ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 13 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, December 9, 2022

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 13

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ዐሥራ ሦስት በዚህች ቀን ቅዱሳን_አእላፍ_መላእክት (፺፱ኙ ነገደ መላእክት) መታሰቢያ ነው፣ የከበረ ባለጸጋ ቅዱስ_አስከናፍር እረፍቱ፣ የከበረ አባት ቅዱስ_ጢሞቴዎስ_ዘእንጽና እረፍቱ፣ ሊቀጳጳሳት ቅዱስ_አባት_ዘካርያስ እረፍቱ ነው።


አእላፍ_መላእክት (፱፱ኙ ነገደ መላእክት)
ኅዳር ዐሥራ ሦስት በዚህች ቀን የአእላፍ መላእክትን የበዓላቸውን መታሰቢያ እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙን ። እሊህም ሥጋ የሌላቸው ረቂቃን የሆኑ ለዓለሙ ሁሉ የሚማልዱ ናቸው ።
ኄኖክም ስለእርሳቸው እንዲህ አለ በሰማይ እያለሁ ነፋሳት በደመና ውስጥ አወጡኝ በእሳት ላንቃም ወደታነፀ ቤት አደረሱኝ በዚያም አእላፋት መላእክትን አየሁ እነርሱም በእሳት ላቦት ላይ የቆሙ ልብሳቸውም እንደ በረድ ነጭ ነው አለ።
ያዕቆብም እንዲህ አለ ከምድር እስከ ሰማይ የምትደርስ መሰላልን አየሁ የእግዚአብሔርም መላእክት በውስጥዋ ይወጡ ይወርዱ ነበር። ሁለተኛም ከሶርያ መመለሻው በሆነ ጊዜ የመላእክት ሠራዊትን አየሁ አለ ።
ሙሴም እንዲህ አለ እግዚአብሔር አሕዛብን በቦታ እንደለያቸው የአዳምን ልጆች እንደበተናቸው እግዚአብሔርን በሚያገለግሉ መላእክት ቁጥር የአሕዛብን አውራጃዎች እንደ ወሰናቸው ። ሁለተኛም እግዚአብሔር ከሲና ተራራ መጥቶ በሴይር ታየኝ ረቂቃን መላእክቶቹም ከእርሱ ጋር ነበሩ አለ ።
ዳዊትም እንዲህ አለ መላእክቱን መንፈስ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ እርሱ ነው ። ሁለተኛም የእግዚአብሔር ሠረገላዎች የብዙ ብዙ ሽህ ናቸው አለ ። ኤልሳዕም የእሳት ሠረገሎችና የእሳት ፈረሶች በዙሪያው ቁመው ሲጠብቁት አየ ።
ዳንኤልም እንዲህ አለ ዙፋኖችን እስቲዘረጉለት ድረስ ደርሶ አየሁ ብሉየ መዋዕል እግዚአብሔር በላያቸው ተቀመጠ ልብሱም እንደ በረድ ነጭ ነው የራሱም ጠጉር እንደ ብዝት ነጭ ነው ዙፋኑም የሚነድ እሳት ነው ሠረገላውም የሚንቦገቦግ ፍም ነው ። የእሳትም ጐርፍ በፊቱ ይፈሳል የብዙ ብዙ የሆኑ መላእክትም ያገለግሉታል የእልፍ እልፍ መላእክትም በፊቱ ይቆማሉ በአደባባይም ተቀምጦ መጻሕፍትን ገለጠ ።
ሉቃስም እንዲህ አለ ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት መጡ እግዚአብሔርንም ሲያመሰግኑ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰው ልጅ በጎ ፈቃድ እያሉ ።
ማቴዎስም እነሆ መላእክትም ሊአገለግሉት መጡ አለ ። ሁለተኛም የሰው ልጅ ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ በጌትነቱ በሚመጣበት ጊዜ ያን ጊዜ በጌትነቱ ዙፋን ላይ ይቀመጣል ። ዮሐንስም ጌታችን ከተናገረው ቃል እንዲህ አለ እውነት እውነት እላችኋለሁ ከእንግዲህ ወዲህ ሰማዮች ሲከፈቱ የእግዚአብሔርም መላእክት ወደ ሰው ልጅ ሲወርዱና ሲወጡ ታያላችሁ አላቸው የሚል ነው ።
ሐዋርያው ይሁዳም እነሆ እግዚአብሔር ይፈርድ ዘንድ አእላፋት የሆኑ ቅዱሳን መላእክቶቹን አስከትሎ ይመጣል አለ። የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም የመዓርጋቸውን ደረጃ ወይም አይነት እንዲህ ብለው ተናገሩ መላእክት አጋዕዝት ሥልጣናት ኃይላት መናብርት መኳንንት ሊቃናት አርባብ ኪሩቤል ሱራፌል ብለው ተናገሩ።

በዚህችም ቀን ዐሥራ ሦስት ወንበዴዎች ስለርሱ በእርሱ ሃይማኖት ከዓለም የተለዩ የከበረ ባለጸጋ አስከናፍር አረፈ ። ይህም አስከናፍር ከሮሜ መኳንንት አንዱ ነው እርሱም ለድኆችና ለምስኪኖች ምጽዋትን የሚሰጥ እንግዶችንና መጻተኞችን የሚቀበል ነው ።
በዚያም ወራት ያገኙትን ሰው ሁሉ የሚነጥቁና የሚያጠፉ ዐሥራ ሦስት ሽፍቶች ነበሩ እንግዳ እንደሚቀበል ይልቁንም መነኰሳትን እንደሚወድ የአስከናፍርን ዜና በሰሙ ጊዜ ወደርሱ ሒደው በተንኮል ይገድሉት ዘንድ ገንዘቡንም ሁሉ ሊወስዱ ተማከሩ ። ከዚህም በኋላ የምንኲስና ልብስ ለብሰው ከደጁ ቆሙ በአያቸውም ጊዜ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እንደሆኑ አንዱ ጌታ ክርስቶስ እንደሆነ አሰበ ሰገደላቸውም ወደ ቤቱም አስገብቶ ማዕድ አቀረበላቸው እግራቸውንም አጠበ ሠላሳ አምስት ዓመት ሽባ ሆኖ በኖረ ልጁ ላይ ያንን እግራቸውን የታጠቡበትን ውኃ ረጨ ወዲያውኑ ልጁ ዳነ ።
እነዚያ ሽፍቶችም የሆነውን በአዩ ጊዜ እጅግ ደነገጡ እርሱ አስከናፍር ግን አባቶቼ ሆይ ጌታ ክርስቶስ ከእናንተ መካከል የቱ እንደሆነ ንገሩኝ እሰግድለት ዘንድ አላቸው የአገር ሰዎችም የመኰንኑ ልጅ እንደዳነ በሰሙ ጊዜ ወደርሳቸው መጥተው ሰገዱላቸው እንዲህም አሏቸው የእግዚአብሔር ቅዱሳኖች ሆይ ባርኩን በሽተኞቻችንን አድኑልን ። ከዚህም በኋላ እሊያ ወንበዴዎች ሾተሎቻቸውን አውጥተው በእርሳቸው ልንገድልህ በወደድንበት እኛን ይገድሉን ዘንድ እሊህን ሾተሎች ውሰድ አሉት እግዚአብሔር በአንተ ጽድቅ የራራልን ባይሆን በአጠፋን ነበር ።
ይህንንም ከአሉት በኋላ ተሰናበቱት ከእርሱም አንድ አንድ መስፈሪያ ምስር ለየአንዳንዳቸው ተቀብለው ሃያ አምስት ቀን ያህል የሚያስጉዝ ጉዳና ወደ ምድረ በዳ ተጓዙ ያንንም ምስር ከአሸዋ ውስጥ በተኑት ፀሐይ በሚገባም ጊዜ ከአሸዋው ውስጥ ሦስት ሦስት ምስር ፈልገው ይቀምሳሉ እንደዚህም ሠላሳ ዓመት ኖሩ ። ከዚህም በኋላ ከሀዲ መኰንን በመጣ ጊዜ እርሱ ወዳለበት ሒደው በጌታችን ታመኑ እርሱም ገደላቸውና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

በዚህችም ቀን የሀገረ እንጽና ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት ጢሞቴዎስ አረፈ ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ ልቡ ንጹሕ የሆነ ጻድቅ ሰው ነው ታላቅ ተጋድሎንም የተጋደለ ነው። የእንጽና አገር መኰንንም ለሰዎች የቀናች ሃይማኖትን በማስተማሩና በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አመነ ይዞ ጽኑዕ ሥቃይን ብዙ ዘመናት አሠቃየው ። ከእሥር ቤትም አውጥቶ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃይቶ ወደ እሥር ቤት ይመልሰው ነበር ከእርሱም ጋር ስለ ሃይማኖት የታሠሩ ብዙዎች ቅዱሳን ሰማዕታት ነበሩ ከእሳቸውም በወህኒ ቤት ጥቂቶች እስከቀሩ ድረስ ያ ከሀዲ መኰንን ብዙዎቹን አውጥቶ አሠቃይቶ ንጹሕ ደማቸውን በማፍሰስ ፈጃቸው ።
ከዚህም በኋላ ከሀዲውን ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስን እግዚአብሔር በአጠፋው ጊዜ እግዚአብሔርን የሚወድ ጻድቅ ሰው ቈስጠንጢኖስ ነገሠ በዚያንም ጊዜ ክርስቶስን በመታመን የታሠሩትን ሁሉ ይፈቱአቸው ዘንድ መልእክቱ በሀገሮች ሁሉ ደረሰች ።
ይህ ቅዱስ አባት ጢሞቴዎስም ከእሥር ቤት በወጣ ጊዜ በሀገረ ስብከቱ ያሉትን መነኰሳቱንና ካህናቱን ሁሉ ሰበሰባቸው ስለዚያ ስለአሠቃየው መኰንን ነፍስ ድኅነትም እግዚአብሔርን እየለመነ ከማታ እስከ ጥዋት ድረስ ፍጹም የሆነ ጸሎትን በማድረግ አደረ ።
እንዲህም ብሎ ጸለየለት አቤቱ ይህን መኰንን ማረው እርሱ ለእኔ ታላላቆች የሆኑ በጎ ነገሮችን አድርጎልኛልና ወደ አንተም ለመድረሴ ምክንያት ሁኖኛልና አቤቱ እንዲሁ በአንተ አምኖ ወዳንተ ይደርስ ዘንድ ምክንያት አድርግለት ። የዚህ አባትም ልብ ከቂም ከበቀል የነጻ በመሆኑ ሰዎች አደነቁ ።
ይምረው ዘንድ ነፍሱንም ያድንለት ዘንድ አባ ጢሞቴዎስ ስለርሱ ወደ እግዚአብሔር እንደሚለምን ለመኰንኑ ነገሩት መኰንኑም ሰምቶ እጅግ አደነቀ እንዲህም አለ እኔ ግን ጽኑ ሥቃይን ስለአሠቃየሁት እንደሚረግመኝ አስብ ነበር አሁን እርሱ ግን ስለ እኔ ምሕረትን ይለምናል የእሊህ ክርስቲያን ሃይማኖታቸው በውስጡ የተሠወረ ሰማያዊ የሆነ ምሥጢር አለ። ከዚህም በኋላ መኰንኑ ልኮ ይህን አባት ጢሞቴዎስን አስመጣውና ስለ ክርስትና ሕግ ያስረዳው ዘንድ ለመነው እርሱም ከዓለም መፈጠር ጀምሮ ያለውን ገለጠለት ዳግመኛም የወልደ እግዚአብሔርን ሰው የሆነበትን ምክንያት ከብዙ ዓመታትም አስቀድሞ ነቢያት ስለርሱ ትንቢት እንደተናገሩ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ልጅ ሰው በመሆኑ ትንቢታቸው እንደተፈጸመ ስለእኛ መከራ ተቀብሎ ተሰቅሎ ስለመሞቱ ስለትንሣኤውና ስለ ዕርገቱ ዳግመኛም ለፍርድ ስለመምጣቱ አስረዳው ።
መኰንኑም በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ በዚህ አባት እጅ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ ሹመቱንም ትቶ መነኰሰ በገድልም ተጠመደ ከዚህም አባት ጢሞቴዎስ መንጋዎች ውስጥ የተቈጠረ ሆነ ። ይህም አባት ጢሞቴዎስ የቀረ ዘመኑን መንጋዎቹን ሁልጊዜ እያስተማረ በቀናች ሃይማኖትም ላይ እያጸናቸው ኑሮ በሰላም በፍቅር አንድነት አረፈ ።

በዚህችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ አራተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ዘካርያስ አረፈ ። ይህም አባት ከእስክንድርያ ሰዎች ወገን ነው በቤተ ክርስቲያንም ንብረት ሁሉ ላይ መጋቢነትና ቅስና ተሾመ እርሱም በተጋድሎ የጸና ንጹሕ ድንግል ነው በጠባዩም የዋህ ቅን የሆነ በዕድሜውም የሸመገለ ነው ።
ሊቀ ጳጰሳት አባ ፊላታዎስም በአረፈ ጊዜ ለዚች ሹመት የሚገባ ሰው ይመርጡ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር ኤጲስቆጶሳት ተሰበሰቡ እነርሱም ለዚች ሹመት ስለሚሻል ሰው በወንጌላዊ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው እየተነጋገሩ ሳሉ እነሆ አንድ ሰው መማለጃ በመስጠት ያለ ኤጲስቆጶሳት ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ ከንጉሥ የመልእክት ደብዳቤ ይዞ እንደሚመጣ ከእርሱም ጋር ከንጉሥ የተቀበላቸው ጭፍሮች እንዳሉ ሰሙ ። ኤጲስቆጶሳቱም የአባቶቻችንን የሐዋርያትን ሥርዓት በመተላለፍ መማለጃ በመስጠት ስለሚደረገው የሊቀ ጵጵስና ሹመት አዘኑ ። ስለዚህም እርሱ ራሱ የመረጠውን ይሾምላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ተግተው በማዘውተር የሚጸልዩና የሚማልዱ ሆኑ ።
እነርሱም እግዚአብሔርን እየለመኑ ሳሉ እነሆ ይህ አባት ዘካርያስ ከቤተ ክርስቲያን ጫፍ በመሰላል ሲወርድ ሆምጣጤ የተመላ እንስራ በእጁ ይዞ ነበር እግሩንም አድጦት ከመሰላሉ ጫፍ እስከታች ወደቀ እንስራውንም እንደያዘ ፈጥኖ ተነሣ እንስራውም አልተሰበረም ሆምጣጤውም አልፈሰሰም ።
ኤጲስቆጶሳቱም ይህን ምልክት በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ የአገሩንም ሰዎች ትንሹንም ትልቁንም ስለርሱ ጠየቋቸው እነርሱም ጽድቁንና ትሩፋቱን ተናገሩ ስለርሱም መሾም ሁሉም ተስማምተው ይህን አባ ዘካርያስን በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት ።
ከዚህም በኋላ ብዙ መከራና ኀዘን በላዩ ከግብጽ ንጉሥ እልሐክም ዘንድ ደረሰበት ይህም ገዢ ማለት ነው ። በዚያም ወራት ከአባ መቃርስ ገዳም አንድ መነኲሴ ወደርሱ መጥቶ ኤጲስቆጶስነት ሹመኝ አለው አባ ዘካርያስም ልጄ ሆይ ታገሥ አባቶቻችን ሐዋርያትም ያዘዙትን ሥርዓት አትተላለፍ ግን ወደ ገዳምህ ተመልሰህ ስለ ነፍስህ ድኅነት ተጋደል እግዚአብሔርም የፈቀደው ይሁን አለው ።
ይህንንም በጎ ምክር በሰማ ጊዜ ያ መነኵሴ ተቆጣ በልቡም ሰይጣን አደረበትና ወደ ግብጽ ንጉሥ ሒዶ በሐሰት ነገር አባ ዘካርያስን ወነጀለው ንጉሡም የከበረ አባት ዘካርያስን ይዞ አሠረው ። ከዚህም በኋላ ተነጣጥቀው ይበሉት ዘንድ ለአንበሶች ጣለው አንበሶችም ከቶ አልቀረቡትም ንጉሡም የአንበሶቹን ጠባቂ ተቆጣ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጉቦ የተቀበለ መስሎት ነበርና ። ከዚህም በኋላ አንበሶቹን አስራባቸውና ሊቀ ጳጳሳቱን የላም ደም ቀብቶ በድጋሜ ለአንበሶች ጣለው እነርሱም ከቶ አልቀረቡትም ንጉሡም አደነቀ ከአንበሶች መካከልም እንዲአወጡት አዘዘ።
ከዚህም በኋላ ሦስት ወር አሠረው ሁል ጊዜም እንዲህ የሚለው ሆነ የክርስቲያንን ሃይማኖት ትተህ ወደእኛ ሃይማኖት ካልገባህ አለበለዚያ እኔ አሠቃይቼ በሰይፍ እገድልሃለሁ ። ዳግመኛ ለአንበሶች እጥልሃለሁ ወይም ከእሳት ውስጥ እጨምርሃለሁ የከበረ አባ ዘካርያስ ግን በሃይማኖቱ በመጽናት ምንም ምን አልፈራም ።
ሁለተኛም ብዙ ቃል ኪዳኖችን ገባለት እንዲህም አለው ትእዛዜን ተቀብለህ ወደ ሃይማኖቴ ብትገባ እኔ ብዙ ሀብት እስጥሃለሁ በሁሉ መሳፍንትም ላይ መስፍን አድርጌ እሾምሃለሁ ቅዱስ አባት ዘካርያስም በዓለም ያለ መንግሥትን ሁሉ ብትሰጠኝም የቀናች ሃይማኖቴን አልተውም ብሎ መለሰለት ።
ከዚህም በኋላ ጥቂት ቀን አሥሮ ለቀቀው ከእሥር ቤትም ወጥቶ አባ ዘካርያስ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ ። ንጉሡንም ስለ መፍራት ከእርሱ ጋር የሔዱ ብዙ ኤጲስቆጶሳት ነበሩ በሚገዛቸው አገሮች ሁሉ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉንም እንዲአፈርሱአቸው ንጉሥ አዞ ነበርና ። ታላቅ ሥቃይንም እያሠቃየ ብዙዎች ክርስቲያኖችን ከሃይማኖታቸው አወጣቸው የክርስቲያንም ወገኖች በዚህ መከራ ውስጥ ዘጠኝ ዓመት ኖሩ ።
ከዘጠኝ ዓመትም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝቡን ይቅር አለ ቊጣውንም መለሰ መከራውንም ሁሉ ከላያቸው አስወገደ ንጉሡ በሚገዛቸው አገሮች በሁሉ ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ ከእነርሱም የወሰዱትን ገንዘባቸውን ሁሉ የምድራቸውን ጒልት እንዲመልሱላቸው ንጉሡ አዘዘ ።
ከዚህም በኋላ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩ ከፊተኛውም እጅግ የተሻሻሉ ሁነው ዳግመኛ ታደሱ ይህም አባት ዘካርያስ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ ክርስቲያኖችም በአብያተ ክርስቲያኖቻቸው በሚጸልዩና በሚቀድሱ ጊዜ ያለ ሥጋት ደወሎቻቸውን እንዲደውሉ ንጉሥ አዘዘ ።
ክርስቲያኖችም በታላቅ ደስታ የሚኖሩ ሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ሁሉ የቀና ሁኗልና ይህም አባት አብያተ ክርስቲያናትን እያሠራ የሚያሻቸውንም እያሰበ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ ።
በአንዲት ዕለትም በሥጋው ለምጽ ያለበት ስሙ መርቆሬዎስ የሚባል ኤጲስቆጶስ ወደርሱ መጣ አባ ዘካርያስም በትሕትና በቅን ልቡና እንዲህ አለው ። ወንድሜ አባ መርቆሬዎስ ሆይ በአንተ ላይ ስለደረሰ ስለዚህ ደዌ እኔም በጸሎቴ ረዳሃለሁ እግዚአብሔር ሙሴን በፍርድ ውስጥ ለማንም አታድላ ያለውን አንተ ታውቃለህ ስለዚህ ይህ የለምጽ ደዌ በላይህ እያለ ክህነት አይገባህም መጽሐፍ ርኲስ ነው ብሎታልና አለው ኤጲስቆጶሱ አባ መርቆሬዎስም አለቀሰና አባቴ በጸሎትህ ርዳኝ አለው ።
ከዚህም በኋላ ከእርሱ ዘንድ ወጥቶ ሔደ በሀገረ ስብከቱ ወዳለች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባ ከዚህም ደዌ ታነጻው ዘንድ ወደርሷ በመጸለይና በመማለድ እያለቀሰ በእመቤታችን ማርያም ሥዕል ፊት ቆመ ከሰኞ ጥዋት ጀምሮ እንዲህ እያደረገ ቀንና ሌሊት እየጸለየና አየጾመ ኖረ ።
በረቡዕ ዕለትም በዘጠኝ ሰዓት ደክሞት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ከበላዩ ካለችበት ግድግዳ ላይ ራሱን አስጠግቶ አንቀላፋ ። በእንቅልፉም ውስጥ ሳለ የሥዕሊቱ እጅ ሥጋውን ሲዳሥሥ አየ በዚያንም ጊዜ ነቅቶ ሥጋው ከለምጹ ነጽቶ አገኘው ታላቅ ደስታም አደረገ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም አመሰገነው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም አመሰገናት ረድኡም ሲመጣ ና ልጄ ሆይ ሥጋዬን እይ እመቤቴ ማርያም ከደዌ አንጽታኛለችና አለው በዚያችም ቤተክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እስከ ቀዳሚት ሰንበት ድረስ ኖረ።
ከዚህም በኋላ ተነሥቶ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዘካርያስ ሔደ በዕለተ እሑድ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያለ በእርሱ ላይ የሆነውን አስረዳው እንዲህም አለው ይህ ሁሉ የተደረገልኝ በከበረች ጸሎትህ ነው ። የከበረ አባ ዘካርያስም እንዲህ ብሎ መለሰለት እግዚአብሔር ንጹሕና ቅን የሆነ ልቡናህን ተመልክቶ ልመናህንና ዕንባህንም ተቀብሎ ከደዌህ አነጻህ አሁንም ከተቀበልከው ጸጋ እንባረክ ዘንድ ቀድሰህ ሥጋውንና ደሙን ልታቀብለን ይገባሃል ። ያን ጊዜም መሥዋዕትን ሠርቶ ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው በቤተ ክርስቲያን ያሉትም ሁሉ ከእርሱ ቡራኬ ተቀበሉ ስለዚች ምልክትም አደነቁ ድንቆች ተአምራትን የሚያደርግ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ።
ሁለተኛም አንድ ዲያቆን ወደ አባ ዘካርያስ መጥቶ ሰገደለት በፊቱም አለቀሰ እግሮቹንም እየሳመ እንዲህ አለው አባቴ ሆይ ራራልኝ እኔ ተሳስቼ በኃጢአት ወድቄአለሁና ወዲያውኑ ሥጋዬ ሁሉ ለምጽ ሆነ ። አባ ዘካርያስም ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር ፊት በድካም ላይ መጽናት ይቻልሃልን አለው አዎን አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ።
በዚያንም ጊዜ በእርሱ ዘንድ በጨለማ ቤት ዘጋበትና እንዲህ ብሎ አዘዘው ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ በመቆም በቀንም በሌሊትም ስለ ኃጢአቱ እየተጸጸተ ወደ እግዚአብሔር በጸሎት እንዲማልድ አባ ዘካርያስም ከሦስት ቀኖች በኋላ ጥቂት እንጀራ በሚዛን መዝኖ ጥቂት ውኃም ሰጠው ሦስት ሱባዔዎችም እንዲህ አድርጎ ሥጋውን ጐበኘ ለምጹንም አገኘው በወር መጨረሻም ጐበኘው ለምጹን በሥጋው ላይ አገኘ።
ልጄ ሆይ በርታ አትፍራ አለው አርባ ቀኖችም ከተፈጸሙ በኋላ ጐበኘው ሥጋው ከለምጹ ነጽቶ አገኘው ዘይትንም ቀባው ልጄ ሆይ እነሆ ድነሃል ነፍስህን ጠብቅ ከእንግዲህም ዳግመኛ ወደ ኃጢአት ሥራ እንዳትመለስ ተጠበቅ አሁንም በሰላም ወደ ቤትህ ግባ አለው እርሱም የተመሰገነ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ገባ ።
እግዚአብሔርም በዚህ አባት እጆች ድንቆች ተአምራትን አደረገ በሹመቱም ወንበር ሃያ ስምንት ዓመት ከኖረ በኋላ በሰላም አረፈ ይኸውም ከንጹሐን ሰማዕታት ዘመን በሰባት መቶ ስልሳ ነው ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages