ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 4 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Sunday, March 12, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 4



ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት፦
1.የቅዱሳን ሊቃውንት ጉባዔ (አሞር ደሴት ውስጥ)
2,ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሰ እስራኤል
3.ቅዱስ ሐኑልዮስ መኮንን (ሰማዕት)
ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
፩. ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ [ወንጌላዊው]
፪. ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬. ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ [ሰማዕት]

መጋቢት አራት በዚች ቀን የአይሁድ ተሳታፊዎች ስለሚባሉ ክፉዎች ሰዎች በአሞር ደሴት የአንድነት ስብሰባ ሆነ። እነርሱ የከበረ የፋሲካን በዓል በኔሳን ወር ማለት በሚያዝያ አሥራ አራት ቀን ከአይሁድ ጋር ያከብሩ ነበርና።
ሰኞ ቢሆን ማክሰኞም ቢሆን ወይም ረብዕ ወይም ሐሙስ ወይም በዓርብ ቀን ወይም በቅዳሜ ሰንበት ከአይሁድ ጋር ያከብሩ ነበርና የደሴታቸውም ኤጲስቆጶስ አወገዛቸው ግን አለተመለሱም።
ስለዚህም ወደ ሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ድምትራጥዮስ ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ ሰረባሞን ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ ድሜጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌሙ ኤጲስቆጶስ ወደ አባ ሲማኮስ መልእክትን ላከ። የእነዚህንም ሰዎች ስሕተታቸውን ነገራቸው።
አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት ከእነርሱ እየአንዳንዳቸው የከበረ የፋሲካ በዓልን በእሑድ ቀን ካልሆነ በቀር ከአይሁድ በዓልም በኋላ ካልሆነ በቀር አታድርጉ የሚል መልእክትን ላኩ። ይህንም ትእዛዝ የሚተላለፈውን ከምእመናን እንዲለይ አወገዙ።
በዚህም ጉባኤ አሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳት ተሰበሰቡ። እነዚያንም ሕግ ለዋጮች አቅርበው የሊቃነ ጳጳሳቱን መልእክቶቻቸውን በፊታቸው አነበቡ ከእነርሱም ከከፋች ምክራቸው የተመለሱ አሉ። በስሕተታቸውም ጸንተው የቀሩ አሉ። ረግመውና አውግዘውም ከምእመናን ለዪአቸው።
አባቶቻቸን ቅዱሳን ሐዋርያትም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣባትን ዕለተ ፋሲካን ያለ እሑድ ቀን የሚያከብር እርሱ በበዓላቸው ከአይሁድ ጋራ ተሳታፊ ነውና ከምእመናን ይለይ ብለው እንዳዘዙ እንዲሁ የፋሲካ በዓል በዕለተ እሑድ እንዲከበርና ሕጉም ጸንቶና ተወስኖ እንዲኖር ተሠራ።
እግዚአብሔር ከሰይጣን ስሕተት ይጠብቀን። በተጋድሎአቸውና በትሩፋታቸው ደስ ባሰኙት በቅዱሳን ጸሎትም ከወጥመዶቹና ከሽንገላውም ያድነን ለዘላለሙ አሜን።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
ቅዱስ ሐኑልዮስ መኰንን
በዚህችም ቀን የከበረና የተመሰገነ መኰንን ሐኑልዮስ ከጵንፍልያ አውራጃ ብርግያ በምትባል ከተማ በሰማዕትነት ሞተ።ይህንንም ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ መውደዱና እርሱንም ስለ ማምለኩ ከዲዮቅልጥያኖስ ተልኮ የመጣ ብርይንኮስ የተባለ መኰንን ያዘው።
በመኰንኑም ፊት በቆመ ጊዜ ምስጋና ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ከፍ ከፍ ባሉ ቃላት አብራርቶ ገለጠ ።ብዙ ምስጋናዎችንም ለእግዚአብሔር አቀረበ የረከሱ ጣዖታትንም ረገማቸው።
መኰንኑም በዕንጨት መስቀል ላይ ይሰቅሉት ዘንድ አዘዘ ስለ ከበረ ስሙም ምስክር ይሆን ዘንድ ስል አደለው ምስጋና ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰገነው። ከዚያም ምስጋና ይግባውና በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages