ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 12 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 12

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ዐሥራ ሁለት በዚችህም ቀን የክብር ባለቤት ጌታ #በቃና_ዘገሊላ ለሰራ ተአምር መታሰቢያ ነው፣ የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል_ቅዱስ_ያዕቆብ_እሥራኤልን የረዳበት ነው፣ ኃይለኛ የሆነ #ቴዎድሮስ_በናድሌዎስ በሰማእትነት ሞተ።


ቃና ዘገሊላ በቀጥታ ትርጉም የገሊላዋ ቃና ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት(ጥር 12) ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ይህ በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ በድምቀት የሚከበር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዳራ ያለው በዓል ነው፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ሀገር ክፍል በምትሆን ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡
የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው የካቲት 23 ቀን ነው፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው የየካቲቱን በዓል ወደ ጥር 12 አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር ለማስኬድ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡
በቃና ዘገሊላ ምን ተፈፀመ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገሊላ ክፍል በምትሆን በቃና በተደረገ ሠርግ ላይ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ ‹‹ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ›› ‹‹የጌታ የኢየሱስ እናትም በዚያ ነበረች›› እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ (ዮሐ 2÷1) እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሰርጉ ላይ ታድማ ነበር፡፡ እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ሥርዓት ስላልሆነ፤ በተጨማሪ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታ ጋር በሰርጉ ታድመዋል፡፡ ይህም መምህርን ጠርቶ ደቀ መዛሙርቱን መተው ሥርዓት ስላልሆነ (ተገቢ ስላልሆነ) ነው፡፡ የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት በሠመረ ባማረ ሁኔታ እየተከናወነ ሳለ ድንገት የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ አስተናባሪዎቹ በጭንቀት ባሕር ሰጥመው ምን እንደሚያደርጉ ግራ በገባቸው በጠበባቸው ጊዜ የችግር ጊዜ ደራሽ የኃዘን ጊዜ አፅናኝ የሆነችው የአምላክ እናት ድንግል ማርያም ቅዱስ ገብርኤል እንደተናገረ በፀጋ የተሞላች ናትና (ሉቃ 1÷28) ማንም ሳይነግራት የልቦናቸውን ጭንቀት አይታ፣ ጎዶሎአቸውን ተመልክታ ወደ ልጇ ወደ ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወር ብላ ‹‹ወይንኬ አልቦሙ›› ‹‹ወይን ጠጅ እኮ አልቆባቸዋል›› አለችው፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ ‹‹የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ›› አለቻቸው፡፡ ጌታም በቦታው የነበሩ ስድስት ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዛቸው፡፡ ውኃውንም ወደ ወይን ለውጦ ለሊቀ ምርፋቅ (ለአሳዳሪው) እንዲሠጡት አዘዘ፡፡ አሳዳሪውም ወደ ወይን የተለወጠውን ውኃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፡፡ ከወዴት እንደመጣ ስላላወቀ ሙሽራውን ‹‹ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ያቀርባል አንተ ግን መልካሙን እስከ አሁን አቆይተሃል›› አለው፡፡ ወይኑም በሰው እጅ ያይደለ በሠማያዊው አባት የተዘጋጀ ስለነበር ጣፋጭ እና ልብን የሚያስደስት ነበር፡፡
‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?››
ይህንን የጌታችንን ንግግር ብዙዎች በዘመናችን ሲሣሣቱበት ይታያል ፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን ይህንን የተናገረው እናቱን ሊያቃልል ሽቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ይህን አረፍተ ነገር መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተናጠል ስንመለከት ‹‹አንቺ ሴት›› ሴት የሚል ቃል የፆታ መጠሪያ ነውና በፆታዋ አክብሮ ሲጠራት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሔዋን ከአዳም በተፈጠረች ጊዜ አዳም እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር ‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል›› (ዘፍ 2÷23) በመሆኑም ጌታ አንቺ ሴት ማለቱ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ መንሣቱን ለማጠየቅ ነው፡፡ ‹‹ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለውን ዐረፍተ ነገር የንቀት ስለመሰለን ብቻ ‘ የዳቦ መልክ የያዘ ድንጋይ፤ ዳቦ ነው እንደማይባል’ የንቀት ንግግር ነው ልንል አይገባም፡፡ ጌታም እንዲህ ሲል ውኃውን ወይን አድርግላቸው ብትይኝ አላደርግም እልሽ ዘንድ ከአንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ ማለቱ ነው፡፡ ይህ ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጽፎ እንደሚገኘው በዕብራውያን ዘንድ የተለመደ የአነጋገር ዘይቤ ነው፡፡ለአብነት ይሆን ዘንድ ጥቂት ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፡-
የሰራፕታዋ ሴት በ 1ነገ 17÷18 ላይ እንደምናገኘው ልጇ በሞተባት ጊዜ ኤልያስን በሐዘን በለቅሶ እንዲህ ብላ ነበር ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› ትወልጃለሽ ብለህ የወለድኩት ልጅ ምን በድዬህ ምንስ አስከፍቼህ ሞተብኝ? ስትል ነው እንጂ አባባሏ የንቀት ወይም የማቃለል አይደለም፡፡
በጌርጌሴኖን አንድ አጋንንት ያደረበት ሰው ወደ ጌታችን ቀርቦ ‹‹የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?›› አለው፡፡ እውነት ይህ ቃል የንቀት ይመስላልን? የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ብሎ አምላክነቱን እየመሰከረ ሊያቃልለው ይችላልን? ደግሞስ ላለመጥፋት ፍፁም የሚፈልግ ሰው ሊያድነው ሥልጣን ያለውን ሊንቅ ይችላልን? አይችልም፡፡ ይህ ቃል የሚያመለክተው ምን አጠፋሁ ስለምን ልታጠፋኝ ወደድክ በማለት መፍራት መራዱን ነው፡፡ (ሉቃ 8÷28-29) ስለሆነም ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለው የንቀት አለመሆኑን ከሁለቱ ጥቅሶች መረዳት እንችላለን፡፡ እመቤታችን እና ጌታ በንግግር አልተቃረኑም ንግግራቸው የፍቅር ነበር፡፡ ንግግራቸው የመግባባት ስለነበር ነው ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› ካላት በኋላ ዘወር ብላ አገልጋዮቹን የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ያለችው፡፡
‹‹ጊዜዬ አልደረሰም›› ጌታ ይህን ቃል የተናገረው ስለ ብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ ጊዜዬ አልደረሰም ማለቱ፡-
እግዚአብሔር ነገሮችን የሚያከናውንበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ በመሆኑም ይህን ተአምር የምፈፅምበት ጊዜዬ አልደረሰም ሲል ነው፡፡
አንድም ጋኖቹ ውስጥ የቀረ ወይን ስለነበረ ባለው ላይ አበርክቶ እንጂ ውኃውን ወደ ወይን አልለወጠውም እንዳይሉ ወይኑ ከጋኑ ተንጠፍጥፎ እስኪያልቅ ድረስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡
አንድም ይሁዳ ከሠርግ ቤት ወጣ ብሎ ነበርና ወደ ሠርግ ቤቱ እሰኪመለስ ጊዜዬ አልደረሰም አለ፡፡ ይሁዳ በቃና የገለጠውን ምስጢር ለእኔ ስላላሣየኝ ተከፍቼበት ከተአምራቱ ቢያጎድለኝ በሞቱ ገባሁበት፤ ሸጥኩት እንዳይል ምክንያት ለማሳጣት እንዲህ አድርጓል፡፡
አንድም እውነተኛ የሕይወት ወይን የሆነውን ደሜን የምሠጥበት ጊዜ ገና ነው ሲል፡፡
የድንግል ማርያም አማላጅነት በገሊላ ቃና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሠርግ ቤት ሣለ የወይኑን ማለቅ የማይመለከት ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን የእናቱን የድንግል ማርያምን አማላጅነት ሊገልጥ ስለወይኑ ማለቅ እስክትነግረው ድረስ አንዳች ነገር አላደረገም፡፡ ኋላ ግን የጭንቀት አማላጅ ድንግል ማርያም ስለ ወይኑ አሰበች ልጇ ወዳጇን ለመነች፡፡ እርሱም የእናቱን ልመና ተቀብሎ ተአምራቱን ፈፀመ፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሣይነግሯት በልብ ያለውን የምታውቅ የምትመረምር እናት ናትና የሠርጉ አስተናባሪዎች ይሄ ጎደለ ሣይሏት የልቦናቸውን ሐዘን ተመልክታ ከልጇ ከወዳጇ አማልዳ የጎደላቸውን ሞልታለች፡፡ያስጨነቃቸውንም አርቃለች፡፡ በችግራቸው ደርሳላቸዋለች፡፡ ታዲያ ሳይነግሯት የልቡናን አይታ ከማለደች ስሟን ጠርተው ለሚለምኗትማ እንዴት አብልጣ አታማልድ?
(ቅዱስ እንጦንስ መንፈሳዊ ማህበር ብሎግ)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች ቀን የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ የሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው በዚች ቀን እስራኤል ወደ ተባለ ያዕቆብ እግዚአብሔር ልኮታልና ከወንድሙ ከኤሳውም ፈርቶ ሳለ አዳነው። ዮርዳኖስንም አሻግሮት ወደ እናቱ ወንድም ወደ ላባ ሔደ።
እርሱም ሁለቱን ልጆቹን ልያንና ራኄልን አጋባው ከዚህም በኋላ ከብዙ ገንዘቡና ከልጆቹ ጋር መንገዱን እየጠረገና እያቀና በሰላም በጤና ወደ አገሩ መለሰው ወንድሙ ኤሳውም በፍቅር በሰላም ተቀበለው ስለዚህም የሊቀ መላእክት ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ሆነ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም እለት የምስራቅ ሰው ፅኑእ ኃይለኛ የሆነ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ በሰማእትነት ሞተ።ይህም ታላቅ ተጋዳይ ከአንፆኪያ አገር ሰዎች ከመንግስት ወገን ነው የአባቱ ስም ሲደራኮስ ይባላል ለንጉሱም የጭፍራ አለቃ ነው የእናቱም ስምበጥሪቃ ይባላል ትርጓሜውም እመቤት ማለት ነው።
ንጉስ ኑማርያኖስም በጦርነት ውስጥ በሞተ ጊዜ ልጂ ዮስጦስም በጦርነት ውስጥ ነበር መንግስትም ያለ ንጉስ ነበረች የቴዎድሮስ አባት ሲድራኮስና ፋሲለደስ ዲዮቅልጣኖስ ነግሶ ሀይማኖቱን እስከ ካደ ድረስ የመንግስቱን አስተዳደር ይመሩ ነበር።
እርሱም ዲዮቅልጥያኖስ አስቀድሞ ከላየኛው ግብፅ የሆነ የዮስጦስ እኅት የንጉስ ኑማርዮስ ልጅ ሚስት ሆነችውና አነገሰችው ።ቅዱስ ቴዎድሮስም በአደገ ጊዜ በጦርነት ውስጥ ፈፅሞ ኃይለኛ ሆነ እርሱ ቅዱስ ቴዎድሮስ በሚሄድበት ጦርነት ሁሉ ጠላቶቹን ድል አድርጎ ያሳድዳቸዋል የፋርስ ሰዎችም ቴዎድሮስ ወደእናንተ መጣ ሲሏቸው ልባቸው ይሰበራል ይገዙለታልም ከእነርሱም ውስጥ ቴዎድሮስ የሮማውያን አምላክ ነው የሚሉ አሉ።
ለዲዮቅልጥያኖስ ክህደት ምክንያት የሆነ የቁዝ ንጉስን ልጅ ኒጎሚዶስን ሁለት ጊዜ የማረከው እርሱ ነው ከአባ አጋግዮስም ዘንድ በአኖረው ጊዜ አጋግዮስ በኒጎሚዶስ ክብደት ልክ ወርቅ አስመዝኖ ከቁዝ ንጉስ ተቀበሎ ወደ አባቱ መልሶታልና።
የከበረ ቴዎድሮስ በናድሌዎስም በጦርነት ቦታ ቡናቢስ በሚባል ወንዝ አጠገብ ሳለ ስሙ ለውንድዮስ የሚባል ወዳጅም ሳለ ከዚህም በኃላ በአንዲት ሌሊት ራእይን አየ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ መሰላል አለ። በላዩም በታላቅ ዙፋን ጌታችን ተቀምጧል በዙሪያውም የብዙ ብዙ አእላፍ መላእክት ያመሰግናሉ ከበታቹም ታላቅ ከይሲ ነበረ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም ቴዎድሮስ በናድሌዎስ ሆይ ከኔ ልጄ ልትሆነኝ ትወዳለህን አለው።
ቴዎድሮስም አቤቱ አንተ ማነህ አለ ጌታችንም እኔ የአብ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ነኝ ለአንተም ስለ ስሜ ደምህ ይፈስ ዘንድ አለህ አለው። በዚያንም ጊዜ ከቆሙት አንዱ ወሰደውና በእሳት ባህር ሶስት ጊዜ አጠመቀው ሁለመናውም በመንበሩ ዙሪያ እንደቆሙት ሆነ።
ቴዎድሮስ በናድሌዎስም ጌታችንን ከወዳጄ ከለውንድዮስ መለየት አልሻም አለው ጌታም እንዲህ ብሎ መለሰለት እርሱ ብቻ አይደለም ለቁዝ ሰራዊት መኮነን የሆነ ኒቆሮስም ነው እንጂ።
ከዚህም በኃላ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ አየ እነዚያ መላእክትም ለውንድዮስንና ኒቆሮስን አመጠቋቸው ከእሳት ባህር ውስጥ አጠመቋቸውና እነርሱን ለቴዎድሮስ በናድሌዎስ ሰጡት ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ራእይን እንዳየ ለለውንድዮስ ነገረው ፈፅሞ ደስ ብሏቸው ተሳሳሙ።
ከዚህም በኃላ የቁዝ የሰራዊት አለቃ ኒቆሮስ ወዳለበት የእግዚአብሄር ኃይል ተሸከመቻቸው እርሱም በደስታ ተቅብሎ አስቀድሞ እንደሚያውቃቸው አቅፎ ሳማቸው እንርሱም እንዳዪት ያንን ራእይ ነገራቸው እጅግም አደነቁ ኒቆሮስም ቴዎድሮስ በናድሌዎስን እኔንና ወንድሜ ለወንድዮስን ለአንተ በእጅህ እንደሰጡን ወንድሜ ሆይ እወቅ አለው።
ከዚህም በኃላ በዚያን ጊዜ ወደ ሰራዊቶቻቸው መጡ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ስሙ ደማቸውን ሊአፈሱ ተስማሙ።ከንጉሰ ቁዝ እንዴት እርቅ እንዳደረገ ሊጠይቀው ያን ጊዜ ንጉስ ወደ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ ላከ ድዮቅልጥያኖስ ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ጣኦታትን በአመለከ ጊዜ ስለዚህ የቁዝ ሰዎች እጅግ ደስ ብሏቸዋልና።
የከበረ ቴዎድሮስ በናድልዮስም ሰራዊቱን ነፍሱን ከሰይፍ ሊያድን የሚወድ ወደ ፈለገው ይሂድ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ግን መጋደልን የሚሻ ከእኛ ጋር ይኑር አላቸው።
ሁሉም በታላቅ ድምፅ አንተ የምትሞትበትን ሞት እኛ ከአንተ ጋራ እንሞታለን አምላክህም አምላካችን ነው ብለው ጪሁ የተመሰገነ ቴዎድሮስም ዳግመኛ ነገራችሁ እውነት ከሆነ ሁላችሁም ወደዚህ ወንዝ ወርዳችሁ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሶስት ጊዜ ተጠመቁ አላቸው።
በዚያንም ጊዜ ልብሳቸውን አውልቀው ወደ ወንዙ ወርደው እንዳላቸውም ተጠመቁ ከውኃውም ሲወጡ ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃልን ሰሙ ምስክሮቼ በርቱ ፅኑ አሸናፊዎችም ሁኑ እኔ ከናንተ ጋር እኖራለሁና።
የከበረ ቴዎድሮስ በናድሌዎስም ወደ አንፆኪያ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ ጊዜ ሰራዊቱን ከከተማ ውጭ ትቶ ከሁለቱ ወዳጆቹ ከለውንድዮስና ከኒቆሮስ ጋር ገባ ንጉስም በክብር ተቀበሎ ስለ ጦርነት ወሬ ስለ ሰራዊቱም ጠየቀው እርሱም የሆነውን ሁሉ ነገረው።
ከዚህም በኃላ ለአጶሎን ስለ መስገድ አወሳ የከበረ ቴዎድሮስ በናድሌዎስም ንጉሱን ገሰፀው ዘለፈውም እንዲሁም ወዳጆቹ ለውንድዮስና ኒቆሮስ ንጉሱን ረገሙት እርሱም ተቆጣ ለውንድዮስንና ኒቆሮስን ወደ ሚዶን አገር ወስደው በዚያ ያሰቃዩአቸው ዘንድ አዘዘ።
ኒቆሮስ የፋርስ ሀገር የሰራዊት አለቃ መኮንን ስለነበረ ከፋርስ ሰዎች የተነሳ ዲዮቅልጣኖስ ፈርታልና በዚያም ለውንድዮስንና ኒቆሮስን በአሰቃዩአቸው ጊዜ በዚች ቀን ጥር አስራ ሁለት የሰማእትነት አክሊልን ተቀበሉ።
የከበረ ቴዎድሮስ በናድሌዎስን ግን ኮሞል በሚባል ታላቅ እንጨት ላይ አስተኝተው ቁጥራቸው መቶ ኃምሳ ሶስት በሆኑ በረጃጅም የብረት ችንካሮች እንዲቸነክሩት አዘዘ። እግዚአብሄርም መልአኩን ሚካኤልን ወደርሱ ልኮ በመከራው ሁሉ አፀናው።
በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለፀለትና የመረጥኩህ ቴዎድሮስ ሆይ ሰላም ይሁንልህ ይህን ሁሉ መከራ ስለ ስሜ ታግሰሃልና ብፁእ ነህ ይህን ከሀዲ ንጉስ ታሳፈረው ዘንድ እሊህን ብርቶች ከስጋህ ውስጥ አውጥቼ እንዳድንህ ትሻለህን አለው።
ቴዎድሮስ በናድሌዎስም ጌታችንን እንግዲህስ ስለ ከበረ ስምህ መሞት ይሻለኛል አለው። ሁለተኛም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጄ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ ሆይ እነሆ ሶስት አክሊላትን አዘጋጅቼልሀለሁ አንደኛው ስለ ድንግልናህ ሁለተኛው የዚህን አለም ክብር ትተህ መከራ ስለመቀበልህ ሶስተኛው ስለ ስሜ ደምህን ስለ አፈሰስክ ነው።አለው።
እኔም ቃል ኪዳንን ሰጠሁህ ስምህን ለሚጠራና መታሰቢያህን ለሚያደርግ በሁሉ ቦታ ከመከራው ሁሉ አድነው ዘንድ ለድኆችም ምፅዋት የሰጠውን ስለ አንተ በቤተ ክርስቲያን መባ ያገባውን የገድልህን መፅሀፍ የፃፈውንና ያፃፈውን ቤተ ክርስቲያንህንምየሰራውን ሁሉንም ኃጢአቱን ይቅር ብዬ መንግስተ ሰማያትን አወርሰዋለሁ። ጌታችንም ይህን ቃል ኪዳን ከሰጠው በኃላ ወደ ሰማይ አረገ ቴዎድሮስም ሶስቱን መላእክት አየ በዚያንም ጊዜ የከበረች ነፍሱን በእግዚአብሄር እጅ ሰጠ።
ቴዎድሮስ በናድሌዎስም ከአረፈ በኃላ ንጉስ ዲዮቅልጣኖስም ለጣኦታት ያሰግዱአቸው ዘንድ ወደ ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰራዊት የጣኦታቱን ካህናት ላከ ሁለተኛም ንጉስን የሚወድ ለአማልክት ይስገድ እያለ የሚዞር ዓዋጅ ነጋሪ አዘዘ።
የቴዎድሮስ በናድሌዎስ ሰራዊትም የነገስታት ንጉስ የጌቶች ጌታ ከሆነ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም ብለው ሁሉም ጮሁ ንጉሱም ሰምቶ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ ።ቁጥራቸውም ሁለት መቶ ኃምሳ እልፍ ሆነ በሰማእታት ራሶች ላይ አክሊልን የሚያኖሩ ብርሀናውያን መላእክት አየሩን ሞሉት።
አምላከ ቅዱሳን ወይነ ቃና ፍቅሩን ያሳድርብን:: ከድንግል እናቱ ምልጃና ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን::

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages