ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 6 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Wednesday, March 15, 2023

ስንክሳር ዘወርኀ መጋቢት 6




መጋቢት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.ጻድቁ ዐፄ ገብረ መስቀል (የኢትዮዽያ ንጉሥ)
፪.ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሰማዕት (አማሌቃውያን የገደሉት)
፫.ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ተአማኒ (ዘቆረንቶስ)
፫.አባ ዘሩፋኤል ጻድቅ
፬.አባ እንጦንስ ገዳማዊ
፭.አባ አርከሌድስ ገዳማዊ
ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
፪.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬ .ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮.ቅድስት ሰሎሜ
፰.አባ አርከ ሥሉስ
፱.አባ ጽጌ ድንግል
፲.ቅድስት አርሴማ ድንግል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!


ሰማዕት ዲዮስቆሮስ
ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ ሰዎች ወገን ነው። በማግባባት በመገፋፋት ከክርስቲያን አውጥተው ወደ እስልምና አስገቡት በእምነታቸውም ጥቂት ጊዜ ኖረ፤ ፍዮም በሚባል አገር ለአንድ ክርስቲያን ሰው የተዳረች አንዲት እህት ነበረችው። ወንድሟ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት እንደ ተወ በሰማች ጊዜ ታላቅ ሀዘንን አዘነች።
ከዚህም በኋላ እንዲህ ብላ ወደርሱ መልእክትን ላከች የክብር ባለቤት ክርስቶስን አንተ እንደ ካድከው ከምሰማ በክርስትናህ ሳለህ የሞትህ መርዶ ቢመጣልኝ እወድ ነበር፤ ከዚያም ከቅዱሳት መጻሕፍት ጠቅሳ ጻፈችለት በደብዳቤዋ ፍጻሜም እንዲህ ብላ ጻፈች ።
"ከዛሬ ጀምሮ ወደክርስትናህ ካልተመለስክ ይህቺ ደብዳቤ በእኔና በአንተ መካከል የፍቅር ፍጻሜ እንደሆነች ዕወቅ ከቶ ፊትህንም እንዳታሳየኝ መልእክትም ቢሆን አትላክልኝ"
የእህቱንም የመልእክት ደብዳቤ በአነበበ ጊዜ መሪር ዕንባን አለቀሰ። ተጸጸተ። ፊቱን ጸፋ። ጽሕሙንም ነጨ። ተነሥቶም ወገቡን ታጠቀ። ረጅም ጸሎትንም በመጸለይ ማለደ። ፊቱንም አዳኝ በሆነ መስቀል ምልክት አማተበ። ከቤቱም ወጥቶ በእስክንድርያ ከተማ ውስጥ ተመላለሰ።
እስላሞችም በአዩት ጊዜ ይዘው ወደ መኰንኑ አቀረቡት። መኰንኑም ከእርሱ ስለሆነው ነገር ጠየቀው። እርሱም ክርስቲያን ነኝ፤ ሌላ ምንም ምን አላውቅም ብሎ መለሰ። መኰንኑም ደግሞ የክርስቲያንን ሃይማኖት ትተህ ወደእኛ እምነት ገብተህ አልነበረምን ብሎ መለሰለት።
ቅዱስ ዲዮስቆሮስም መልሶ እንዲህ አለ በወልድ የማያምን ሕይውትን አያያትም የእግዚአብሔር የቁጣው መቅሠፍት በላዩ ይወርዳል እንጂ የሚል በከበረ ወንጌል ተጽፏል። ስለዚህ እኔ በክብር ባለቤት በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ። እኔም ትውልዴ ከክርስቲያን ነው። አሁንም በክርስትናዬ እሞታለሁ። መኰንኑም እጅግ ተቆጥቶ ከዚህ ምክርህ ካልተመለስክ እኔ የጸና ቅጣት እቀጣሃለሁ አለው። ቅጣቱንም ፈርቶ ከመልካም ምክሩ አልተመለሰም።
ከዚያም በኋላ ታላቅ ግርፋት ገርፎ አሠረው። በእሥር ጥቂት ቀናት ቆየ። ከእሥር ቤትም አውጥቶ ከምክሩ ከሐሳቡ ቢመለስ ብዙ ገንዘብ ሊሰጠው ቃል ገባለት። ይህ ካልሆነ ግን በእሳት እንደሚአቃጥለው ነገረው። ቅዱሱም ሕያው በምታደርግ ከክርስቲያን ሃይማኖት በቀር በሌላ አልሞትም ብሎ መለሰለት።
መኰንኑም በእሳት እንዲአቃጥሉት አዘዘ። ከከተማም ውጪ ታላቅ ጉድጓድ ቆፈሩለት። ዕንጨትም መልተው አነደዱት። ነበልባሉም እጅግ ከፍ ከፍ አለ። ያን ጊዜም ብዙ ገርፈው ሥጋውን በሰይፍ ሰነጣጠቁ፤ ወደ እሳትም ጨመሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጥቶ በመንግሥተ ሰማያት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።
ጸሎቱና በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።
#ቅዱስ ቴዎዶስዮስ
በዚችም ዕለት ታማኝ የሆነ ኤጲስቆጶስ የቅዱስ ቴዎዶስዮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፤ የዚህንም ቅዱስ ዜና ከዲዮቅልጥያኖስ የተሾመ የቆጵሮስ ገዥ ዮልዮስ ሰማ፤ ወደርሱም አስቀርቦ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክዶ ለረከሱ ጣዖቶች ዕጣን እንዲአጥን መሥዋዕትም እንዲአቀርብ ፈለገ።
ቅዱስ ቴዎዶስዮስም እኔስ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ ለእርሱም እሠዋለሁ በሎ መለሰ። ትእዛዙንም ባልሰማ ጊዜ ጽኑዕ ግርፋትን ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ ገረፈው። ከዚያም ሰቅሎ ሥጋውን ሁሉ ሰነጠቀ። አውርዶም በእሳት በአጋሉት በብረት አልጋ ላይ አስተኛው። ጌታችንም ከዚህ ሥቃይ ጠብቆ አዳነው።
ከዚህ በኋላ እጆቹንና እግሮቹን በረጃጅም ችንካሮች ቸንክረው እስከ ወህኒ ቤት ጐትተው በዚያ ጣሉት፤ እግዚአብሔርም ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስን አጥፍቶ ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ እስከ ነገሠ ድረስ በወህኒ ቤት ኖረ፤ ቈስጠንጢኖስም የመንግሥት ሥልጣን በያዘ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የታሠሩትን ሁሉ እንዲፈቷቸው አዘዘ፤ ከዚያም በኋላ ወደ አገሩ ተመልሶ በጵጵስናው ሹመት ላይ ሁኖ ምእመናንን በበጎ አመራር እየመራ ኖረ፤ ዕድሜውንም ፈጽሞ በሰላም አረፈ።
የፈጣሪው በረከትም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

የቅዱሳኑ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን
አሜን!!!

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages