ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 11 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 11

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር አስራ አንድ በዚች ቀን የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተጠመቀ፣ የከበረ #እንጣልዮስ በሰማእትነት ሞተ፣ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ #አባ_ዮሀንስ አረፈ፣ የከበረ ተጋዳይ ለሆነ አባት #አባ_ወቅሪስ የእረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡


ጥር አስራ አንድ በዚች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአጥማቂው ዮሀንስ ዘንድ በዮርዳኖስ ወንዝ ውኃ ተጠመቀ።
ይችም እለት በዮናኒ ቋንቋ ኤጲፋንያ ትባላለች ትርጓሜውም "መለኮት የተገለጠበት ማለት ነው። "ልዩ የሆነች የሶስትነቱን ምስጢር ገልጦባታልና አብ ከሰማይ ሆኖ የምወደው በርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት እያለ ሲመሰክር ወልድም በዮርዳኖስ ወንዝ ቁሞ ሳለ መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል በወልድ ራስ ላይ ሲቀመጥ ይህ አጥማቂው ዮሀንስ እንደመሰከረ።
እንዲህ ሲል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከውኃ በወጣ ጊዜ ወዲያውኑ ሰማይ ተከፈተ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወረዶ በጌታችን ራስ ላይ ተቀመጠ ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ነው እርሱንም ስሙት።
በዚች እለት ጌታችን ራሱን ገልጦአልና ከዚህ በፊት ሰላሳ አመት ያህል ራሱን አልገለጠም ነበር ግን በዚች እለት ለእስራኤል ልጆች ራሱን ገለጠ እነሆ የእግዚአብሔር በግ የአለምን ኃጢአት የሚያስወግድ ብሎ መጥምቁ ዮሀንስ እንደገለጠው የከበረ ወንጌል ምስክር ሆነ።
እኔ አላውቀውም ነበር ነገር ግን እስራኤል ያውቁት ዘንድ በውኃ ላጠምቅ ስለዚህ መጣሁ አለ። በዚህም በዓል የእግዚአበሄር ልጅ የክርስቶስ የጌትነቱ ክብር ተገልጧል እርሱም የአለሙን ሁሉ ሀጢአት ለማስወገድ የሚሰዋ የእግዚአብሔር አማናዊ በግ ነው።
ስለዚህም ይህ በዓል በክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ዘንድ የከበረና ከፍ ከፍ ያለ ሆነ በርሱም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ በአከበረው ውኃ ይነፁበታል የተቀበሉትንም ንፅህና ጠብቀው ቢኖሩ በውስጡ የኃጢአታቸውን ስርየት ያገኛሉ።
ስለዚህም ከክፉ ነገር ሁሉ ተጠብቀን የፈጣሪያችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የቸርነቱን ብዛት ልናመሰግን ይገባናል እርሱ ስለ እኛ ሰው ሆኖ ከኃጢአታችን አድኖናልና።
ለእርሱም ከቸር አባቱ ሕይወት ከሆነ መንፈስ ቅዱስም ጋር ክብር ምስጋና ስግደትም ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን ከፋርስ አገር ሰዎች ወገን የሆነ የከበረ እንጣልዮስ በሰማእትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ በሮም አገር የሰራዊት አለቃ መኰንን ሆኖ አስራ አምስት አመት ኖረ።
የክብር ባለቤት ክርስቶስን ንጉስ ዲዮቅልጣኖስ በካደው ጊዜ ይህ ቅዱስ ሰማያዊ መንግስትን መረጠ የዚህ የኃላፊውንም አለም ክብር ንቆ ተወ መጥቶም በከሀዲው ንጉስ ፊት በመቆም እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ ንጉሱም ስለ ድፍረቱ ደነገጠ።
ከፋርስ ሰዎችም ከታላላቆቹ ወገን እንደሆነ በአወቀ ጊዜ በሽንገላ በጎ ነገርን ተናገረው ምናልባት ከጌታ ክርስቶስ ሀይማኖት ልቡን መመለስ ቢችል ብሎ ለሰራዊት አለቃ ለኅርማኖስ ሰጠው። ኅርማኖስም ጌታ ክርስቶስን ከማምለክ ሀሳቡን ሊአስለውጠው ባልተቻለው ጊዜ ወደ ንጉሱ መለሰው እርሱም በየራሱ በሆነ ስቃይ አሰቃየው።
ጌታችንም መልአኩን ልኮ ከመከራው ሁሉ ያፀናውና ያረጋጋው ነበር በብዙ በተለያዩ ስቃዮችም እየተሰቃየ ለረጅም ጊዜ ኖረ ብዙ ጊዜም ሰቅለውታልና ከዚያም አርደው ቆዳውን ገፈፉት ምላሱንም ቆረጡት ለነጣቂዎች አውሬዎችም ጣሉት በጨለማ ቤትም ዘጉት ሶስት ጊዜም ነፍሱን አሳለፈ እግዚአብሔርም አስነሳው።
ዲዮቅልጥያኖስም ማሰቃየቱን በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡት የሰማእትነት አክሊልንም በመንግስተ ሰማያት ተቀበለ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት የከበረ አባ ዮሀንስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባ አራተኛ ነው። ይህም አባት ሊቀ ጵጵስና ከመሾሙ አስቀድሞ ወደ ህንድ አገር በባሕር ላይ በመርከብ እየሄደ ሁልጊዜ የሚነግድ ነጋዴ ሆኖ ነበር ከዚያ ፊት ግን በምስር ሀገር በሰማዕቱ በቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን በፀሀፊነት የሚያገለግል ዲያቆን ነው ፀሀፊነቱንም ትቶ የሚነግድ ሆነ።
በዘጠኝ መቶ አራት አመተ ሰማእታት የካቲት አራት በእሁድ እለት ኤጲስቆጶሳቱ መርጠው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በመልካም አጠባበቅም መንጋውን የሚጠብቅ ሆነ።ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ ከመሾሙ በፊት ሀያ ሽህ ያህል የወርቀወ ዲናር ነበረው ከመሞቱ በፊት ለድኆችና ለችግረኞች ለአብያተ ክርስቲያን ለገዳማትም ሁሉን ገንዘቡን ሰጥቶ ጨረሰ።
በሹመቱም ወራት ከህዝብ ምንም ምን እጅ መንሻ አልተቀበለም በሹመቱም ሀያ ስምንት አመት ኖረ በዘጠኝ መቶ ሰላሳ ሁለት አመተ ሰማእታት በዚች ቀን በጥምቀት በአል አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም እለት የከበረ ተጋዳይ ለሆነ አባት አባ ወቅሪስ የእረፍቱ መታሰቢያ ነው። ይህም ቅዱስ አባት በባስልዮስ ዘንድ አደገ እርሱም ቅስና ሾመው ይህም ቅዱስ በደም ግባቱ በላህዩ ደስ የሚል ፊቱም የሚያምር ነበር።
በቀድሞው ግብሩ ወጣት ሆኖ ሳለ የሹሙን ሚስት ተመኛትና እጅግም ወደዳት እርሷም ወደደችው ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ፍላጎታቸውን ይፈፅሙ ዘንድ ተማከሩ ለዚህም ነገር ሲዘጋጁ በህልሙ ራእይን አየ። እርሱ ታስሮ በፍርድ አደባባይ ቆሞ ነበር ሌሎችም ብዙዎች እስረኞች ከእርሱ ጋር አሉ ስለ በደላቸውም እያንዳንዳቸውን ይመረምሯቸው ነበር እርሱም በልቡ የታሰርኩት በምን ይሆን ባሏን ልነጥቀው ስለፈለግሁ ስለዚያች ሴት ነውን እርሱ ከስሶኝ ወደዚህ ታላቅ ግዳጅ ላይ አደረሰኝን አለ።
በዚህም ነገር እየተሸበረ ሳለ በቀድሞ ወዳጁ አምሳል አንድ ሰው መጣና የታሰርከው በምንድን ነው? አለው ስለ ሀጢያቱ ስለ አፈረ ሊሰውረው ወደደ ግድ ባለውም ጊዜ እንዲህ ነገረው ወዳጄ ሆይ እገሌ ስለሚስቱ የከሰሰኝ ይመስለኛል ስለዚህም ፈርቼ እሸበራለሁ በወዳጁ አምሳል ወደርሱ የመጣው መልአክም ወዳጄ ሆይ ይህን ስራ እንዳትሰራ ወደርሱም እንዳትመለስ በቅዱስ ወንጌል ማልልኝ እኔም ዋስ እሆንሀለሁ አለው በወንጌልም ማለለት በዚያንም ጊዜ ከእንቅልፉ ነቃ ያየው ራእይም እውነት እንደሆነ አወቀ።
ስለዚህም አገሩን ትቶ ወደ እስክንድርያ ሄደ በዚያም ስሟ ኄራኒ የሚባል እግዚአብሄርን የምትፈራ አንዲት ሴት አገኘ በተነጋገሩም ጊዜ የልቡን ሁሉ ነገራት እርሷም እነዚህን ያማሩ ልብሶችህን ተው ተርታ ልብስንም ለብሰህ እግዚአብሄርን አገልግለው አለችው።ከዚያም ወደ በርሀ ሄደ ከብዙ ተጋድሎ የተነሳ ሆዱ እንደ ድንጋይ እስከ ደረቀ ድረስ ቅጠላቅጠል እየበላ ኖረ ጌታችንም ወደርሱ መጥቶ ፈወሰው።
አጋንንትም ስለሚፈታተኑትና ስለሚያሰቃዩት እርሱ በፆምና በፀሎት በመጋደል በክረምት ዝናብ እየወረደበት ራቁቱን ቆሞ ያድራል በበጋም በቀን የፀሀይ ትኩሳት በሌሊትም ቁር ሰማያዊ ሀብት እስከተሰጠው ድረስ መላእክትም ወደርሱ መጥተው ሰማያዊ ኅብስትን ሰማያዊ መጠጥን ይመግቡት ነበር።
የተሰወሩ ራእዮችን ያውቅ ዘንድ ተገባው ሶስት ድርሰቶችንም ደረሰ አንዱ በበረሀ ስለሚኖሩ ሁለተኛው በአንድነት ስለሚኖር መነኮሳት ሶስትኛው ስለካህናት ነው።
በአንዲት አለትም ስሙ ቡላ የሚባል ገዳማዊ ወደርሱ መጥቶ እርስ በርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ አባ ብላም እንዲህ አለው ወንድሜ ወቅሪስ ሆይ በቻህን አትሁን ጥቂት ወንድሞችን ካንተ ጋር አኑር እንጂ ያረጋጉህ ዘንድ ከሰይጣንም ጦርነት እንድትድን እንዲሁም አደረገ።
ከዕለታትም በአንዱ ሀይማኖትን በለወጡ በአርዮስ በንስጥሮስና በማኒ አምሳል ሆነው ሶስት ሰይጣናት ወደርሱ መጥተው በሀይማኖታቸው ተከራከሩት እርሱም በቅዱሳት መፃህፍት ቃላትና ሀይማኖታቸው በቀናች አባቶች ትምህርት ረታቸውና አሳፈራቸው።
ብዙዎችም የሆኑ ድንቆች ተአምራቶችን የሚሰራ ሆነ በአንዲትም እለት ወደ ቤተ ክርስቲያን በሄደ ጊዜ ተዘግታ አገኛት መነኮሳቱም መክፈቻ ፈልገው አላገኙም በላይዋም በአማተበ ጊዜ በሩ ተከፈተለት።
አባትህ ሞተ ብለው በነገሩት ጊዜ ዋሽታችኃል አባቴስ የማይሞት ሰማያዊ ነው አለ ተብሎ ስለርሱ የሚነገርለት ወቅሪስ ይህ ነው ዜንውም በገድሉ መፅሀፍና የአባቶች ዜና በተፃፈበት መፅሀፍ አለ።ከዚህም በኋላ ፈፅሞ በአረጀ ጊዜ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ሄደ።
አምላከ ቅዱሳን በጥምቀቱ ይቀድሰን:: ከበረከተ ጥምቀቱም ያድለን::

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages