአቡነ መድኃኒነ እግዚእን እምነታቸውን በእምነት ሆኖ የያዘን ሰው ንብረቱን ሌባ ቀማኛ ዘራፊ አይሰርቀውም፤ የመኪና አደጋ አይደርስበትም፤ ጥይት አይመታውም፡፡ ‹‹በእምነት ሆኖ የያዘን ሰው›› መባሉን ልብ ይሏል፡፡ ይኸውም ለጻድቁ የተሰጣቸው ታላቅ ቃልኪዳን ነው፡፡

ዳግመኛም በዚህች ቀን አቡነ ፍሬ ካህን አረፉ።
ጻድቁን በመጀመሪያ ከጎጃም ተነሥተው በታዘዘ መልአክ መሪነት ትግራይ ደብረ በንኮል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ሄደው መንነው መነኮሱ፡፡ ጻድቁ ስድስት ክንፍ የተሰጣቸው ሲሆኑ በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ ይታወቃሉ፡፡ አቡነ ፍሬ ካህን ወንጌልን ሲሰብኩ ሙታንን እያስነሡ በሲኦል ውስጥ ስላለው መከራና ሥቃይ እንዲመሰክሩ ያደርጓቸው ነበር፡፡ ጻድቁ ሐይዳ ገዳም ታቦት ተቀርጾላቸው ገድል የተጻፈላቸው ቢሆንም ሙሉ ገድላቸው ታትሞ ለምእመኑ አልተዳረሰም፡፡ አቡነ ቶማስ ካረፉ በኋላ አቡነ ፍሬ ካህን ገዳማቸውን ተረክበው በጽድቅ መንገድ መነኮሳቱን አስተዳድረዋል፡፡
አቡነ ፍሬ ካህን አፈር ከኢየሩሳሌም አምጥተው ዋልድባ ሲደርሱ መነኮሳቱ "ገዳሙን በአህያ አታስረግጥ" ቢሏቸው አህዮቹን ክንፍ አውጥተው እንዲበሩ አድርገዋቸዋል፡፡
አባታችን ሽሬ ደብረ ሐይዳ አቡነ ፍሬ ካህን የተባለ ትልቅ ገዳም አላቸው፡፡ ገዳሙ ከአቡነ ቶማስ ዘሐይዳ ገዳም ጋር አንድ ነው፡፡ ወደዚህ ገዳም ውስጥ ሥጋና ቅቤ ተበልቶም ሆነ ተይዞ መውጣት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ አልታየሁም ተብሎ በድብቅ ሥጋ ተይዞ ቢገባ ሥጋው ይተላል፡፡ ሥጋና ቅቤ የበላ ሰውም ዕለቱን በድፍረት ወደ ገዳሙ ቢገባ ሆዱ በኃይል ይነፋል በዚህም ይታወቅበታል፡፡ ከብቶችም ቢሆኑ ወደ ገዳሙ አይወጡም፣ ማንም ሳይመልሳቸው ራሳቸው ይመለሳሉ፡፡ የአቡነ ፍሬ ካህን ዕረፍታቸው ኅዳር 3 ነው፡፡

በዚህች ቀን ከቆሮንቶስ አገር ቅዱስ አባት ኪርያቆስ አረፈ።
የዚህም አባት ወላጆቹ ሃይማኖታቸው የቀና የከበሩ ናቸው የቤተክርስቲያንን ትምህርትና የቀናች ሃይማኖትን አስተማሩት ከዚህም በኋላ የቆሮንቶስ አገር ኤጲስቆጶስ ወደ ሆነ ወደ አባ ጴጥሮስ አቀረቡት እርሱም በላዩ ጸልዮ አናጒንስጢስነት ሾመው ለአባ ጴጥሮስም የወንድሙ ልጅ ነው።
ከዚህም በኋላ ዘወትር መጻሕፍትን የሚያነብ የቃላቸውንም ትርጓሜ የሚመረምር የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓቷንና ሕጓን የሚያጸና ሆነ በትምህርቱና በእውቀቱም ከብዙዎች ከፍ ከፍ አለ ኤጲስቆጶሱም መጻሕፍት ማንበብን እንዳያቋርጥ ያዝዘው ነበር እርሱም ለሕዝቡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለኤጲስቆጶሱም በቤቱ ያነብለት ነበር። መጻሕፍትንም በሚያነብለት ጊዜ ኤጲስቆጶሱ በእርሱ ደስ ይለው ነበርና።
ዕድሜውም ዐሥራ ስምንት ዓመት በሆነ ጊዜ ሚስትን ያጩለት ዘንድ ወላጆቹ ጠየቁት እርሱ ግን ይህን አልወደደም ግን ከገዳማት ወዳንዱ ይሔድ ዘንድ እንዲአሰናብቱት ወላጆቹን ለመናቸው ከዚያም በኋላ አዘውትሮ ወደ ገዳማት የሚሄድና ወደ ወላጆቹ የሚመለስ ሆነ። መመላለሱም ከበዛ ዘንድ የከበረች የምንኲስናን ልብስ ሊለብስ ወዶ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ ከኢየሩሳሌሙ ኤጲስቆጶስ ከአባ ቄርሎስ ጋር ተገናኝቶ ስለ ምንኲስና ኀሳቡን ሁሉ ነገረው። እርሱም በጎ ሥራን ወደሃል አለው ታላቅ አባትም እንደሚሆንና በእርሱም የብዙዎች ነፍሳት ብሩሃን እንደሚሆኑ ትንቢት ተናገረለት።
ከዚህም በኋላ የመነኰሳት አባት ወደ ሆነ በፍልስጥዔም ወደ ሚኖር ወደ ክቡር አባ ሮማኖስ ላከው እርሱም በደስታ ተቀብሎ የምንኵስናን ልብስ አለበሰው። የምንኵስናንም ሥርዓት ያስተምረው ዘንድ የሰይጣንንም ተንኮል ያስረዳው ዘንድ በዚያው ገዳም ለሚኖር አንድ አረጋዊ ሰጠው። ከዚህም በኋላ በጾም በጸሎት በስግደት በመትጋት በታላቅ ድካም በቀንና በሌሊት በገድል ተጸምዶ በትዕግሥት በትሕትና በቅንነት ኖረ።
እግዚአብሔርም የመፈወስን ሀብት ሰጥቶት ወደርሱ የሚመጡትን በሽተኞች ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ የትሩፋቱና የቅድስናውም ዜና በሁሉ ቦታ ተሰማ ። የኢየሩሳሌሙ ኤጲስቆጶስ አባ ቄርሎስም የክብር ባለቤት የሆነ መንፈስ ቅዱስን ስለ አቃለለ መቅዶንዮስ መቶ ሃምሳው ኤጲስቆጶሳት አንድነት ወደሚሰበሰቡበት ወደ ቊስጥንጥንያ በሚሔድ ጊዜ ይህን አባት ኪርያቆስን አባ ቄርሎስ ከእርሱ ጋር ወሰደው በላያቸው በአደረ መንፈስ ቅዱስ ስም ተከራክረው ከሀዲ መቅዶንዮስን ረቱት ከምእመናንም ለይተው አሳደዱት።
ከዚህም በኋላ በመልካም ሽምግልና እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ። ከዕረፍቱም በኋላ እግዚአብሔር ድንቆች የሆኑ ብዙ ተአምራትን ከሥጋው ገለጠ ከእርሳቸውም አንዱ ከኢየሩሳሌም ገዳማት በአንዱ ሥጋው ይኖራል። ከአረፈበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሥጋው አልተለወጠም ወደ ኢየሩሳሌም የሚሔዱ ሁሉ ያዩታል እነርሱም በቅርብ ጊዜ እንዳረፈ ያስባሉ እርሱ ግን ያረፈው ለአኖሬዎስና ለአርቃዴዎስ አባታቸው በሆነ በታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን ነው።

በዚችም ቀን አባ አትናቴዎስና እኅቱ ኢራኢ አረፉ። እሊህንም ቅዱሳን ከሀዲ ንጉሥ መክስምያኖስ ጽኑዕ የሆነ ሥቃይን አሠቃያቸው።
በማሠቃየትም በደከመ ጊዜ ዕራቁታቸውን ከጉድጓድ ጨመራቸው በላያቸውም የጒድጓዱን አፍ ዘጋ በውስጧም ነፍሳቸውን አሳለፉ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ።

በዚችም ቀን ለኢትዮጵያ ነገሥታት ለዘርዐ ያዕቆብ፣ ለበእደ ማርያም፣ ለእስክንድር የሠራዊት አለቃ የሆነ ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል አረፈ።
የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ገላውዴዎስ የእናቱም ስም ኤልሳቤጥ ነው እነርሱም በዚህ ዓለም ገንዘብ ይልቁንም በሃይማኖትና በበጎ ሥራ የበለጸጉ ናቸው። ይህንንም ቅዱስ በቅዱሳን አርባዕቱ እንስሳ በዓል ወለዱት ስሙንም ዓምደ ሚካኤል ብለው ሰየሙት።
ከተወለደም አንድ ዓመት ሲሆነው ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከመንበሩ ከርሠ ሐመር ውስጥ ማንም ያየው ሳይኖር እየዳኸ ገብቶ ሦስት ቀን ሰነበተ ወላጆቹም እርሱ እንደሞተ ተጠራጥረው እያለቀሱለት ኖሩ።
ከዚህም በኋላ በሦስተኛው ቀን ቄሱ ሊዓጥን ገባ ዕጣንንም ሲፈልግ በከርሠ ሐመሩ ውስጥ ሕፃኑን በሕይወት አገኘው በበታቹም ምንም ምን ጉድፈት አልነበረም። ቄሱም ለወላጆቹ ነገራቸው እነርሱም እጅግ ደስ እያላቸው መጥተው ከዚያ ወሰዱት።
ከዚያንም ጊዜ ጀምሮ በጥበብና በዕውቀት አደገ ነገሥታት ገዥ እስከ አደረጉት ድረስ በቤት ውስጥ በሚሠራው ላይ ሁሉ አሠለጠኑት። እርሱም ለድኆች በፍርዱና በምጽዋቱ አባት ሆናቸው በገንዘቡም አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ አደሰ በዘመኑም ሰላም ሆነ በጾሙና በጸሎቱ በምጽዋቱም በቅዱሳንም የጸሎት ርዳታ በወዲያም በወዲህም አገሮችን የሚያጠፉ ጠላቶችንና ዐመፀኞች ጠፉ። ጠላቶችም ሁሉ ለነገሥታቱ ተገዙና ግብርን ገበሩ።
የዚህም ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ልቡ በእግዚአብሔር ፍቅር የታሠረ ነው በተጸለየበት ውኃ ሳይጠመቅና ሳይጠጣ አይመገብም ነበር ገንዘቡንም ሁሉ በምጽዋት ጨረሰ።
እግዚአብሔርም በጎ ሥራውን በአየ ጊዜ እንዲፈተን ፈቀደለት ዐመፀኞች ሰዎችም በእርሱ ላይ ተነሡ እንዲገድለውም በንጉሥ ዘንድ በሐሰት ነገር ወነጀሉት ንጉሡ ግን እጅግ ስለሚወደው ራራለት በነገራቸውም በዘበዘቡትና በአስጨነቁትም ጊዜ ከጭንቀት የተነሣ ወደ ሩቅ አገር አሥሮ አጋዘው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም የሚራዳው ሆነ ሰማያዊ ኅብስት የወይን ጽዋ እያመጣለት ይመግበዋል።
ቅዱስ ቁርባንንም መቀበል በሚሻ ጊዜ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን አምጥቶ ይመግበዋል። ከዚህም በኋላ እሊያ ነገረ ሠሪዎች ይገድሉት ዘንድ ንጉሥ እንዲፈቅድላቸው ተማከሩ በፈቀደላቸውም ጊዜ ወደ ንጉሥ የፍርድ ሸንጎ አምጥተው ገደሉት።
በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ መነኵሴ በድኑን ሊያይ ተነሥቶ ሔደ ሥጋውንም ሲያጥኑ ሦስት መላእክትን አገኛቸው። እርሱም እንዳልዋሸ በሕያው እግዚአብሔር ስም እየማለ ይህን ተናገረ። ዳግመኛም የብርሃን ፋና ከሰማይ ሲወርድለት ብዙ ቀን የተመለከቱም አሉ።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አዘነ ተጸጸተም በጎ ሥራውንም ሁሉ አሰበ እነዚያንም ሐሰተኞች ረገማቸው በሞትም ቀጣቸው ቅዱስ ዐምደ ሚካኤልም በአባቶቹ መቃብር አክብረው እንዲቀብሩት አዘዘ። እርሱ ቅዱስ እንደሆነ በበጎ ስም አጠራር እንዲጠሩት እንጂ ስሙን በክፉ እንዳይጠሩ አዋጅ አሳወጀ። መታሰቢያውንም አቆመለት ልጆቹንም አከበራቸው እጅግም ወደዳቸው።
ከዚህም በኋላ ልብነ ድንግል በነገሠ ጊዜ ከእርሱ ጋር ያለውን የአባቱ የበእደ ማርያምን ቃል ኪዳን ሰምቶ ከዚያ አፍልሰው ወደ አትሮንስ ማርያም እንዲወስዱትና በዚያ በነገሥታት መቃብር እንዲቀብሩት አዘዘ።

ቅዱስ_ነአኩቶ_ለአብ_ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
ዳግመኛም በዚችም ቀን የጻድቁ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነአኵቶ ለአብ መታሰቢያው።
ሃገራችን ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ቅድስና ያላቸው ቅዱሳን ባለቤት ናት። በዘመኑ ያለን ወጣቶችም ሆነ ጐልማሶች ከቤተ ክርስቲያንና ከቅድስና ሕይወት ለምን እንደራቅን ስንጠየቅ ከምንደረድራቸው ምክንያቶች አንዱ ሥራችን ነው።
ነገር ግን ሥራው በራሱ ኃጢአት እስካልሆነ ድረስ በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ቢሆን ቅድስናን ማስጠበቅ እንደሚቻል አበው አሳይተውናል። ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም ከእነዚህ ቅዱሳን አንዱ ነው።
እርሱ ንጉሥ ነው። ግን ገዳማዊ ሕይወትን በቤተ መንግስቱ ውስጥ ያሳየ ጻድቅ ነው።
ሁሉ በእጁ ነው። እርሱ ግን ንጹሕና ድንግል ነው።
እርሱ የጦር መሪ ነው። ግን በእጁ ደም አልፈሰሰም።
እርሱን "ወደድንህ ሞትንልህ" የሚሉ ብዙ ሰዎች በአካባቢው ነበሩት። ለእርሱ ግን ፍቅር ማለት ክርስቶስ ነበር።
የሃገር መሪ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት እንደ መሆኑ እጅግ ባተሌ (busy) ነው። ግን ደግሞ ለክርስትናው ጊዜ ያጣ ሰው አልነበረም።
እኛ ቤተ ክርስቲያንን "በሐኪ" ለማለት (ለመሳለም) እንኳ "ጊዜ የለኝም" ስንል እርሱ ግን አብያተ ክርስቲያናትን ይፈለፍል፣ ያንጽ፣ በክህነቱ ያገለግል፣ ማዕጠንት ያጥን፣ ለረጅም ሰዓትም ይጸልይ ነበር።
እኛ "ሥራ ውያለሁና ደክሞኛል" ብለን ከስግደት ስንርቅ እርሱ ግን ንጉሥ ሆኖ ሳለ ...ጦር በፊት በኋላ በቀኝና በግራ ተክሎ ይሰግድ ስለ ነበር ደሙ እንደ ውኃ በምድር ላይ ፈሷል። ይህንን ሁሉ ያደረገው ቅዱሱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ነአኩቶ ለአብ ነው።
ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በዛግዌ ሥርወ መንግስት ከነገሡ 11 ነገሥታት አንዱ ሲሆን ከመጨረሻውም ሁለተኛ ነው። እርሱን በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን የወለዱት ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ (ገብረ ማርያም) እና መርኬዛ ናቸው። ዘመኑ ቅድስና በላስታ ዙሪያ የመላበት በመሆኑ ቅዱስ ሐርቤ ከመመነኑ በፊት ነበር ነአኩቶ ለአብን የወለደው።
እናቱ መርኬዛ እርሱን ልትወልድ ምጥ ተይዛ ሳለ ጀሮዋ ቅዳሴን ይሰማ ነበር። ቅዳሴው ሲጀመር የጀመራት ምጥ ድርገት ሲወርዱ (ሥጋ ወደሙ ሲሰጥ) ተፈታላትና ልጇን ተገላገለች። ሕጻኑን አንስታ ስትታቀፈው ዲያቆኑ ማቁረቡን ፈጽሞ "ነአኩቶ" እያለ ሲዞር ሰማችው።
እዚያው ላይም "ነአኩቶ ለአብ" (አብን እናመስግነው) ስትል ስም አወጣችለት። ወዲያው ግን አባቱ ቅዱስ ሐርቤ መንግስቱን ለቅዱስ ላሊበላ ሰጥቶ በርሃ በመግባቱ ቅዱሱ ሕጻን ወደ አጐቱ ላሊበላ ቤተ መንግስት ውስጥ ገባ።
የቅዱስ ላሊበላ ቤት ደግሞ በቅድስና ያጌጠ ነውና ከርሱና ከሚስቱ (ቅድስት መስቀል ክብራ) ሕጻኑ ነአኩቶ ለአብ ምናኔና ፍቅረ ክርስቶስን ተማረ። በዘመኑ ብዙ ሊቃውንት ስለ ነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በደንብ አጠና። ክህነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግልም እድሜው 30 ደረሰ።
በወቅቱ ቅዱስ ላሊበላና ባለቤቱ መስቀል ክብራ ልጃቸው ይትባረክ እያለ ንግሥናቸውን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አወረሱ። ቅዱሱ ነአኩቶ ለአብም ምን እንደሚሠራ ሲያስብ አንድ ነገር ተገለጠለት። ቤተ መንግስቱን እንደሚገባ ካደራጀ በኋላ በቤት ውስጥ አንድ ጉድጓድን በቁመቱ ልክ አስቆፈረ።
በውስጡም በ4 አቅጣጫ ጦሮችን ተከለባቸው። ድንግል ካህን ነበረና ቀን ቀን ሃገር ሲያስተዳድር ቅዳሴ ሲቀድስ በጾም ይውላል። ሌሊት ደግሞ ወዳስቆፈረው ቦታ ገብቶ ያለማቋረጥ እየጸለየ ይሰግዳል።
ወደ ምድር ሲሰግድ በፊቱ ያለው ጦር ይወጋዋል። ቀና ሲል ደግሞ የጀርባው ይቀበለዋል። እንዲህ እያለ የፈጣሪውን ሕማማት ይካፈላል። በተለይ ዐርብ ዐርብ ሲሆን ደሙ፣ እንባውና ላበቱ ተቀላቅሎ ይፈስ ነበር። እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ጌታውን ይከተል ዘንድ መርጧልና።
ከተጋድሎው ጐን ለጐን ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አብያተ ክርስቲያናትንም ያንጽ ነበር። በተለይ በ1211 አካባቢ ያነጻት አሸተን ማርያም ልዩ ናት። እርሷን ካነጸ በኋላ ከቤተ መንግስቱ በደመና ሠረገላ ተጭኖ እየሔደ ያጥናት ይቀድስባትም ነበር።
ታዲያ አንድ ቀን አጥኖ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ብዙ ሥውራን ቅዱሳን መቅደሱን ከበው ተመለከተ። እርሱም "ወገኖቼ! ከወዴት መጣችሁ?" ቢላቸው "መዐዛ እጣንህን አሽተን መጣን" ሲሉ መለሱለት። በዚህ ምክንያትም እስከ ዛሬ ድረስ "አሽተን (አሸተን) ማርያም" ስትባል ትኖራለች።
ዛሬ ታቦቱ ያለበት ገዳሙም በእርሱ የታነጸ ሲሆን እጅግ ተአምረኛ ቦታ ነው። ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የነገሠ በ30 ዓመቱ ነው። ለ40 ዓመታት በእንዲህ ያለ ቅድስና ኑሮ 70 ዓመት ሞላው። በዚህ ጊዜም ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ሰላምታንም ሰጠው።
"ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ! አንተ ስለ እኔ ፍቅር ለ40 ዓመታት መከራን ተቀብለሃልና ሞት አያገኝህም። ክፍልህ ከነ ኤልያስ ጋር ነውና። የሚያከብርህን አከብረዋለሁ። ደጅህን የሳመውን፣ ይህ ቢያቅተው በሩቁ ሆኖ በአድናቆት የተመኘህን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እምርልሃለሁ" አለው።
ቀጥሎም "ይሕች ቤት አንተ ስትደማ እንደኖርክባት እርሷም እስከ ምጽዓት ድረስ ለመታሰቢያህ ስትደማ ትኑር" አለው። እነሆ ዛሬም ድረስ ከመቅደሱ ጠበል ይንጠበጠባል። ለዚህም ደግሞ እኛ ኃጥአን ምስክሮች ነን። ሳይገባን የቅዱሱን ደጅ ተመልክተናልና።
ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም የዚህን ዓለም ተጋድሎውን ፈጽሞ ወደ ብሔረ ሕያዋን መላእክት ወስደውታል። የተሰወረበትን ዕለት ስንክሳር ሕዳር 1 ሲያደርገው አንዳንድ መዛግብት ደግሞ በ3 ነው ይላሉ። በዙፋኑም ላይ የአጐቱ የላሊበላ ልጅ አፄ ይትባረክ ተተክቷል።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages