ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 14 - አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

አትሮንስ ሚዲያ - Atrons Media

ስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት ማቴ 16፤15


በቅርብ የተጻፉ

Post Top Ad

Monday, April 24, 2023

ስንክሳር_ዘወርኀ_ሚያዝያ 14


 

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

ሚያዝያ አሥራ አራት በዚች ቀን በእስክንድርያ ለተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት ዐሥራ አምስተኛ የሆነ የከበረ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ መክሲሞስ አረፈ። ይህም አባት መንፈሳዊና በሥራው ሁሉ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው።
እርሱም ከእስክንድርያ ሰዎች ወገን ነው ወላጆቹም ሃይማኖታቸው የቀና ነበረ የዮናናውያንንም ጽሕፈትና መጽሐፋቸውን ጥበባቸውንም ሁሉ ተምሮ ፍጹም አዋቂና አስተዋይ ሆነ በዮናኒ ቋንቋ።
ከዚህም በኋላ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ልዑል እግዚአብሔር የሠራውን ሕግና ሥርዓት ተማረ። አባት ያሮክላም ዲቁና በእስክንድርያ ሾመው ከዚያም በኋላ ዲዮናስዮስ ቅስና ሾመው በተሾመባት ሁሉ ላይ ተጠምዶ የሚአገለግልና የሚጋደል ሆነ ።
አባ ዲዮናስዮስም በአረፈ ጊዜ አዋቂዎች ኤጲስቆጶሳትና ካህናት ማኅበሩም ሁሉ መረጡት በእግዚአብሔርም ፈቃድ በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት ።
ዲዮናስዮስም ስለ ጳውሎስ ሳምሳጢ በአንጾኪያ ከተማ የተጀመረው የኤጲስቆጶሳት ማኅበር ጉባኤ ተጀመሮ ሳይፈጸም አረፈ። ይህም አባት መክሲሞስ በተሾመበት ወንበር በተቀመጠ ጊዜ በማኅበሩ ጉባኤ ስለ ተወሰነውና ከሀዲው ጳውሎስ ሳምሳጢን እንደአወገዙት ከጉባኤው ሹማምንት መልእክቶች ወደርሱ ደረሱ። በትምርቱ ያመኑትንም መልእክቶቹንም ካህናቱ በአንድነት በተሰበሰቡበት አነበበው።
ከዚያም በኋላ ዳግመኛ ከራሱ መልአክቶችን ጽፎ የጳውሎስ ሳምሳጢን ስሕተት ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልዩና እንዲማልዱ እያዘዘ ወደ ግብጽ አገሮች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያና ወደ ኖባ አገር ላካቸው ።
የክብር ባለቤት ጌታችን ልመናቸውን ተቀበለ ይህም ከሀዲ ከጥቂት ቀኖች በቀር አልኖረም በፍጥነት አጠፋው እንጂ የረከሰች ሃይማኖትንም ከዓለም አስወገደ አራቀ።
በዚህም አባት ዘመን ከምሥራቅ አገር ማኒ የሚባል ራሱን የዕውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስን ያደረገና ክፉ ስሕተትን የሳተ ሰው ተገለጠ። ወደ ሶርያ ምድርም ደረሰ አርኬላዎስ የሚባል ኤጲስቆጶስም ከእርሱ ጋራ ተከራከረ ስሕተቱንም ገላልጦበት አሳፍሮ ከአገሩ አሳደደው ። ከዚያም ተመልሶ ወደ ፋርስ ሔደ ራሱንም ነቢይ አደረገ የፋርስ ንጉሥ ብህራምም ይዞ ከሁለት ሠነጠቀው። ተከታዮቹ የሆኑ ሁለት መቶ ሰዎችን ዘቅዝቆ እስከ ወገባቸው በምድር ውስጥ ተከላቸው እነሆ ከሰው አትክልትን ተከልሁ አለ።
ይህም አባት መንጋውን በመጠበቅ ሲጋደልና በቀናች ሃይማኖትም ሲያጸናቸው ኖረ ከመናፍቃንና ከከሀድያን ችግር እስከ አረፈባት ቀን ድረስ በድርሳናትና በተግሣጻት ጠብቆ አዳናቸው። በማርቆስም ወንበር ዐሥራ ስድስት ዓመት ኑሮ በሰላም አረፈ።
በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።

No comments:

Post a Comment

Post Bottom Ad

Pages