አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ዐስራ ሰባት በዚችም ቀን የእግዚአብሔር ሰው የሆነ የዋህ ቅን ጻድቅ #የሊቀ_ነቢያት_ሙሴ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ በዚህች ቀን ከላይኛው ግብጽ ከአክሚም መንደር #መነኰስ_ቅዱስ_ሚናስ በሰማዕትነት ሞተ።
የካቲት ዐስራ ሰባት በዚችም ቀን የእግዚአብሔር ሰው የሆነ የዋህ ቅን ጻድቅ የሊቀ ነቢያት ሙሴ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ይህ ነቢይ ነፍሱን ስለእሳቸው አሳልፎ እስከ መስጠት ከእግዚአብሔር ወገኖች ጋር የደከመ ነው እርሱም በግብጽ አገር በኤርትራ ባሕርም ድንቆች ተአምራትን ያደረገ ነው።
ይህም ስለ ፈርዖን ትእዛዝ ወላጆቹ በግብጽ ወንዝ ውስጥ በጣሉት ጊዜ አውጥታ ላሳደገችው ለፈርዖን ልጅ ለተርሙት ልጅዋ መባልን አልወደደም። እርሱ ፈርዖን የዕብራውያንን ወንዶች ልጆች ይገድሏቸው ዘንድ አዝዞ ነበርና። በአገኘችውም ጊዜ ለርሷ ልጅ ሊሆናት ወስዳ በመልካም አስተዳደግ አሳደገችው።
አርባ ዓመትም በሆነው ጊዜ አንዱን ዕብራዊ የግብጽ ሰው የሆነ ሲያጠቃው አየ ለዕብራዊውም ተበቅሎ ግብጻዊውን ገደለው። በማግሥቱ ደግሞ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አያቸው ሊአስታርቃቸውና በመካከላቸው ሰላምን ሊአደርግ ወደደ። አንዱ ዐመፀኛም ትላንት ግብጻዊውን እንደገደልከው ልትገድለኝ ትሻለህን አለው።
ስለዚህም ነገር ሙሴ ፈርቶ ወደ ምድያም አገር ሸሸ በዚያም ሚስት አግብቶ ሁለት ልጆችን ወለደ በዚያም አርባ ዓመት ኖረ በጳጦስ ቍጥቋጦ ውስጥም እሳት እየነደደ ራእይን አየ። አይቶ ሊረዳ በቀረብ ጊዜ ጳጦስ በተባለ ቊጥቋጦ ውስጥ እግዚአብሔር ተናገረው። ወደ ግብጽ አገርም ሒዶ የእስራኤልን ልጆች ከዚያ እንዲአወጣቸው አዘዘው።
ከዚህን በኋላ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ በግብጻውያን ላይ ዐሥር መቅሠፍቶችን አመጣ። መጀመሪያው የወንዙን ውኃ ደም ማድረግ የመጨረሻው የግብጻውያንን የበኵር ልጅ መግደል ነው።
ከዚህም በኋላ ሕዝቡን ከግብጽ አገር አወጣቸው የኤርትራንም ባሕር ከፍሎ በውስጡ አሳለፋቸው የባሕሩንም ውኃ በጠላቶቻቸው በፈርዖንና በሠራዊት ላይ ገልብጦ አሠጠማቸው።
ከዚህም በኋላ በምድረ በዳ ውስጥ አርባ ዓመት ሙሉ መና አወረደላቸው ውኃንም ከአለት አፈለቀላቸው ይህን ሁሉ በጎ ሥራ በዚህ በደግ ነቢይ ሙሴ እጅ እግዚአብሔር አደረገላቸው እነርሱ ግን ይዘልፉት ነበር ብዙ ጊዜም በድንጊያ ሊወግሩት ሽተው ነበር።
እርሱ ግን በእነርሱ ላይ ልቡን አስፍቶ በመታገሥ ስለርሳቸው ወደ እግዚአብሔር ይማልዳል። እነርሱንም አብዝቶ ከመውደዱ የተነሣ እግዚአብሔርን አቤቱ የዚህን ሕዝብ በደሉን ይቅር ካላልክ ከሕይወት መጽሐፍህ ሰርዘኝ አለው።
ሰው ከወዳጁ ጋር እንደሚነጋገር አምስት መቶ ሰብዓ ቃላትን ከእግዚአብሔር ጋር እንደተነጋገረ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። የእስራኤል ልጆችም በሚያዩት ጊዜ እንዳይሞቱ ፊቱን እስከ ሸፈነ ድረስ በእግዚአብሔር በጌትነቱ ብርሀን ፊቱ በራ።
መቶ ሃያ ዓመት የሆነ ዕድሜውም በተፈጸመለት ጊዜ ለአገልጋዩ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ ሕዝቡን እርሱ እንደጠበቃቸው እንዲጠብቃቸው በእጁ ውስጥ እንዲአስረክበው እግዚአብሔር ሙሴን ለኢያሱ አስረክብ ብሎ አዘዘው።
ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አዘዘው ሕጉንም እንዲጠብቅ ሕዝቡንም ለኢያሱ በእጁ አስረከባቸው ወደ ምድረ ርስትም እርሱ እንደ ሚአስገባቸው አረጋገጠለት፡፡ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በምስክሩ ድንኳን ውስጥ የሚሠራውን ሁሉ ሠርቶ ከአዘጋጀ በኋላ በተራራ ውስጥ አረፈ በዚያም በመላእክት እጅ በሥውር ተቀበረ። የእስራኤል ልጆች ወስደው እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን ሥጋ ሠወረ።
በእስራኤል ልጆች ውስጥ እንደ ሙሴ ያለ ደግ የዋህ ቅን የሆነ ነቢይ እንደማይነሣ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። ሰይጣንም የሙሴን ሥጋ ለእስራኤል ሊገልጥላችው በወደደ ጊዜ ሐዋርያው ይሁዳ በጻፈው መጽሐፉ እንደመሰከረ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ገሠጸው ከዚህም ሥራ ከለከለው የእስራኤል ልጆችም አርባ ቀን አለቀሱለት።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_ሚናስ_ግብጻዊ (ሁለተኛው)
በዚህች ቀን ከላይኛው ግብጽ ከአክሚም መንደር መነኰስ ሚናስ በሰማዕትነት ሞተ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ምድርን የሚያርሱ ክርስቲያን ገበሬዎች ናቸው እርሱም ይህን ዓለም ንቆ ትቶ በሀገረ አክሚም በሚገኝ በአንድ ገዳም መነኰሰ ለመብልና ለመጠጥ ሳይገዛ በየሁለት ቀን እየጾመ ብዙ ቀኖችን ኖረ ከዚያም ወጥቶ ወደ እስሙናይን ሀገር ሒዶ በአንድ ገዳም ውስጥ እያገለገለና እየተጋደለ ከገዳሙ ደጃፍ ሳይወጣ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ።
እስላሞችም በግብጽ አገር በነገሡ ጊዜ ለእግዚአብሔር ከርሱ ጋር ለዘላለሙ ህልው የሆነ ከባሕርዩ የተወለደ ልጅ የሚሠርፅ መንፈስ ቅዱስም የለውም እንደሚሉ ሰማ ስለዚህም ነገር እጅግ አዘነ።
ከአበ ምኔቱም ቡራኬ ተቀበለ ወደ እስሙናይን ከተማ ወጥቶ ሔደ የእስላሞች ሠራዊት አለቃ በሆነ በመኰንኑ ፊት ቁሞ እንዲህ አለው። እናንተ ለእግዚአብሔር ከባሕርዩ የተወለደ ልጅ እንደሌለው አድርጋችሁ የምትናገሩ እውነት ነውን መኰንኑም አዎን ልጅ አለው ማለትን ከእግዚአብሔር እናርቃለን አለ።
አባ ሚናስም ያለ ልጅ ልታምኑ አይገባም እርሱም ያለ ዘር ያለ ሩካቤ የሆነ ነው ከባሕርዩ ተወለደ እንጂ አለው። መኰንኑም ልጅ አለው ማለት በሕጋችን ክህደት ነው አለ አባ ሚናስም እንዲህ አለው መኰንን ሆይ እወቅ የከበረ ወንጌል በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው በእግዚአብሔር ልጅ በወልድ ያላመነ ሕይወትን አያይም የእግዚአብሔር ቁጣ በላዩ ይወርዳል እንጂ ብሏልና።
ስለዚህም መኰንኑ እጅግ ተቆጣ ራሱንም በሰይፍ እንዲቆርጡ ሥጋውንም በየቊርጥራጭ ቆራርጠው በባሕር እንዲጥሉት አዘዘ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው በበጎ አገናነዝ ገንዘው ቀበሩት መታሰቢያውንም አደረጉ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment