“መኑ ይመስለከ" (ማን ይመስልሃል?') መዝ ፹፰-፮ - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, November 6, 2022

“መኑ ይመስለከ" (ማን ይመስልሃል?') መዝ ፹፰-፮






“ዕፍረት ምዑዝ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ኢየሱስ ክርስቶስ መአዛዉ ያማረ ሽቶ ነዉ”። ኤፌ ፭-፪ አንድም ኢየሱስ ክርስቶስ ምዑዘ ባህሪይ ነዉ።
 
”ንዑ ንስግድ ሎቱ፤እንሰግድለት ዘንድ” ፊል ፪-፲  
“ወንዕቀብ ትዕዛዛቲሁ፤ትዕዛዙን እንጠብቅ ዘንድ ኑ”።
”ከመ ይሥረይ ለነ ኃጣዉኢነ፤ኃጢአታችንን ያስተሰረይልን ዘንድ” ኑ 
መጽሐፈ ቅዳሴ ንባቡና ትርጓሜዉ ገጽ ፹፪//ሉቃ ፭-፳፬/።
 
ክፉ መአዛችንን በበጎ መአዛህ የለወጥህ። በመልዕልተ መስቀል ተሰቅለህ በወርቀ ደምህ ፈሳሽነት ወደ ገነት መንግሥተ ሰማያት ያቀረብኸን መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነህ።ውሉደ አዳም ደቂቀ አዳም የወደቀበትን የሞት የኃጢአት ዕዳ ከላዩ ለማንሳት አቅም አልነበረውም።የሰዉ ልጅ ሞቱን በሕይወት ለመለወጥ ችሎታ አልነበረውም።በባሕሪህ ምዑዝ የሆንህ አምላክ ወልደ አምላክ አንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሁሉን ማድረግ ተችላለህ።ስለዚህም በሥልጣንህ ለአዳም ዘር የሚበጀውን ሁሉ አደረግህ።
በዚህና በሌላም ቁጥር በሌለው ምክንያት ነዉ “መኑ ይመስለከ” የምንልህ::“መኑ ይመስለከ እምነ አማልክት እግዚኦ”አቤቱ አማልክት ከተባሉ በአማልክት ከተመሰሉ በመፍጠር በማሳለፍ አንተን የሚመስልህ ማነው?”/መዝ ፹፰-፮/አንተ ውእቱ ዘትገብር መንክረ፤አቤቱ ተአምራት የምታደርግ አንተ ነህ”/ሁል ጊዜ የሚያደርግውን ተአምራት ነው።አንድም ሥጋውን ደሙን መለወጡን ነው/።”አርአይኮሙ ለሕዝብከ ኃይለከ ወአድኃንኮሙ ለሕዝብከ በመዝራዕትከ’’ኃይልህን ለሕዝብህ አሳየሃቸዉ በፅኑ ሥልጣንም ሕዝብህን አዳንህ።
”ሖርከ ዉስተ ሲኦል ወአዕረገ ጼዋ” ወደ ሲኦል በአካለ ነፍስ ወርደህ ነፍሳትን ከሲኦል አወጣህ/፩ኛ ጴጥ ፫-፲፱/።”ወጸጎከነ ምዕረ ዳግመ ግዕዛነ”ዳግመኛም ግዕዛነ ንፍስን/የነፍስን ነጻነት/ ሰጠኸን።”እስመ መጻእከ ወአድኀንከነ”ከወዲያ ዓለም ወደዚህ ዓለም መጥተህ አንድም ሰው ሆነህ አድነኸናልና።”በእንተ ዝንቱ ንሴብሐከ ወንጸርሕ ኀቤከ እንዘ ንብል ቡሩክ አንተ እግዚኦ ኢየሲስ ክርስቶስ” ሰዉ ሆነህ ስላዳንኸን አሰምተን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህሪይ አምላክ ነህ እያልን እናመሰግንሃለን።/መጽሐፈ ቅዳሴ ንባቡና ትርጓሜዉ ገጽ ፺፮/
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በመዝራዕትህ ከሲኦል ግዞት ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ያወጣኸን አንተ ነህ።አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን በባርነት የማቀቁ ነፍሳትን ከሲኦል ሞት ነጻ ያደረግህ አንተ ነህ።ደጅ የተጠኑ ዕጣን የታጠኑ፣ወይፈን አሰዉተው፣እጅ መንሻ ሽተው፣ግብር ያስገበሩ፣አማልክት ነን ያሉ ብዙዎች አልፈዋል።ለሰዉ ልጅ ግን የበጁት አንድም ነገር የለም።”መኑ ይመስለከ”አንተን ግን ማን ይመስልሃል?የሞት ወጥመድን በመስበር የሚመስልህ ማን አለ?እዉነተኛ አምላክ የፍጥረታት ሁሉ ጌታ አንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ነህ።
“ፈቀደ እግዚእ ያግዕዞ ለአዳም ሕዙነ ወትኩዘ ልብ” አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ የነበረ አዳምን ነጻ ያደርገው ዘንድ ወደደ።/አትብላ ያለኝን ዕፀ በለስ በልቼ ከፈጣሪ ትእዛዝ ወጣሁ ብሎ ያዘነ አዳምን ነጻ ያደርገው ዘንድ ወደደ/::”ወያገብኦ ኀበ ዘትካት መንበሩ” ወደ ቀደመ ቦታዉ ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰዉ ዘንድ ወደደ።/ክብር ቢሉ ልጅነት ቦታ ቢሉ ገነት ነዉ//የሰኞ ዉዳሴ ማርያም/።
ትዕዛዝህን አፍርሶ ሕግህን ጥሶ የወደቀ አዳምን በዓይነ ምኅረት ተመለከትኸዉ።ሀዘኑን መከራውን ሞቱን አይተህ አዘንህለት።ወደ ቀደመ ርስቱ ልትመልሰው ወደድህ።መድኅን ዓለም ክርስቶስ ሆይ በሱራፊ የእሳት ሰይፍ የታጠረ ርስቱን አንተ ባትከፍትለት ማን ይመልስለት ነበር?ትዕዛዝህን በስህተቱ ለጣሰ፣በራሱ ላይ የሞት ድግስ ለደገሰ ለአባታችን ለአዳም ስትራራ ለሁላችንም ራርተሃል።የወገቡ ፍሬዎች ነንና ሁላችንን በእርሱ ዉስጥ አይተኸናል።ለዚህ ርህራሄ ለዚህ ደግነት ለዚህ ቸርነት ምሥጋና ይገባል።ለአዳም ብቻም ያይደል ለሁላችን ገነት ርስታችንን አንተ ባትመልስልን ከወዴት እናገኛት ነበር?ወደ ቀደመ ርስታችን አንተ ባትመልሰን ፍጻሜያችን እንዴት መራራ በሆነ ነበር።
ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ አዳም አባቱን ይጠይቃል።”ኦ አዳም ምንተኑ ረሰይናከ ዘአምጻእከ ፍትሐ ሞት ላዕሌነ” አዳም ሆይ የሞትን ፍርድ ያመጣህብን ምን አደረግንህ ምን በደልንህ።/ቢነደዉ ቢቊጨዉ ያማርራል/።”ኦ አዳም ምንተኑ ረሰይናከ ዘኢኃደገነ ንትፈጋዕ በገነተ ፍግዕ በአብያተ እግዚእ”።ተድላ ደስታ በሚደረግበት በጌታ ማደሪያ በገነት ደስ ይለን ዘንድ ያልተዉኸን ምን አደረግንህ።”ኦ ሔዋን ምንተኑ ረሰይናኪ” ሔዋን ሆይ ምን አደረግንሽ ምን በደልንሽ።”ናሁ ጸልመ ሥጋነ በብዝኃ ኃጣዉዕ”።ከኃጢአት ብዛት የተነሣ አንድም በኃጢአት ብዛት ሰውነታችን በሐዘን ጠቆረ።”ኦ ሔዋን ምንተኑ ረሰይናኪ” ሔዋን ምን አደረግንሽ ምን በደልንሽ።
ሊቁ አዳምና ሔዋንን ከጠየቀ በኋላ መልሶ እናንተን መክሰስ አይቻለንም እናንተ እኛን ናችሁ እኛም እናንተን ይላል።አስከትሎም “ኦ አዳም ወሔዋን አንትሙሰ ነሳህያን በተግሳጸ እግዚእ መሐሪ” ፈጽመንም እንዳንነቅፋችሁም ይቅር ባይ የሚሆን ጌታ በመጣባችሁ መከራ ንሰሐ ገብታችኋል።”ኦ አዳም ወሔዋን አንተሙሰ በአማን ድኁኃን” እናንተስ በእዉነት ድናችኋል ያለመከልከል ወደ ነበራችሁበት ወደ ቀደመ ረስታችሁ ወደ ገነት ገብታችኋል።”በደመ ዚአሁ ለዘተቤዘወክሙ” ቤዛ ሆኖ ባዳናችሁ በጌታ ደም ድናችኋል ይላል/መጽሐፈ ቅዳሴ ንባቡና ትርጓሜው ገጽ ፫፻፲፪/።
አዳምና ሔዋን ወደ ቀደመ ርስታቸዉ የገቡት ሚጠተ ነፍስ ያገኙት በአንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ነዉ።መራራው የሰዉ ልጅ የመከራ ሕይወት የጣፈጠዉ በአንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ነዉ።በተደረገልን ታላቅ የቸርነት ሥራ ምክንያት የሀዘን የመከራ እንጉርጉሯችን ወደ ምሥጋና ተለዉጧል።አንደበታችን ስለአንተ ተናጋሪ ድንቅ ሥራህን ሌትና ቀን መስካሪ ሆኗል።ለሰው ልጆች ያለህን ፅኑ ፍቅር በመሰቀል ሞት ስለገለጥኸልን በመዐልት ወበሌሊት እናመሰግንሃለን።
ጌታችን ሆይ“ያብአነ ቤተ መርዓሁ ውስተ ደብተራሁ አመ ይትጋብኡ ለምሳሕ ሥርግዋን ሐራሁ”እንዳለ/መጽሐፈ ሰዓታት ገጽ ፪፻፵/ የተመረጡ እድምተኞች በማዕድህ ዙሪያ በተሰበሰቡ ጊዜ እኛንም ወደ ሠርጉ አዳራሽ አግባን።ለአዳም ያደረግኸውን ምሕረት ቸርነት ለእኛም አድርግልን።ፀአዳ የለበሱ ንጽሕናቸውን በኃጢአት ያላሳደፉ ቅዱሳን በፊትህ ሲታደሙ እኛንም ይቅር እንድትለን እንማጸናለን።”ኲናኔ ሥጋ ወነፍስ” በነፍስና በሥጋ የሚፈርድ ለማዳንም ለመግደልም ሥልጣን ያለው እንዳንተ ማን አለ?መኑ ይመስለከ የሚተካከለዉ በሌለ በዚህ መለኮታዊ ሥልጣንህስ አንተን ማን ይመስልሃል?
ክርስቶስ ሆይ “ሰራዬ ኃጢአት ወደምሳሴ አበሳ” ነህ ስለ ሥጋ ፣ስለ ነፍስ ስለ ጊዜዉ፣ስለ ዘላለሙ፤በውስጥ በአፍአ፣በነፍስ በሥጋ ኃጢአታችንን የምታሥተሰርይልን ነህ።”ሥርግዋን ሐራሁ”የተመረጡ የሰማያዊው ሠርግ እድምተኞችን ስናስብ እኛ ማን ነን? እንላለን።በሠርግህ አዳራሽ በዚያ ልዕልት፣ወክብርት፣መልዕልተ ፍጡራን፣መትሕተ ፈጣሪ፣ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን አለች።አማላጅነቷ ከሲኦል ሞት ያድነንና ድንግል የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋ በየማንህ ትቆማለች።ወጽአ ነገሮሙ የተባሉ ደቀ ማዛሙርትህ ሐዋርያት ከጻድቃን ከሰማዕታት ሁሉ ጋር አስበ ፃማቸዉን ልትከፍላቸዉ በሠርግህ አዳራሽ ይታደማሉ።ስለ ስምህ በአላውያን ነገሥታት በመናፍቃን ጳጳሳት መከራ የተቀበሉ ሁሉ እድምተኞች ናቸዉ።
”ንኡስ አነ እም አኀዉየ”ከወንድሞች ሁሉ የማንስ እኔ ባሪያህ ስለሠርግህ ሳስብ እጅግ እፈራለሁ።””አመ ትመጽእ ለኮንኖ ምስለደመ ገቦ አእጋር አማኅፀንኩ ነፍስየ ውስተ እዴከ ክቡር”/መጽሐፈ ሰዓታት ገጽ ፪፻፵፩/በዳግመኛ ምጽአትህ ጎንህ በጦር እንደተወጋ እጆችህና እግሮችህም እንደተቸነከሩ ሆነህ ለፍርድ ስትመጣ ነፍሴ በከበረ የእጅህ መዳፍ እረፍት እንድታገኝ አደራ እልሃለሁ/እማፀንሃለሁ/ማቴ ፳፭-፴፩/።ስለ ግርፋትህ፣ሞትህ፣መራብ፣መጠማትህ ሁሉ ብለህ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ።
ቀሲስ ያሬድ ገብረ መድኅን
(ኮለምበስ ኦሀዮ )
(ጥቅምት ፳፯ ፪ ሺህ ፲፭ ዓ.ም)

 

1 comment:

Post Bottom Ad

Pages