ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 18 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር 18

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ጥር ዐስራ ስምንት በዚች ቀን የሰማዕታት አለቃ #የቅዱስ_ጊዮርጊስ አፅሙ ተቃጥሎ ተደቁሶ የተበተነበት ነው፣ የሀገረ ንጽቢን ኤጲስቆጶስ #አባ_ያዕቆብ አረፈ፣ #የቅዱስ_አቤላክ (ባኮስ) ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ መታሰቢያው ነው፣ የአልዓዛር እህቶች #የማርያ_እና_የማርታ መታቢያቸው ነው፡፡


ጥር ዐስራ ስምንት በዚች ቀን የሰማዕታት አለቃ የቅዱስ ጊዮርጊስ አፅሙ ተቃጥሎ ተደቁሶ የተበተነበት ነው፡፡
ይኸውም ሰባ ነገሥታት ማሰቃየት በሰለቻቸው ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ መጭመቂያ ሆኖ ከተሠራ የስቃይ መሣሪያ ላይ አውጥተው ሰውነቱን እንዲሰነጥቁት ንጉሥ ዱድያኖስ አዘዘ፡፡ አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረግፉት ድረስ እንዲህ አደረጉበት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስቃይ ብዛት የተነሳ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ሥጋውንም በሙሉ በእሳት አቃጠሉት አመድም ሆነ፡፡
ከሐዲው ንጉሥ ዱዲያኖስ የተቃጠለውን የሥጋውን አመድ አፍሰው በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደሚባል ተራራ ወስደው ምዕመናን ራሩን አመዱን እንኳን እንዳያገኙት በነፋስ እንዲዘሩት አዘዘ፡፡ ደብረ ይድራስ ማለት ምድረ በዳ ማለት ነው፡፡ ወታደሮቹም የሥጋውን አመድ በተራራ ላይ ነስንሰው የተመለሱበት፣ የሥጋው አመድ ያረፈበት ዕፅዋት ሁሉ ጊዮርጊስ ጊዮርጊስ ያሉበት፣ ጌታችን ከመላእክት ጋር ተገልጦ አራቱን የምድር ነፋሳትንም የቅዱስ ጊዮርጊስ የሥጋውን ትቢያ እንዲሰበስብ አዞ። "የኔ ሆይ! የመረጥኩህ ወዳጄ ጊዮርጊስ ከሞት ተነሥ አትፍራ፤ እኔ አዝዤሀለሁና" ሲል ኀያሉን ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠራው። ያን ጊዜ ልዑል ንዑድ ጊዮርጊስም ከጫጉላ ቤት እንደሚወጣ ሙሽራ ምንም ሕማም ሳይኖርበት ተነሣ።
መድኃኒታችንም ባረከው። "አትፍራ፤ ይኸንን ከሀዲ ንጉሥም እስክታሳፍረው ድረስ እኔ አጸናሀለሁ። ከእንዲህስ ወዲህ አምላኩ ከእጃችን ሊያአድነው አይችሉም እንዳይሉ እነዚህን ከሐድያን ነገሥታትና የረከሱ ጣዖታቸውን ታሳፍራቸው ዘንድ ተነሣና ወደ አገር ውጣ፤ ሰላሜ ለዘለዓለም ከአንተ ጋር ይሁን" አለው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ተናግሮ ሳመው። በፍጹም ምስጋናም ወደ ሰማይ ዐረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጌታችን ይህንንም ቃል ኪዳን የተቀበለበት ቀን ነው፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚህችም ዕለት በገድል የተጸመደ የከበረ አባት ለቅዱስ ኤፍሬምም መምህሩ የሆነ የሀገረ ንጽቢን ኤጲስቆጶስ አባ ያዕቆብ አረፈ፡፡ ይህም ቅዱስ ተወልዶ ያደገው በንጽቢን ከተማ ነው እርሱ ግን ሶርያዊ ነው ከታናሽነቱም የምንኵስና ልብስ መልበስን መረጠ ከጠጕር የተሠራ ማቅንም ለበሰ በጾም በጸሎት ተወስኖ በቀን በሌሊት በበጋ በሐሩር በክረምት ቊር የሚጋደል ሆነ ያንንም ማቅ ከቶ ከሥጋው ላይ አያወጣውም ነበር ምግቡም ቅጠላቅጠል ነው የሚጠጣውም የዝናብ ውኃ ብቻ ነው ስለዚህ ሥጋው ብሩህ ሆነ ነፍሱም እጅግ በራች።
እግዚአብሔርም ሀብተ ትንቢት ድንቆች ተአምራቶችንም የመሥራት ጸጋን ሰጠው ለሰዎችም ከመሆኑ በፊት የሚሆነውን ይነግራቸውና እንዲሁም ይሆናል። ተአምራቱም እጅግ ብዙ ነው በአንዲትም ቀን ሴቶች በውኃ ምንጭ ላይ ያለማፈር ሲጫወቱና ሲሣለቁ አያቸው የውኃውንም ምንጭ አደረቀ የራሳቸውንም ጠጒር ነጭ ሽበትን አደረገ በተጸጸቱና የውኃውን ምንጭ እንዲመልስላቸው እየሰገዱ በለመኑት ጊዜ የውኃቸውን ምንጭ መለሰላቸው እንዳይታበዩም ይገሠጹ ዘንድ የራሳቸውን ጠጒር ነጭ እንደሆነ ተወው።
በአንዲት ዕለትም በጐዳና አልፎ ሲሔድ አንዱን ሰው አስተኝተው ሰዎችን አገኛቸው መገነዣ ልብስም ይሰጣቸው ዘንድ ቅዱሱን ለመኑት እርሱ ግን በጸሎቱ ሰውዬውን ምውት አደረገው ሰዎችም ወደርሱ በተሰበሰቡ ጊዜ ሙቶ አገኙት ተጸጽተውም ሁለተኛ ያድንላቸው ዘንድ ለመኑት አዳነላቸውም። ትሩፋቱና ደግነቱም በተሰማ ጊዜ መርጠው በአገረ ንጽቢን ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት የክብር ባለቤት የክርስቶስን መንጋዎች ከአርዮሳውያ ተኵላዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ።
ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱን የከበሩ አባቶች በኒቅያ ከተማ በሰበሰባቸው ጊዜ ይህ አባት አብሮ አለ ከእርሳቸውም ጋር አርዮስን አውግዞ ከክርስቲያን አንድነት ለየው የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓትና በሁሉ ምእመናን ዘንድ የታወቀች የሃይማኖት ጸሎትን ሠራ። ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በደረሰ ጊዜ የሞተውን ሰው በጉባኤው ውስጥ አስነሥቷል።
የፋርስ ንጉሥም መጥቶ አገረ ንጽቢንን በከበባት ጊዜ ይህ ቅዱስ ያዕቆብ የጭጋግ ደመና በሠራዊቱ ላይ አመጣ ትንኞችም ፈረሶቻቸውንና ጐበዛዝቶችን ነደፏቸው ፈረሶችም ማሠሪያቸውን ቆርጠው ፈረጠጡ የፋርስ ንጉሥም አይቶ ታላቅ ፍርሀትን ፈራ ተነሥቶም ሽሽቶ ወደኋላው ተመለሰ። ነፍሱን የመንጋዎቹንም ነፍስ ጽድልት ብርህት አድርጎ ገድሉንም በፈጸመ ጊዜ ዐረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
የመጀመሪያው የአፍሪካ ሐዋርያ ቅዱስ አቤላክ (ባኮስ)፡- ይኽም ጃንደረባ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንግሥት የሆነችው የህንደኬ የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊና አዛዥ የነበረ ነው፡፡ ከአባቱ እብነ መላክ ከእናቱ ስሂነ ሕይወት ታኅሣሥ29 ቀን ተወለደ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ለበዓለ ፋሲካ በቤተ መቅደስ ይሰግዱ እንደነበረው ሁሉ ይኽም ጃንደረባ ከ4ሺህ ማይልስ በላይ ተጉዞ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ በመለስ ላይ ነበረ፡፡
ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ በተለይም ስለ ጌታችን መከራ መስቀል በዝርዝር የሚናገረውን ክፍል 53ኛውን ምዕራፍ ያነብ ነበር ነገር ግን ጃንደረባው ስለማን እንደሚናገር አልገባውም ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በአካባቢው ወንጌልን ይሰብክ የነበረውን ሐዋርያውን ቅዱስ ፊሊጶስን ላከለት፡፡ እርሱም ጃንደረባው ያነበው የነበረውን መጽሐፍ ተረጎመለት፣ የከበረች ወንጌልን ሰበከለት፣ በመጨረሻም አጠመቀው፡፡ ሐዋርያው ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በጃንደረባው ላይ ወረደ፡፡ ሐዋ 8፡26-40፡፡
ይህን ለእኛ ለኢትዮጵያውን እጅግ የሚያኮራን ታሪካችን ነው፡፡ ዛሬ በእጃችን ላይ በመገኘው መጽሐፍ ውስጥ ባይኖርም በቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥራዞች ላይ ግን ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ጃንደረባውን ባጠመቀውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያው ጃንደረባ ላይ እንደወረደ ተጽፏል፡፡ (v.39.cord.alexand. in bible reg. angl-alique plures codd.mss)
ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ ጃንደረባውን ያጠመቀበት ወንዝ "ቤተ ሳሮን" በተባለችውና እስከዛሬም ድረስ ከኢየሩሳሌም 20 ማይልስ ርቀት በምትገኘው መንደር በኬብሮን መካከል ባለው ኮረብታ ሥር የሚመነጭ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጀሮም ጃንደረባውን "የኢትዮጵያውያን ሐዋርያ" በማለት ይጠራዋል፡፡ በሰፊው ለኢትዮጵያውያን ወንጌልን የሰበከ እርሱ ነውና፡፡
ጌታችን የመረጣቸው የከበሩ ሐዋርያት እንኳን ወንጌልን በዓለም ለመስበክ ገና ከኢየሩሳሌም ባልወጡበት ወቅት በ34ዓ.ም ነው። ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ በክርስቶስ አምና ወንጌልን የተቀበለችው፡፡ በምድሪቱም ላይ ወንጌል መነገር የጀመረው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከኢየሩሳሌም ወንጌልን ተምሮና ተጠምቆ ወደ አክሱም እንደተመለሰ በመጀመሪያ ያጠመቀ ንግሥቲቷ ሕንደኬን ነው፡፡ ከእርሷም በኋላ መኳንንቱና መሳፍንቱ ሁሉ አምነው በባኮ እጅ ተጠመቁ ይኸውም በ34 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ባኮስ እስከ ኑብያ ድረስ ሄዶ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ አጥምቋል፡፡ በዚህም ጊዜ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በባኮስ እየተሰጠ የነበረውን የወንጌል ብርሃን የበለጠ እንዲበራ አድርጓል፡፡ ከጃንደረባውም ጋር ሆነው በብዙ ቦታዎች አብረው ወንጌልን ሰብከው አምልኮተ ጣዖትን አጥፍተዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ባኮስ ወደ የመን በመሄድ በዚያም ክርስትናን በማስተማር ብዙዎችን አሳምኖ ካጠመቀ በኋላ ወደ ፐርሺያ ከዚያም ወደ ሕንድ፡ በመሄድ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሟል፡፡ በመጨረሻም ጥንት ታፕሮባና (taprobana)፡ ዛሬ ሲሎን በምትባለው ደሴት ወንጌልን በማስተማር ላይ እያለ በሰማዕትነት እንዳረፈ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ (lives of the most eminent fathers of the church, page 87) በሌላም በኩል ሐዋርያው ባኮስ (አቤላክ) ከመጠመቁ በፊት 35 ዓመት ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ41 ዓመት ኖሮ በኢየሩሳሌምም 3ዓመት ተቀምጦ ወንጌልን ዞሮ ካስተማረ በኋላ በመጨረሻ በ79ዓመቱ ጥር 18 ቀን በሰሜን ተራራዎች ላይ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ እንደተሰወረ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱሳት_ደናግል_ማርያ_ወማርታ (የአልዓዛር እህቶች)
በዚህችም ዕለት ከአራ ቀኖች በኋላ ጌታችን ከመቃብር ያስነሳው የአልዓዛር እህቶች የማርያ እና የማርታ መታቢያቸው ሆነ፡፡ በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ 'እንተ ዕፍረት-ባለ ሽቱ' ተብለው የሚጠሩ 2 እናቶች ነበሩ:: 2ቱም ስማቸው ማርያም ስለ ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን 'ማርያም ኃጥዕት ከኃጢአት የተመለሰች': 2ኛዋን ደግሞ 'ማርያም እኅተ አልዓዛር - በቢታንያ የነበረችው ብለው አበው ይጠሯቸዋል::
በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል 12:1 ላይ ያለችው የአልዓዛር እህት (ድንግሊቱ) ናት:: ዛሬም የምናስባት ይህቺውን እናታችን ነው::
ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሚያስተመርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር የነበረች ድንግል ወጣት ናት:: ወላጆች ባልነበረበት ቤት ውስጥ ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል::
በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን ወደዳቸው:: አልዓዛርን ከ72ቱ አርድእት: ማርያምና ማርታን ደግሞ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል:: ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር::
ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ:: በ4ኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት ሰግዳ "እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እሑየ-አንተ በዚህ በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር" ብላ አለቀሰች:: (ዮሐ.11)
ጌታም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አምላክነቱ አራርቶት አለቀሰ:: ወዲያውም በስልጣነ ቃሉ አዞ አልዓዛርን አስነሳው:: ከፋሲካ (ጌታ ከመሰቀሉ 6 ቀናት) በፊትም ቅዱሳኑ ለጌታ ግብር አገቡ:: እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ታደመላቸው:: (ዮሐ. 12:1)
በዚያም አልዓዛር ከጌታ ጐን ሲቀመጥ: ቅድስት ማርያም ከጌታ ሥር ተንበርክካ: ናርዶስ የሚሉትን የ300 ዲናር ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች:: መዓዛ መለኮቱና ሽቱው ሲገናኝ "መልዐ መዓዛሁ" እንዲል ምስጥ የሚያደርግ ሽታ ቤቱን ሞላው::
በወቅቱ ይሁዳ ቢቃወምም ጌታ ምላሹን ሰጥቶታል:: ቅድስት ማርያምንም "ማርያምሰ ኃርየት መክፈልተ ሠናየ ዘኢየኃይድዋ" ብሎ አመስግኗታል:: ያስመሰገናት ቁጭ ብላ በተመስጦ መማሯ ብቻ እንዳልሆነ አባ ሕርያቆስ መስከሯል::
ሲመክረንም "አርምሞንና ትዕግስትን እንደ ማርያም ገንዘብ እናድርግ" ብሎናል:: (ቅዳሴ ማርያም) ቅድስት ማርያም በጌታችን ክርስቶስ በኅማሙ ጊዜ: ሲቀብሩት ነበረች:: ትንሳኤውንም ዐይታለች::
ከጌታ እርገት በኋላም መንፈስ ቅዱስን ተከትላ ለወንጌል አገልግሎት ተግታለች:: ቅድስት እናታችን ማርያም እንተ ዕፍረት ዛሬ በዓሏ ከእህቷ ቅድስት ማርታ ጋር ይከበራል::
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages