ንጉሥ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተመንግስቱ ገብቶ በከሃዲያኑ ሰባው ነገሥታት ፊት ክርስቲያን መሆኑን በመመስከር የጌታችንን አምላክነት መሰከረ፡፡ ዱድያኖስም የቅዱስ ጊዮርጊስን ማንነቱን ከተረዳ በኋላ ‹‹አንተማ የኛ ነህ በዐሥር አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ›› አለው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ‹‹ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዱድያኖስ እጅግ ተናዶ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን አደረሰበት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ጌታችንን ‹‹ይህን ከሃዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰዳት›› በማለት መከራውን ይታገስ ዘንድ ለመነው፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ፈቃዱን ይፈጽምለት ብዙ በመከራው ሁሉ ጽናትን ሰጥቶታል፡፡ ሦስት ጊዜም ከሞት አስነሥቶታል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም የደረሱበት እጅግ አሠቃቂ መከራዎች የሰው ኅሊና ሊያስባቸው እንኳን የማይችላቸው ናቸው፡፡ በመጀመሪያም ዱድያኖስ በእንጨት ላይ ካሰቀለው በኋላ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው፣ ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ አለው፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል፡፡ ዳግመኛም በሰባ ችንካሮች አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ፡፡ ሥጋውንም በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነሰነሰበት፡፡ ሥጋውም ተቆራርጦ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ ከፈወሰውና ‹‹ገና ስድስት ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣ በ4ኛውም ታርፋለህ›› ካለው በኋላ በመከራውም ሁሉ እርሱ እንደማይለየው ነገረው፡፡
ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከዚያ ካደረሰበት አሠቃቂ መከራዎች ሁሉ ድኑ ፍጹም ጤነኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ እጅግ ደንግጦ ‹‹የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ብዙ ወርቅ እሰጠዋለሁ›› ብሎ ተናገረ፡፡ አትናስዮስ የተባለ መሠርይ አንዲትን ላም በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ስትሞት ለንጉሡ አሳየውና ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲሚያሸንፍ ምልክት አሳየ፡፡ ንጉሡም ‹‹ያሸንፍልኛል›› ብሎ ደስ አለው፡፡ መሠርይውም ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞበት እንዲጠጣው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ጊዜ ጠንቋዩ እጅግ ተገርሞ ‹‹ማረኝ›› ብሎ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እግሩ ሥር ወደቀ፡፡ ዳግመኛም ‹‹አምላክህ አምላኬ ይሁነኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ ሰማዕቱም የዚያን መሠርይ ጠንቋይ መመለሱንና ማመኑን አይቶ የቆመባትን መሬት በእግሩ ረግጦ ውሃን አፍልቆ ወደ ጌታችን በጸሎት ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስ በመንፈስ መጣና መሠርይ የነበረውን ሰው አትናስዮስን አጠመቀው፡፡ አትናስዮስም ‹‹ከቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ በቀር ሌላ አምላክ የለም›› በማለት የጌታችን አምላክነት በከሃድያኑ ነገሥታት ፊት መስክሮ በዛሬዋ ዕለት ጥር 23 ቀን አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡ የልዳው ፀሐይ የኢትዮጵያ ገበዝ ቅዱስ ጊዮርጊስ እኛንም ለክብር ያብቃን፡፡
ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሐዋርያ ረድኡ ለጳውሎስ፡- ይኸውም አሕዛብን ለሚያስተምር ለቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ የሆነ የከበረ ሐዋርያ ነው፡፡ ልደቱና ዕድገቱ ልስጥራን ከሚባል አገር ነው፡፡ አባቱ ከዋክብትን የሚያመልክ ዮናናዊ ነው፡፡ እናቱ ግን በኦሪት ሕግ ጥላ ሥር ነበረች፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በልስጥራ አገር በሰበከ ጊዜ ጢሞቴዎስ ትምህርቱን ሰምቶ እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያደርጋቸውን ድንቅ ድንቅ ተአምራት አይቶ በጌታችን አመኖ ተጠመቀ፡፡
የቅዱስ ጳውሎስም ደቀ መዝሙር ሆኖ ወደ ብዙ አገሮች ተከትሎት በመሄድ ከእርሱ ጋር ስለ ወንጌል ብዙ ደከመ፡፡ ብዙ ታላላቅ መከራዎችና ብዙ ኃዘናት ደርሰውበታል፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም በኤፌሶን ውስጥ በአንዲት አገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾመው፡፡ በአገሪቱም ላይ ቅዱስ ወንጌልን ሰብኮ ሕዝቡን ከአምልኮ ጣዖት መልሶ እግዚአብሔርን ወደማምለክ አምጥቷቸዋል፡፡ በዙሪያዋ ባሉ አገሮችም እየተዘዋወረ በማስተማር ብዙዎችን አጥምቆ የክርስቶስ ተከታዮች አድርጓቸዋል፡፡
ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ሁለት መጻሕፍትን በስሙ ጽፎ ልኮለታል፡፡ መልእክቶቹም በዋነኛነት ሕዝቡን እንዲያስተምርባቸውና ራሱም ከቢጸ ሐሳውያን የሚጠበቅባቸው ናቸው፡፡ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ለቅዱስ ጳውሎስ ተወዳጅና ታማኝ ልጁ ስለነበር የተለያዩ መልእክቶቹንም ወደ ተለያዩ ሀገራት በእርሱ እጅ ይልክ ነበር፡፡ አይሁድንና ዮናናውያንን በትምህርቱ ይገሥጻቸው ሕዝቡንም እያስተማረ ያጠቃቸው ስለነበር ቀንተው በጠላትነት ተነሱበትና ተሰብስበው ይዘው ጥር 23 ቀን ገደሉት፡፡ ምእመናንም ሥጋውን አንሥተው ቀበሩት፡፡ ደገኛው ታላቁ ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ ጥር 27 ቀን ሥጋውን አፍልሶ ወደ ቍስጥንጥንያ በታላቅ ክብር አስመጥቶ በክብር አኑሮታል፡፡ የሐዋርያው የቅዱስ ጢሞቴዎስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
ዳግመኛም በዚህች ዕለት የከበሩ ሰማዕታት የጌርሎስና የአትናቴዎስ የጻድቁ ንጉሥ የቴዎዶስዮስም መታሰቢያቸው ነው በማለት ስንክሳሩ ስማቸውን የጠቀሳቸው ቅዱሳን ዓመታዊ በዓላቸው ነው፡፡ በረከታቸው ከእኛ ጋር ትሁን፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ በጻፈለት ሁለት መልእክታት ውስጥ ልብን የሚነኩና እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በእምነት ጉዳይ ላይ በዓለም የሚፈጠረውን ነገር ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ነጥቦችን በዝርዝር ነግሮታል፡፡ በወቅቱ ሐዋርያው ‹‹ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ!›› እያለ የጻፋቸው መልአክቶቹ ስለዘመናችን የተነገሩ ትንቢቶች ናቸው፡፡ በተለይም ብዙዎቹ እውነተኛዋንና የመጀመሪያዋን ሃይማኖት እንደሚክዷት የተነገሩት ትንቢቶች ናቸውና እስቲ አስተውለን በደንብ እንመልከታቸው፡፡
‹‹ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ! አስቀድሞ ስለ አንተ እንደ ተነገረው ትንቢት፥ በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፡፡›› /1ኛ ጢሞ 1÷19/
‹‹በግልፅ በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ፡፡›› /1ኛ ጢሞቴዎስ 4:1/
‹‹ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፣ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ፡፡›› /2ኛ ጢሞ4÷3/
‹‹ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ! በእናትህ በኤውንቄ፣ በአያትህ በሎይድ ጸንታ ያለች መጠርጠር የሌለባትን ሃይማኖትህን አይቼ ደስ አለኝ፡፡ ባንተ ጸንታ እንዳለች አምኜ ፈጽሞ ደስ ይለኛል፡፡›› /2ኛ ጢሞ 1÷5/
‹‹አንዳንዶች ስተው የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ፥ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል፡፡›› /1ኛ ጢሞ 1÷7/
‹‹ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ፥ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ ይህ እውቀት አለን ብለው፥ አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና፡፡” /1ኛ ጢሞ 6÷20/
‹‹ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ። ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም…አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል፡፡” /2ኛ ጢሞ 3÷8-15/
የሐዋርያቱ የቅዱስ ጳውሎስና የልጁ የቅዱስ ጢሞቴዎስ ረድኤት በረከታቸው በሁላችን በተዋሕዶ ልጆች ልጆች ላይ ይደርብን፡፡ ትንቢታቸው የሚፈጸሙን ከመሆን ጸሎታቸው ይታደገንና በእምነታቸው እስከመጨረሻው ያጽናን፡፡
No comments:
Post a Comment