ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 13 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 13

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር አስራ ሶስት በዚች ቀን #አቡነ_ዘርዓ_ቡሩክ ኢትዮዽያዊ አረፉ፣ #ቅዱሳን_ሰባቱ_ደቂቅ አረፉ፣ #አባ_ነካሮ አረፈ።


ጥር አስራ ሶስት በዚች ቀን አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ኢትዮዽያዊ እረፍታቸው ነው። ከመወለዳቸው አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አባታቸው ደመ ክርስቶስ ዐይነ ሥውር የነበረ ሲሆን አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በተወለዱ ጊዜ ግን የአባታቸውን ዐይን አብርተውለታል፡፡ አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ገና በሰባት ዓመታቸው ነው ረቡዕና ዓርብ መጾም የጀመሩት፡፡ በዚሁ በሰባት ዓመታቸውም ‹‹ይህን ዓለም ክፋቱን እንዳላይ ዐይኖቼን አሳውርልኝ›› በማለት ዐይናቸውን እንዲያጠፋላቸው አምላካቸውን ለምነው እንደፈቃዳቸው ዐይነ ሥውር ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ከሰባት ዓመት በኋላ በ12 ዓመታቸው ጌታችን "ለዓለም የምታበራ ብርሃን አደርግሃለሁና ዐይንህም ይብራ" በማለት ዐይነ ብርሃናቸውን መልሶላቸው እንዲያዩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ዕድሜያቸው (በ12 ዓመታቸው) ሰባቱንም አጽዋማት ይጾሙ ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሁሉ ገለጠላቸው፡፡ መጻሕፍተ ብሉያትን፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትን፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን፣ መጻሕፍተ መነኮሳትን፣ አዋልድ መጻሕፍትን ሁሉ ገልጦላቸዋል፡፡ ከሟርት መጻሕፍት በቀር ያስቀረባቸው ነገር አልነበረም፤ የቅዱስ ያሬድንም ዜማ እንዲሁ ገለጠላቸው፡፡
ጻድቁ ከሁሉ ቅዱሳን በበለጠ ሁኔታ ዐሥራ ሁለት ክንፍ የተሰጣቸው ሲሆን በ12 ክንፎቻቸውም የሰማይን ደጆች ሁሉ ገሃነመ እሳትንም አልፈው በመሄድ ቀጥታ በሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ይቆሙ እንደነበር ቅዱስ ገድላቸው ይናገራል፡፡ እጅግ በሚደንቅና ከአእምሮ በላይ በሆነ ሁኔታ አባታችን ለሰባት ቀናት በየቀኑ ለሰባት ሰዓት ያህል በሲኦል ውስጥ ቆመው ይጸልዩ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ቅዱሳን በምልጃቸው ነፍሳትን ከሲኦል ሲያወጡ ነው የምናውቀው እንጂ እንደ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በሲኦል ውስጥ ገብቶ ጸሎት የጸለየ ጻድቅ እስካሁን እኔ አላጋጠመኝም፡፡
አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እንደ አባታችን ተክለሃይማኖት ለጸሎት በመቆም ብዛት አንድ እግራቸው እስኪሰበር ድረስ በብዙ መከራ ተጋድለዋል፡፡ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር መንበሩን ያጥኑ ዘንድ ከፈጣሪአቸው ታዘው አጥነዋል፡፡ ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ፍጥረታትን ከመፍጠር በቀር ያልሰጣቸው ሥልጣን የለም፡፡ "እግዚአብሔር ብፁዕና ቅዱስ ለሚሆን አባታችን ዘርዐ ቡሩክ "እኔ ከሥልጣኔ ሥልጣንን፣ ከክብሬም ክብርን፣ ከጥበቤም ጥበብን፣ ከተአምራቴም ተአምራትን፣ ከስጦታዬም ስጦታን፣ ከትዕግስቴም ትዕግስትን፣ ከፍቅሬም ፍቅርን፣ ከትሕትናዬም ትሕትናን፣ ከባለሟልነቴም ባለሟልነትን ሰጥቼሃለሁና ሁሉ ከሥልጣንህ በታች ሆኖ ይታዘዝልህ" የሚል እጅግ ድንቅ ቃልኪዳን ነው የሰጣቸው፡፡ ልዩ ልዩ ሀብታትን ሁሉ ሰጣቸው፡፡ "ለሥላሴ ከሚገባ ከስግደትና በቃልና በሥልጣን ፍጥረታትን ለመፍጠር በቀር ምንም ያልሰጠሁህ የለም" ብሎ ጌታችን በማይታበል ቃሉ እንደነገራቸውና ቃል እንደገባላቸው በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡ (የአባታችን ገድላቸው ከመጥፋቱ የተነሣ በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ ነጋዴዎች አንዱን ፍሬ ከ3 ሺህ ብር በላይ እየሸጡት ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ቲሊሊ የሚገኘው ገዳማቸው በድጋሚ አሳትሞታል፡፡
አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በወቅቱ በነበረው ገዥ ፊት በሐሰት ተከሰው ለ5 ዓመታት ያህል በእስርና በእንግልት ሲኖሩ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ምግብ የሚባል አይቀምሱም ነበርና ከእስር ሲፈቱ አምስት ዓመት ሙሉ ሲሰጣቸው ያጠራቅሙት የነበረው ምግብ ትኩስ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ያሳሰራቸውንም ንጉሥ ገና ሕፃን ሳለ እናቱ ልታስባርከው ወደ አባታችን ዘንድ ወስዳው ነበር፡፡ አቡነ ዘርዐ ቡሩክም ሕፃኑን ከባረኩት በኋላ ለእናቱ "ይህ ልጅሽ ወደፊት ይነግሣል በንግሥናው ዘመንም እኔን ያስርና ያንገላታኛል" ብለው ይህ እንደሚሆን አስቀድመው ትንቢት ተናግረው ነበር፡፡ እንዳሉትም ልጁ አድጎ ሲነግሥ ጭፍሮቹ "ንጉሥ ሆይ አንተን የማይወድ ለቃልህም የማይታዘዝ አንድ መነኩሴ አለ" በማለት ምንም እንኳን ንጉሡ ባያውቃቸውም በሐሰት ነገር ስለከሰሱለት በግዞት እንዲኖሩና እንዲታሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ጻድቁ በግዞት ሲወሰዱ "እነዚህን መጻሕፍቶቼን ለሰዎች አደራ ብሰጣቸው ይክዱኛል፣ ቤተ ክርስቲያን ባስቀምጣቸው ይጠፉብኛል" በማለት ሰባት መጽሐፎቻቸውን ለግዮን (ለዓባይ) ወንዝ አደራ የሰጡ ሲሆን ከ5 ዓመት በኋላ ከእስር ተፈተው ሲመለሱ በወንዙ አጠገብ እንደደረሱ ጸሎት ካደረጉ በኋላ "ግዮን ሆይ በእግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)" ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ አውጥተዋቸል፡፡ እንዲያውም አቧራውን ከመጻሕፍቶቻቸው ላይ እፍ ብለው አራግፈውታል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው የጠለቀው ምሳር እየተንሳፈፈ ወደ ኤልሳዕ እንደመጣ ሁሉ አሁንም እንዲሁ የቅዱስ አባታችን መጽሐፎች አብሯቸው ከነበረውና ዘሩባቤል ከሚባለው ደቀ መዝሙራቸው ጋር ወዳሉበት ተንሳፈው ሊመጡ ችለዋል፡፡ መጽሐፎቻቸውንም አብሯቸው ለነበረው ደቀ መዝሙራቸው ካሳዩት በኋላ እንዲይዛቸው ሰጥተውታል፡፡
የግዮን ወንዝ "ግሺ ዓባይ" ወይም "ዓባይ" እየተባለ መጠራት የጀመረው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ "ግዮን ሆይ በእግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)" ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ ካወጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ አባታችን በቦታው ላይ 30 ዓመት ሙሉ ቆመው ጸልየው ቦታውን የባረኩት ሲሆን ጌታችንም በቦታው ላይ ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ "ብፁዕ አባታችን ለግዮን ወንዝ መጽሐፎቹን በአደራ ሰጥተው በኋላም ከደቀ መዝሙራቸው ከዘሩባቤል ጋር መጽሐፎቹን ከግዮን ምንጭ ውስጥ ከተቀበለ በኋላ "በግዮን ውኃ ውስጥ ሳይረጥቡ በደረቅ መጽሐፎቼን የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን" ብሎ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡ "ያንጊዜም በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ፣ ሕመምተኞች ሁሉ ይዳኑብሽ፣ መካኖች ይውለዱብሽ" ብሎ ግዮንን በቃሉ መረቃት፣ በእጁም ባረካት፡፡ ብፁዕ አባታችንም በዚህች ቦታ ላይ ፈውስ፣ ረድኤት፣ በረከት ይደረግብሽ ብሎ ብዙ ዘመን ቆሞ ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ "ይህ በረከት፣ ረድኤት፣ ሀብት፣ ፈውስ እንደወደድህ እስከዘለዓለሙ በዚህ ቦታ ይሁንልህ" አለው" ተብሎ ነው በቅዱስ ገድላቸው ላይ የተጻፈው፡፡
ጻድቁ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ሌላው የሚታወቁበት "ብሄሞትና ሌዋታን" የተባሉ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት ዘንዶዎችን ጥርሳቸውን ቆጥረው ምላሳቸው ሲጣበቅ የዓለም ፍጻሜ እንደሚሆን አስቀድመው ያወቁ ድንቅ ነቢይ የሆኑ አባት በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህም እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት እንስሳት ሴትና ወንድ ሆነው ምድርን እንደመቀነት ከበው የያዙ ናቸው፡፡ ዝርዝር ታሪካቸው በመጽሐፈ አክሲማሮስ (ሥነ ፍጥረትን በሚያስረዳው መጽሐፍ) ላይ በስፋት ተጠቅሰዋል፡፡
አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ሳይጠመቁ ለሚሞቱ አሕዛብም ጭምር ትልቅ ቃልኪዳን የተሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ይኸውም በቅዱስ ገድላቸው ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል- "በሥራው ሁሉ ፍጹም የሆነና ገድሉ ያማረ ቅዱስ አባታችንን በአድማስ ራስ ቆሞ ምሥራቁንና ምዕራቡን፣ ሰሜኑንና ደቡቡን እንዲባርክ በአፉ እስትንፋስም የምሕረት እስትንፋስን እፍ እንዲል እስትንፋሱንም ከአድማስ እስከ አድማስ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ በእግዚአብሔር በቅዱስ ስሙ ያልተጠመቁ አሕዛብ በእስትንፋሱ ምክንያትና የምሕረት እስትንፋስን እፍ እንዲል እስትንፋሱንም ከአድማስ እስከ አድማስ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ በእግዚአብሔር በቅዱስ ስሙ ያልተጠመቁ አሕዛብ በእስትንፋሱ ምክንያት ልጅነት አግኝተው እንዲከብሩ በቃል ኪዳኑ ተማፅነው ሳይጠመቁ በሚሞቱበት ጊዜ "ይህ ከእኔ የተቀበልከው ቃልኪዳን ከጎኔና ከሰውነቴ እንደፈሰሰው ደሜ ይሁንላቸው" በማለት ለዓለም መድኃኒት አድርጎ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡
ዳግመኛም በቅዱስ አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ስም ከእግዚአብሔር ምሕረትን ለምነው በሚሞቱበት ጊዜ በውኃና በመንፈስ ቅዱስ እንደተጠመቁ ይሁንላቸው ብሎ ነገረው፡፡ በከበረና በገናና ስሙ የተጠመቁ ሕዝቡም በኃጢአታቸው በወደቁ ጊዜ በሥራቸውም በረከሱ ጊዜ በጻድቁ ጸሎት ቢማጸኑ በቃልኪዳኑ ቢያምኑ ይህ እስትንፋሱ የኃጢአት ማስተሠርያ ይሁናቸው ብሎታል፡፡ ጻድቁ አባታችንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሰማ ጊዜ ከዚያ በፊት ለሌሎች ያልተሰጠ ቃልኪዳን ተቀብሎ በአድማስ ላይ ቆመ፡፡ በዚያም ቆሞ መንፈሳዊ እስትንፋሱን በምድር ላይ እፍ አለ፡፡ ያም የሕይወት እስትንፋስ በአራቱ ማዕዘን ደርሶ በኃጢአታቸው መከራ የተቀበሉ ለበደላቸውም የተገዙ ሰዎች በፈጣሪያቸው ስም እንዲከብሩ ዓለሙን ሁሉ ባረከ" ይላል ቅዱስ ገድላቸው፡፡ ይህም የሚያሳያየው መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሰውን ልጆች ምን ያህል እንደወደዳቸውና በትንሽ ምክንያት የመዳንን መንገድ ያዘጋጀላቸው መሆኑን ነው፡፡
ሌላው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እሳቸው በባረኳት ምድርና በልጆቻቸው ላይ ችግርና ርኀብ እንደማይደርስባቸው ቃልኪዳን የተሰጣቸው ድንቅ አባት ናቸው፡፡ ይኸውም በቅርቡ እንኳን በ1977ቱ የርሃብ ዘመን በግልጽ ስለታየ ታሪክ ይመሰክረዋል፡፡ በዚህ ወቅት ከወሎና ከሌሎችም ቦታዎች በርሃብ ተሰዶ ጎጃም ለመጣው የሀገራችን ሕዝብ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ በረከት ከበቂ በላይ ነበር፡፡
ጻድቁ በጎጃም ባሕር ዳር አካባቢ ሁለት ቤተ ክርስቲያን አላቸው፡፡ የዓባይ ምንጭ መነሻ የሆነው ፈለገ ግዮን ግሽ ዓባይ ከባሕር ዳር ከተማ 174 ኪ.ሜ የሚርቅ ሲሆን ከባሕር ዳር ቲሊሊ፣ ከቲሊሊ ሠከላ በመሳፈር በቦታው ላይ ለብዙ ዘመን ቆመው በመጸለይ ታላቅ ቃልኪዳን የተቀበሉበትን እጅግ ተአምረኛና ፈዋሽ የሆነውን ጸበላቸውን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቦታው መጽሐፋቸውን ለዓባይ ወንዝ አደራ የሰጡበት ነው፡፡
ሌላኛው ቤተ ክርስቲያናቸው ከባሕር ዳር የሁለት ሰዓት የመኪና መንገድ ርቀት ላይ በምትገኘውና አዴት በምትባለው ቦታ የሚገኘው ነው፡፡ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ መካነ መቃብራቸውና ከሰማይ የወረደላቸው መስቀል እዚህ ይገኛሉ፡፡ ቦታውን የረገጠ ሁሉ ከመካነ መቃብራቸው ላይ እምነት ይወስዳል፣ በመስቀሉም ይባረካል፡፡ ነገር ግን ጻድቁ በቃል ኪዳናቸው መሠረት በዚህ መስቀላቸው የተባረከ ሁሉ ዲቁናን፣ ክህነትን መቀበል ስለሚችል ሴቶች አይባረኩበትም፡፡ መካነ መቃብራቸው ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከመቅደሱ ውጭ የሚገኝ ሲሆን ከመቃነ መቃብራቸው ላይ ያለው አፈር ሁልጊዜ እየፈላ መጠኑ ይጨምራል፡፡ ይህን የእምነቱን አፈር ቢዝቁት አያልቅም፣ ባዶ እንኳን ቢደረግ በተአምራት ሞልቶ ይገኛል፡፡ ለብዙ ሕመምተኞች ፍጹም ፈውስ የሆነው ይህ እምነት አጠቃላይ ሁኔታው ለዕይታ አመቺ ስለሆነ ይህንን ማንኛውም ሰው ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ማየትና እምነቱን ወስደው መጠቀም ይችላሉ፡፡
ጻድቁ አባታችን በ482 ዓመታቸው በዚህች ዕለት ጥር 13 ቀን በታላቅ ክብር ያረፉበት በዓላቸው በድምቀት ይከበራል፡፡ በዕረፍታቸው ዕለት ከቤተ ክርስቲያኑ አደባባይ ላይ አትሮንስ ወጥቶ ገድላቸው ይነበባል፡፡ ገድላቸው ሲነበብም ከአትሮንሱ ሥር ሰባት ጠርሙሶችና አንድ ማሰሮ ይቀመጥና በጠርሙሶቹ ውስጥ አንድ አንድ ስኒ ውኃ ይደረግባቸዋል፡፡ የአባታችን ቅዱስ ገድላቸው ሲነበብ ውኃው ይፈላል፣ ገድሉ ተነቦ እንዳለቀ ጠርሙሶቹና ማሰሮው በተአምራት ተሞልተው ይገኛሉ፡፡
ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ትንባሆን ስለሚጠጡ ሰዎች ታላቅ ምሥጢርን እንደነገራቸው በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡ ቅዱስ አባታችን በየቀኑ ለሰባት ሰዓት ያህል በሲኦል ውስጥ ቆመው በመጸለይ ብዙ ነፍሳትን ከእሳት ያወጡ ነበር፡፡ አንድ ቀን ብዙ ነፍሳትን ካወጡ በኋላ አንዲት ነፍስ ግን ከሲኦል ግደግዳ ጋር እንደ ሰም ተጣብቃ እምቢ አለቻቸው፡፡ አባታችንም ያቺን ነፍስ አወጣለሁ ሲሉ ቆመው ይጸልዩበት የነበረው የሲኦል እሳት አሁን ያችን ነፍስ አወጣላሁ ባሉ ሰዓት ግን አቃጠላቸው፡፡ እሳቸውም ያችን ነፍስ እዚያው ሲኦል ጥለው በመውጣት ጌታችንን "የዚያች ነፍስ ኃጢአቷ ምንድን ነው?" አሉት፡፡ የዚህን ጊዜ ነው ጌታችን ትንባሆን ስለሚጠጡ ሰዎች ታላቅ ምሥጢርን የነገራቸው፡፡ ይኸውም አባ ሐዊ የሚባሉ ጻድቅ ያስተላለፉትን ውግዘትና ግዝት የጸና እንደሆነ ነው ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የነገራቸው፡፡
ዝርዝር ታሪኩም በድርሳነ መድኃዓለም ላይ እንዲህ ተጽፎ ይገኛል፡- ትንባሆ የሚጠጡ ሰዎች ለምን ለማቆም እንደሚቸገሩና መጨረሻቸውም ምን እንደሆነ፡- "ይቅርታውና ምሕረቱ ከሁላችን የጥምቀት ልጆች ጋር ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኔዓለም ያደረገው ተአምር ይህ ነው፡- አባታችን ዘርዓ ቡሩክ መድኃኔዓለምን እንደወደደውና በየወሩ በሃያ ሰባት ቀን በዓሉን እንደሚያከብር በአሥራ ስድስት ቀንም ኪዳነ ምሕረትን እንደሚያከብር እነሆ እንነግራችኋለን፡፡ ባለሟልነትን ባገኘ ጊዜና መድኃኔዓለም የእሳት ፈረስንና የመስቀል ምልክት ያለበት የወርቅ በትርን በሰጠው ጊዜ "ወደ ሲዖል ሂድና መሸከም የምትችለውን ያህል ነፍሳትን አውጣ› አለው፡፡ ሄዶም ወደ ሲዖል ገባ፣ ነፍስ በነፍስ ላይ እንደ ንብ እየተጨናነቁ በሰውነቱ ላይ ታዘሉ፡፡ ነፍሳትንም ይዞ ሲወጣ አንድ ኃጢአተኛ ‹ዘርዓ ቡሩክ ብቻዬን ቀረሁ፣ አውጣኝ" አለው፡፡ ዘርዓ ቡሩክም ወደ እርሱ ተመልሶ ሳበው፡፡ ሰም ከፈትል ጋራ እንደሚጣበቅ ከሲዖል ጥልቅ ጋራ ተጣብቆ እምቢ አለው፡፡ የእሳቱ ነበልባልም ዘርዓ ቡሩክን አቃጠለው፣ እርሱም ተወው፡፡ ክብር ይግባውና እነዚያን ነፍሳት ይዞ ወደ ጌታው ወደ መድኃኔዓለም ሄደ፡፡
ሄዶም "ጌታዬ ሆይ! አንዲት ነፍስ ስሜን እየጠራች ቀርታለች ማርልኝ" አለው፡፡ መድኃኔዓለምም "ዘርዓ ቡሩክ ሆይ! በእኔ ዘንድ ባለሟልነትን ብታገኝ ትንባሆ የሚጠጣውን ማርልኝ ትለኛለህን?" አለው፡፡ እርሱም "ጌታዬ ሆይ! ይህቺ እንጨት በምን ትከፋለች?፣ ከሁሉ ኃጢአትስ በምን ትበልጣለች?" አለው፡፡ ወይቤሎ መድኅን ኢሰማዕከኑ ግብራ ለዛቲ ዕፅ ዘከመ ዘርዓ ሰይጣን ውስተ ገራህተ ዓለም፡፡ መድኃኔዓለምም "የዚህችን እንጨት ሥራ በዓለም እርሻ ሰይጣን እንደዘራት አልሰማህምን?" አለው፡፡ እነሆም እንነግራችኋለን፣ ስሙ ሐዊ የሚባል የፈጣሪውንም ሕግ የሚጠብቅ አንድ መምህር ነበረ፡፡ በዓርብ ቀንም ወደ ሰማይ ይሔዳል፤ በቀዳሚት ሰንበትና በእሑድ ከፈጣሪው ጋር ይነጋገራል፡፡ በሰኞ ቀንም ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ ለሀገር ሰዎችም በጉባኤ ይነግራቸዋል፣ በአዋጅ ነጋሪ ቃልም ይሰበሰባሉ፡፡ ይህቺ ሀገር ትልቅ ናትና እስከ ዓርብም ያስተምራቸዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ሰይጣን ቀና፡፡ አባ ሐዊም እንደልማዱ በዕለተ ዓርብ ወደ ሰማይ በሄደ ጊዜ ያ ሰይጣን በመቀመጫው ተቀምጦ በእርሱ በሐዊ ተመስሎ በቀዳሚት ሰንበት ቀንም ተገልጦ "ፈጣሪያችን የሚወዳትን ነገር እነግራችሁ ዘንድ ሁላችሁም ተሰብሰቡ" አለ፡፡ ሁላቸውም ተሰበሰቡ፡፡ "አባት ሆይ! ያለ ልማድህ ዛሬ ለምን መጣህና ጠራኸን?" አሉት፡፡ ያ ጠላት ዲያብሎስም "ጌታዬ ለሕዝቦቼ የዚያችን በቤትህ አንፃር ያለችውን እንጨት ቅጠል በጥርሳቸው ይጨምሩ ዘንድ፣ በአፋቸውም ያጤሱ ዘንድ ዛሬ ካልነገርሃቸው ወዳጄ አይደለህም አለኝ" አላቸው፡፡ ይህችንም እንጨት ባያት ጊዜ እንዲህ አደረገ፣ ሔዋንን በእንጨት እንዳሳታት አሳታቸው፡፡ ዛሬ እንደሚያደርጉትም የጥንባሆ ዕቃን አደረጉ፡፡ ቅጠሏንም አምጥተው ቀጥቅጠው በእሳት አጢሰው ትንሹም ትልቁም፣ የከበረውም የጎሰቆለውም ሁላቸውም ጠጡ፡፡
ሐዊም በሰማይ ሳለ በጸጋ አውቆ አዘነ፣ ነገር ግን ስለ ሰንበታት ክብር ብሎ አደረ፡፡ ሰኞ በነግህም ሐዊ መጣ፣ ሰይጣንም እንደ ጢስ በኖ ጠፋ፡፡ እርሱም ሰዎቹን ሰብስቦ "ይህን ማን አስተማራችሁ?" አላቸው፡፡ "አንተ ነህ" አሉት፡፡ "ሰይጣን ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፣ ከዛሬ ጀምሮ ተው" አላቸው፡፡ "ትናንት ጠጡ፣ ዛሬ ተው" ይለናል ብለው እምቢ አሉት፡፡ እርሱም አወገዛቸው፡፡ "በእርሻው የዘራት፣ በአፉም የጠጣት፣ በእጁም የያዛት የተረገመ ይሁን" አላቸው፡፡ ጋኔኑም በቅሉ ውስጥ ሆኖ ይነጋገራል፣ በውጭ ያሉትንም አጋንንት ይጠራቸዋል፡፡ በዚህን ሰዓት የተውም አሉ፣ እምቢም ያሉ አሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያቺ እንጨት ተረገመች፡፡ ሰውም በጠጣት ጊዜ የአምስት ቀፎ ሙሉ ንቦችን የሚያህሉ አጋንንት ይመጣሉ፡፡ በሁለቱ ዓይኖቹ ውስጥ፣ በሁለቱ አፍንጫዎቹም፣ በሁለቱ ጆሮዎቹም፣ በአፉም፣ በታች በሰገራ መውጫም በእነዚህ ሁሉ እንደ ቀፎ ንብ ይገባሉ፣ ይወጣሉ፡፡ ትምክህትን፣ ትዕቢትን፣ መግደልን፣ ሥርቆትንም፣ ክፉውንም ሁሉ ይመሉታል፡፡ ወሶበ ይሰትያ ብእሲ ይመጽኡ አጋንንት ዘየአክሉ መጠነ ፭ቱ ቀፈዋት ዘመልኡ አንህብት ወይበውኡ ውስቴቱ፡፡ በ፪ አዕይንቲሁ፣ ወበ፪ አዕናፊሁ፣ ወበ፪ አዕዛኒሁ ወበመንፈሱ ዘታህት በአፉሁ በዝንቱ ኵሉ ከመ ንህብ ዘቀፎ ይበውኡ ወይወጽኡ፡፡ ወይመልእዎ ትምክህተ፣ ወትዕቢተ፣ ቀትለ፣ ወሠሪቀ ወኵሎ ዕከያተ እንዲል መጽሐፍ፡፡
አባታችን ዘርዓ ቡሩክም ይህን ሰምቶ እጆቹን በትከሻው አመሳቅሎ አለቀሰ፣ በሥዕሉም አለ፣ በዚያን ጊዜ ወደ ዓለም ወጣ፡፡ ይህችን የተረገመች እንጨት እንዲህ ብሎ አወገዛት፡- "በአፉ የጠጣት፣ በእጁም የያዛት፣ የዘራት፣ የሸጣት፣ የገዛትም የጥምቀት ልጅ አይደለም፤ በሥጋው አይጠቀምም፣ ነፍሱም ወደ ሲዖል ትወርዳለች፡፡ ልጄ የሆነ ግን መድኃኔዓለምንና ኪዳነ ምሕረትን ያክብር፡፡ ጥንባሆንም አይጠጣ› አለ፡፡ የዚህ ጻዲቅ በረከቱ ያልታዘዝንውን ከመብላት ይጠብቀን አሜን" በማለት ተአምረ መድኃኔዓለም ወገድለ መባዓ ጽዮን ነገረ ጥንባሆን በሰፊው ዘግቦታል፡፡ በሌላም በኩል ትንባሆን በተመለከተ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የሰጣቸው ቃልኪዳን በራሳቸው በዘርዐ ቡሩክ ገድል ላይ የተጻፈውን ወደፊት እናያለን፡፡ እንዲሁም ይህችን የተረገመች ዕፅ የሚጠቀሙባት ሁሉ የሰይጣን ማደሪያዎች እንደሚሆኑና ክፉውንም ሁሉ እንደሚያሠሩት በሌላም ቦታ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ገድል ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ዳግመኛም በዚህች ቀን ስማቸው አርሰሌዳስ ዱአሚዶስ አውጋንዮስ ድሜጥሮስ ብርጥስ እስጢፋኖስ ኪራኮስ የተባሉ ሰባቱ ደቂቅ አረፉ።
እሊህ ቅዱሳንም ሀይማኖታቸው ለቀና ለታላላቅ የሀገር ሰዎች ልጆቻቸው ናቸው እነርሱም ክርስቲያኖች እንደሆኑ በከሀዲ ንጉስ ዳኬዎስ ዘንድ ሰዎች ነገር ሰሩባቸው ወደርሱም አስቀርቦ ለጣኦት እንዲሰግዱ ግድ አላቸው እምቢ ባሉትም ጊዜ ከልባቸው ጋር ይመክሩ ዘንድ ቀጠሮ ሰጣቸውና እርሱ ወደ ተግባሩ ሄደ።
እሊህ የተባረኩ ሰባቱ ደቂቅም ወደ ቤታቸው ሄዱና ገንዘባቸውን ለድኆችና ለምስኪኖች በተኑ የቀረውንም ለስንቃቸው ይዘው ሄዱ ከከተማውም በስተምስራቅ በዋሻ ውስጥ ዱአሚዶስ ወደ ከተማ ሂዶ ምግባቸውን በመግዛት የሚያገለግላቸው ሆነ የሰማውንም ነገር ይነግራቸዋል።
ንጉስ ዳኬዎስም ከሄደበት በተመለሰ ጊዜ እሊህን ሰባት ልጆች ፈለጋቸው በዋሻ ውስጥ ተሸሽገው እንዳሉ በነገሩት ጊዜ የዋሻውን አፍ በደንጊያ እንዲደፍኑ አዘዘ የእነዚህንም ቅዱሳን ነፍሳቸውን በተኙ ጊዜ ጌታችን ወሰደ።
ሶስት መቶ ሰባ ሁለት አመትም እንዲአንቀላፉ አደረጋቸው ከንጉስ አሽከሮችም ስማቸው ቴዎድሮስና መቅዶስዮስ የተባሉ ሁለት የእርሳስ ሰሌዳዎች ወስደው የእሊህን የሰባቱ ደቂቅን ዜናቸውንና የዘመኑን ቁጥር ፅፈው ቀርፀው ከዋሻው አፍ አኖሩት።
ከዚህም በኃላ ዳኪዎስ ሞተ እስከ ደጉ ንጉስ እስከ ቴዎዶስዮስ ዘመነ መንግስት ብዙ ነገስታት ነገሱ በዚህም ደግ ንጉስ ዘመን ትንሳኤ ሙታን የለም የሚሉ ከሀዲያን ሰዎች ተነሱ እሊህም ሰባቱ ደቂቅ የሚነቁበት ጊዜ ሲቀርብ ለበጎቹ ማደሪያ ሊአሰራ ሽቶ ደንጊያ እየፈለገ የዋሻቸውን አፍ አንድ መኮነን ከፈተው።
እሊህ ቅዱሳንም በሶስት መቶ ሰባ ሁለት አመት በነቁ ጊዜ ምግባቸውን ይገዛ ዘንድ ዱአሚዶስን ላኩት የአገር ሰዎችም የዳኬዎስ ስም የተፃፈበትን ዲናር በእጁ ውስጥ በአዩ ጊዜ የተሸሸገ የወርቅ ሳጥን ያገኘ መስሎአቸዋልና ይዘው ወደዳኞቹና ኤጲስቆጶሳት አቀረቡት በመረመሩትም ጊዜ እነርሱ ሰባት ልጆች እንደሆኑ ነገራቸው።
በሄዱም ጊዜ ፊታቸው እንደ ፀሀይ ሲበራ አገኙአቸው ኤጲስቆጶሱም የእርሳስ ሰሌዳ አየ አንስቶም በላዩ የተፃፈውን ዜናቸውንና የዘመኑን ቁጥር አነበበ በዳኬዎስ ዘመን እንዳንቀላፉ ህዝቡ ሰምተው እጅግ አደነቁ እግዚአብሄርንም አመሰገኑት።
ከዚህም በኃላ ወደ ንጉስ ቴዎዶስዮስ ላኩ እርሱ መጥቶ እጅ ነሳቸው ከእነርሱም ተባረከ ከሰራዊቱ ጋር ከተነጋገሩም በኃላ ሁሉንም ባርኳቸውና በምድር ላይ ተኙ ነፍሳቸውንም በእግዚአብሄር እጅ ሰጡ በዚያችም ዋሻ ውስጥ ቀበሩአቸው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን አባ ነካሮ አረፈ ይህም ቅዱስ ሰው ሳያውቀው በስውር የሚጋደል ሆነ እርሱም ከምንጣፉ በታች እሾህ ይጎዘጉዛል ጤና አግኝቶ እንዳይተኛ ነው በቀንና በሌሊትም ለፀሎት ይተጋ ነበር።
ከትሑትነቱም የተነሳ የበር ጠባቂ አደረጉት ።በዚያም ገዳም በመንፈስ ቅዱስ የተሰወሩ ነገሮችን የሚያይ ባህታዊ መነኮስ አለ በአንዲትም ሌሊት በህልሙ በከፍታ ቦታ ላይ ቆሞ አየ ከበታቹም ፍሬው በየአይነቱ የሆነ አትክልት አለ ወንዞችም ከበውታል አባ ነካሮም በመካከላቸው ሆኖ በወዲያና በወዲህ ያጠጣቸው ነበር ።
ያ መነኰስም ወንድሜ ነካሮ ሆይ ይህ አትክልት የማን ነው አለው አባ ነካሮም እኔ የተከልኃት ናት ብሎ መለሰለት መነኩሴውም ከፍሬዋ ትሰጠኝ ዘንድ እሻለሁ አለው አባ ነካሮም ሶስት የሮማን ፍሬ ቆርጦ ሰጠው በልብሱም ቋጠረው።
በነቃም ጊዜ እነዚያን የሮማን ፍሬዎች አገኛቸው ወዲያውኑ ወደ አባ ነካሮ ሄደ ከበር ቆሞ አገኘውና ወንድሜ ነካሮ ሆይ በዚች ሌሊት አይተኸኛልን አለው እርሱም አዎን አይቼሀለሁ ሶስት የሮማን ፍሬዎችን ሰጥቼህ የለምን አለው። በዚያንም ጊዜ ያ መነኩሴ ወደ ገዳሙ ሄዶ የሆነውን ሁሉ ለአበምኔቱና ለመነኩሳቱ ነገራቸው እነዚያንም የሮማን ፍሬዎች አሳያቸው መነኰሳቱም ከአባ ነካሮ ቅድስና የተነሳ አደነቁ ያን ጊዜም የበጋ ወራት ነበርና የሮማንም ጊዜው አልነበረምና።
በዝቅተኛ ማእረግ ላይ ስለአደረጉት መነኮሳቱ አዘኑ በከፍተኛም ማእረግ ሊያደርጉት አዘኑ በከፍተኛም ማእረግ ሊያደርጉት ሽተው ወደርሱ በሄዱ ጊዜ አጡት ታላቅ ኀዘንንም አዘኑ ከዚህም በኃላ በዚች እለት እንዳረፈ መፃተኞች ነገሩአቸው።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ትኑር አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages