ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 7 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Thursday, March 16, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት 7

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሰባት በዚህች ቀን የከበሩ ቅዱሳን_ፊልሞንና_አብላንዮስ በሰማዕትነት አረፉ፣ ቅዱስ_ቴዎዶጦስ በሰማዐትነት አረፈ፡፡

መጋቢት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ጻድቁ ኢትዮዽያዊ ንጉሥ ዐፄ ቴዎድሮስ
2.ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ፊልሞን ሰማዕት
4.ቅዱስ አብላንዮስ ሰማዕት
ወርሐዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)
መጋቢት ሰባት በዚህች ቀን የከበሩ ፊልሞንና አብላንዮስ በሰማዕትነት አረፉ። ይህ ፊልሞንም የእንዴናው ገዥ በሆነ በአርያኖስ ፊት በአዝማሪነት ይጫወት ነበር ከአዝማሪው አብላንዮስም ጋራ እርስ በርሳቸው ወዳጆች ሆኑ ለክብር ባለቤት ክርስቶስም ስለ ስሙ ምስክሮች ሊሆኑ ተስማሙ።
አዝማሪው ፊልሞንም ልብሱን ወስዶ ለአብላንዮስ ሰጠው እርሱም የአብላንዮስን ልብስ ለብሶ ወደ መኰንኑ ወደ አርያኖስ ገብቶ በፊቱ ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ።
መኰንኑም ተመልክቶ አዝማሪው አብላንዮስ እንደሆነ አሰበ በፍላጻም እንዲነድፉት አዘዘ ያንጊዜም አዝማሪው ፊልሞን መሆኑን አውቆ እጅግ ተቆጣ። ደግሞ አብላንዮስን እንዲነድፉት አዘዘ ሁለቱንም ነደፉአቸው አንዲት ፍላጻም ወደ መኰንኑ ተመልሳ ዐይኑን አወጣቻት እጅግም አሠቃየችው። የከበሩ ፊልሞንና አብላንዮስ ግን ገድላቸውን ፈጽመው የሕይወት አክሊልን ተቀበሉ።

በዚህችም ዕለት ደግሞ ቅዱስ ቴዎዶጦስ በሰማዕትነት አረፈ። እርሱም ከገላትያ አገር የሆነ በምክርና በተግሣጽ አምልኮተ እግዚአብሔርንም በማጽናት ያደገ ነው። ወደ ከሀዲ መኰንንም ሒደው የክርስቲያን ወገን እንደሆነ ነገር ሠሩበት መኰንኑም አሥረው እንዲአመጡት አዘዘ።
ቅዱሱም ይህን በሰማ ጊዜ ሳይዙት ወደ መኰንኑ ሔዶ መኰንኑንና የረከሱ ጣዖቶቹን ረገመ ዘለፋቸውም መኰንኑ እሱን በማስፈራት ሁኖ የሥቃይ መሣሪያዎችን ሁሉ አሳየው ለጣዖት እንዲሠዋ በመሸንገል አስገደደው ቅዱሱም ስለ ድንቁርናው ረገመው ዘለፈውም።
ከዚህ በኋላም የውስጥ ዕቃው እስከሚታይ ሰቀለው ጐኖቹን ይሠነጣጥቁ ዘንድ መኰንኑ አዘዘ። ከዚያም ወደ ወህኒ ቤት ይጨምሩት ዘንድ ደግሞ አውጥተው በዕንጨት እንዲሰቅሉት ቊስሎቹንም እንዲአድሱ ጐኖቹንም እንዲሠነጣጥቁ አዘዘ።
እርሱ ግን መኰንኑ የሚያመጣውን ሥቃይ እንደ ኢምንት አደረገው በክብር ባለቤት በጌታችን ክርስቶስ በፍቅሩ ፍላጻነት ልቡ ተነድፏልና ዐይኖቹም ወደላይ ይመለከቱ ነበር። መኰንኑም ብርታቱን በአየ ጊዜ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ።
ቅዱስ ቴዎዶጦስም የራሱን መቆረጥ ሰምቶ እጅግ ደስ እያለው ወጣ። ወደ እግዚአብሔርም ሲጸልይና ሲማልድ እንዲህ አለ። የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አመሰግንሃለሁ ከተከታተለኝ ክፉ ነገር ሁሉ አድነኸኛልና በጠላትነት የተነሡብኝንም ወደ ገሃነም አውረድካቸው እኔንም ከሞት በር ከፍ ከፍ አድረግኸኝ።
ይህንንም ብሎ በሰገደ ጊዜ ወታደሩም የቅዱሱን ዐይን ይሸፍን ዘንድ መሸፈኛ አመጣ። ቅዱሱም ይህ ሞትን ለሚፈሩ ነው እኔ ግን በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሞትን አልፈራም አለ። ወታደሩም ሰይፉን መዝዞ የከበረች ራሱን ቆረጠ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages