ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 26 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር 26

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ኅዳር ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት #አቡነ_ኢየሱስ_ሞዓ ዕረፍት ነው፣ #የአቡነ_ሀብተ_ማርያም ዕረፍት ነው፣ #የሀገረ_ናግራን_ሰማዕታትና የአባታቸውም #የቅዱስ_ኂሩት መታሰቢያቸውም ነው፣ #የቅዱስ_ቢላርያኖስ_ሚስቱ_ኪልቅያና_እኅቱ_ታቱስብያ በሰማዕትነት ያረፉበት ነው።


ኅዳር ሃያ ስድስት በዚህች ዕለት አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ዘሐይቅ እረፍታቸው ነው። በጐንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ዳህና ሚካኤል በተባለው ቦታ ከአባታቸው ከዘክርስቶስና ከእናታቸው ከእግዚእ ክብራ በ1210 ዓ.ም ነው ተወለዱ። ዕድሜያቸው 3ዐ ዓመት እስከሚደርስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ124ዐ ዓ.ም ይኼንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ። በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን እያጠኑ፣ ትምህርተ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ ምንኩስናን ተቀበሉ (1247 ዓ.ም.)።
አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ (ገድልህና ትሩፋትህ በዓለም ሕዝብ ሁሉ ትተህ የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራ ሂድ) አላቸው። አባታችን "ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ" በማለት ቢጠይቁት "ተነሥ። ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ" አላቸው። አባ ኢየሱስ ሞዓ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበአታቸው ተነሥተው ተከተሉት። የብዙ ወራት መንገድ የሆነው ጐዳናም በስድስት ሰዓት አለቀላቸው።
በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ። ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከመግባታቸውም በፊት ለ6 ወራት ያህል በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል። ያገለግሉበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር። በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበውም ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው እንደነበር ዛሬ በገዳማቸው የሚገኘው ገድለ ኢየሱስ ሞዓ ያስረዳል።
በመጨረሻም በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ። ሐይቅ እስጢፋኖስ ማለት ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሰረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብጻዊ ጻድቅ ናቸው፤ ገዳሙን ከሰሩ በኃላ የማንን ታቦት እናስገባ ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ ሁለት ታቦት አገኙ አንዱ የእስጢፋኖስ አንዱ የጊዮርጊስ " ይህንን ታቦት በእየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚያብሔር ታዘው የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍም አገኙ ይላል። ይህ ከሆነ ከ 400 ዘመን በኃላ ነው አባ እየሱስ ሞኣ ወደዚህ ቦታ የመጡት ለ 52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ስራቸውን ይሰራሉ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ።
አባ ኢየሱስ ሞዓ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማስገልበጥ ብሎም በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል። በዚሁ ገዳም ውስጥም የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ትምህርት ቤት በማቋቋም 8ዐዐ መነኮሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ በመላ ሀገሪቱ እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል።
ከተማሪዎቻቸውም መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ዘደብረ ሊባኖስ)፣ አባ ተክለሃይማኖት ያመነኮሱ አባት ናቸው። አባ ኂሩተ አምላክ (ዘጣና ሐይቅ)፣ አባ ጊዮርጊስ (ዘጋሥጫ)፣ አባ ዘኢየሱስ፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል፣ አባ አሮን (ዘደብረ ዳሬት) ጥቂቶች ናቸው። አፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት ያነፁት እርሳቸው ናቸው።
እንደዚህ ነው የመነኮሳት አባት እንጦንስ ነው እንጦንስ መቃርስን ወለደ መቃርስ ጳኩሚስን ጳኩሚስ አቡነ አረጋዊን አቡነ አረጋዊ አባ ዮሐኒን አባ ዮሐኒ የሐይቁን አባ እየሱስ ሞአን ወለዱ አባ ኢየሱስ ሞዓ ደግሞ ተክለሃይማኖትን ወለዱ።
በዮዲት ጉዲት ተጐድታ የነበረችው ሀገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት እንዲይነጥፉባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኮሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አባ ኢየሱስ ሞዓ ናቸው። በተለይም የሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈራቸው 8ዐዐ ሊቃውንት በመላዋ ሀገሪቱ በመሠማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኞቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውናል።
አባታችን አባ ኢየሱስ ሞዓ ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከቆዩ በኋላ ኅዳር 26/1292 ዓ.ም በዕለተ እሑድ በ82 ዓመታቸው ዐረፉ። በዚያች ዕለትም በቦታው የታየው ብርሃን ሀገሪቱን መልቷት እንደነበረ ገድላቸው ይመሠክራል።

በዚህችም ቀን የተመሰገነና የከበረ ንጹሕም የሆነ የኢትዮጵያዊ አባታችን የሀብተ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
የዚህ ቅዱስ አባት የትውልድ አገሩ የራውዕይ በምትባል በስተ ምሥራቅ ባለች ሀገር ውስጥ ነው በዚያም ስሙ ፍሬ ቡሩክ የሚባል አንድ ሰው ነበረ ይህም ክቡራንና ታላላቅ ከሚባሉት ከዚች አገር ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው ። እጅግም ሀብታም ነበር ብዙ ንብረትም አለው በሕጋዊ ጋብቻም ስሟ ዮስቴና የምትባል ብላቴና ድንግልን አገባ ይቺም የተመረጠች በበጎ ሥራ የተሸለመችና ያጌጠች ናት።
ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕግ ባሏ ጋር በንጹሕ ጋብቻ እግዚአብሔርን በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የዋህነትን ትሕትናን ፍቅርን ትዕግሥትን ገንዘብ አድርጋ በጾም በጸሎት ተወስና እንደኖረች እንነግራችኋለን ። በእንደዚህም ሳለች ጌታችን በወንጌል ሰው ዓለሙን ቢያተርፍ ነፍሱን ካጠፋ ምን ይጠቅመዋል እንዳለ ላንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሽ የሚል ሐሳብ መጣባት ።
ከዚህም በኋላ ወጣች ፈጥናም በሀገርዋ ትይዩ ወደሆነ ምድረ በዳ ደርሳ ወደ መካከሉ ገባች በዚያም በረሀ አራዊት እንጂ ሰው አይኖርበትም በዚያም ደጃፍዋ የተከፈተ ታናሽ ዋሻ አግኝታ ምንም ምን ሳትነጋገር ወደ ውስጧ ገብታ ቆመች የዳዊትንም መዝሙር የሚጸልይ ሰው አይታ ደነገጠች።
እርሱም ባያት ጊዜ ፍርሀትና መንቀጥቀጥ በላዩ ወረደበት በመስቀል ምልክትም በላይዋ አማትቦ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ እንዳልሸሸችም አይቶ ሰው መሆንዋን አወቀ በአወቀም ጊዜ እንዲህ ብሎ ገሠጻት ወደዚህ ምን አመጣሽ ለእኔ እንቅፋት ልትሆኚ ነውን አሁንም ከዚህ ፈጥነሽ ሒጂ አላት ።
እርሷም አባቴ ሆይ አንተ እንዳሰብከው አይደለሁም እኔ ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዩ ነኝ እንጂ በእርሱ ፍቅርና በእናቱ በእመቤቴ በቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር ያለኝን ሁሉ ትቼ ንቄ ከዓለም ወጥቼ ወደዚህ መጣሁ በዚህ ቦታም ከአራዊት በቀር ሰው እንዳለ አላወቅሁም አሁንም አባቴ ይቅርታ አድርግልኝ ወደ ሌላ ቦታ እሔዳለሁ አለችው ።
በዚያንም ጊዜ ከርሷ የሚሆነውን መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት እንዲህ አላት ዜናው ወደ ዓለም ሁሉ የሚወጣ በሕይወተ ሥጋም እያለ የብዙዎች ሰዎች ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣ እንደ መላእክትም ክንፎች ተሰጥተውት ወደ አርያም ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትና የሦስትነትን ምሥጢር የሚያይ ልጅን ትወልጂ ዘንድ አለሽና ወደ ቤትሽ ተመለሽ አላት ።
ቅድስት ዮስቴናም ከዚያ ሽማግሌ ባሕታዊ ይህን በሰማች ጊዜ አድንቃ የፈጣሪዬ ፈቃዱ ከሆነ ብላ ወደቤቷ ተመለሰች።
ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ፀንሳ ይህን ደም ግባቱ መልኩ የሚያምር ልጅን ወለደች በእናትና በአባቱ ቤትም ታላቅ ደስታ ሁኖ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ለዘመዶቻቸውና ለጎረቤቶቻቸው ታላቅ ምሳ አደረጉ እነርሱም በጠገቡ ጊዜ እነርሱንም ሕፃኑንም መረቋቸው ።
ሕፃኑም አርባ ቀን በሆነው ጊዜ እንደ ሕጉና እንደ ሥርዓቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዱት ካህኑም ተቀብሎ በአጠመቀው ጊዜ ስሙን ሀብተ ማርያም ብሎ ሰይሞ ለክርስትና አባቱ ሰጠው ሕፃኑም ጥቂት በአደገ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ሲሉ ሰምቶ ሕፃኑ ሀብተ ማርያም በልቡ ይቺ ጸሎት መልካም ናት እኔም መርጫታለሁ በዚህ ዓለም ስሕተትን አስቦ ከመሥራት በሚመጣውም ዓለም ከገሀነም እንደምድንባት አውቃለሁና አለ ። ይህንንም ብሎ የሚሠራውን ማንም ሳያውቅበት ይህን ጸሎት ከማዘውተር ጋር ሌሊቱን ሁሉ በመስገድ ይፀልይ ነበር ።
ከዚህም በኋላ አባቱ የበጎች ጠባቂ አደረገው በአንዲት ዕለትም በጎቹን አየጠበቀ ሳለ ብዙ የበግ ጠባቂዎች እሸት ተሸክመው መጥተው ና እንብላ አሉት እርሱ ግን ከወዴት እንዳመጣችሁት የማላውቀውን አልበላም አላቸው እነርሱም በቁጣ ዐይን ተመልክተው ተጠቃቀሱበት ።
እሸቱንም በልተው ከጨረሱ በኋላ የከበረ ሕፃን ሀብተ ማርያምም ታላቅ ዝናም ስለመጣ ወደየቤታችን እንመለስ ከዚህ የምንጠለልበትና የምንጠጋበት ቤት ወይም ዋሻ የለምና አላቸው ። እነርሱም እኛ የማናየውን የሚያይ ሌላ ዐይን አለህን በሰማይ ፊት ምንም ደመና ሳይኖር ሀገሩም ብራ ሆኖ ሲታይ እንዴት ይዘንማል ትላለህ አሉት እርሱም እኔ የማውቀውን እናንተ አታውቁትም ግን ወደ ቤታችሁ ግቡ አላቸው እረኞችም ባልሰሙት ጊዜ ፈጥኖ ተነሥቶ በጎቹን እያስሮጠ ወደ ቤቱ ገባ ። ወደ ቤቱም በገባ ጊዜ ታላቅ ዝናም መጣ ነፋሳትም ነፈሱ መብረቆችም ተብለጨለጩ ነጎድጓድም ተሰማ ደመናትም ተነዋወጹ ይህ ሁሉ በላያቸው ሲወርድ መሸሺያ አላገኙም ።
ከጥቂት ቀኖችም በኋላ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ ብዙ የበግ እረኞችም አብረውት ነበሩ አንድ የበግ ጠባቂም መጥቶ የወጣት ሀብተ ማርያምን በትር ነጠቀውና ሔደ ብላቴና ሀብተ ምርያምም በትሬን ለምን ትቀማኛለህ አለው እረኛውም በትዕቢት ቃል በጉልበቴ ነጥቄሃለሁ አለው ብላቴና ሀብተ ማርያምም እኔ ኃይል የለኝም ነገር ግን በጎቼን የምጠብቅበትን በትሬን እንዳትወስድብኝ በሕያው እግዚአብሔር ስም አምልሃለሁ አለው ያም የበግ ጠባቂ እምቢ አልኩህ አለው ።
ብላቴናው ሀብተ ማርያምም አንድ ጊዜ በፈጣሪዬ ስም አማልኩህ ከእንግዲህ ወዲያ ደግሜ አላምልህም በአንተ ላይ የሚደረገውን ራስህ ታውቀዋለህ ይህንንም ተናግሮ ዝም አለ ። በዚያንም ጊዜ ያ የበግ ጠባቂ በአየር ውስጥ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሀብተ ማርያም ማረኝ እያለ ይጮህ ጀመረ የልዑል እግዚአብሔርን ስም አቃልሏልና ተሰቅሎ ዋለ እረኞች ሁሉም አይተው አደነቁ ፈሩትም ይህን ሰነፍ ማርልን እግዚአብሔር ያደረገልህን ኃይል አይተናልና አሁንም ስለ እምቤታችን ድንግል ማርያም ይቅር በለው አሉት ። ብላቴናው ሀብተ ማርያምም በውኑ እኔ የሰቀልኩት ነውን በእግዚአብሔር ስም አማልኩት እንጂ የኃይሉን ጽናት በላዩ ሊገልጥ እርሱ እግዚአብሔር ሰቀለው አሁን እርሱ ከፈቀደ ያውርደው እርሱ መሐሪና ይቅር ባይ ነውና ይህንንም በተናገረ ጊዜ ወርዶ በእግሩ ቆመ ወደርሱም መጥቶ ሰገደለት ።
ከረጂም ዘመናትም በኋላ ስሟ እለአድባር ወደምትባል ገዳም ሒዶ ከዚያም የምንኩስናን ሥርዓትና ሕግ በአበምኔቱ በተመረጠ አባ መልከጸዴቅ እጅ ተቀበለ ከዚያም ቅዱሳን መነኰሳት ወደሚኖሩበት ሔዶ ታላቅ ተጋድሎ ጀመረ ።
እርሱም በባሕር መካከል በመቆም የዳዊትን መዝሙር ሁሉንም ያነባል በባሕር ውስጥም ሰጥሞ ግምባሩ አሸዋ እስቲነካው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳል ከሰንበት ቀኖችም በቀር እህል አይቀምስም ነበር ከዚህም በኋላ እህልን ትቶ እንደ ዋልያዎች የዱር ቅጠል የሚመገብ ሆነ ።
አርባ አርባ ሰማንያ ሰማንያ ቀን የሚጾምበት ጊዜ አለ በባሕር ውስጥ በሌሊት ቁሞ በማደር በቀንም አራቱን ወንጌላት ያነባል ሌሎች መጻሕፍትንም በእንዲህ ያለ ሥራ ብዙ ዘመን ኖረ።
ብዙ ተጋድሎንና ድካምንም በአስረዘመ ጊዜ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ ተገልጦ መጣ ከእርሱ ጋርም የመላእክት አለቆች የከበሩ ሚካኤልና ገብርኤል የመላእክት ማኅበርም ሁሉ በዙሪያው ሁነው እያመሰገኑት ነበር ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ላንተ ይሁን አለው ። በዚያንም ጊዜ ከግርማው የተነሣ ወድቆ እንደ በድን ሆነ ጌታችንም በከበሩ እጆቹ አንሥቶ እፍ አለበትና ጽና ኃይልህን ላድሳት እንጂ ላጠፋህ አልመጣሁምና ተጋድሎህና ድካምህ ሁሉ በኢየሩሳሌም ሰማያዊት እንደ ተጻፈ በእውነት እነግርሃለሁ ።
እነሆ እኔ በጎ ዋጋህን በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም እከፍልሃለሁ የማቴዎስንና የማርቆስን ወንጌል በምታነብ ጊዜ በተራራዎችና በዋሻዎች በፍርኩታ ተሠውረው ወደሚኖሩ እንዳንተ ካሉ ቅዱሳን ጋር ለመገናኘት በላዩ ተቀምጠህ ወደ ምሥራቅ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንና ደቡብ የምትበርበት የብርሃን ሠረገላ ሰጠሁህ ሉቃስና ዮሐንስ የጻፉትን ወንጌል ባነበብክ ጊዜ ሥጋዬንና ደሜን በዚያ ትቀበል ዘንድ በላዩ ተቀምጠህ ወደ ኢየሩሳሌም የምትሔድበት የእሳት ሠረገላ ሰጠሁህ አለው ።
ከብዙ ዘመናትና ከብዙ ተጋድሎ በኋላ የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ ለሞቱ ምክንያት የሚሆን ቸነፈር ያዘው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጥቶ ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሰላም ላንተ ይሁን ዛሬ ግን የመጣሁት ከድካም ወደ እረፍት ልወስድህ ነው እነሆ ሰባት አክሊላትን አዘጋጅቼልሃለሁና አንዱ ስለ ድንግልናህ ሁለተኛው ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉን ትተህ በመውጣትህ ሦስተኛው ፍጹም ስለሆነው ምንኩስናህ አራተኛው አራቱን ወንጌሎች አዘውትረህ የምታነብ በመሆንህ አምስተኛው ስለ እኔ ፍቅር መራብና መጠማትን ስለታገሥክ ስድስተኛው በልብህ ቂምና በቀልን ባለማሳደርህ ሰባተኛውም ስለ ንጹሕ ክህነትህና ስለምታሳርገው ያማረ የተወደደ ዕጣንህና መሥዋዕትህ ሰጠሁህ እሊህ ሰባቱ አክሊላትም ለየአንዳንዳቸው ዐሥራ አምስት ዐሥራ አምስት ኅብር አላቸው ።
መታሰቢያህን ካደረጉና በጸሎትህ ከተማፀኑ ጋር የምትገባበትን ቤት በውስጧ አምስት መቶ የወርቅ አምዶች የተተከሉባትን ሰጠሁህ ደግሞ የእሳት መስቀልን የወርቅ ጫማን የብርሀን ልብስን ሥውር የሆነ መና እሰጥሃለሁ አለው ።
መድኃኒታችንም ይህን ቃል ኪዳን ሲሰጠው በየነገዳቸውና በየሥርዓታቸው ዘጠና ዘጠኝ የመላእክት ሠራዊት መጥተው ወዳጃችን ሰላም ላንተ ይሁን ዛሬስ ከፀሐይ ሰባት እጅ ወደምታበራ ሀገራችን በዝማሬና በማኅሌት አክብረን ልንወስድህ መጣን አሉት ። አባታችን አባ ሀብተ ማርያምም በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ሆነ የሰው ነጻነቱ ሊሰጠው አለ ።
ይህንንም በተናገረ ጊዜ ጌታችን በሦስትነቱ ተገልጦ ታየውና የመጥምቁ ዮሐንስን ሀገር ተጠጋግታ ያለች ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ ሀገርን እሰጥህ ዘንድ በራሴ ማልኩልህ አለው ።
መታሰቢያህን የሚያደርገውን በስምህ ለቤተ ክርስቲያን መባ የሚሰጠውን ስምህንም የጠራውን ወደዚች አገር አገባዋለሁ አራቱን ወንጌሎችም እያነበብክ ስለኖርክ የየአንዲቱን ቃል ፍሬዋን አንዳንድ ሽህ አደረግሁልህ ይኸውም ካንተ በኋላ ለሚመጡ ልጆችህ መጽሐፈ ገድልህን ለሚያነቡና በእምነት ለሚሰሙ የገድልህ መጽሐፍ በተነበበበት ውኃ ለሚረጩ ለሚነከሩበት ይህን ቃል ኪዳን ሰጥቼሃለሁ ።
ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አፉን ሦስት ጊዜ ሳመው በዚያንም ጊዜ ከፍቅሩ ጣዕም ብዛት የተነሣ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ጌታችንም ተቀብሎ አቅፎ ከእርሱ ጋር አሳረጋት ። በመላእክት ጉባኤም ብዙ ምስጋና ተደረገ ።

በዚህችም ቀን የሀገረ ናግራን ሰማዕታትና የአባታቸውም የቅዱስ ኂሩት መታሰቢያቸው ነው። ይህም ዮስጢኖስ ለቁስጥንጥንያ በነገሠ በአምስተኛው ዓመት ለኢየሩሳሌም አባ ዮሐንስ ለእስክንድርያ አባ ጢሞቴዎስ ለቁስጥንጥንያም አባ ጢሞቴዎስ ለአንጾኪያ አባ አውፍራስዮስ ሊቃነ ጳጳሳት ሁነው ሳለ በኢትዮጵያም ጻድቁ ካሌብ ነግሦ ሳለ በዚያን ወራት ለአይሁድ ስሙ ፊንሐስ የሚባል አይሁዳዊ ነገሠ ።
በመጀመሪያ ግን ሳባ የተባለች አገር በኢትዮጵያ ነገሥታት እጅ ውስጥ ነበረች የሮም ነገሥታት አስባስያኖስና ጥጦስ ከኢየሩሳሌም አይሁድን በአሳደዷቸው ጊዜ ይቺን ሳባን አይሁድ ወረሷት።
በውስጧም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ብዙዎች ክርስቲያኖች የሚኖሩባት ታላቅ ከተማ አለች ይህም የተረገመ አይሁዳዊ ፊንሐስ ሊአጠፋት በመጣ ጊዜ የዚችን የከበረች ሀገር በመስቀል ምልክት በዙሪያዋ ያለ ቅጽርዋን በበሮቿና በግንብ አጥርዋ ላይ ያሉ ብዙ አርበኞች ሠራዊትን አይቶ በምንም ምክንያት ሊገባባት ስለአልተቻለው ተቆጣ ። እግዚአብሔር አጽንቷታልና ነገር ግን በውጭ ያገኛቸውን ገበሬዎች ገደለ ታናናሾችንም ማርኮ ለባሮቹ ሰጣቸው ።
ይህም ዲያብሎስን የሚመስለው አይሁዳዊ የኦሪትና የነቢያት ፈጣሪ በሆነ በእግዚአብሔር ስም እየማለ በተንኰል መልእክትን ላከ እንዲህም አላቸው እኔ ከእናንተ ጋር ጠብ አልሻም ከሀገር ሰው አንዱን እንኳ ማጥፋት አልፈልግም በሀገሪቱም ውስጥ የደም ጠብታ አይፈስም ነገር ግን የከተማዋን አሠራርዋን አደባባዮቿን ገበያዎቿን ማየት እሻለሁ ለሀገር ሰዎችም የተናገረው ዕውነት መሰላቸው ።
የካዕቢ ልጅ አባት ኂሩት ይህን አይሁዳዊ አትመኑት ሐሰተኛ ነውና ደጁንም አትክፈቱለት አላቸው አባት ኂሩትንም አልሰሙትም ደጁንም ከፈቱለትና ገባ ከገባ በኋላም አስቀድሞ የአገሪቱን ሰዎች ገንዘባቸውን እንዲዘርፉአቸው አዘዘ ። ሁለተኛም ነበልባሉ ወደ አየር እስቲደርስ እሳትን አንድደው የሀገሪቱን ኤጲስቆጶስ አባ ጳውሎስን እንዲአመጡት አዘዘ እርሱ እንደ ሞተም በነገሩት ጊዜ ዐፅሙን ከመቃብር አውጥቶ አቃጠለው ።
ከዚህም በኋላ ቀሳውስትን ዲያቆናትን መነኰሳትን አንባቢዎችንና መዘምራኑን በቀንና በሌሊት መጻሕፍትን በማንበብ የሚተጉትን ሰበሰበ እነርሱንም ከእሳት ውስጥ ጨመራቸው ቁጥራቸውም አራት ሺህ ሃያ ሰባት ነፍስ ሆነ ክርስቲያኖችን በዚህ ሊአስፈራራቸው አስቧልና።
ዳግመኛም የብረት ዛንጅር በቅዱስ አባት ኂሩት አንገት ውስጥ እንዲአስገቡ እጆቹንና አግሮቹንም እንዲአሥሩት አዘዘ ታላላቆችንና የሀገሩን መኳንንትንም እንዲአሥሩአቸው ክርስቶስን የማይክደው ሁሉ እንዲህ ተሠቃይቶ በክፉ አሟሟት ይሞታል የሚል ዐዋጅ ነጋሪ እየጮኸ በከተማው ውስጥ እንዲአዞሩአቸው አዘዘ ።
ቅዱሳን የክርስቲያን ወገኖች በሰሙ ጊዜ እንዲህ እያሉ ጮኹ እኛ ያመንበትንና በስሙ የተጠመቅንበትን ክብር ይግባውና ክርስቶስን አንክደውም ይህ ርጉም አይሁዳዊም ሰምቶ ወንዶችና ሴቶችን ወጣቶችንና ሕፃናትን ሽማግሎችን ሁሉንም እንዲገድሉ አዘዘና ገደሉአቸው ቁጥራቸውም አራት ሺህ ሁለት መቶ ኃምሳ ሁለት ነፍስ ሆነ ።
ከዚህም በኋላ የቅዱስ ኂሩትን ሚስት ቅድስት ድማህን ከሁለት ሴቶች ልጆቿ ጋር ያዧት እነርሱም በቤታቸው መስኮት ከሚገባው በቀር ፀሐይ ያልነካቸው ናቸው ደርሰውም በአይሁዳዊ ንጉሥ ፊት በቆሙ ጊዜ እርሱም ሃይማኖታቸውን ያስክዳቸው ዘንድ በብዙ ተንኮል ሊሸነግላቸው ጀመረ እምቢ ባሉትም ጊዜ የራሳቸውን መሸፈኛ እንዲገልጧቸው አዘዘ የሀገር ሴቶችም እስከ ሚያለቅሱ ድረስ ከልጆቹም የምታንስ አንዲቱ ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆነ ከንጉሡ ፊት ላይ ምራቋን ተፋችበት ።
ወታደሩም አይቶ ሰይፉን መዝዞ አንገቷን ቆረጠ የእኅቷንም አንገት ቆረጠ ። ይህ የረከሰ አይሁዳዊ ንጉሥም ለቅድስት ድማህ የልጆቿን ደም እንዲአጠጧት አዘዘ እርሷም ቀምሳ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶሰ ሆይ አመሰግንሃለሁ እንደቁርባን መሥዋዕት የሆነውን የልጆቼን ደም እኔ ባሪያህ እንድቀምስ አድርገሃልና አለች ። በዚያንም ጊዜ ርሷንም በሰይፍ አንገቷን እንዲቆርጡ ዳግመኛ አዘዘ ተጋድሎአቸውንም ፈጸሙ ።
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ኂሩትን ከእሥር ቤት እንዲአመጡት ንጉሥ አዘዘ ከርሱም ጋር አንድ ሺህ አርባ እሥረኞች ሰዎች አሉ ሃይማኖቱንም ይተው ዘንድ አስገደደው ። ቅዱስ ኂሩትም ንጉሡን እንዲህ አለው ክብር ይግባውና ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን እያመለክሁት ስኖር ሰባ ስምንት ዓመት ሆነኝ እስከ አራት ትውልድ ለማየትም ደርሼአለሁ ዛሬም ስለ ከበረ ስሙ ምስክር ሁኜ ስሞት እጅግ ደስ ይለኛል ።
እኔኮ አስቀድሜ መሐላህን እንዳያምኑ ለወገኖቼ ነግሬአቸው ነበር አንተ ሐሰተኛ ነህና ነገር ግን ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው የሆነው ለዚህም ተጋድሎ ላደረሰኝ ለእርሱ ምስጋና ይሁን ንጉሡም ይህን ሰምቶ ተቆጣ ወደ ወንዝም ወስደው በዚያ አንገቱን እንዲቆርጡት አዘዘ ።
ቅዱስ አባት ኂሩትም በሰማ ጊዜ ደስ አለው የሮምንና የኢትዮጵያን መንግሥት ያጸና ዘንድ የተረገመ የአይሁዳዊውን መንግሥት ያጠፋ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ሕዝቡንም ባረካቸው ።
ከእርሳቸው ጋር በሰላምታ ተሰናበታቸው ከዚህም በኋላ የቅዱሳኑን ራሶቻቸውን ቆረጧቸው በዚያም የአምስት ዓመት ልጅ ያላት አንዲት ክርስቲያን ሴት ነበረች ከቅዱሳን ደም ወስዳ ተቀባች ልጅዋንም ቀባችው ወታደሮችም አይተው አሥረው ወደ ንጉሡ አድርሰው ከእሳት ጨመርዋት ልጅዋን ግን አይሁድ ወደ እነርሱ ወስደው ወደ ንጉሡ አቀረቡት ንጉሡም እኔን ትወዳለህን ወይስ ክርስቶስ የሚሉትን አለው ሕፃኑም እኔስ የእጁ ሥራ ነኝና ክርስቶስን እወደዋለሁ ይልቅስ ልቀቀኝ ወደ እናቴ ልሒድ አለው በከለከለውም ጊዜ እግሩን ነከሰው አምልጦም ሩጦ ከእሳቱ ውስጥ ገባ ።
ሁለተኛም የዐሥር ወር ሕፃን እንደ ተሸከመች አንዲትን ሴት አመጧት እርሷም ልጄ ሆይ ላዝንልህ አልቻልኩም አለችው ያ ሕፃንም እናቴ ሆይ በፍጥነት ወደ ዘላለም ሕይወት እንሒድ ይቺን እሳት ከዛሬ በቀር አናያትምና አላት በዚያንም ጊዜ ከልጅዋ ጋር ወደ እሳት ውስጥ ተወረወረች ።
የክርስቲያን ወገኖችም ይህን አይተው እኩሌቶቹ ወደ እሳት እኩሌቶቹም ወደ ሰይፍ ተቀዳደሙ የአይሁድ ጉባኤ ዕጹብ ዕጹብ ብለው እስኪያደንቁ ድረስ ከዚህም በኋላ እሳቱ በሰማይ ውስጥ መልቶ አርባ ቀን አርባ ሌሊት ታየ ።
የአይሁድ ንጉሥ ፊንሐስም ወደሀገሩ በሔደ ጊዜ ወደ ነገሥታቱ ሁሉ በኃይሉ እየተመካ ላከባቸው የሮሜ ንጉሥ ዮስጢኖስም ሰምቶ ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ ጢሞቴዎስ ላከ በሀገረ ናግራን ለሚኖሩ የክርስቲያን ወገኖች ደማቸውን ይበቀል ዘንድ ለኢትዮጵያ ንጉሥ ለካሌብ መልእክት እንዲልክ ነው ።
የኢትዮጵያ ንጉሥ ካሌብም መልእክት በደረሰው ጊዜ ፈጥኖ ተነሣ በዋሻ ከሚኖር ከአባ ጰንጠሌዎን በረከትን ተቀብሎ ከብዙ ሠራዊት ጋር በመርከቦች ተጭኖ ሔደ በደረሰም ጊዜ የሳባን ንጉሥ የፊንሐስን አገር አጠፋ ሰውም ሆነ እንስሳም ሆነ ሸሽቶ የሚያመልጥ እንኳ ምንም ምን ሳያስቀር አጠፋቸው የናግራንን ከተማ ሕንፃዋን አደሰ የሰማዕታትንም መታሰቢያ አቆመ ። ከዚህም በኋላ ወደ ሮሜ ንጉሥ ዮስጢኖስ ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጢሞቴዎስ የምሥራች ላከ እነርሱም ሰምተው እጅግ ደስ አላቸው እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

ዳግመኛ በዚህች ቀን ቅዱስ ቢላርያኖስ ሚስቱ ኪልቅያና እኅቱ ታቱስብያ በሰማዕትነት አረፉ ።
ይህም ቅዱስ የሮም አገር ሰው ነው ወላጆቹም አረማውያን ናቸው ከሮሜ አገር ከታላላቆች ሰዎች ልጆች ውስጥ ሚስትን አጋቡት እርሷም ስሟ ኪልቅያ የሚባል ክርስቲያን ናት እጅግም ወደዳት እንደወደዳትም በአወቀች ጊዜ የቀናች የክርስቲያን ሃይማኖትን በግልጽ ታስተምረው ጀመረች እርሱም አምኖ ተጠመቀ ልቡም ብሩህ የሆነ መለኮታዊት ጸጋም አደረችበት እርሱም ታቱስብያ የተባለች እኅቱን አስተማራት እርሷም አምና ተጠመቀች ።
ይህም ቅዱስ ቢላርያኖስ መላእክት ሁልጊዜ ወደርሱ መጥተው የሚሻውን ምሥጢራትን እስከሚገልጡለትና እስከሚያስተምሩት ድረስ ታላቅ ተጋድሎን መጋደል ጀመረ ።
ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስም በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖችን አሠቃያቸው ብዙዎችንም አሠቃይቶ በሰማዕትነት አረፉ ። ይህ ቅዱስ ቢላርያኖስም ከእኅቱ ታቱስብያ ጋር እየዞሩ የሰማዕታትን በድናቸውን እያነሡ የሚቀብሩዋቸው ሆኑ አንድ ክፉ የሆነ ሰውም በአወቀባቸው ጊዜ የንጉሥ ወዳጁ ለሆነ ለአግማስዮስ ሒዶ ነገረው እርሱም ወደርሱ እንዲአቀርቧቸው አዘዘ በፊቱም በቆሙ ጊዜ ስለ ሃይማኖታቸው ጠየቃቸው እነርሱም ክርስቲያኖች እንደሆኑ አመኑ ።
ይህም መኰንን ሸነገላቸው ለአማልክት ይሠዉ ዘንድ ብዙ ቃል ኪዳንንም ገባላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም እንዲህም ብሎ አሰፈራራቸው ካልሰማችሁኝና ለአማልክት ካልሠዋችሁ እኔ በጽኑ ሥቃይ አሠቃያችኋለሁ አላቸው እነርሱም ሥቃዩን ከቶ አልፈሩም ።
ጽናታቸውንና ትዕግሥታቸውን አይቶ አንገታቸውን ለሚቆርጥ አሳልፎ ሰጣቸው ራሶቻቸውንም በቆረጧቸው ጊዜ ከዚያ ያሉ ሁሉ ነፍሶቻቸውን በደስታ ሲቀበሉ ብርሃናውያን መላእክትን አዩአቸው መኰንኑም ይህን አይቶ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ። ንጉሡም ሦስት ቀን አሠረው በአራተኛውም ከእሥር ቤት አውጥቶ ራሱን በሰይፍ አስቆረጠው ከቅዱስ ቢላርያኖስና ከሚስቱ ኪልቅያ ከእኅቱ ታቱስብያ ጋር የሰማዕትነት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages