ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 28 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Friday, March 3, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ታኅሣሥ 28

 አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ታኅሣሥ ሃያ ስምንት በህች ዕለት #የጌና_በዓል ሆነ። ይኸውም የልደት በዓል ነው፣ ከእንዴናው አገር ሰዎች መቶ ሃምሳ ወንዶች ሃያ አራት ሴቶች በሰማዕትነት ሞቱ።


ታኅሣሥ ሃያ ስምንት በዚህች ዕለት የጌና በዓል ሆነ። ይኸውም የልደት በዓል ነው። ይህም እንዲህ ነው በአምላካችን በረቀቀ ጥበቡ ሰዎች ሁሉ ይቈጠሩ ዘንድ ስማቸውንም ይጻፋና ይመዘገቡ ዘንድ ከንጉሥ ቄሣር ትእዛዝ መጣ። ስለዚህም ከእመቤታችን ከከበረች ድንግል ማርያም ጋር ሊቆጠር ዮሴፍ ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም የርሱንና የቡርክት ድንግል ማርያምን ስም ሊስመዘግብ ወጣ እርሱ ከይሁዳ ነገድ ከዳዊት ወገን ነውና ቤተልሔምም የዳዊት ቦታው ናትና።
የከበረ ወንጌል እንደተናገረ ከዚህም በኋላ ከዚያ ሳሉ የምትወልድበት ቀን ደረሰ የበኵር ልጇንም ወለደች አውራ ጣቱንም አሠረችው በጨርቅም ጠቅልላ በበረት አስተኛችው ለማደሪያቸውም ቦታ አልነበራቸውምና። በዚያ ሰፈር እረኞች ነበሩ ሌሊትም በየተራቸው ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር። እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ አጠገባቸው ቆመ የእግዚአብሔርም ብርሃን በላያቸው በራ ታላቅ ፍርሀትም ፈሩ መልአኩም "ለእናንተና ለመላው ዓለም ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ" አላቸው።
"እነሆ ዛሬ በዳዊት አገር መድኅን የሆነ ጌታ ክርስቶስ ተወልዶላችኋልና። ለእናንተም ምልክት እንዲህ ነው ሕፃኑ አውራ ጣቱን ታሥሮ በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ" አላቸው። ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ "በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም በሰው በጎ ፈቃድ እያለ መጡ።
ከዚህም በኋላ መላእክት ከእነርሱ ዘንድ ባረጉ ጊዜ እነዚህ እረኞች ሰዎች እርስበርሳቸው "ኑ ወደ ቤተ ልሔም ሔደን ይህን እግዚአብሔር የገለጠውንን ነገር እንወቅ" አሉ። ፈጥነውም ሔዱ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በበረት ውስጥ ተኝተ አገኟቸው። አይተውም የነገሩዋቸው ስለዚህ ሕፃን እንደሆነ አወቁ እረኞች የነገሩዋቸውን የሰሙ ሁሉ አደነቁ። እረኞችም ለሕፃኑ ሰግደው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደ ቦታቸውም ተመለሱ።
ከወገናችን ሰው ሁኖ ለጐበኘንና ይቅር ላለን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#174ቱ_ሰማዕታት (የቅዱስ ጳውሎስ ማኅበር)
በዚችም ዕለት ደግሞ ከእንዴናው አገር ሰዎች መቶ ሃምሳ ወንዶች ሃያ አራት ሴቶች በሰማዕትነት አረፉ።
እሊህም ቀድሞ ከሀ*ዲያን ነበሩ የእንዴናው መኰንን የከበረ ሶርያዊ ጳውሎስን በሚያሠቃየው ጊዜ ከዚያ ነበሩ ሲአሠቃየውም ይመለከቱ ነበር መኰንኑም ችንካሮችን በእሳት አግለው ዐይኖቹን እንዲአወልቁ አዘዘ ይህንንም ባደረጉበት ጊዜ ዐይኖቹ ወለቁ ከወህኒ ቤትም ጣሉት። በማግሥቱም እሊኒ ሰዎች ሊያዩት በሔዱ ጊዜ ያለ ምንም ጉዳት ድኖ ጤነኛ ሁኖ አገኙት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አድኖታልና።
ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው እጅግ አደነቁ ጣዖ*ቶቻ*ቸውም ምንም መሥራት እንደማይችሉ አስተዋሉ። የክርስቲያኖች አምላክ እርሱ እውነተኛ አምላክ እንደ ሆነ አወቁ ወደከበረ ጳውሎስ ሒደው ሰገዱለት እንዲጸልይላቸውም ለመኑት እርሱም ባረካቸው እግዚአብሔር እምነታችሁን ተቀብሎ ከሰማዕታት ጋር ይቊጠራችሁ አላቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ቀርበው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ራሶቻቸውን ቊረ*ጡ ብሎ አዘዘና ቈረ*ጧቸው በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages