አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መጋቢት ዐሥራ አምስት በዚች ቀን የከበረች ተጋዳይ መነኰሳዪት ሣራ አረፈች። ይቺም ቅድስት ከላይኛው ግብጽ ናት ወላጆቿም የክብር ባለቤት ክርስቶስን የሚያመልኩ ክርስቲያን ናቸው። እጅግም ባለጸጎች ነበሩ ነገር ግን ከእርስዋ በቀር ልጆች የሏቸውም በመልካም አስተዳደግም አሳደጓት ለክርስቲያን የሚገባ ትምህርትን ሁሉ አስተማሩዋት ደግሞም ጽሕፈትን አስተማሩዋት ሁልጊዜም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት ታነባለች ይልቁንም የመነኰሳትን ዜና ታነብ ነበር።
መጻሕፍትንም አዘውትራ ስለምታነብ የምንኲስና ልብስ ለመልበስ ፈለገች በላይኛው ግብጽ ከሚገኙ ገዳማትም ወደ አንዱ ገዳም ሒዳ ገባች ብዙ ዘመናትም ደናግልን እያገለገለች ኖረች።
ከዚህም በኋላ የምንኲስና ልብስን ለበሰች ሰይጣንን ድል እስከ አደረገችው ድረስ ሰይጣን የሚያመጣውን ሥጋዊ ፍትወት እየታገለች ዐሥራ ሦስት ዓመት ኖረች። ንጽሕናን ከመውደዷ ጽናት በተሸነፈ ጊዜ በትዕቢት ሊጥላት ወዶ በቤት መዛነቢያ ልትጸልይ ቁማ ሳለች ተገልጦ ሣራ ሆይ ሰይጣንን ድል አድርገሽዋልና ደስ ይበልሽ አላት እርሷም መልሳ እኔ ደካማ ሴት ነኝ ከክብር ባለቤት ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ድል አድርጌ ላበረው አልችልም አለችው።
ይህችም ቅድስት አብረዋት ላሉ ደናግል ጥቅም ያላቸውን ብዙ ትምህርቶችን ታስተምራቸው ነበር እንዲህም ትላቸዋለች ከቀን ብዛት ጠላት እንዳያስተኝ እኔ እንደምሞት አስቀድሜ ሳላስብ እግሬን ከአንዱ መወጣጫ ደረጃ ወደ ሁለተኛም አውጥቼ አላኖራትም።
ዳግመኛም ለሰው ርኅራኄ ማድረግ በተሻለው ነበር ይህንንም በሚያደርግ ጊዜ የኋላ ኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ ይኖራል በዜና አረጋውያን መነኰሳት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ ሌሎች ብዙ ቃሎችንም ተናግራለች።
ታላቅ ተጋድሎም እየተጋደለች በዓቷም በባሕር ዳርቻ ሁኖ ሰባት ዓመት ኖረች አንዲት ቀን እንኳ ከሰው አንዱም አላያትም እርሷ ግን ሁሉን ታይ ነበር። ሸምግላ እስከ ሰማንያ ዓመት በደረሰች ጊዜ ከዚህ ዓለም የሕይወት ማሠሪያ ተፈትታ የዘላለም ተድላ ደስታ ወደሚገኝበት ሔደች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
በዚችም ቀን ዳግመኛ የቅድስት አስጠራጦኒቃ እጮኛዋ ቅዱስ ሰለፍኮስ በሰማዕትነት አረፈ።
የዚህን ቅዱስ ዜና ክርስቲያን እንደሆነ ከሀዲ ንጉሥ በሰማ ጊዜ ያመጡት ዘንድ አዘዘ ወደርሱም ሲቀርብ የአስጠራጦኒቃ እጮኛዋ ሰለፍኮስ የተባልክ አንተ ነህን አለው አዎን ነኝ አለ። ዳግመኛም ማንን ታመልካለህ አለው እርሱም እኔ የክብር ባለቤት የሆነ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አመልከዋለሁ ብሎ መለሰ። ንጉሡም መርዝ ያላቸው እባቦች ወዳሉበት እንዲጨምሩት አዘዘ እግዚአብሔርም አዳነው።
ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዝዞ ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment