ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 28

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር አሥራ አራት በዚህች ቀን #ጻድቁ_አቡነ_አረጋዊ (ዘሚካኤል) የተወለዱበት እና ወደ ደብረ ዳሞ የወጡበት ነው፣ የከበረችና የተመረጠች #ቅድስት_ምህራኤል በሰማእትነት አረፈች፣ በገድል የተጠመደ የከበረ #ቅዱስ_አባ_አርከሌድስ አረፈ፣ የከበረች #ቅድስት_እምራይስ በሰማእትነት አረፈች።


ጥር አሥራ አራት በዚህች ቀን ታላቁና የከበረው አባታችን አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) የተወለዱበት እና ወደ ደብረ ዳሞ የወጡበት ነው።
እኚህ አባት ከ9 ቅዱሳን አባቶች አንዱ ሲሆኑ አባታቸው ይስሐቅ የሮም ንጉስ ነበሩ፡፡ እናታቸው ንግስት እደና ይባሉ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ስማቸው ዘሚካኤል ነው፡፡ ጥበብ መንፈሳ ሲማሩ አድገው ወደ እስክንድርያ ገዳም ገቡ፡፡ አበምኔቱ አባ ጳኩሚስ በፈቃደ እግዚአብሔር የመጡ መሆናቸውን አውቀው መዓረገ ምንኩስና ሰጥተዋቸዋል፡፡
የንጉሳዊ የቅንጦት ኑሮ ንቀው ትተው ገዳም ገብተው በምንኩስና ተወስነዋል፡፡ አባታችን በተጋድሏቸውም ከአባ እንጦንስ፣ ከአባ ጳውሊ እና ከአባ መቃርስ ቀጥሎ በአራተኛ ማዕረግ አበ መነኮሳት ሆነው ተመርጠዋል።
በገዳመ ዳውናስ 7 ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ ሮም ተመልሰው ሲያስተምሩ የሀገራችን ኢትዮጵያን ዜና ሰምተው ለመምጣት በ480 ዓ.ም ከአባ ፍሬምናጦስ በኋላ መንገድ ጀመሩ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም በክንፉ ተሸክሞ አክሱም አድርሷቸዋል፡፡
ተመልሰውም ሄደው ስለ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መስክረዋል፡፡ ሐዋርያ ሳይላክላት በሃይማኖት በምግባር ጸንታ ትኖራለች ብለው ለሰባቱ ዘመዶቻቸው አበው መነኮሳት ነገሯቸው፡፡ ስምንቱም ጓዛቸውን ጠቅልለው በሮም ነግሶ የነበሩ ይስሐቅን (አባ ገሪማን) ጨምረው ንጉስ አልአሜዳ በነገሰ በአምስተኛ ዓመት ማለትም በ480 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ዘጠኝ ሆነው መጥተዋል፡፡
አባ አረጋዊ እናታቸው ቅድስት እድናን ደቀ መዝሙራቸውን ማትያስን አስከትለው እግረ መንገዳቸውን እያስተማሩና ድውያንን እየፈወሱ ደብረ ዳሞ ደረሰዋል፡፡
ከእግረ ደብር ሆነው አሁን ይህን ተራራ በምን ልወጣው እችላለሁ እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ በንግግሩ ሐሰት የሌለበት አምላካችን በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ በመዝሙር 90/91፥11-16 ላይ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። እንዳለው የታዘዘ ዘንዶ መጥቶ ስደሳ ክንድ በሚያህል ጅራቱ ጠምጥሞ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ እሳት ይዞ እየጠበቃቸው ከተራራው አናት አድርሷቸዋል፡፡
ወዲያው ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ብለው አመስግነዋል፡፡ ቦታውም ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሏል፡፡ በዚያ ዕለት ግማሽ ህብስት በልተው ጠገቡ፤ ከዚያ በኋላ ግን ምድራዊ ሕብስት አልተመገቡም፡፡ በሰንበተ ክርስታያን ከቅዳሴ በኋላ ሕብስተ ሰማያዊ እያመጡላቸው ይመገቡ ነበር እንጂ፡፡ ኋላም ዜና ጽድቃቸውን ሰምተው ከስድስት ሺህ ያላነሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውላቸዋል፡፡
ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሞላቸው ጌታ በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾ ምድራዊ መንግስትህን ትተህ ስላገለገልከኝ ህልፈት ሽረት የሌለባት ሰማያዊ መንግስቴን አወርሰሃለሁ ብሎ ቃልኪዳን ሰጣቸው፡፡ በስምህ የተማጸነውን እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሃለሁ አንተም ከሞት ገጽ ትሰወራለህ ብሎ ተስፋቸውን ነገራቸው፡፡ እሳቸው መነኮሳቱን ሰብስበው ከእንግዲህ በሥጋ አታዩኝም ብለው ነግረዋቸው አበምኔት ሾመውላቸው በደብረ ዳሞ ተራራ በስተምስራቅ አቅጣጫ ተሰውረዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህች እለት ጠምዋህ ከሚባል ሀገር ሰዎች የከበረችና የተመረጠች ምህራኤል በሰማእትነት አረፈች።
የዚችም ቅድስት ወላጆቿ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ክርስቲያኖች ናቸው አባቷም ስሙ ዮሐንስ የሚባል ቄስ ነው እናቷም ኢላርያ የምትባል ደግ ናት።ነገር ግን ልጅ ስለሌላቸው ስለዚህ እያዘኑ ወደ እግዚአብሔር ይለምኑ ነበር ከብዙ ዘመንም በኃላ ይህቺን የከበረች የተቀደሰች ልጅ ተሰጠቻቸው ስሟንም ምህራ ኤል ብለው ጠርዋት።
ዐስራ ሁለት ዓመትም በሆናት ጊዜ በላይዋ በአደረ በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ድንቆች ተአምራቶችን መስራት ጀመረች።ከዚህም በኃላ ከሀዲ ንጉስ ዲዮቅልጣኖስ በተነሳ ጊዜ ወደ ባህር ዳርቻ ወጣች መርከበም አግኝታ በላዩ ተሳፈረች ለሰማእትነት ከሚሄዱት ጋር በመሄድ ወደ እንፅና ከተማ በደረሰች ጊዜ ስሙ ፍልፍልያኖስ በሚባል መኮንን ፊት ቆመች በአያትም ጊዜ ስለታናሽነቷ ራርቶላት ሊተዋት ወደደ።
ሊተዋትም እንደወደደ አውቃ እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን በድፍረት ረገመች።ስለዚህም መኮንኑ ተቆጥቶ ፅኑእ የሆነ ስቃይን አሰቃያት ከቀናች ሀይማኖቷ ሸንግሎ ይመልሳት ዘንድ በተሳነው ጊዜ ጊንጦችን እፉኝቶችንና እባቦችን ሰብስበው በዳውላ ውስጥ እንዲጨምሩአቸው እርሷንም ከእነርሱ ጋር በዳውላ ውስጥ እንዲጨምሩ አጥማጆችን አዘዛቸው እነርሱም እንዲሁ አደረጉ።
ያን ጊዜ የእግዚአብሄር መልአክ ተገለፀላትና ከጌታችን ዘንድ የተሰጣትን ቃል ኪዳን አስረከባት ከዚህም በኃላ ነፍሷን አሳለፈች የምስክርነት አክሊልንም ተቀበለች ከዳውላውም ውስጥ አውጥተው በዚያች ቦታ ቀበሩዋት።
ከዚህም በኃላ አባቷና እናቷ በሰሙ ጊዜ ስጋዋ ወዳለበት ከብዙ ህዝብ ጋር መጡ ከዚያም ስጋዋን አፈለሱና ወሰዱአት በታላቅ ክብርም ገንዘው በአማረች ሳጥን ውስጥ አኖሩዋት በስውር ቦታም ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሰሩላት ከእርሷም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ቀን በገድል የተጠመደ የከበረ አባት አርከሌድሰ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከሮሜ ሀገር ከታላለቆች ወገን ነው የአባቱ ስም ዮሀንስ የእናቱም ስም ሰንደሊቃ ነው ሁለቱም እውነተኞች የሆኑ በእግዚአብሄር ህግ ያለ ነቀፋ የፀኑ ናቸው።
ቅዱስ አርከሌድስም እድሜው አስራ ሁለት አመት በሆነው ጊዜ አባቱ ሞተ እናቱም ሚስት ልታጋባው አሰበች እርሱ ግን ይህን አልወደደም።
ከዚህም በኃላ ወደ ንጉስ ሄዶ የአባቱን ሹመት ይቀበል ዘንድ መከረችው ከእርሱም ጋር ሁለት አገልጋዮችን ላከች ልንጉስም እጅ መንሻ የሚሰጠውን ብዙ ገንዘብ ሰጠችው።በመርከብም ተጭኖ በባህር መካከል ሳለ ጥቅል ነፋስ በላዩ ተነሳ ማእበሉም እጅግ ከፍ ከፍ ብሎ መርከቡ ተሰበረ እርሱም በአንዲት የመርከብ ስባሪ ሰሌዳ ተንጠልጥሎ ወደ የብስ አደረሰችው።
ከባህሩም ሲወጣ ማእበል የተፋው በድን አገኘ ተቀምጦም በላዩ አለቀሰ የአለምን ኃላፊነትም አሰበ ነፍሱንም የሚገስፃትና የዚህ የኃላፊው አለም ገንዘብ ምኔ ነው ላንቺስ ምንሽ ነው ከሞትኩ በኃላ ወደ አፈር እመለሳለሁና የሚላት ሆነ።
በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት ወደ ሆነ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመነ የቀና መንገድን ይመራው ዘንድ ከዚህም በኃላ ተጓዘ በቅዱስ ሮማኖስ ስም በሶርያ አገር ወደ ተሰራ ወደ አንድ ገዳም ደረሰ። ከገንዘብም ከእርሱ ጋር የቀረውን ሁለት መቶ የወርቅ ዲናር ለአበ መኔቱ ሰጠው የምንኩስና ልብስንም እንዲያለብሰው ለመነው ።
የከበረ አርኬሌድስም ከመምጣቱ በፊት ለአበምኔቱ መንፈስ ቅዱስ አስረድቶት ነበር ወደርሱም በደረሰ ጊዜ አበ መኔቱ ደስ አለው የከበሩ መነኮሳትን ሁሉንም ሰበሰባቸውና በቅዱስ አርከሌድስ ላይ ፀለዩ። አበ ምኔቱም የምንኩስና ልብስን አስኬማንም አለበሰው መነኮሳቱ ሁሉም በእርሱ ደሰወ አላቸው የእግዚአብሄር ፀጋ በላዩ ተገለፃለችና።
ከዚህም በኃላ የከበረ አርከሌድስ በጠባብ መንገድ ተጠመደ ፅኑ ገድልን ተጋድሏልና ሁልጊዜ በየሰባት ቀን የሚፆም ሆነ በቀንና በሌሊትም ይፀልያል እግዚአብሄርም ሀብተ ፈውስን ሰጥቶት በእምነት ወደርሱ የሚመጡትን ብዙዎች በሽተኞችን አዳነቸው።
የሴቶችንም ፊት ከቶ እንዳያይ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ቃል ገባ ከእናቱ ዘንድም አስራ ሁለት አመት ያህል ወሬው መሰማቱ በዘገየ ጊዜ በእርሱም የሆነውን አላወቀችም የሞተ መስሏታልና እጅግ አዘነች።
ከዚህም በኃላ የእንግዶችና የመፃተኞች መቀቢያ የሚሆን ቤትን ሰራች መንገደኞችም እንዲአድሩበት አደረገች በአንዲትም እለት የብፁእ አርከሌድስን ዜና ሲናገሩ መንገደኞችን ሰማቻቸው እንርሱም ቅድስናውን ተጋድሎውን ምልክቶቹንም የመልኩንም ደም ግባት ሰምታ ልጅዋ እንደሆነ አወቀች ደሰግመኛም መንገደኞችን ጠየቀቻቸው ስራውን ሁሉ ነገሩዋት እርሱ ህያው እንደሆነ ተረዳች።
በዚያንም ጊዜ ተነስታ ወደ ከበረ ሮማኖስ ገዳም ሄደች ወደ ልጅዋ ወደ አርከሌድስም እንዲህ ብላ ላከች እነሆ ፊትህን አይ ዘንድ ወድጄ እኔ እናትህ መጥቻለሁ። እርሱም ከቶ የሴቶችን ፊት እንዳለሰይ ከክበር ባለቤት ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ቃል ገብቻለሁና ቃል ኪዳኔን ማፍረስ አይቻለኝም ብሎ መልሶ ወደርሷ ላከ ።ዳግመኛም ፊትህን ካላሳየኸኝ እኔ ወደ ዱር እሄዳለሁ አራዊትም ይበሉኛል ብላ ወደርሱ ላከች።
የከበረ አርከሌድስም እርሷ እንደማትተወው እርሱም ለእግዚአብሄር የገባውን ቃል ኪዳን ማፍረስ እንደማይቻለው በአወቀ ጊዜ ነፍሱን እንዲወስዳት ወደ ጌታችን ለመነ ከዚህም በኃላ የበሩን ጠባቂ ወደ እኔ ትገባ ዘንድ እናቴን ተዋት አለው ።በገባችም ጊዜ ሙቶ አገኘችውና በታላቅ ድምፅ በመጮህ አለቀሰች ነፍሷንም ይወስድ ዘንድ ወደ እግዚአብሄር ለመነች ልመናዋንም ተቀብሎ ነፍሷን ወሰደ።
ከዚህም በኃላ ስጋዋን ከልጅዋ ስጋ ለይተው ለብቻዋ ሊቀበሩ ወደዱ ከከበረ አርከሌድስም በድን የእናቴን ስጋ ከስጋዬ አትለዩ በህይወቷ ሳለች ታየኝ ዘንድ ልቧን ደስ አላሰኘሁምና የሚል ቃል ወጣ።ይህንንም ቃል በሰሙ ጊዜ አጅግ አደነቁ እግዚአብሄርንም አመሰገኑት ሁለቱንም በአንድ መቃብር ውስጥ ቀበሩአቸው ጌታችንም ለበሽተኞች ታላቅ ፈውስን ከስጋው ገለጠ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም እለት የከበረች እምራይስ በሰማእትነት አረፈች። ይቺም ብፅእት በክርስቶስ ሀይማኖት ለፀኑ ለከበሩ አባቶች ልጅ ናት ፈሪሀ እግዚአብሄርንም እየተማረች አደገች።በአንዲትም እለት ውኃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ስትወርድ ስለ ክርስቶስ የታሰሩ እስረኞችን አየች።
እንርሱም ጳጳሳት ቀሳውስትና ዲያቆናት ናቸው ከእነርሱም ጋር ስሟን ይፅፍ ዘንድ መዘጋቢውን ለመነችው መዘገባትም ወደ ከሀዲውም መኮንን ወደ ቁልቁልያኖስ አቀረባት።እርሱም ለጣኦት ትሰግድ ዘንድ በብዙ ነገር ሸነገላት እምቢ ባለችውም ጊዜ ቸብቸቦዋን ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ከተባባሪዎቿም ጋር ምስክርነቷን ፈፀመች።
አምላከ ቅዱሳን ለቅዱሳኑ ካደለው ፍቅራቸው ለእኛም አይንሳን:: በረከታቸውንም ያብዛልን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages