ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 3 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Saturday, March 11, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 3መጋቢት 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ቆዝሞስ (የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት)
2.አባ በርፎንዮስ ክቡር
ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

 አባ_ቆዝሞስ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መጋቢት ሦስት በዚች ቀን በእስክንድርያ ለተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት ሃምሣ ስምንተኛ የሆነው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ወቅዱስ አባ ቆዝሞስ አረፈ። ይህም አባት እውነተኛና ንጹሕ የዋህ ርኅራኄው የበዛ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍትና ትርጓሜያቸውን የሚያውቅ ነበር።
እግዚአብሔርም በወንጌላዊው ማርቆስ መንበር ላይ ለሊቀ ጵጵስና ሹመት መረጠው የግብጽ ንጉሥ መቅትር በነገሠ በአሥራ ስምንት ዓመት ሊቀጳጳሳት ሆኖ ተሾመ። በተሾመም ጊዜ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መንጋዎች በፈሪሀ እግዚአብሔርና በጥበብ ጠበቃቸው።
ለእርሱ ከሚገባው ከግብሩ ገንዘብ የሚተርፈውን ለጦም አዳሪዎች ይሰጣቸው ነበር ደግሞም ቤተክርስቲያን ሕንፃ ማሠሪያ ያወጣ ነበር። መልካም ተጋድሎውንም በአየ ጊዜ ሰይጣን ያለ ኀዘን አልተወውም ነገር ግን የሚያዝንበትን ምክንያት በላዩ አመጣ።
ይህም እንዲህ ነው ጴጥሮስ የሚባል ጳጳስ ለኢትዮጵያ አገር ሹሞ ነበር። አባ ጴጥሮስም ወደ ኢትዮጵያ በደረሰ ጊዜ ጥቂት ዘመን በሰላም ኖረ። ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሥ ታመመ አባ ጴጥሮስንም ጠርቶ ሁለቱን ልጆቹን አቀረበ ዘውዱንም ከራሱ ላይ አንሥቶ ለአባ ጴጥሮስ ሰጠው እነሆ እኔ ወደ ክብር ባለቤት ወደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እሔዳለሁ እነሆም ሁለቱ ልጆቼ በፊትህ ናቸው አንተም ለመንግሥት የሚሻለውን አውቀህ ከሁለቱ አንዱን ከእኔ በኋላ አንግሥ አለው።
ንጉሡም ካረፈ በኋላ ጳጳሱ መኳንንቱና የጦር ሠራዊቱ አለቆችና የመንግሥት ሠራዊት አለቆች ተማከሩ እርስ በርሳቸውም ለመንግሥት የሚሻል የሚያንሰው ነው ተባባሉ። ጳጳሱ አባ ጴጥሮስም ታናሹን የንጉሥ ልጅ ቀብቶ አነገሠው በኢትዮጵያ መንግሥት ዙፋን ላይም አስቀመጠው ጥቂት ዘመንም በሰላም ኖረ።
በዚያም ወራት ከሶሪያ አገር በሆኑ በሁለት መነኰሳት ልብ ሰይጣን አደረ ከአባ እንጦንስ ገዳም እስከ ሚደርሱ ከቦታ ወደቦታ ይዞሩ ነበር። በዚያም በአባ እንጦንስ ገዳም ጥቂት ቀኖች ተቀመጡ ስለ ሥራቸውም ክፋት አባረሩአቸው። ከዚህም በኋላ አንዱ ጳጳስ ሁለተኛውም ረዳት ሊሆን እርስ በርሳቸው ተስማሙ። ተነሥተውም ወደ ኢትዮጵያ ደረሱ። የሐሰት ጽሑፍንም ጻፉ ያ ጽሑፋቸውም እነርሱ ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ከአባ ቆዝሞስ ዘንድ ተሹመው እንደ መጡ የሚገልጥ ነበር።
በዚያ ጽሑፍም እኛ ያልሾምነውና ወደ እናንተ ያልላክነው ራሱን ጳጳስ ያደረገ ስሙ ጴጥሮስ የተባለ ሰው ወደ እናንተ እንደመጣ ሰምተናል እርሱ ሐሰተኛ ነው እንጂ እውነተኛ አይደለም። ይህን ጽሑፍ ይዞ የሚመጣው ግን ስሙ ሚናስ የሚባል ጳጳስ በእውነት እኛ የሾምነውና ወደ እናንተ የላክነው እውነተኛ ነው አሉ።
ሁለተኛም እንዲህ ብለው ጻፉ ጳጳሱ ጴጥርስ ታላቁን ትቶ ታናሹን የንጉሥ ልጅ አነገሠው ይህም የማይገባ ነው ዐመፅ ነውና። እሊህም ክፉዎችና ሐሰተኞች ሁለቱ መነኰሳት ሚናስና ፊቅጦር የሐሰት ጽሑፋቸውን ሳይጽፉ ወደ ጳጳሱ ጴጥሮስ ደርሰው ወርቅ ይስጣቸው ዘንድ ፈለጉ እርሱም ምንም አልሰጣቸውም። ይህንንም የከፋና የረከሰ ሥራ ሰይጣን አስተማራቸው ። የሐሰት ደብዳቤም ጽፈው ወደ ታላቁ የንጉሥ ልጅ ወሰዱ እርሱም ከጥቂት ሰዎች ጋር ለብቻው ይኖር ነበር እነዚያንም የሐሰት ደብዳቤዎች አነበቡለት እጅግም ደስ አለው።
ከዚህም በኋላ ብዙ ሠራዊት ሰብስቦ እሊያን የሐሰት ደብዳቤዎች በፊታቸው አነበበላቸው ከንጉሡ ወንድሙ ጋራም ጦርነት ገጥሞ ድል አደረገው ወንድሙንም አሠረው የመንግሥቱንም ሥልጣን ያዘ እንዲሁም ጳጳሱን ጴጥሮስን አሠረው በሩቅ አገርም አጋዘው ያንንም ሐሰተኛ ሚናስን በጳጳሱ በጴጥሮስ ፈንታ አስቀመጠው።
ከጥቂት ቀንም በኋላ ሐሰተኞች ፊቅጦርና ሚናስ እርስ በርሳቸው ተጣሉ ፊቅጦርም በመንበረ ጵጵስና ያለውን ገንዘብ ሁሉ ሰርቆ ወደ ግብጽ ሀገር ሸሽቶ ሔደ። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ካደው። ከመንበረ ጵጵስናው የሰረቀውንም ገንዘብ ሁሉ እግዚአብሔር የማይወደውን ሥራ በመሥራት አጠፋው።
ሊቀ ጳጳሳት ቆዝሞስም ሐሰተኛ ሚናስ ያደረገውን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ደብዳቤም በመጻፍ አውግዞ ለየው። የኢትዮጵያ ንጉሥም ሰምቶ እጅግ አዘነ ሐሰተኛው ሚናስንም ይዞ ገደለው። ጳጳሱ ጴጥሮስንም ከተሰደደበት ይመልሱት ዘንድ መልእክተኞችን ላከ ግን ሙቶ አገኙት። ይህም ነገር በሊቀ ጳጳሳት በቆዝሞስ ዘንድ ተሰማ ሁለተኛም ጳጳስ አልሾመላቸውም ከእርሱም በኋላ የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳት አባ መቃርስ አባ ታውፋንዮስ አባ ሚናስ አባ አብርሃም በእነዚህ ዘመን ከዘጠኝ መቶ አሥራ አንድ ዓመተ ምሕረት እስከ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አምስት ዓመተ ምሕረት ድረስ ለሰማንያ አራት ዓመታት ያህል ለኢትዮጵያ ሰዎች ጳጳስ ተሹሞ አልተላከላቸውም።
የኢትዮጵያ ንጉሥ ግን የጳጳሱ የጴጥሮስ ረዳት የነበረውን ወስዶ በመምህርህ ፈንታ ጳጳስ ሁነህ ተቀመጥ አለው። እርሱም እኔ ጳጳስ ልሆን አይገባኝም የሐዋርያትንም ሥርዓት ተላልፌ ይህን ልሠራ አይቻለኝም ግን ልቀቀኝና ወደ ግብጽ ልሒድ ጳጳስ እንዲሾምላችሁም ሊቀ ጳጳሱን እለምነዋለሁ ከዚያም በኋላ ወደ እናንተ እመለሳለሁ እያለ ንጉሡን ማለደው። ንጉሡም ወደ ግብጽ እንዲሔድ አላሰናበተውም ያለ ውዴታው ወስዶ የጵጵስናውን ልብስ አለበሰው እንጂ። የጵጵስናውንም ሥራ እንዲሠራ አደረገው።
አባ ቆዝሞስም እጅግ ሸመገለ የሹመቱም ዘመን ድኀንነትንና ሰላምን የተመላ ነበር በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበርም አሥራ ሁለት ዓመት ኖረ በሰላምም አረፈ፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages